Google search engine

“በሊጉ የሚያሰጋን ቡድን ማንም የለም፤ እንደውም እኛን ነው የሚፈሩን” “በቶፕ አራት ውስጥ ሆነን ሊጉን እናጠናቅቃለን” ቃልኪዳን ዘላለም /ወላይታ ድቻ/

“በሊጉ የሚያሰጋን ቡድን ማንም የለም፤ እንደውም እኛን ነው የሚፈሩን”
“በቶፕ አራት ውስጥ ሆነን ሊጉን እናጠናቅቃለን”
ቃልኪዳን ዘላለም /ወላይታ ድቻ/
በወላይታ ድቻ እግር ኳስ ክለብ ታሪክ አሁን ላይ እየተመዘገበ የሚገኘው ውጤት አርኪ በመሆኑ የቡድኑን ደጋፊዎች እና አመራሮች እንደዚሁም ደግሞ ተጨዋቾቹንና የኮቺንግ ስታፍ አባላቱን ስኬቱ በጣም እያስደሰታቸው ይገኛል፤ ወላይታ ድቻ በዘንድሮ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ሻምፒዮና ቅ/ጊዮርጊስን በመከተል በሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ሲሆን የውድድር ዘመኑ ሲጠናቀቅ ክለባቸው በቶፕ አራት ውስጥ ሆኖ ሊጉን እንደሚያጠናቅቅ የቡድኑ ተጨዋች ቃልኪዳን ዘላለም ከሊግ ስፖርት ጋዜጠኛው መሸሻ ወልዴ /G.BOYS/ ጋር ባደረገው ቆይታም አስተያየቱን ሰጥቷል፤ ለወላይታ ድቻ በፊት መስመር የኮሪደር ስፍራ ላይ በመጫወት አበረታች እንቅስቃሴን እያሳየ የሚገኘው ቃልኪዳን ዘላለም በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ስኬታማ ውጤትን ከማምጣት አንፃር የቱ ቡድን ያሰጋችኋል የሚል ጥያቄም ቀርቦለት ምላሹን ሲሰጥ “በሊጉ እኛን የሚያሰጋን ቡድን ማንም የለም፤ እንደውም እኛን ይፈሩናል” ሲልም አስተያየቱን ጨምሮ ሰጥቷል፡፡
ከወላይታ ድቻው ቃልኪዳን ዘላለም ጋር በተለያዩ ጥያቄዎች ዙሪያ ያደረግነው ቆይታም የሚከተለውን ይመስላል፤ ተከታተሉት፡፡
በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ በሐዋሳ ከተማ እና በድሬዳዋ ከተማ ላይ ስለነበራቸው የአንደኛው ዙር የውድድር ተሳትፎ
“እንደ አጠቃላይ ሲታይ ውጤቱ ከእቅዳችን በላይ ያሳካነው ነበርና በጣም ጥሩ የሚባል ነው፤ በተለይም ደግሞ የድሬዳዋው ቆይታችን ከሐዋሳው የተሻለ እና አሪፍም ነበር”፡፡
የድሬዳዋ ከተማ ቆይታቸው ከሐዋሳ ከተማ የተሻለ ስለነበረበት ሁኔታ
“በሐዋሳ ሳለን አራት ጨዋታዎችን ተሸንፈን ነበር፤ ከዛም ድሬዳዋ ላይ በነበረን ቆይታ በክፍተቶቻችን ዙሪያ ላይ ሰርተን ስለመጣን የተሻለ ውጤት ልናመጣ ቻልን”፡፡
አሁን ላይ በስኬታማነት ውጤት ከመገኘታችሁ አንፃር በእዚህ ደረጃ ላይ እንገናኛለን ብላችሁ ጠብቃችሁ ነበር….?
“እኛ ያሰብነው የፊት የፊት ግጥሚያዎቻችንን ልክ እንደ ጥሎ ማለፍ ጨዋታዎች እያሸነፍን ስለመጓዝ ነበር፤ ውጤቱ እየቀናን ሲሄድ ግን ስለ ውጤት ማሰብ ጀመርን”፡፡
ላለመውረድ ይጫወት የነበረው ወላይታ ድቻ አሁን ላይ ከመሪዎቹ ክለቦች ተርታ ስለመሰለፉ
“አሪፍ ውጤት እንደምናመጣ እንጂ በእዚህ ደረጃ ላይ እንገኛለን ብለን አልጠበቅንም ነበር”፡፡
የውድድር ዘመኑ ሲጀመር ከውጤት ደረጃ ያቀዱት
“አንደኛው እቅዳችን በሊጉ መቆየት ነው፤ ሁለተኛው ደግሞ ቶፕ አራት ውስጥ ሆኖ ውድድሩን መጨረስ ነው”፡፡
በወላይታ ድቻ ክለብ ውስጥ ያለህ ቆይታህ ተመቸህ….?
“አዎን፤ አሪፍ ነው በጣምም ተመችቶኛል”፡፡
በበርካታ ጨዋታዎች ላይ ስለመሰለፉ
“ይህን እድል ማግኘቴ ለእኔ ብዙ ትርጉም አለው፤ አንደኛ ብቃቴ ከጨዋታ ወደ ጨዋታ እያደገ ነው የሚሄደው፤ ከዛ በዘለለ ደግሞ የመታየትም እድሉ ይኖረኛልና ይህንን ነው ለማለት የምፈልገው”፡፡
ለወላይታ ድቻ በአጥቂ ስፍራው ላይ እንደ መጫወትህ ግብ ከማስቆጠር አንፃር እልሜን እያሳካው ነው ትላለህ…..
“በፊት መስመርና በመስመር ስፍራ ላይ ስትጫወት የጎል እድሎችን ከመፍጠርም ጋር ሆነ ጎል ከማስቆጠር ጋር በተያያዘ ስኬታማ የምትሆንበት እድልህ አንድ አይደለምና ለዛ ነው ብዙ ጎሎችን ለማስቆጠር ያልቻልኩት፤ ከዛም በመነሳት ክለቤን ገና በምፈልገው መልኩም እያገለገልኩት አይደለምና ወደፊት በሚኖረኝ የተጨዋችነት ቆይታዬ ገና ወጣት ተጨዋችም ነኝና ብዙ ጥቅምን እንደምሰጥ እርግጠኛ ነኝ”፡፡
በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ የአንደኛው ዙር ውድድር ያስቆጨህ እና ያስከፋህ ግጥሚያ
“በጣም ያስደሰተኝ ጨዋታ ከሰበታ ከተማ ጋር ያደረግነውና ያሸነፍንበትን ነው፤ ያስቆጨኝ ደግሞ ብዙ የግብ ኳስ አግኝተን ለመሳት ችለናልምና ያን ነው የምጠቅሰው”፡፡
ባሳለፈው የእግር ኳስ ህይወቱ ደስተኛ ስለመሆኑ
“በጣም ደስተኛ ነኝ፤ ፈጣሪ ከፈቀደም ወደፊት ብዙ ነገሮችን እሰራለው ብዬም አስባለሁ”፡፡
በኳስ ህይወትህ ስለተከፋህበት ሁኔታስ
“የለም”፡፡
የኢትዮጵያ ቡናው አቡበከር ናስር ዓምና የውድድሩ ክስተት ሆኖ ነበር፤ በዘንድሮው የአንደኛው ዙር ውድድርስ የቱ ተጨዋች ጎልቶ ወጣ…?
“ለእኔ ጎልቶ የወጣብኝ ተጨዋች የቅ/ጊዮርጊሱ ኢስማሄል ጎሮ አጎሮ ነው፤ እሱ ነው ለየት ያለብኝ”፡፡
በእግር ኳስ ተጨዋችነት ቆይታው ራሱን የት ጫፍ ላይ ማስቀመጥ እንደሚፈልግ
“የመጀመሪያው እና ዋንኛው ዓላማዬ በሊጉ ከሚገኙት ምርጥ አጥቂዎች ተርታ ራሴን ማሰለፍ መቻል ነው፤ ከዛ በኋላ ደግሞ ስለ ሌሎች ነገሮች ማሰብን ትጀምራለህ”፡፡
የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ የሁለተኛው ዙር በአዳማ ከተማ እና በባህርዳር ከተማ ላይ ይካሄዳል፤ የሚኖራችሁ ተሳትፎ ምን ይሆናል?
“የሁለተኛው ዙር ውድድር በጣም ከባድ ነው፤ ወራጁና ሻምፒዮናው ቡድንም የሚለይበት ስለሆነ ግጥሚያዎቹም ሁሉ ይጠነክራሉ፤ ከዛም በመነሳት እኛ ለእዚህ ውድድር ተሳትፎአችን እንደ ዝግጅት በክፍተቶቻችን ላይ ጥሩ ነገርን እየሰራን ስለመጣን በቶፕ አራት ውስጥ ሊጉን እንጨርሳለን”፡፡
በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ቅ/ጊዮርጊስን በመከተል በሁለተኛ ደረጃ ላይ ትገኛላችሁ፤ የቱ ቡድን እናንተን ያሰጋችኋል?
“በሊጉ የሚያሰጋን ቡድን ማንም የለም፤ እንደውም እኛን ነው የሚፈሩን”፡፡
በዘንድሮ የውድድር ዘመን ተሳትፎአችሁ ጠንካራ እና ደካማ ጎናችሁ ምንድን ነው?
“በጠንካራ ጎንነት የሚገለፅልን የመጫወት ፍላጎታችን ላይ ነው፤ በተለይም ደግሞ በማጥቃቱና በመከላከሉ ላይ ያለን ብቃት ጥሩም ስለሆነ ይሄ ነው ለውጤት እያበቃን የሚገኘው፤ በክፍተት ደረጃ ደግሞ ያለብንን ችግር እስካሁን እኔ አልተመለከትኩም”፡፡
የወላይታ ድቻ ደጋፊዎች እንዴት እና በምን መልኩ ይገለፃሉ?
“ደጋፊዎቻችን ምርጦች እና በየውድድሩ ስፍራም በመምጣት እኛን እያነቃቁን የሚገኙ ናቸው፤ ለውጤታማነታችንም እንደ 12ኛ ተጨዋች ሆነውም እያገለገሉን የሚገኙም ናቸውና አሁን ላይ የያዝነውን ውጤት አጠንክረን በመጓዝ እነሱን ልናስደስታቸው ተዘጋጅተናል”፡፡
አንድ ነገር በልና እናጠቃል…
“ቤትኪንጉ በጣም ጥሩ ፉክክር እየተደረገበት ነው፤ ሊጉ አንድ ደረጃም ከፍ ብሏል፤ ከእዚህ በኋላም ውድድሩ እየጠነከረም ነው የሚሄደውና ሁለተኛው ዙርም ከአንደኛው ዙር በበለጠ በድምቀት ደረጃም ለየት ብሎ ይቀርባል ብዬም እጠብቃለው”፡፡

spot_img
ተመሳሳይ ጽሁፎች

አስተያይት ያስፍሩ

እባክዎን አስተያይትዎን ያስፍሩ
እባክዎን ስምዎን እዚህ ያስገቡ

ትኩስ ዜናዎች

%d bloggers like this:
P