Google search engine

“በመሀል ሰፋሪነት ሊጉን ልናጠናቅቅ ተዘጋጅተናል” “ኔይማርን በሁሉም መልኩ የምወደውና የማደንቀው ተጨዋች ነው” እዮብ አለማየሁ  /ጅማ አባጅፋር/

“በመሀል ሰፋሪነት ሊጉን ልናጠናቅቅ ተዘጋጅተናል”

“ኔይማርን በሁሉም መልኩ የምወደውና የማደንቀው ተጨዋች ነው”

እዮብ አለማየሁ  /ጅማ አባጅፋር/

ጅማ አባጅፋር  ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በአጥቂው ክፍል ላይ ከሚጠቀምባቸው ተጨዋቾች  መካከል ወጣቱ  እዮብ አለማየሁ  ይጠቀሳል፤ ይህ ተጨዋች ከአጥቂው ክፍል በተጨማሪ በኳስ ህይወቱ የመስመር አጥቂ ሆኖም ተጫውቷል፤  በወላይታ ድቻ የኳስ ህይወቱን የጀመረው ይኸው ተጨዋችን በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ክለባቸው እያደረገ ስላለው የውድድር ተሳትፎ ዙሪያና ስለ ራሱ እንደዚሁም ደግሞ ከኳስ የህይወት ጉዞው ጋር በተገናኘ  ከሊግ ስፖርት ጋዜጠኛው መሸሻ ወልዴ ጋር  ቆይታ አድርጎ ነበርና አስተያየቱን በሚከተለው መልኩ ሰጥቷል።

ስለ ውልደቱ እድገቱና የኳስ ጨዋታ አጀማመሩ

“ተወልጄ ያደግኩት ከወላይታ ሶዶ 17 ኪሎ ሜትር በሚርቀው ጉኖ ከተማ ላይ ሲሆን ኳሱን የጀመርኩትም በልጅነት ዕድሜዬ ላይ በእዛው አካባቢ ነው”።

ከቤተሰባቸው አባላት ውስጥ ስፖርተኛው እሱ ብቻ እንደሆነ

“አራት እህቶችና አንድ ወንድም ያለኝ ቢሆንም ስፖርተኛው እኔ ብቻ ነኝ”።

የልጅነት ዕድሜው ላይ ኳስ በመጫወቱ በኩል ይከለከል እንደነበር

“አዎን፤ ትምህርትን እንድማር ይፈለግ ስለነበር ኳስን  እንዳልጫወት ይፈለግ ነበር፤ ያም ሆኖ ግን የኳሱ ስሜት ከባድ ስለነበር በኋላ ላይ መጫወቱ ሊፈቀድልኝ ችሏል”።

ስለ መጀመሪያው  ክለቡ

“ወላይታ ድቻ የመጀመሪያ ክለቤ ነው፤ ከወረዳ ውድድር ላይም ነበር ልጅ ሳለው ለቡድኑም የተመረጥኩት፤ ወደ ቡድኑ  ስገባም በቅድሚያ ለu-17 አሰልጣኝ ዘነበ ፍስሃ በያዘው ጊዜ ተመረጥኩ ጥሩ ቆይታ ስለነበረኝም  ወደ ዋናው ቡድን አደግኩ”።

በልጅነት ዕድሜው አድንቆት ስላደገው የሀገር ውስጥና የባህርማዶ ተጨዋች

“ከሀገር ውስጥ ተጨዋቾች አድንቄ ያደግኩት ሳላህዲን ሰይድን ሲሆን ከባህርማዶ ደግሞ የኔይማርና ሲቀጥል ደግሞ የክርስቲያኖ ሮናልዶ አድናቂ ነኝ፤ እነሱም ናቸው ተምሳሌቶቼ”።

ስለ ሊጉ የመጀመሪያ ጨዋታው

“በሐዋሳ ከተማ ላይ ተካሂዶ በነበረው የሲቲ ካፕ ውድድር  ላይ ነበር ለመጀመሪያ ጊዜ በአሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ አማካኝነት ቡድኑ በሚመራ ሰዓት  የተሳተፍኩት፤  ያኔ ለኢትዮጵያ ወጣት ቡድንም በመመረጥ ከእነ አቡበከር ናስር ጋርም የተጫወትኩበት ጊዜያትም ስለነበር በእዛም ጨዋታ ላይ  እሱ ደፋር ሆኖና በእኔም ላይ ተማምኖ  አሰልፎኝ ይህን ግጥሚያን በጥሩ ብቃት ላይ  ሆኜ በማድረጌ  በጣም ነው የተደሰትኩት”።

ከእግር ኳስ መጫወት ውጪ በትምህርቱ ላይ ስላለው ተሳትፎ

“የ12ኛ  ክፍል ትምህርቴን ካጠናቀቅኩኝ በኋላ ወላይታ ከተማ ውስጥ በሚገኘው usa  ኮሌጅ ውስጥ በአካውንቲንግ ቢዝነስ  ማኔጅመንት የርቀት ትምህርትን በመማር በዲፕሎማ ልመረቅ ችያለው”።

ስለ መጀመሪያ ግቡ

“የመጀመሪያው ግቤ 2010 ላይ በፋሲል ከነማ ላይ ያስቆጠርኩት ነው፤ በዛ ግቤም በጣም ተደስቻለው፤ በጨዋታው ላይም  ፋሲል ከነማ ላይ ሀትሪክ ሰርቻለው”።

ምርጡ ጓደኛው

“ለቅ/ጊዮርጊስ የሚጫወተው የቀድሞው የወላይታ ድቻው ተጨዋች በረከት ወልዴ ጓደኛዬ ነው፤  ከእሱ ጋር በጣም ጥሩ  ቅርርብም አለን”።

ከእግር ኳስ ውጪ ስለሚወደው ነገርና ጊዜውን ስለሚያሳልፍበት ሁኔታ

“መፅሀፍ ማንበብ በተለይም ደግሞ  የመፅሀፍ ቅዱስን ሳነብ በጣም ይመቸኛል፤  የምወደውም ያን ነው፤  ከእዛ ውጪ ሌላው የሚመቸኝ ደግሞ መንፈሳዊ መዝሙሮችን ማድመጥ መቻሌ ነው፤ ከኳሱ ውጪ ብዙ ጊዜዬን የማሳልፈው በልምምድ ነው”።

ከባህርማዶ ቡድኖች የሚደግፈው

“ቼልሲን ነው፤ በተለይም ደግሞ  ሀዛርድ እያለ በጣም አደንቀው ስለነበር ደጋፊያቸው ልሆን ችያለው”።

ስለ አለባበስ ምርጫው

“ሙሉ ነጭ ወይንም ደግሞ ሙሉ ጥቁር ልብስን ማድረግ በጣም ይመቸኛል፤ ያ ነው ምርጫዬ”።

ብዙ ጊዜ ለመጎብኘት የሚያስበው ቦታ

“ኔይማር  በእነዚህ አገራቶች ላይ ስለማይጠፋ ፈረንሳይና ብራዚልን መጎብኘት ቀዳሚው ምርጫዬ ነው”።

በዓለም ላይ በቀዳሚነት ማግኘት የሚፈልገው ሰው

“በጣም ስለምወደው ኔይማርን ማግኘት ነው የምፈልገው”።

ስለ ግል ባህሪው

“ፀባይኛ ነኝ፤ ከማንም ጋርም ተጣልቼ አላውቅም”።

ከቤቱ ሲነሳ በተደጋጋሚ የሚሄድበት ቦታ

“በወላይታ እያለውም ሆነ አዲስ አበባ በምመጣበት ሰዓት ጊዜዬን የማሳልፈው ከጓደኞቼ ጋር ካፌ ውስጥ በመገናኘት በመጨዋወት ነው”።

በሊጉ  እያደረጉት ስላለው  ተሳትፎ

“በውድድሩ ላይ  በነበረን  ቆይታችን ሐዋሳ ላይም ሆነ ድሬዳዋ ላይ ስንጫወት በአቋም ደረጃ  ልዩነት ነበረን፤  በሐዋሳ ሳለን  ረጅም ጊዜን ነው በጨዋታ ያሳለፍነው ና  ቡድናችን  ወደሚፈልገው የጨዋታ ሪትም ለመምጣት  በአዲስ መልክ እየተሰራ ስለነበር  በመቀናጀቱና  በመዋቀሩ በኩል ወጣ ገባ ያለ እንቅስቃሴን ነው ስናሳይ የነበረው፤ እኔም ለቡድኑ አዲስ ስለሆንኩም በተወሰነ መልኩም ቢሆን ተቸግሬ ነበርና ይሄን ልመለከት ችያለሁ። ወደ ድሬዳዋ ከብሄራዊ ቡድናችን የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ  ቆይታና እረፍት በኋላ  ስንመጣ ደግሞ  ምንም እንኳን በወልቂጤ ከተማ ቡድን ሽንፈትን ሰሞኑን አስተናገድን እንጂ አሁን ላይ ያለን አቋም በብዙ ነገሮች እየተስተካከለልን ነው፤ ከእዚህ በኋላም ነጥብ ላለመጣል የምንጫወትበት ሁኔታም ስለሚኖር የቡድናችን ውጤት ይቀየራል”።

ስለ ቡድናቸው ጠንካራና ክፍተት ጎን

“በማጥቃቱ ላይ ከወገብ በላይ ጠንካራ ነን፤ በክፍተት ደረጃ የማነሳው ደግሞ ከኋላ በኩል በመከላከሉ ረገድ እንደ ቡድን ችግር ያለብን መሆኑ ነውና ይህን ክፍተት ቶሎ ልንቀርፈው ይገባናል”።

በውድድር ዘመኑ ጅማሬ ሊያመጡት አቅደው ስለነበረው ውጤትና አሁን ላይስ….

“ሊጉ ሲጀመር መሀል ሰፋሪ ላይ  ሆኖ ውድድሩን ማጠናቀቅን ነበር ያቀድነው፤ አሁንም ስለ እሱ እና ምንአልባትም ደግሞ ብዙም ባልራቀ መልኩ እስከ 6ኛ እና 7ኛ ደረጃ ላይ ሆኖ ሊጉን ስለመጨረስም ነው በማሰብ ላይ የምንገኘው”።

በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ካደረጉት ጨዋታ ለእሱ የቱ  ፍልሚያ አስደሳችና አስከፊ እንደነበር

“በሐዋሳ ከተማ የውድድር ቆይታዬ በሁለት  ጨዋታዎች ላይ ብቻ ተሳትፌ ስለነበር   ቡድናችን ካደረጋቸው ጨዋታዎች ከባዱና የተቸገርንበት ፍልሚያ  ከሲዳማ ቡና ጋር ያደረግነው ነው፤ በጨዋታው ጥሩ አልነበርንም፤ በጣም ወርደን ነበር፤ እሱ ግጥሚያ በጣም የተከፋሁበት ስለነበር እኔን አላስደሰተኝም፤ ከእዛ ጨዋታ ውጪ ሌላው ያስቆጨኝ ጨዋታ ደግሞ ከቅ/ጊዮርጊስ ጋር ተጫውተን  እኛ ያስቆጠርነው ግብ ኦፍሳይት ተብሎ ተሽሮብን እነሱ ያስቆጠሩት ኦፍሳይት ግብ ደግሞ የፀደቀ በመሆኑ ነው።  ለእኛ አሁን ላይ እያስደሰተን ያለው ጨዋታ ደግሞ በድሬዳዋ ቆይታችን ውጤት እያስመዘገብን ያሉትን ጨዋታዎች ነው”።

በእግር ኳስ ተጨዋችነት የወደፊት ምኞቱ

“በፕሮፌሽናል ተጨዋችነት ከሀገር ወጥቶ መጫወት ምኞቴ ነው፤ ሌላው ደግሞ ሀገሬን ወክዬም መጫወትን እመኛለው”።

ከዋና ስሙ በተጨማሪ ስለሚጠራበት

“በልጅነት ዕድሜዬ ላምፓርድ ተብዬ  ነው  እጠራ የነበረው”።

እናጠቃል

“በኳሱ ለዛሬ እዚህ ደረጃ  ላይ መድረሴ ብዙ ሰዎች ከፍተኛ አስተዋፅኦን አበርክተውልኛል፤ አሰልጣኝ ዘነበ ፍስሃን፣ አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪን፣ አሰልጣኝ ደለለኝ ደቻሳንና በጉዳት ከአመት በላይ በቆየሁበት ወቅት ወደ ጨዋታ ተመልሼ እንድመጣ ያደረገኝን አሰልጣኝ  በቀለንና  በወጣት ብሄራዊ ቡድን ያሰለጠነኝን አሰልጣኝ አጥናፉ አለሙን እንደዚሁም ደግሞ ቤተሰቦቼንና ከሁሉም በፊትም ፈጣሪን ለማመስገን እወዳለው”።

spot_img
ተመሳሳይ ጽሁፎች

አስተያይት ያስፍሩ

እባክዎን አስተያይትዎን ያስፍሩ
እባክዎን ስምዎን እዚህ ያስገቡ

ትኩስ ዜናዎች

%d bloggers like this:
P