ክለባቸው የፕሪምየር ሊጉን መሪነት ለመጨበጥ የቻለው ከጨዋታ ወደ ጨዋታ መሻሻልን በማሳየታቸው እና በጉዳት ላይ የነበሩትም የቡድኑ ተጨዋቾች ወደ ሜዳ በመመለሳቸው መሆኑን አስተያየቱን ለሊግ ስፖርት ጋዜጣ ሊሰጥ ችሏል፡፡
የቅ/ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለብ በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ የኢትዮጵያ ቡና መሸነፍን ተከትሎና ራሱም ወልዋሎ አዲግራት ዩንቨርስቲን ለማሸነፍ በመቻሉ አሁን ላይ የሊጉን መሪነት ለመጨበጥ የቻለ ሲሆን በቀጣይ በሚደረጉ ጨዋታዎችም ይህን መሪነት አስጠብቆ እስከመጨረሻው ሰዓት ድረስ ለመጓዝ የሚቻላቸውን ጥረት ሁሉ እንደሚያደርጉ የቡድኑ ተጨዋች በኃይሉ አሰፋ ይናገራል፡፡
የቅ/ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለብ በሊጉ የውድድር ተሳትፎው እያደረገ ስላለው ጉዞ፣ በቀጣይነት ስለሚኖሩት ጨዋታዎችና ለሻምፒዮናነት ስለሚኖረው ፉክክር የቡድኑን ተጨዋች በኃይሉ አሰፋን ያናገርነው ሲሆን የተጨዋቹም ምላሽ የሚከተለውን ይመስላል፡፡
ሊግ፡- ቅ/ጊዮርጊስ የሊግ መሪነቱን ከቡና ላይ በመረከብ ከአናት ተቀምጧል፤ ወደዚህ ደረጃ እንዴት ልትመጡ ቻላችሁ?
በኃይሉ፡- የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የዘንድሮው አጀማመራችን ጥሩ ያልነበረና ተደጋጋሚም ነጥብ የጣልንበት ቢሆንም ወደ መሪነት ስፍራው እንደምንመጣ አስቀድመን እናውቅ ነበር፤ የሊግ ውድድሩን ለበርካታ ሳምንታት ከስር ከስር ሆነን ስንከተል ነበር፤ የአሁኑ ሰአት ላይ ግን ተደጋጋሚ የድል ውጤቶችን ልናስመዘገብ ስለቻልንና በመሪነት ደረጃ ላይ የሚገኘው ኢትዮጵያ ቡና ደግሞ ነጥቦችን በመጣሉ የመሪነቱን ስፍራ እኛ ልንረከበው ችለናል፡፡
ሊግ፡- ፋሲል ከነማን በሜዳችሁ እና በደጋፊዎቻችሁ ፊት ነገ ትፋለማላችሁ፤ ለጨዋታው የተለየ ዝግጅትን አድርጋችኋል? ምንስ ውጤት ትጠብቃላችሁ….?
በኃይሉ፡- ከፋሲል ከነማ ጋር ለሚኖረን የነገው ጨዋታ የተለየ ዝግጅትን አላደረግንም፤ ክለባችን ሁሌም ከማንም ጋር ይጫወት በሜዳ ላይ የሚያገኘው ነጥብ 3 ካልሆነ ደግሞ 1 ስለሆነ ለሁሉም ቡድኖች ነው እኩል ግምት ሰጥቶና ተዘጋጅቶ የሚመጣው፤ በሊጉ የምናደርጋቸው እያንዳንቸው ጨዋታዎችም ለሻምፒዮናነት ለምናደርገው ጉዞ በጣም ወሳኞች ስለሆኑም ከፋሲል ጋር የሚኖረንን ጨዋታ አሸንፈን ከሜዳ ለመውጣት ዝግጁ ሆነናል፡፡
ሊግ፡- ቅ/ጊዮርጊስ ከጨዋታ ወደ ጨዋታ ውጤቱን አሳምሮ በመሪነቱ ላይ ተቀምጧል፤ ለስኬታማነታችሁ የተለየ ብለህ የምትጠቅሰው ምክንያት አለ?
በኃይሉ፡- የክለባችንን የውጤት መሻሻል አስመልክቶ በመሪነት ደረጃ ላይ ለመቀመጥ እንደምንችል የምናውቅበት ሁኔታ ስለነበር በተለየ ምክንያት የምገልፀው ነገር ምንም የለም፤ ለቡድናችን ውጤት መሻሻል የረዳን አብዛኛዎቹ ተጨዋቾች እኔን ጨምሮ ጉዳት ላይ ነበርንና ሁላችንም ወደሜዳ መመለሳችን እና ክለባችንን ለመጥቀም መቻላችን ለውጤታማነት ሊያበቃን ችሏል፤ የውድድር ዓመቱ ጅማሬ ላይ ሳላህዲን ሰይድ ተጎደቶብን ነበር፤ አሁን እሱ ወደ ሜዳ ተመልሶ እየጠቀመን ይገኛል፤ ምንተስኖት አዳነም ተጎድቶ ነበርና የእሱም ወደሜዳ መመለስ የሚጠቅመን ሆኗል፤ ሳላህዲን ባርጌቾም ተጎድቶ የነበረ ቢሆንም ወደሜዳ ተመልሶ ነው አሁን ላይ በድጋሚ ሊጎዳ የቻለው፡፡ አቤል ያለውም ተጎድቶ እሱም አሁን ድኖ ክለቡን እያገለገለ ይገኛል እና እነዚህ ሁኔታዎች ናቸው በጣም እየጠቀሙን የሚገኙት ቀጥሎ ደግሞ አሁን ጉዳት ላይ የሚገኘው ጌታነህ ከበደ እና ሳላህዲን ባርጌቾም ወደ መልካም ጤንነታቸው ሲመለሱ ደግሞ የክለባችንን የሜዳ ላይ ጥንካሬ የበለጠ ስለሚያሳድጉልን ይሄንን ነው እየጠበቅን የምንገኘው፡፡
ሊግ፡- የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ፉክክርን በርካታ ክለቦች በተቀራረበ ነጥብ ላይ ከመገኘታቸው አኳያ እንዴት ተመለከትከው?
በኃይሉ፡- የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የእዚህ አመት አጠቃላይ ፉክክርን ገና ከጅማሬው አንስቶ እንዳገኘሁት በአንድ ጨዋታ ላይ የምታስመዘግበው የድል ውጤትም ሆነ ሽንፈት ደረጃህን ወደላይ ከፍ የምታደርግበት አሊያም ደግሞ ወደታች ዝቅ የምትልበትን ውጤት የምታስመዘግብበት ስለሆነ ለእያንዳንዱ የሊግ ውድድር ከፍተኛ ትኩረት ሰጥተህ ነው ወደ ሜዳ የምትገባው እና ሊጉ ጥሩ ፉክክር እየተደረገበት ነው፡፡
ሊግ፡- የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጅማሬዎች ላይ ሐዋሳ ከነማ የደረጃ ሰንጠረዡን ለመምራት ችሎ ነበር፤ በመቀጠል ደግሞ ኢትዮጵያ ቡና መሪ ሆነ፤ አሁን ደግሞ እናንተ በመሪነቱ ደረጃ ላይ ተቀምጣችኋል፤ ይሄን መሪነት ታስቀጥላላችሁ ወይንስ ሌላ መሪ ይመጣል?
በኃይሉ፡- የፕሪምየር ሊግ መሪነትን አሁን ላይ ክለባችን ሊጨብጥ ቢችልም በቀጣይነት ስለሚኖሩት ነገሮች የእግር ኳስ ጨዋታ ነውና ከወዲሁ እንዲህ ነው ብለህ የምትናገረው ነገር አይደለም፤ እኛ አሁን የሊጉ መሪ ነን የያዝነውን መሪነትም እስከመጨረሻው ሰአት ድረስ አስጠብቀን ለመጓዝ ነው የምንችለውን ሁሉ ጥረት የምናደርገው፡፡
ሊግ፡- ቅ/ጊዮርጊስ ውስጥ የጨዋታ ልምድህን በመጠቀም ክለቡን እያገለገልክ ይገኛል፤ በቀጣይነትስ ከአንተ ምን ይጠበቅ?
በኃይሉ፡- የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ውስጥ አሁን የስድስተኛ አመቴን ይዣለሁ፡፡ በቡድኑ ውስጥ በሚኖረኝ ቆይታም ጤነኛ እስከሆንኩ ድረስ ያለኝን አቅም ሁሉ አውጥቼ ቡድኑን ከጓደኞቼ ለመጥቀም በሚገባ ዝግጁ ነኝና በእዚህ አመት ላይ ጥሩ የሆነውን የሜዳ ላይ ግልጋሎቴን ለክለቤ አበረክታለሁ፡፡
ሊግ፡- የፕሪምየር ሊጉ የውድድር ተሳትፎ ላይ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ጎል የማስቆጠር ምክንያት ከሆኑት ተጨዋቾች መካከል አንዱ አንተህ ነበርክ፥፤ የአንተ ብዙ የመስመር ላይ ኳሶችም ለአጥቂዎች ደርሰው ጎል ይሆኑም ነበር አሁን ላይ ያ ብዙ የማይታየው ከአጨዋወት ታክቲክ ጋር ነው…?
በኃይሉ፡- ቅዱስ ጊዮርጊስ በበፊት የአጨዋወት ታክቲኩ ላይ እኔን ይጠቅም የነበረው በመስመር አጥቂነት ስፍራ ላይ ስለነበር ከጓደኞቼ የምቀበላቸውን ኳሶች በክንፍ በኩል ሮጬ በማምለጥ ለአጥቂዎች የተሳኩ ኳሶችን አድርሼ ተደጋጋሚ ጎል የምናስቆጥርበት እድሉ ነበረን፤ የአሁን ሰአት ላይ ግን እኔ እየተጫወትኩ ያለሁት ከመከላከሉ ክፍል ከኋላ ተነስቼ በተመላላሽ /በፉልባክ/ ደረጃ ነው የምጫወተው እና ለዛ ነው ከጨዋታው ታክቲክ ጋር በተያያዘ በማጥቃቱ ላይ በተደጋጋሚ የማልታየው፤ ያም ሆኖ ግን አሁን የምጫወትበት የጨዋታው ታክቲክ ይቀየር እንጂ ለአጥቂዎች ተደጋጋሚ ኳሶችን የማቀብልበት ግልጋሎት ይቋረጣል ብዬ ግን ፈፅሞ አላስብም፡፡
ሊግ፡- የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የዘንድሮው ተሳትፎ ላይ ከእናንተ ቡድን የተለየ እና አበረታች እንቅስቃሴን አሳይቷል ብለህ የምትጠቅሰው ተጨዋች አለ?
በኃይሉ፡- የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ውስጥ ዛሬ ብቻ ሳይሆን ሁልጊዜም ቢሆን እያንዳንዱ ተጨዋች የራሱ የሆነ የግል ብቃት ቢኖረውም ቡድናችን እንደ ቡድን የሚንቀሳቀስ ስለሆነ በሚኖሩን ጨዋታዎች አንድ ወይንም ደግሞ ሁለት ተጨዋችን ብቻ ጠቅሰህ የምታሞግስበት ነገር የለም፤ ሁሉም የቡድናችን ተጨዋቾች ናቸው አበረታች እንቅስቃሴን የሚያሳዩት፤ ለዛም ነው የሊጉን ዋንጫ እንደ ቡድን ስለምንጫወት በተደጋጋሚም ስናነሳ የሚስተዋለው፡፡
ሊግ፡- ቅዱስ ጊዮርጊስ የሜዳ ውጪ ጨዋታዎቹን ብዙ ጊዜ ከሌሎች ክለቦች አንፃር በስኬት ለማጠናቀቅ ይችላልና የእዚህ ውጤት የማግኘት ሚስጥሩ ምንድነው?
በኃይሉ፡- የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ አብዛኛዎቹን የሜዳ ውጪ ጨዋታዎቹን በስኬት የሚያጠናቅቅበት ዋናው ምክንያት ለእያንዳንዳቸው ጨዋታዎች አንዱን ከአንዱ ሳያበላልጥ ከፍተኛ ትኩረትን ስለሚሰጥ እና ጥሩ አቋምንም ይዞ ስለሚቀርብ ነው፤ በዛ ላይ ደግሞ የውድድር አመቱ ሻምፒዮና ለመሆን ወደ ክልል ሄደህ የምታደርጋቸው ጨዋታዎችን ማሸነፍ መቻል ግድ ስለሆነም ነው አጥቅቶም የሚጫወተው፤ ለዛም ነው ሻምፒዮና ለመሆን ስለምንፈልግም ዘንድሮም የሜዳችን ውጪ ጨዋታን እያሸነፍን የምንገኘው፤ በሊጉ ውድድር አምና ዋንጫን ስናጣ በዋናነት የጎዳን የሜዳችን ውጪ ጨዋታዎችን ቁጥሩ ከፍ ባለ መልኩ ስላላሸነፍን ነው፤ ሁለት ጨዋታን ብቻ ከሜዳችን ውጪ ማሸነፋችን የውድድሩ ተጠቃሚ እንዳንሆን አድርጎናል፤ ዘንድሮ ግን ክልል ወጥተንም ሆነ በሜዳ ላይ የምናደርጋቸውን ቀጣይ ጨዋታዎች እንዳለፉት ጊዜ ግጥሚያዎቻችን ለማሸነፍ የምንችልበት እድሉ ስላለን ሻምፒዮና የመሆን እልማችንን እናሳካለን፡፡
ሊግ፡- ቅዱስ ጊዮርጊስ በሊግ ውድድሩ ያለበት ክፍተት ምንድነው?
በኃይሉ፡- የእግር ኳስ ጨዋታ ላይ ሁሌም ቢሆን ክፍተት አለ፤ ዋናው ነገር እነዛን ክፍተቶች አርመህ እና አስተካክለህ ለቀጣዮቹ ውድድሮች መዘጋጀት ነውና እነዚህን ችግሮች በቀጣይ ጨዋታዎቻችን እያስተካከልን እንመጣለን፡፡