Google search engine

“በመቐለ 70 እንደርታ ቆይታዬ ምርጥ ጊዜን አሳልፌያለሁ፤ አዲሱ ቡድኔንም በቅርቡ አሳውቃለሁ” ዳንኤል ደምሱ


የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሻምፒዮኑን መቐለ 70 እንደርታን ባለፈው የውድድር ዘመን በመቀላቀል በክለቡ ጥሩ ጊዜን አሳልፏል፤ ዳንኤል ደምሱ በእዚህ ቡድን ቆይታውም ከ17 ጨዋታዎች በ15ቱ ተሰልፎም ሊጫወት ችሏል፤ ዳንኤል ከመቐለ 70 እንደርታ ጋር የነበረውን ውል በሰኔ 30 ያጠናቀቀ ሲሆን ይህን ተከትሎም ከተለያዩ ቡድኖች ጋር እያደረገው ባለው ድርድር ወደ አንዱ ቡድን ያመራል ተብሎም እየተጠበቀ ይገኛል፡፡
የእግር ኳስን በክለብ ደረጃ ለአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ፣ ለኢትዮጵያ መድን፣ ለኢትዮጵያ ቡና እና ለመቐለ 70 እንደርታ ክለቦች ተጫውቶ ያሳለፈው እና በአዲስ አበባም የ4 ኪሎ ዩንቨርስቲ የሁለተኛ ዓመት የባዮሎጂ ላብራቶሪ ተማሪ የነበረውን ዳንኤል በኳስ ህይወቱ ቆይታና ሌሎችንም ጥያቄዎች አቅርበንለት ምላሹን በሚከተለው መልኩ ሰጥቶናል፡፡


ሊግ፡- በቅድሚያ እንኳን ለአዲሱ ዓመት በሰላም አደረሰህ?
ዳንኤል፡- እናንተንም እንኳን አደረሳችሁ፤ የአዲሱ ዓመትም የመጀመሪያ እንግዳ አድርጋችሁኝ ስላቀረባችሁኝም ሳላመሰግናችሁ አላልፍም፡፡
ሊግ፡- አዲስ ዓመትን እንዴት ልትቀበል ተዘጋጅተሃል? /ያነጋገርነው ረቡዕ ዕለት ነው/፡፡
ዳንኤል፡- የ2013 አዲስ ዓመትን ለመቀበል የተዘጋጀሁት ኮቪድ 19 ካመጣብን ጭንቀት ተላቀንና በሀገራችን ውስጥ የተፈጠረውን አለመረጋጋትም ወደ ኋላ ረስተንና ትተን በሰላም ወይንም ደግሞ በፍቅር የምንኖርበት ዓመት እንዲሆንልን ነው በመጠባበቅ ላይ የምገኘው፡፡
ሊግ፡- የአዲስ ዓመትንና በዓልን ከዚህ ቀደም እንዴት ነበር የምታሳልፈው? ዘንድሮስ እንዴት ታሳልፋለህ?
ዳንኤል፡- በአጋጣሚ የእዚህ ዓመት በዓልን የማሳልፈው ከኮቪድ 19 ጋር በተያያዘ አሁን ያለው ወቅታዊ ሁኔታ ጥሩ ስላልሆነ ከቤተሰቦቼ ጋር ነው፤ ከዚህ ቀደም ግን እኛ አጠቃላይ ስፖርተኞች በዝግጅት ላይ ስለምንሆን ወደ ተለያዩ ክልሎች በመሄድ ከቤተሰብ ውጪ ነበር በዓሉን የምናሳልፈው፡፡
ሊግ፡- በኮቪድ 19 ከእግር ኳሱ ከራቅህ በርካታ ወራቶችን አስቆጥረሃል፤ ያ ለመሆን በመቻሉ በውስጥህ ምን አይነት ስሜት ተፈጠረብህ? ወቅቱንስ እንዴት እያሳለፍክ ነው የምትገኘው?
ዳንኤል፡- አሁን የመጣብን ወረርሽኝ መጥፎ ነው፤ ደስ የማይል ጊዜም ላይ ነው የምንገኘው፤ ከዚህ አንፃር እንደ አንድ እግር ኳስ ተጨዋች ለእዚህን ያህል ጊዜ ከኳሱ ለመራቅ መቻሌ ጥሩ ያልሆነ ስሜት ነው እንዲሰማኝ ያደረገው፡፡ ከዛ ውጪ አሁን ያለውን ወቅት እያሳለፍኩ የምገኘው አንተ በምትፈልገው መልኩ እንቅስቃሴን ማድረግ በማትችልበት ሁኔታ ነው፤ በግል አንድአንድ እንቅስቃሴዎችን ለማድረግ ብትችልም ያለ ኳስ ግን ስራዎች ሁሉ አሰልቺ ነው የሚሆኑብህና ያለፉት 6 ወራት ጥሩ ጊዜ አልነበረም፤ አሁን አሁን ግን ራሳቸውን ከሚጠብቁ ልጆች ጋር ፈጣሪ ይመስገን አስፈላጊውን ጥንቃቄ እያደረግንየመሀል ባልገባን እንጫወታለን፡፡
ሊግ፡- ከኮቪድ 19 ወረርሽኝ መግባት በኋላ ምን ነገር ናፍቆሃል?
ዳንኤል፡- ከእግር ኳሱም ርቀን አይደል፤ እኔን የናፈቀኝ የሊጋችን ጨዋታ ተጀምሮ ታክል መግባት ነው፡፡
ሊግ፡- በእግር ኳስ ባሳለፍከው የተጨዋችነት ዘመንህ ደስተኛ ነህ?
ዳንኤል፡-አዎን፤ ፈጣሪ ይመስገን፤ በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡ የእግር ኳስን ተጫውቼ የመጣሁበት መንገድም ትምህርቴን በመማር ጭምርም ነው፤ በአዲስ አበባ በሚገኘው የ4 ኪሎ ዩንቨርስቲ ስማር ለአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ኳስን እጫወት ነበር፤ ደረጃ በደረጃም በራሴ ላይ ከፍተኛ መሻሻል በማሳየትም በሀገሪቱ ውስጥ ለሚገኙ ትላልቅ ቡድኖች ውስጥ ገብቼ እስከመጫወትም ደርሻለሁና በአብዛኛው ደስተኛ ያደረጉኝ ነገሮች እነዚህ ናቸው፡፡ በተለይ ደግሞ ወደ ቡና ስገባ ክለቡን አስቀድሞም ልጫወትበት የምመኘው ቡድን ስለነበር የቡናን ማልያ ለብሼ መጫወቴ ያስደስተኛል፤ ከክለቡ ጨዋታ መካከልም ከአዳማ ጋር በነበረን የሲቲ ካፑ ፍልሚያ ለእኔ ግጥሚያው በቡድኑ ማልያ የመጀመሪያዬ ሆኖ 4-0 ስናሸንፋቸው እኔም የጨዋታው ኮከብ ልባልበትም ስለቻልኩ ያም ነው የሚያስደስተኝ፡፡
ሊግ፡- በእግር ኳስ ተጨዋችነት ዘመንህ ተከፍቻለሁ ብለህ ያሰብክበትስ?
ዳንኤል፡- የኢትዮጵያ ቡና ክለብ ተጨዋች በነበርኩበት ሰዓት በአሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ የመሰልጠን ከፍተኛ ፍላጎት ነበረኝ፤ በእሱ አዲስ የአጨዋወት ታክቲክ ውስጥም ሰልጥኜ በማለፍ ቡናን በጣም መጥቀም እፈልግ ነበር፤ ያም ሆኖ ግን እሱ ወደ ክለቡ በመጣበት ዓመት ላይ እኔ ልለቅ ስለቻልኩ ያ ዓመት ይቆጨኛል፤ ከቡና በመውጣቴም በወቅቱ ከፍቶኛል፡፡ ከዛ ውጪ በኳስ ህይወቴ የተከፋሁት ለቡና በምጫወትበት ሰዓት ሐዋሳ ላይ በተደረገው የኢትዮጵያ ጥሎ ማለፍ የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታ የመከላከያው ምንይህሉ ወንድሙ ባስቆጠረብን የፍፁም ቅጣት ምት ግብ ተሸንፈን የወጣንበትን ነው፡፡
ሊግ፡- የእግር ኳስ ጨዋታ ዘመንህ ምርጡ ግብ የቱ ነው?
ዳንኤል፡- ምርጧ ግቤ ለአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ስጫወት በአሰልጣኝ አብዶ ከድር ይመራ በነበረው የመድን ቡድን ላይ ከመሀል ሜዳ አካባቢ በመምታት ያስቆጠርኳት የቺፕ ግብ ናት፤ ግቧ ለእኔ ብርቅ ስለነበረችም በተደጋጋሚ ጊዜ ሳወራላትም ነበር፤ ያኔ የቡድኑ በረኛ ዘነበ ነበር፤ አሁን በአሜሪካን ሀገር ይገኛል፤ የፌስ ቡክ ጓደኛዬም ነው፤ ከጨዋታ በኋላ ላገባሁበት ግብ አድናቆትን ሰጥቶኝ አንተ ወደፊት ጥሩ ደረጃ ላይ ትደርሳለህ ብሎኝም ነበርና ከእሱ ጋር አልፎ አልፎ እናወራለን፡፡ ያኔ መድንን 2-1 ባሸነፍንበት ጨዋታም በውጤቱ ተደስተንም ዩንቨርስቲ ውስጥ ስናቅራራም ነበር፡፡
ሊግ፡- ከእግር ኳስ መጫወት ውጪ በአዲስ አበባ አራት ኪሎ ዩንቨርስቲ ትማር ነበር፤ ያን ትምህርት አጠናቀቅ?
ዳንኤል፡- አላጠናቀቅኩም፤ የሁለተኛ ዓመት የባዮሎጂ ላብራቶሪ ተማሪ እያለው ነበር በኳስ የተነሳ ድሮ ላደርግ የቻልኩት፤ ዘንድሮ ግን ይህን ትምህርቴን የርቀትም ቢሆን በመማር ለማጠናቀቅ ዝግጁ ነኝ፡፡
ሊግ፡- ከኢትዮጵያ ቡና ወደ መቐለ 70 እንደርታ በማምራት ተጫውተሃል፤ ኮቪድ የሊጉን ውድድር እስካቋረጠበት ጊዜ ድረስ ዓመቱ ለአንተ እንዴት አለፈ?
ዳንኤል፡- የመቐለ 70 እንደርታ ክለብ ውስጥ የነበረኝ ቆይታ በጣም አሪፍ እና ጥሩም የውድድር ዓመትን ያሳለፍኩበት ነበር፤ ክለቡ ተመችቶኝም ነበር፤ ካደረግናቸው 17 ጨዋታዎች ውስጥ በ15ቱም በቋሚ ተሰላፊነት ልጫወት ችያለሁ፤ ሁለቱን ጨዋታም ሳልጫወት የቀረሁትም ባጋጠመኝ የጡንቻ ህመም ምክንያት ነበርና በአጠቃላይ መልካም ጊዜን ነው ያሳለፍኩት፡፡
ሊግ፡- በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመቐለ 70 እንደርታን የዓምና ጉዞ እንዴት ትገልፀዋለህ?
ዳንኤል፡- መቐለ 70 እንደርታ ባለፈው ዓመት የፕሪምየር ሊጉ ተሳትፎው ውድድር ሲጀመር አንድአንድ ክፍተቶች ነበሩበት በኋላ ላይ ግን አቋሙ እየተስተካካለ በመሄዱ በውጤት ደረጃ ጥሩ ጉዞን አድርገን ነበር፤ ከመሪው ፋሲል ከነማ ጋርም በአንድ ነጥብ ብቻ ተበልጠን ሁለተኛ ደረጃ ላይም እንገኝ ነበር፤ በተለይ ከባህር ዳር ከነማ ጋር የነበረንን ጨዋታ በአቻ ውጤት ባናጠናቅቅ እና ማሸነፍ ብንችል ኖሮ ፋሲል ነጥብ ከመጣሉ ጋር መሪም መሆን እንችል ነበርና ውድድሩ እስኪቋረጥ ድረስ ጥሩ ቡድን ነበረን፡፡
ሊግ፡- በኮቪድ 19 የሊግ ውድድሩ ባይቋረጥ ኖሮ የውድድር ዓመቱ ሻምፒዮና ማን ይሆን ነበር?
ዳንኤል፡- እኛ ነና! ምክንያቱም ቡድናችን የሁለተኛው ዙር ግጥሚያዎች ሲጀመሩ ከጨዋታ ወደ ጨዋታ ከፍተኛ መሻሻልን ነበር እያሳየ የመጣው ከዛ አኳያ ዋንጫው ወደ መቐለ ያመራ ነበር ብዬ አስባለው፡፡
ሊግ፡- በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ላይ መጫወት ፈልገህ ባለመጫወትህ የሚቆጭህ ግጥሚያ አለ?
ዳንኤል፡- አዎን፤ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር በነበረን ጨዋታ መጫወትን በጣም ፈልጌ ሳልጫወት ቀርቻለው፤ በዛ ግጥሚያም ራሴን በደንብ አሳይበታለው ብዬም እየተዘጋጀው ነበር፤ ያም ሆኖ ግን በመርፌ እና ፕሮፌሽናሉ የቡድናችን ግብ ጠባቂ ከውጪ ሀገር ባስመጣው እግር ላይ የሚሰካ የራሱ ማቴሪያልን አድርጌ በመግባት ልጫወት ከፈለግኩ በኋላ ከፍተኛ አደጋ እንዳይፈጥርብኝ እና የነበረብኝንም የጡንቻ ህመም እንዳያባብስብኝም ብዬ ስለሰጋው ግጥሚያውን ላላደርግ ችያለሁ፤ ያ ስለሆነም በጣሙን ሊቆጨኝ ችሏል፡፡
ሊግ፡-በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የሁለተኛው ዙር ላይም ከመቐለ 70 እንደርታ ጋር ልትጫወቱ ስትቃረቡ ኮቪድ ሊገባ ችሏል፤ በዛ ዙሪያስ ምን የምትለው ነገር ይኖርሃል?
ዳንኤል፡- የመቐለ 70 እንደርታ ደጋፊዎች ለኳስ ካላቸው ከፍተኛ ፍቅር የተነሳ ከቡና ጋር በሚኖረን የአዲስ አበባ ስታድየም የሁለተኛው ዙር ጨዋታ ላይ ግጥሚያው ተደርጎ የእኛም ሆኑ የቡና ደጋፊዎች በሚሰጧቸው ድጋፎች የስታድየሙን ድባብ በጣም ደማቅ አድርገው የሚወጡበት፤ የእግር ኳስ ጨዋታውም ከዚህ በፊት ከነበረው የብሄር ክፍፍል ተላቆ የፍቅር፣ የሰላም፣ የወንድማማችነት፣የወዳጅነት እና ለኳሱ እድገታችንም አንድ ነገርን የምናይበትን ሁኔታ ልንጠብቅ ብንችልም በኮቪድ መግባት የፕሪምየር ሊጋችን አጠቃላይ ጨዋታዎች በመቋረጣቸው የተነሳ ግጥሚያው ሊሰረዝ ችሏልና ያ መሆን መቻሉ አስከፍቶኛል፤ ምክንያቱም ቡናና መቐለ 70 እንደርታ የመጀመሪያ ዙር ጨዋታቸውን ሲያደርጉ ጥቂት የቡና ደጋፊዎች ብቻ ነው የነበሩት እና ያን ከመመልከት አኳያም ነው ምናለበት ኮቪድ ከገባ አይቀር የእኛና የቡና ጨዋታ በብዙዎች ደጋፊዎች ፊት ከተደረገ በኋላ ቢሆን ብዬ እስከመመኘትም ደርሻለሁ፡፡
ሊግ፡- በመቐለ 70 እንደርታ የዶርም ጓደኛህ ማን ነበር?
ዳንኤል፡- ጓደኛዬ አስናቀ ሞገስ /ጀበና/ ነው፤ ከእሱ ጋር በባህር ዳር ከተማ ቡድን ውስጥ አብረን ተጫውተናል፤ የአምስት ዓመት ጓደኛዬም ነው፡፡


ሊግ፡- በመቐለ 70 እንደርታ ቆይታ የቡድናችሁን ተጨዋቾች የሚያዝናናቸው ማን ነው?
ዳንኤል፡- እኔ ነኝ የማዝናናቸው፤ ዳኒ ካለ ሳቅና ጨዋታም አለ ብለው ስለሚያስቡ ቡና በሚጠጡበት
ስፍራ ሁሉ ነው ፈታ ለማለት አንድ ነገርን ጣል አድርግ ስለሚሉኝ ሳዝናናቸው የምቆየው፡፡
ሊግ፡- ከመቐለ 70 እንደርታ ጋር የውል ጊዜህን ጨርሰሃል፤ እዛው ነው የምትቀጥለው? ወይንስ ወደ አዲስ ቡድን ታመራለህ?
ዳንኤል፡- በእዚህ ዙሪያ አሁን ላይ ያወቅኩት ምንም ነገር የለም፤ ያም ሆኖ ግን ከመቐለ 70 እንደርታ ጋር የውል ጊዜዬን መጨረሴን ተከትሎ ከሁለት እና ከሶስት ቡድኖች ጋር እየተነጋገርኩ ስለሆነ የምገባበትን ቡድን በቅርቡ አሳውቃለው፡፡
ሊግ፡- ከኢትዮጵያ እና ከባህር ማዶ ተጨዋቾች የምታደንቀው?
ዳንኤል፡- ከሀገር ውስጥ የዳዊት እስጢፋኖስ አድናቂ ነኝ፤ በጣም ነው የምወደው፤ ከዛ ውጪም ከእሱ ጋር ተቃራኒ ሆኜ ስጫወትም እሱን መንካትና ማነጫነጭም በጣም ነው ደስ የሚለኝ፡፡ ከባህር ማዶ ተጨዋቾች ደግሞ የማደንቀው የማንቸስተር ዩናይትድ ደጋፊም ነኝና ሮይ ኪንን ነው የማደንቀው፡፡
ሊግ፡- በእግር ኳስ ከአጠገብህ ሆኖ እንዲጫወት የምትመኘው ተጨዋች?
ዳንኤል፡- ዳዊት እስጢፋኖስ ነዋ! ከእሱ አጠገብ ሆኜ መጫወትን በጣም አልማለው፤ በተለይ ደግሞ እኔ እየታገልኩና ኳሱንም እየነጠቅኩ ለእሱ ባቀብለው ሁሌም ነው ደስ የሚለኝ፡፡
ሊግ፡- የማንቸስተር ዩናይትድ ደጋፊ ነህ፤ ሊቨርፑል የሊጉን ዋንጫ ሲያነሳ ምን ተሰማህ?
ዳንኤል፡- የሊቨርፑል ወዳጅ ባልሆንም ስለ ታሪካቸው ብዙ ባላውቅም፤ ስቴቨን ጄራርድ የማንቸስተር ዩናይትድን ማልያ አለብስም እንዳለው ሁሉ እኔም ለእነሱ ጥሩ ነገርን ልመኝ ባልችልም የእዚህን ዓመት የሊግ ዋንጫን ማግኘት መቻላቸው ግን ለሊቨርፑሎች ይገባቸዋል፤ ምርጥ ቡድንም ነበራቸው፡፡
ሊግ፡- የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ዛሬ ይጀመራል፤ ዘንድሮ ምን አይነት ፉክክር ይኖራል?
ዳንኤል፡- ሁሉም ክለቦች ቡድናቸውን በጣም እያጠናከሩ ነው፤ በተለይ ደግሞ ትላልቅ የሚባሉት ክለቦች እያስፈረሟቸው ያሉት ተጨዋቾች ሊጉን ደማቅ እና ጥሩም ፉክክር የሚታይበትም ያደርገዋልና ይሄን ሳይ ምናለ ኮቪድ ጠፍቶ በበርካታ ደጋፊዎቻቸው እና የእግር ኳስ ተመልካቾች ፊት ቢከናወን ብዬም እየተመኘው ነው፡፡
ሊግ፡- በፕሪምየር ሊግ የዘንድሮ የውድድር ዘመን ተሳትፎ ራስህን በምን መልኩ ለማቅረብ ዝግጁ ነህ?
ዳንኤል፡- በእግር ኳስ ተጨዋችነት ዘመኔ ያለብኝን ክፍተት እና ችግሬን አሁን ላይ በሚገባ እያወቅኩት ነው፤ በተለይ በቡና ቆይታዬ አቅሙና ችሎታው ኖሮኝ ብልጭ ብዬ የጠፋሁበትንም ነገር ልረዳ ችያለሁ፤ ይኸውም ጎል የማግባት ችግር በጣሙን አለብኝ፤ ይሄን ችግሬንም የቀድሞው እግር ኳስ ተጨዋች እና በሙሉዓለም ረጋሳም በጣም የሚደነቀው ጓደኛዬ ሲሳይ ቱፋም እየነገረኝ ነው፤ እሱ ብዙ ጊዜ ጎል ስታገባ ነው እይታ ውስጥ የምትገባው ብሎም አንድ አንድ ነገሮችን ስለሚነግረኝ ከእሱ ጋር ሆኜ ደብረዘይትም አብረን ተጉዘን በእግር ባላገባ እንኳን በቴስታ ግቦችን ማግባት እንዳለብኝም በሚያስችል መልኩ አስፈላጊውን ልምምድ እየሰራሁ ነው የምገኘውና በዘንድሮ የውድድር ዘመን በምርጥ ብቃቴ ነው የምቀርበው፡፡
ሊግ፡-ዳንኤል በባህሪው እንዴት ይገለፃል?
ሊግ፡- ስንት ወንድም እና እህት አለህ?
ዳንኤል፡- በቤት ውስጥ ያለነው እኔን ጨምሮ ሶስት ወንዶች ነን፤ ቡኤ ስንጨፍር ሁሉ ሌላ ሰው አናስገባምም ነበር፡፡
ዳንኤል፡- ስለ ራስ መግለፅ በጣም የሚከብድ ቢሆንም፤ ረጅም ሰው የዋህ ነው ይባል የለ እኔም እንደዛው ነኝ፤ ከዛ ውጪም ቶሎ የሚከፋኝና የምናደድም ነኝ፡፡
ሊግ፡- የተለየ አመጋገብ አለህ?
ዳንኤል፡- ኸረ የለኝም፤ ያም ሆኖ ግን ለትዳር ብዙ አላስቸግርምና ፍርፍር መብላትን በጣም ነው የምወደው፡፡
ሊግ፡- ከጎበኘካቸው ስፍራዎች በጣም የወደድከው?
ዳንኤል፡- ላሊበላን ነዋ! ወልዲያ በነበርኩበት ሰዓት ለሁለት ቀን አድሬ ነበር፤ የኢትዮጵያን ታሪክ በደንብ ታይበታለህ፤ ታውቅበታለህም፤ ቦታው ደስ ይላል፤ እናት እና አባቴን ባሳያቸው ብዬ ራሱ ምኞትን ላሳድርም ችያለሁ፡፡
ሊግ፡- በአውሮፕላን ለመጀመሪያ ጊዜ መች ሄድክ? ምንስ ገጠመህ?
ዳንኤል፡- ለመጀመሪያ ጊዜ በአውሮፕላን የተጓዝኩት የመድን ተጨዋች በነበርኩበት ወቅት ነው፤ ያኔም ከአጠገቤ ኢብራሂም ሁሴን ነበርና ጉዞውን አካብዶብኝ ስለነበር ፕሌኑ ትንሽ ነቅነቅ ሲል በጣም ልፈራ ቻልኩ፤ እንደዛም ሆኖ ግን ፍራቻው ቢኖርም በመጓዜ ደስ ያለኝም ሁኔታ አለና ያን ፈፅሞ አልረሳሁም፡፡
ሊግ፡- ሙዚቃን ታዳምጣለህ?
ዳንኤል፡- አዎን፡፡
ሊግ፡- የእነማንን ሙዚቃ ነው የምትሰማው?
ዳንኤል፡- ሴቶች ስለሆኑ ሳይሆን የጂጂን፣ የዘሪቱን እና የአስቴር አወቀን /አስቱካን/ ሙዚቃዎች ስሰማ በጣም ደስ ይለኛል፤ አድናቂያቸውም ነኝ፤ በተለይ ደግሞ ጂጂን፡፡
ሊግ፡- ካናበብካቸው መፅሀፎች የወደድከው?
ዳንኤል፡- በኮቪድ 19 ምክንያት አሁን ላይ ቤት ተቀምጬ መፅሀፎችን እያነበብኩ ነው፤ የመፅሐፍ ማንበብ ትርጉሙንም አሁን ላይ በሚገባ እያወቅኩት ነው፤ መፅሀፍ ማንበብ መጥፎ ነገሮችንም እንድትረሳም ያደርግሃልና እመጓን ሳነብ የተለየ ስሜትም ነው የተሰማኝ፤ እመጓ ሊነበብ የሚገባውም መፅሀፍ ነው፡፡
ሊግ፡- የምታሽከረክረው መኪና ምን አይነት ነች?
ዳንኤል፡-ያሪስ 2010፡፡
ሊግ፡- ጋብቻህ መች ሆነህ?
ዳንኤል፡- ጋብቻዬን ጓደኛዬ ከሆነችው እመቤት ገመቹ ጋር በክረምቱ ወራት እፈፅማለው ብዬ ነበር፤ ያም ሆኖ ግን በተከሰተው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት ምቹ ሁኔታዎች ስላልተፈጠሩና የእሷ እናትም ወ/ሮ ዘነበወርቅ በውጪ ሀገር ስለሚኖሩና ከወቅቱ አንፃርም ወደዚህ ሊመጡ ስላልቻሉ ሊራዘም ችሏል፤ ያም ሆኖ ግን ከፈጣሪ እርዳታ ጋር ዘንድሮ ይህ ጋብቻዬ እውን ይሆናል፡፡
ሊግ፡- ቤተሰቦችህን በሚመለከት ምን ትላለህ?
ዳንኤል፡- ስለ እነሱ አውርቼና ተናግሬ አልጠግብም፤ አባት እና እናቴ ለእኔ የእግር ኳስ ተጨዋችነት ህይወት ትልቅ መስዋዕትነትን ነው የከፈሉት፤ ኦፕራሲዮን ሆኜም በጉዳት ላይ በነበርኩበት ሰዓትም በሆስፒታል ከአጠገቤ ሳይለዩም አብረውኝ ነበርና በእኔ አቅም የእነሱ ውለታ ተከፍሎ አያልቅምና ሁሌም ነው እነሱን ሳላመሰግን ማለፍን የማልፈልገው፤ ቤተሰቦቼን በተመለከተ ሌላ አንድ ነገር ማለት የምችለው ነሐሴ 21 ቀን ላይ እናቴም አባቴም የፈጣሪያችንን ስጋና ደሙን በመቀበል ሊቆርቡልኝ ስለቻሉ ያ በጣሙን አስደስቶኛል፤ ከእነሱ ጋር በደብረዘይት ከተማ ዩሃንስ ቤተክርስቲያን 16ቷን ቀን በመፆም ስናስቀድስ ነበር፤ ከዛ አልፈው ሲቆርቡ ሳይ በህይወቴ ትልቁን ደስታን ለማግኘት ችያለው የራሴን ህይወትም ከእዚህ በኋላ እጀምራለውና ይሄ የቡናን ማልያ ለመጀመሪያ ጊዜ ሳጠልቅ ከነበረው ደስታ በኋላም የመጣ ሌላው ደስታ ነውና ለወላጆቼ በእዚሁ አጋጣሚ ፈጣሪ ረጅሙን ዕድሜ ይስጣቸው እላለሁ፡፡
ሊግ፡- በመጨረሻ…?
ዳንኤል፡- ፈጣሪ ሀገራችንን ሰላም ያድርግልን፤ ይባርክልንም፤ ከዛ ውጪም ኪዳነምህረት ታክላባትም ከምንሰማቸው እና ከምናያቸው ጥሩ ያልሆኑ ነገሮች ተላቀን አዲሱን ዓመት የሰላም፣ የደስታ እና የተሻለ ነገርን የምንሰራበት ጊዜም ያድርግልን፡፡

spot_img
ተመሳሳይ ጽሁፎች

አስተያይት ያስፍሩ

እባክዎን አስተያይትዎን ያስፍሩ
እባክዎን ስምዎን እዚህ ያስገቡ

ትኩስ ዜናዎች

%d bloggers like this:
P