በኢትዮጵያ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ሻምፒዮና በቀድሞ ስሙ መጠራት የጀመረው የመቻል እግር ኳስ ክለብ ከባህርዳር ከተማ ጋር በሳምንቱ አጋማሽ ያደረገውን ጨዋታ 3-2 በሆነ ውጤት ማሸነፉ የሚታወስ ሲሆን ለክለቡ የተቆጠሩትንም ግቦች በሀይሉ ግርማ፣ በረከት ደስታና በመጨረሻው ሰዓት ላይም ከነዓን ማርክነህ ከመረብ ሊያሳርፉት ችለዋል።
መቻል በፕሪምየር ሊጉ በተጠበቀው መልኩ ሊጓዝ ባይችልም አሁን ላይ ደግሞ በተከታታይ ጨዋታዎች ላይ በውጤት ደረጃ ለውጦችን እያሳየ በመሆኑ ቀጣይ ጉዞው ደግሞ በመጠበቅ ላይ ይገኛል። በአሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ ሀላፊነት የሚመራው መቻል በሊጉ የእስካሁኑ ጨዋታ ስለተጓዘበት መንገድና በራሱ አቋም ዙሪያ እንደዚሁም ስለ ኳታሩ የዓለም ዋንጫ የሊጉ ስፖርቱ ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ /G.BOYS/ የቡድኑ ተጨዋች ለሆነው በሀይሉ ግርማ /ባባ/ የተለያዩ ጥያቄዎችን አቅርቦለት ምላሹን ሰጥቶታል።
ባህርዳር ከተማን በሳምንቱ አጋማሽ ድል ስላደረጉበት ጨዋታ
“የሁለታችን የጨዋታ አጀማመር ምንም እንኳን ለእኛ ትንሽ ቀዝቀዝ ብሎብን የነበረ ቢሆንም ጨዋታው እንደ አጠቃላይ ጥሩ ነበር። መጀመሪያ ላይ እነሱ የተሻሉ ስለነበሩም ጎል ሊያስቆጥሩብን ችለዋል፤ እኛ ላይ ጎል ከገባብን በኋላም ወደ ጥሩነት ለመመለስ በመቻላችን ጨዋታውን አቻ ልናደርገው ቻልንና ከእረፍት በኋላም ማሸነፍ አለብን በሚል ስሜት እስከ መጨረሻው ሰዓት ድረስ ጠንክረን ስለተጫወትን የግጥሚያው ባለድል ሆነናል”።
በጨዋታው ላይ ስለነበራቸው ጠንካራና ክፍተት ጎን
“የጥንካሬው ዋናው ጎናችን ሁላችንም ጨዋታውን ለማሸነፍ የነበረው ፍላጎታችንና መነሳሳታችን ጥሩ መሆኑ ነበር፤ በድክመት ደረጃ የማነሳው ደግሞ ጨዋታውን ለማሸነፍ ያለን መነሳሳት እንዳለ ሆኖ ያለንን አቅም የማያስወጣ ማለትም የፍላጎት መብዛት ነበርና ይህንን ነው የተመለከትኩት”።
ስለ ዕለቱ ተጋጣሚያቸው
“ባህርዳር ከተማ ጥሩ ቡድን ነው፤ ኳስን ይዘውም ይጫወታሉ። ጥሩ ስብስብን የያዘና በጥንካሬያቸው ያከበርኳቸውም ክለብ ነው። ያም ሆኖ ግን የእግር ኳስ ውጤት በ90 ደቂቃ ውስጥ የሚወሰንና የሚታወቅ በመሆኑና እኛም ከእነሱ የተሻልን ሆነንም ስለቀረብን ጨዋታውን አሸንፈን ለመውጣት ችለናል”።
ብዙዎች መቻልን በተጠበቀው ልክ እየተጓዘ አይደለም ስለማለታቸው
“ልክ ነው፤ ብዙዎች በተለያዩ ጨዋታዎች ላይ ነጥብን ስለጣልን ነው እንደዛ ሊሉን የቻሉት፤ አሁን ላይ ግን ከአስረኛው ጨዋታ ጀምሮ እንዳየከን ክለባችን እየተስተካከለ ነው። ባለፉት ሶስት ጨዋታዎች ላይም ሰባት ነጥብን ልንይዝም ችለናል። የውድድሩ መቋረጥ ባይኖር ደግሞ ለእኛ ይበልጥ ጥሩ ይሆንልንም ነበር። ያም ሆኖ ግን ቡድናችን በጥሩ ሁኔታ ላይ የሚገኝ በመሆኑ ወደፊት ደግሞ በጥሩ ደረጃ ላይ መቀመጣችን የማይቀርም ነው”።
በባህርዳርና በድሬዳዋ ከተማ ላይ ስለነበራችሁ የ13 ሳምንታት አጠቃላይ ቆይታ ምን አልክ?
“እንደ አጠቃላይ ስመለከተው ገባ ወጣ ባለ መልኩ ነው በመጓዝ ላይ የምንገኘው፤ ዛሬ ያሸንፍና ነገ ይሸነፋል። በተለይም ደግሞ ማሸነፉ ላይ ትንሽ ተቸግረንም ነበር። አሁን ላይ ደግሞ ወደ መጨረሻዎቹ ጨዋታዎች ላይ ስናመራ ነገሮች እየተስተካከሉልን በመምጣታቸው ወደ አሸናፊነቱ ልንመጣ ችለናል”።
መቻል ውጤት በሚያጣበት ሰዓት የክለባችሁ አመራሮችና አሰልጣኞቻችሁ ጋር ያለው ስሜትና ምን እንደሚሏችሁ
“በአብዛኛው ጨዋታዎች ላይ የእኛን ቡድን ውጤት ያሳጣው በኳስ በሚያጋጥም የሽንፈት ነገር እንጂ ጥሩ ሳንጫወት ቀርተን አይደለም። አሰልጣኛችን እንደሚታወቀው ጎበዝ ባለሙያ ነው። በትክክልም ያለውን ነገር በልምምድ ሜዳ ላይም ነው ጨርሶ የሚመጣውና ሁሌም አሰልጣኞቻችንም ሆኑ የቡድናችን አመራሮች ጋር ያለው ነገር በብዙ ሁኔታ ከጎናችን ናቸው። ቤተሰብ ጋር ችግር ካለብን ቀርበውም ያወሩናል። ቡድኑን በተመለከተም ክፍተቱ ቀላል ስለሆነ ልናስተካክለው እንደምንችልም ነግረናቸዋል። በጣም ምርጥ አመራሮች ስላሉንም ሊመሰገኑም ይገባቸዋል”።
አንደኛው ዙርን በምን ውጤት እንደሚያጠናቅቁና የሁለተኛው ዙር ዋናው ግባቸው
“የአንደኛው ዙር ግጥሚያ ሊጠናቀቅ የሁለት ጨዋታ ቢቀርም በውጤት ደረጃ የምንገኝበት ስፍራ አሪፍ /ጥሩ/ አይደለም በመባባላችን አሁን ላይ ግጥሚያው በመቋረጡ በእዚህ የእረፍት ወቅት ያለብንን ክፍተት በመድፈን ወደ ውድድር ስንመለስ የአንደኛው ዙር ቀሪ ግጥሚያዎችንም ሆነ የሁለተኛው ዙር ጨዋታዎቻችንን በጥሩ ሁኔታ በማጠናቀቅ መቻልን ወደ ጠንካራ ተፎካካሪነቱና ውጤታማነቱ የምንወስድበት ጊዜ ሩቅ አይደለም፤ ከእዛ ውጪም ዘንድሮ ምርጥ ከሚባሉት አምስት ቡድኖች ውስጥም አንዱ እንሆናለን፤ “።
ጎል እያስቆጠረ ስለመሆኑና ለቡድኑ እየሰጠ ስላለው ግልጋሎት
“አሁን የምጫወትበት ቦታ በጣም ተመችቶኝ ያለ ነው፤ ከአጠገቤም ተስፋዬ አለባቸው አለ። እኔ ወደፊት ሄጄ ስለምጫወትና ይሄም የአሰልጣኜ ውሳኔ ስለሆነ ጎል ለማስቆጠር እየቻልኩ ነው። አሁን ከያዝኩት አጨዋወት አኳያም ወደፊት የተሻለውን በሀይሉም የምንመለከትም ይመስለኛል”።
ስለ አጠቃላይ የሊጉ ውድድር
“ውድድሩን እንደምትጠብቀው አይደለም የምታገኘው። ዛሬ ያሸንፋል ያልከው ቡድን በተቃራኒ ሆኖ ይመጣብሃል። ትንሽ የምትለው ቡድን ትልቁን ነጥብ ሲያስጥለው ታያለህ። የ90 ደቂቃን ውጤትንም ነው በመመልከት ላይ ያለነው። ከእዚህ በመነሳትም ለቀጣዮቹ ጨዋታዎቻችን ከወዲሁ በጥሩ መልኩ ተዘጋጅቶ ስለመምጣትም እያሰብን ነው የምንገኘው”።
በውድድር ዘመኑ መቻልን እያስቆጩት ያሉት ጨዋታዎች
“እንደ ቡድን ብዙ ጨዋታዎች ያስቆጩኛል፤ አንዳንዶቹን እንደውም ከፈጣሪም ጋር ነው የማያይዘው። ምክንያቱም በብዙ ጨዋታዎች ላይ ጎል ጋር ደርሰን ስንስትና ለሰው አቀብለናል ብለንም እኛ ላይ ጎል ሲቆጠርብን ስናይና ከእዛ ውጪ ደግሞ ከአርባምንጭ ጋር ስንጫወት ሁለት ጎሎች ሲገባብን ሹት የተመቱት ኳሶች እንደ አሲስት ሆነው ነው። ሹት የመታው ልጅ ተበላሽቶበትም ነው ኳሷ ወደ ግብነት የተቆጠረችውምና በቃ እድለኛ ስላልሆንና ፈጣሪ ስላልፈቀደው ብለንም ነው የምናልፈው”።
ስለ ኳታሩ የዓለም ዋንጫ
“በውድድሩ ላይ ዋንጫውን እንዲበላ እፈልግ የነበረው ብራዚልን የነበረ ቢሆንም እሷን አጥተናታል። ያም ሆኖ ግን የሊዮኔል ሜሲ አድናቂ ስለነበርኩ ለእሱ ስል አርጀንቲና እንድትበላ በቀጣይነት ፈልጌ ያን ልታሳካ ችላለች። በውጤቱ ደስም ብሎኛል። ወደ ዓለም ዋንጫው አጠቃላይ ውድድር ስናመራ ደስ የሚል ፉክክር ነበረው። አፍሪካዊቷ ሞሮኮ በጣም የተደነቀችበትና ሰርፕራይዝም የሆነችበት ነበር። ብዙ አሪፍ አሪፍ ተጨዋቾችንም አይተንበታል። የእነ ሜሲንና ምባፔን ድንቅ ብቃትን ለማየትም ችለናል”።
በኳታሩ የዓለም ዋንጫ ምርጡ ጨዋታ
“ለእኔ ምርጡ ጨዋታ ብራዚል ከክሮሺያ ያደረገችው የሩብ ፍፃሜው እና አርጀንቲና ከፈረንሳይ ያደረገችው የፍፃሜ ጨዋታ ነው፤ እነዚህ ጨዋታዎች አዝናንተውኛልም። በተለይም ሜሲ ያለውን ሁሉ ለእግር ኳሱ ስለሰጠና ዋንጫውንም በማንሳቱ ደስ ልሰኝም ነው የቻልኩት”።
ስለ ትዳር ህይወትህ እና ስለ ባለቤትህ የምትለን ነገር ካለ
“የትዳሩን ሁኔታ በተመለከተ ይሄን ህይወት መስርቼው በጥሩ ሁኔታ ነው እየኖርኩት ያለሁት፤ አሁን ላይ የእኛ ህይወት ከክልል ክልል ሄደን ኳስን የምንጫወትበት ሁኔታም ስለሆነ ከሶስት ወራት በኋላም ነው
በናፍቆት ሰሞኑን እነሱን በማግኘት ከልጆቼ ከባለቤቴና ከባለቤቴ እህት ጋር ቤት ውስጥ ሆኜ ደስ በሚል ሁኔታም እያሳለፍኩ ያለሁት።
ባለቤቴን በተመለከተ ሜሮን ማንደፍሮ ትባላለች፤ የእግር ኳስን በጣም ትወዳለች። ትከታተላለችም። አንዳንዴ የሲቲ ካፕን ጨምሮ ሜዳ በመምጣት ጨዋታዎችን ያየችበት ጊዜም ነበር። የባለቤቴ ኳስ መውደድና ከጎኔ መሆን ለህይወቴ ብዙ አስተዋፅኦን እያደረገልኝም ነው። ከእዛ ውጪም እሷ ሁለት ልጆችን ማለትም የአራት ዓመት ዕድሜ ያለውን ናታን በሀይሉንና የዘጠኝ ወር ዕድሜ ያለውን ሌዊ በሀይሉንም ልታስገኝልኝም ችላለች በእዚሁ አጋጣሚ ስለ ሁሉም ነገሯ ላመሰግናት እፈልጋለሁ”።
በኳስ ህይወት ዘመንህ በጣም የተቆጨህበትና የተደሰትክበት ጊዜ
“በጣም የተደሰትኩት በ2006 ዓ/ም ላይ ሙገር ሲሚንቶ በነበርኩበት ሰዓት እንደ ግልም እንደ ቡድንም ጥሩ ስለነበርንና ሊጉንም በአራተኛ ደረጃ ላይ ሆነን ስላጠናቀቅን ነው። ያኔ እኔም በግሌ በምርጥ ብቃት ላይም ነበርኩና ያ ጊዜ ፈፅሞ አይረሳም። ጥሩ ወቅትን ስላሳለፍኩም በዓመቱ ወደ መቻል ልገባም ቻልኩ።
በኳሱ ቆይታዬ በጣም የተከፋሁበት ወቅት ደግሞ እኔ በቡድኑ ውስጥ ባልኖርበትም ሙገር በወረደ ጊዜ ነው። ከእዛ ውጪ የአሁኑ ቡድኔ መቻልም በ2011 ላይ ከያዘው ጥሩ የተጨዋቾች ስብስብ አኳያ አንዳንድ ወንጀሎችም ጭምር ተሰርቶበትና ውጤትም ተበላሽቶበት ከሊጉ የወረደበትን ጊዜ በኳስ ህይወቴ የማልረሳው አሳዛኙ ወቅት ነው”።
እናጠቃል
“የሊጉ ውድድር አሁን ላይ በዲ. ኤስ. ቲቪ እየታየ ነው፤ ጥሩ ጥሩ ችሎታ ያላቸውን አዳዲስና ወጣት ተጨዋቾችንም እየተመለከትን ነው። የእዚህ ጨዋታ መተላለፍ መቻል የሀገራችንን ኳስ ወደ ላይ ከፍ ያደርገዋል። አቡበከር ናስር ወደ ደቡብ አፍሪካ እንደሄደው ሌሎች ተጨዋቾችም ወደፊት ይወጣሉና ሁሉም ተጨዋች ራሱን ጠብቆ ወደ ተሻለ ነገር ለመምጣት መዘጋጀት ይኖርበታል፤ ከእዛም ውጪም በኳታሩ የዓለም ዋንጫ ላይ እንደተመለከትነው እንደ ሞሮኮ እና ሌሎች መሰል ከሆኑ ጥሩ ሀገራት ላይ ብዙ ልምዶችንም ብንካፈልና እግር ኳሳችን ተሻሽሎ ባይ በጣም ደስ ይለኛል”።