Google search engine

“በሐዋሳ ከተማ መለያ ብቻ ለ12 ዓመታት ለመጫወት መቻሌ ለእኔ ትልቅ ታሪክ ነው፤ የኳስ ጊዜዬንም በዚሁ ቡድን ካጠናቀቅኩም ደስታዬ እጥፍ ድርብም ነው የሚሆነው” አዲስዓለም ተስፋዬ /ሐዋሳ ከተማ/

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ለአንድ ክለብ ብቻ ለ12 ዓመታት የተጫወተው ተጨዋች

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የተጨዋችነት ዘመን ቆይታው ሐዋሳ ከተማን ለ12 ዓመታት በመጫወት ማገልገሉን ይናገራል፤ ይሄ ተጨዋች አዲስዓለም ተስፋዬም ይባላል፤ ጥሩ ችሎታ ያለው የተከላካይ ስፍራ ተጨዋችም ነው፤ በቀጣይ ጊዜ የቡድኑ ቆይታም በዚሁ ቡድን መለያ ብቻ የኳስ ጊዜውን ቢያጠናቅቅ ደስታው እጥፍ ድርብ ሊሆንለት እንደሚችልም ለዝግጅት ክፍላችን አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡
የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ለእዚህን ያህል ዓመት በአንድ ክለብ መለያ ብቻ ተወስኖ በመጫወት በብዙዎቹ ዘንድ አግራሞትን እየፈጠረለት እንደሆነና ደስተኛ መሆኑንም የሚናገረው ይኸው ተጨዋች ስላሳለፋቸው የኳስ ህይወቱ ብዙ ብሏል፤ ከእነዛ መካከልም “ለረጅም ዓመታት በአንድ ክለብ ብቻ ተወስኖ ኳስን ለመጫወቱም ጠንካራ ሰራተኛ መሆኑና የባለቤቱም ከፍተኛ እገዛ አስተዋፅኦ እንዳበረከተለትም ይናገራል፤ ከዚህ ቤተሰቡ ውስጥ ካሉት አንድ ወንድሙ እና አራት እህቶቹ ውስጥ ሁለተኛ ልጅ ሆኖ ይህቺን ዓለም የተቀላቀለው ተጨዋች ከሊግ ስፖርት ለቀረቡለት ጥያቄዎች ምላሹን በሚከተለው መልኩ ሰጥቷል፡፡
ሊግ፡- ለሐዋሳ ከተማ በመጫወት ብቻ 12ኛ ዓመትን ልትይዝ ችለሃል፤ የፕሪምየር ሊጉ ውድድር ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶም በእዚህ መልኩ የተጫወተን ተጨዋች ማግኘት ከባድ ሆኗል፤ ይሄን ስታይ መታደል ነው ማለት ይቻላል?
አዲስዓለም፡- በጣም፤ ለአንድ ክለብ ብቻ በመጫወት 12 ዓመት፤ ይሄ በጣም የሚገርም ታሪክ ነው፤ በሊጉ የውድድር ቆይታም ለእዚህን ያህል ዓመት የተጫወተ ተጨዋችን ሰምቼም አላውቅ፤ ምን አልባት ብዙ ተጨዋቾች የተለያዩ ክለቦችን ቀይረው ለበርካታ ዓመታት ተጫውተዋል፤ ለአንድ ክለብ ብቻም ደግሞ ከእኔ ያነሰ ዓመት የተጫወቱ ተጨዋቾችም አሉ፤ የእኔ ግን ይለያል፤ ላሳደገኝ ክለቤ ብቻ ለ12 ዓመት ለመጫወት መቻሌ ከመታደል አልፎ ልዩ የደስታ ስሜትንም ነው እየፈጠረብኝ የሚገኘው፡፡
ሊግ፡- የሌላ ክለብን ማልያ ሳትለብስ ለሐዋሳ ከተማ ብቻ ለእዚህን ያህል ዓመታት የመጫወት ሚስጥርህ ምን ይሆን?
አዲስዓለም፡- ምንም ሚስጥር የለውም፤ በክለቡ ለመቆየት እና ለበርካታ ዓመታትም ለመጫወት የቻልኩበት ዋንኛው ምክንያት የመጀመሪያው ሁሌም እንደ ቡድንም ሆነ እንደ ግል ተገቢ የሚባሉ ልምምዶቼን ጠንክሬ የምሰራ ተጨዋች ስለሆንኩ ነው፣ ከዛ ውጪ ደግሞ ራሴን ስለምጠብቅ፣ አስፈላጊ የሆኑ እረፍቶችን ስለማደርግ፣ ቡድኑ ያደግኩበት ስለሆነና በምሰለፍባቸው ጨዋታዎች ላይም ተመሳሳይ የሆኑ ጥሩ አቋሜን በሜዳ ላይ ስለማሳይና ከክለቡም ጋር እንደ ቤተሰብ ያህል የምንተያይ በመሆናችንም ተፈላጊ ተጨዋች ሆኜ ነው ለእዚህን ያህል ጊዜ ለክለቡ ለመጫወት የቻልኩት፡፡
ሊግ፡- ለሐዋሳ ከተማ በምትጫወትበት ሰዓት የሌሎች ክለቦች ጥሪ አልደረሰህም?
አዲስዓለም፡- በተደጋጋሚ ጊዜ ነው የደረሰኝ፤ ያም ሆኖ ግን ሌሎች ክለቦች ለእኔ የሚያቀርቡልኝ ክፍያ የእኛው ክለብ ካቀረበልኝ አንፃር ብዙም ልዩነት የሌለው በመሆኑና ያደግክበትን ክለብ ደግሞ በእዚህ መልኩ መልቀቅ አስፈላጊ ነው ብዬ ስለማላስብ ለሐዋሳ ከተማ ቡድን ለበርካታ ዓመታት እየተጫወትኩ እገኛለው፡፡
ሊግ፡- ለሐዋሳ ከተማ በቀጣዩ ዓመት የምትጫወተው ውልህን አራዝመህ ነው ወይንስ ቀሪ ውል ኖሮህ?
አዲስዓለም፡- ውሌንማ ጨርሼ ነበር፤ ያም ሆኖ ግን ለክለቡ እየሰጠሁት ካለው ጥሩ ግልጋሎት አንፃር ነው አድሼ የመጪም የውድድር ዘመን ላይም ኳስን ልጫወት እየተዘጋጀው የምገኘው፡
ሊግ፡- በሐዋሳ ከተማ የረጅም ዓመታት የተጨዋችነት ቆይታህ አንተን ያጋጠሙህ ጥሩ እና ጥሩ ያልሆኑ ጉዳዮች ምንድን ናቸው?
አዲስዓለም፡- በእግር ኳስ ጨዋታ ዘመኔ ከፋ በሚባል ደረጃ ያጋጠመኝ የኳስ ህይወት እስካሁን የለም፤ አብዛኞቹን ስመለከታቸውም ለእኔ ጥሩ ጊዜያቶች ናቸው፤ ምንአልባት ግን ጥሩ ወቅት አላጋጠመኝም ብዬ ልናገር የምችለው አንዴ ብቻ እኔን ያሳዘነኝ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶብኝ ከሜዳ ለሶስት ወራት የራቅኩበት ሁኔታ አጋጥሞኛልና ያን ነው ልጠቅስ የምፈልገው፤ እንደዛም ሆኖ ግን ወዲያው ራሴን ስለምጠብቅ ብቻ በፍጥነት ከህመሜ በማገገም ወደ ሜዳ የተመለስኩበት ሁኔታም ነበርና ያ ደግሞ በጣም አስደስቶኛል፡፡
ሊግ፡- ወደ እግር ኳስ ተጨዋችነቱ ባትመጣ ኖሮ በምን ሙያ ላይ እናገኝህ ነበር?
አዲስዓለም፡- በንግድ ነዋ! በተለይ ወላጅ አባቴ ጊዜውን ሁሉ የሚያሳልፈው በዛ ስለሆነም እሱን ጭምር በስራው አግዘውም ነበር፡፡
ሊግ፡- የእግር ኳስ ተጨዋች ለመሆን ተቸግረህ ነው የመጣኸው? የቤተሰብህ ተፅህኖስ ነበረብህ?
አዲስዓለም፡- በፍፁም፤ ምንም አይነት ተፅህኖም ሆነ ክልከላ ሳይኖርብኝ ነው ወደ ኳስ ተጨዋችነቱ ለመምጣት የቻልኩት፤ በተለይ ኳስ ተጨዋች ለመሆን እንድችልም የታላቅ ወንድሜም ኳስን መሞካከርና እሱንም ለመመልከት መቻሌም ሌላው አጋዥ ሀይል ሆኖኛልና በዛም ነው የኳሱ ስሜት አሸንፎኝም በምንም ነገር ሳልቸገር ወደ ኳስ ተጨዋችነቱ ሙያ ዘልቄ ልገባ የቻልኩት፡፡
ሊግ፡- በሐዋሳ ከተማ የተጨዋችነት ቆይታህ ለረጅም ዓመታት በስኬታማነት ለመጫወት ብትችልም እንደ አንድ እግር ኳስ ተጨዋች ደግሞ ያላሳካካቸው ነገሮች አሉ፤ ስለእነዛ ምን ትላለህ?
አዲስዓለም፡- ልክ ነህ፤ ጥሩ ችሎታውና አቅሙ ኖሮኝ የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ ከዚህ ክለብ ጋር አላነሳውም፤ ከዛ በተጨማሪም ለብሔራዊ ቡድን ልመረጥ ባለመቻሌም ሀገሬን ለበርካታ ጊዜያቶች ለማገልገል አልቻልኩም፤ ሌላው ደግሞ ካለኝ ጥሩ ችሎታ አኳያም የራሴ ኤጀንት ኖሮኝ ወደ ውጪ ሀገር በመውጣትም ለመጫወት ጥረቶችን ያላደረግኩባቸው ጊዜያቶችም አሉና እነዚህ በጣም የሚቆጩኝ ነገሮች ናቸው፡፡
ሊግ፡- ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተመርጦ የመጫወት አቅሙ አሁን ላይ አብሮህ አለህ?
አዲስዓለም፡- አዎን፤ ይሄን በድፍረትም ነው ልነግርህ የምፈልገው፤ ያን ለማሳካትም ራሴን ማስተካከል እና ያለብኝንም ችግር መቅረፍ ብቻ ነው የሚጠበቅብኝ፤ ይሄን ደግሞ ልመረጥ እንጂ መጫወት እንደምችል በሜዳ ላይ አቅሜን አሳያለው፤ በአዲስ ዓመት ላይ ደግሞ በኳሱ በጥሩና ወጥ በሆነ አቋሜም እንደምቀርብ የምትመለከቱኝም ነው የሚሆነው፡፡
ሊግ፡- በሐዋሳ ከተማ የተጨዋችነት ቆይታህ ምርጡ የውድድር ጊዜያችን ብለህ በዋናነት የምትጠቅሰው የቱን ነው?
አዲስዓለም፡- አንዴ ነው፤ ያኔ በጥቃቅን ስህተቶች የሊጉንም ዋንጫ ልናጣም ችለናል፤ በዛን ዓመት ሊጉን በሶስተኝነት በፈፀምን ሰዓት ሁለተኛ ሆኖ ባጠናቀቀው በኢትዮጵያ ቡናም በሁለት ነጥብ ብቻ ተበልጠንም ውድድሩን የፈፀምንበት ሁኔታም ስለነበር የዛን ዓመት ላይ የነበረን ቡድን ለእኔ ምርጡ ነበር፡፡
ሊግ፡- ለሐዋሳ ከተማ ያደረግከውን የመጀመሪያ ጨዋታህን ታስታውሳለህ?
አዲስዓለም፡- አዎን፤ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ነበር፤ በዛ ጨዋታ የቡድናችን ተከላካይ አንዱዓለም ነጋ /ቢጣ/ ተጎድቶ ከሜዳ ሲወጣ እኔ ነበርኩ ተቀይሬ የገባሁት ይሄ ጨዋታም ከቢ ቡድን አድጌ የተጫወትኩበት የመጀመሪያዬ ጨዋታም ሊሆን ችሏል፡፡
ሊግ፡- ሐዋሳ ከተማ የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ ለሁለት ጊዜ ለማንሳት ችሏል፤ በእናንተ ጊዜስ ይሄ ድል ይሳካል?
አዲስዓለም፡- ይመስለኛል፤ የሊጉን ዋንጫ የማንሳት እና ሻምፒዮና የመሆን አቅሙ አለን፤ ሆኖም ግን ወደ ክልል ለጨዋታ ስንወጣ በሜዳ ላይ የሚያጋጥሙንን አንድአንድ ችግሮችን በወጣቶች የተገነባው የእኛ ቡድን ተጨዋቾች ሊቋቋሙት ስላልቻሉ ይሄ ሊጎዳን ችሏል፤ በቀጣይ የውድድር ጊዜ ግን ይህን ሁኔታ የቡድናችን ተጨዋቾች ከስነ-ልቦናው አኳያ ለመቋቋም ከቻሉ ዋንጫውን በእኛ ጊዜም የማናነሳበት ምክንያት ምንም አይኖርም፡፡
ሊግ፡- በሳላፍከው የእግር ኳስ ተጨዋችነት ዘመንህ የራሴ ድክመት እና ክፍተት የምትላቸው ነገሮች የትኞቹ ናቸው?
አዲስዓለም፡- በጨዋታ ወቅት ስሜታዊ የምሆንበት ነገር ነበር፤ ተደጋጋሚ ካርዶችንም እመለከት ነበር፤ ያን ችግሬን ግን አሁን ላይ ከጨዋታ ወደ ጨዋታ ባመራሁበት ሰዓት ላሻሽለው በቅቻለው፡፡
ሊግ፡- ሐዋሳ ከተማ የቀድሞ ስምና ዝናውን ይመልሳል?
አዲስዓለም፡- በእርግጠኝነት አዎን ነው የምልህ፤ ለዛም በምክንያትነት የማስቀምጥልህ ነገር በክለቡ አሁን ላይ ያለው ሁኔታ በጣም ጥሩ ስለሆነ፣ ቡድናችንም በአብሮነት ስለዘለቀና በወጣት ተጨዋቾችም የተገነባ አስተማማኝ ቡድን ስለሆነ፤ ከዛ ውጪ ደግሞ አሰልጣኙ ሙሉጌታ ምህረትም ቢሆን ከእኛ ጋር ተጫውቶ ያሳለፈና ስለ ክለቡ ታሪክና ባህልም የሚያውቅ በመሆኑም ይሄ እኛን ተጠቃሚ ያደርገናል፡፡
ሊግ፡- ለ12 ዓመታት የዘለቀውን የእግር ኳስ ተጨዋችነት ዘመን ቆይታህን ባሳደገህ እና እስካሁንም ድረስ የሌላ ክለብ ማልያን ሳትለብስ በተጫወትክበት ክለብህ ሐዋሳ ከተማ ማሊያ የምታጠናቅቅ ይመስልሃል?
አዲስዓለም፡- እንደዛ ቢሆን ደስ ይለኛል፤ ማጠናቀቅ የምፈልገውም በዛ መልኩ ነው፤ ምክንያቱም በአገራችን የእግር ኳስ ጉዞ አሁን ላይ እንደምንሰማቸው የኢትዮጵያ ቡናው የቀድሞ ተጨዋች አሸናፊ በጋሻው አይነት ለአንድ ክለብ ብቻ በመጫወት ታሪካዊ ተጨዋችም መባልን ስለምፈልግ ነው፤ በሐዋሳ ከተማ የተጨዋችነት ዘመን ቆይታዬ እስካሁን ድረስ የፕሪምየር ሊጉ ውድድር ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ በአንድ ክለብ መለያ ለረጅም ዓመታት የተጫወትኩ ተጨዋች እኔው ነኝ፤ ከክልል ክለቦችም በአንድ ክለብ ውስጥ ለረጅም ዓመታት የተጫወትኩት አሁንም እኔው ነኝና በዛ እድለኛ ነኝ፤ ፈጣሪ ከፈቀደ ብቻ ደግሞ በሐዋሳ ከተማ ክለብ ማልያ የኳስ ዘመኔን ባጠናቀቅ በጣሙን ነው ደስ የሚለኝ፡፡
ሊግ፡- በእስካሁን የተጨዋችነትህ ጉዞ ከአንተ የእግር ኳስ ህይወት ጀርባ እነማን ነበሩ?
አዲስዓለም፡- ቤተሰቦቼ፣ ባለቤቴ እና ከስር ጀምሮ አሰልጥነውኝ ያለፉ፤ እነሱም እንደ እነ ጋሽ ከማልና ተመስገን ዳናን የመሰሉ አሰልጣኞች አሉና ለእነሱ ትልቅ የሚባል ቦታ አለኝ፤ እነዚህን የእግር ኳሱ ባለሙያዎች መቼም ቢሆን አልረሳቸውም ፤ ከእነሱ ውጪም ሌሎችም ከጎኔ ሆነው የሚያበረታቱኝ አካላቶች አሉም ከእነዛ መካከልም ለወላይታ ድቻ የሚጫወተው ጓደኛዬ ዘላለም ታደለም የሚመክረኝ እና የሚጠቀስም ነውና በአጠቃላይ ሁሉንም ለማመስገን ነው የምፈልገው፡፡
ሊግ፡- ስለ ባለቤትህ ምን ትለናለህ? ማንስ ትባላለች?
አዲስዓለም፡- ባለቤቴ የውብዳር በየነ ትባላለች፤ ስለ እሷ ለመናገር የምፈልገውም በጣም ጥሩ የሆነች የትዳር አጋሬ እንደሆነች ነው፤ ከዛ ውጪም ሁሌም ትፀልይልኛለች፤ ከቤት ወጥቼ እስክገባ ድረስም ትጨነቅልኛለች፤ ሌላው ደግሞ ጠንካራ ሴት መሆኗ ለእኔ የጠቀመኝ ነገር ስላለና በኳሱም ለብዙ ዓመታት ለመቆየቴ ዋናዋ ሚስጥሬ ስለሆነችም ለእሷ ሁሌም ነው ከፍተኛ ቦታም የምሰጣት፡፡
ሊግ፡- በኮቪድ 19 ለረጅም ዓመታት ከእግር ኳሱ ርቅሃል፤ ያ በመፈጠሩ ምን አይነት ስሜት ተሰማህ??
አዲስዓለም፡- ከኳስ ለእዚህን ያህል ጊዜ መራቅ በጣም ያሰለቻል፤ ከባድ ሁኔታም ነው ሊፈጠርብኝ የቻለው፤ በተቃራኒነት ስታየው ደግሞ ከቤተሰቦቼ ጋር ሆኜ ረጅሙን ወቅት እያሳለፍኩም ነውና ያ ደግሞ ያስደሰተኝ ነገር ነው፤ በአጠቃላይ ግን ከኳሱ በኮቪድ ምክንያት እኔም ሆንኩ ሌሎች ስፖርተኞች ለመራቅ እንድንችል ሁሉንም ነገር ፈጣሪ ያመጣው ነገር ስለሆነ ያን መቀበል የግድ ነው የሚለን፡፡
ሊግ፡- በኮቪድ 19 ወቅቶቹን በምን መልኩ እያሳልፍክ ነው?
አዲስዓለም፡- አብዛኛውን ጊዜዬን ከባለቤቴ እና ከሁለቱ ልጆቼ ቃልአብ እና ከነዓን ጋር ነው የማሳልፈው፤ አልፎ አልፎ ደግሞ የሩጫ ልምምድን እሰራለው፡፡
ሊግ፡- በህዳሴው ግድብ ሙሌት ዙሪያ አንድ ነገር ብትል?
አዲስዓለም፡- የህዳሴ ግድቡን ሙሌት አስመልክቶ መናገር የምፈልገው በእኛ ዘመን ይህ ጉዳይ እውን ለመሆን በመቻሉ በጣም ነው ደስ ያለኝ፤ ምክንያቱም ለዘመናት ስንጓጓለት የነበረውን እና አባይን ለሌላ አካል ስንገብር የነበረበት ሁኔታም አለና አሁን ላይ ግን እኛ በራሳችን ሀብት ተጠቃሚ በመሆናችን ያ ያስደስተኛል፡፡
ሊግ፡- የእግር ኳሱ ዳግም እንዲመለስ ምን ትላለህ?
አዲስዓለም፡- ለዛ ፈጣሪ ይርዳን፤ ሁሉም ነገር ጥሩ ሆኖ ወደ ኳሱ ከተመለስንም በጣም ደስ ይላል፡፡
ሊግ፡- በእግር ኳሱ አርአያ የሆነ ተጨዋች ማን ነበር?
አዲስዓለም፡- የቀድሞ የሐዋሳ ከተማ እና የብሄራዊ ቡድናችን ተጨዋች ዘውዱ በቀለ ነው፤ እሱ የወንድሜ ጓደኛም ስለነበር ያኔ የእነሱን ትጥቅ በመያዝም ነበር እነሱን በመመልከት ጭምር ተምሳሌቴ ላደርገው የቻልኩት፡፡
ሊግ፡- ሐዋሳ ከተማ በ1996 የሊጉን ዋንጫ ሲያነሳ አንተ የት ነበርክ?
አዲስዓለም፡- ያኔ ልጅ ነበርኩ፤ ወደ ስታድየም ለመግባት ስላልቻልኩ ለኳሱ ካለኝ ፍቅር የተነሳ ከውጪ ተራራ ላይ ሆኜ በደንብ ባይታየኝም ትንሽ ትንሽ በጨረፍታ ኳሱን ስመለከት ነበር፡፡
ሊግ፡- በመጨረሻ …?
አዲስዓለም፡- ኮቪድን በተመለከተ ነው ለመናገር የምፈልገው፤ አሁን ላይ ህብረተሰቡ ዘንድ በጣም መዘናጋቶች ይታያሉ በወረርሽኙም እየተጠቁና እየሞቱ ነው፤ ስለዚህም ማስተላለፍ የምፈልገው ነገር በጥንቃቄ ይሄን ጊዜ እንድናልፈው ነው፡፡

spot_img
ተመሳሳይ ጽሁፎች

አስተያይት ያስፍሩ

እባክዎን አስተያይትዎን ያስፍሩ
እባክዎን ስምዎን እዚህ ያስገቡ

ትኩስ ዜናዎች

%d bloggers like this:
P