ሰበታ ከተማ፣ ወልቂጤ ከተማ እና ሀዲያ ሆሳህና የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዓመቱን ሙሉ ሲያካሂድ የነበረውን የከፍተኛ ሊግ ውድድር አንድ አንድ ጨዋታ እየቀራቸው በቀዳሚነት በማጠናቀቅ የመጪው ዘመን የፕሪምየር ሊጉ ተሳታፊ መሆናቸውን አረጋግጠዋል፡፡
ወደ ፕሪምየር ሊጉ በማለፍም ለሰበታ ከተማ እና ለሀዲያ ሆሳህና ሁለተኛ ጊዜያቸው ሲሆን ለወልቂጤ ከተማ ደግሞ የመጀመሪያው ሊሆንም ችሏል፡፡
የሶስቱ ክለቦች ወደ ፕሪምየር ሊጉ ማለፍን ተከትሎም ከሰበታ ከተማው አሰልጣኝ ክፍሌ ቦልተና ጋር፣ ከወልቂጤው አሰልጣኝ ደረጄ በላይ ጋርና ከሀዲያ ሆሳህናው ተጨዋች ሱራፌል ጌታቸው ጋር የተለያዩ ጥያቄዎችን በማንሳት ቆይታ ያደረግን ሲሆን ምላሻቸውንም በሚከተለው መልኩ አቅርበነዋል፡፡
ሊግ፡- ወልቂጤ ከተማን ዘንድሮ ከዚህ በፊት ደግሞ ሰበታ ከተማን እና ጅማ አባጅፋርን በአሰልጣኝነት ሕይወትህ ወደ ፕሪምየር ሊጉ አስገብተሃል፤ በዚህ በኩል ያለህ ስሜት ምን ይመስላል?
አሰልጣኝ ደረጄ፡- በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ውስጥ አንድን ቡድን በኃላፊነት ስትመራ በአንድ ጊዜ ወደ ፕሪምየር ሊግ ማሳለፍ መቻል በጣም ከባድ ነገር ነው፤ በእኔ የአሰልጣኝነት ዘመን ግን ከአንድም ሶስት የተለያዩ ክለቦችን በማሰልጠን ሶስቱንም ወደ ፕሪምየር ሊጉ ያሳለፍኩ በመሆኑ የሚሰማኝ ስሜት የተለየ ነው፤ በታችኛው ሊግ የሙያው ቆይታዬም ማሸነፍን የለመድኩና በስኬታማነትም የማልጠግብ አይነት ባለሙያም ስለሆንኩ በዚህ የስራ ጥንካሬዬ በጣሙን እየተደሰትኩም ነው የምገኘው፡፡
ሊግ፡- ወልቂጤ ከተማ የፕሪምየር ሊጉን የተቀላቀለው በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው፤ ለውድድሩ ስታልፉ እዛ የነበረው ስሜት ምን ይመስል ነበር?
አሰልጣኝ ደረጄ፡- የእዚያን ዕለቱን የደስታ ስሜት በቃላት የምትገልፀው አይደለም፤ ሁሉንም ነገር ስትመለከትም የሰው ስሜት ለየት የሚልና በጣምም ከባድ ነበር፤ የፕሪምየር ሊጉን የመቀላቀል እልምና ፍላጎታችን ገና ከውድድሩ አመቱ መጀመሪያ አንስቶ ነበር፤ ይሄ ቡድን ከዚህ በፊት ከአንድም ሁለት ጊዜ ለማለፍ ከጫፍ እየተቃረበ ሳይሳካለት ቀርቶም ስለነበር በእኔ የአሰልጣኝነት ዘመን ይሄ ጣፋጭ ድል ሲሳካላቸው ደስታቸው የሚያስገርም አይነት ሆኖም ነው ያገኘሁት፡፡
ወልቂጤ ከተማ የፕሪምየር ሊጉን ሲቀላቀል ከ7 አመት ህፃን ልጆች አንስቶ፣ በወጣቶች፣ በ30 እና በ40 አመት መሃል በሚገኙ ጎልማሶች፣ እንደዚሁም ደግሞ እስከ 80 እና 90 አመት በሚደርሱም ቡድኑን በሚደግፉ አዛውንቶች ጭምር የሚደገፍ ክለብ ስለሆነና ድሉም ሁሉንም ደጋፊ ያስደሰተም ስለነበር ያ ቀኑን ለየት እንዲል አድርጎታል፤ የደስታውም መጠን አሁንም ድረስ ከደጋፊዎቹ ውስጥ ሳይወጣም ቀርቷል፡፡
ሊግ፡- ወልቂጤ ከተማን ወደ ፕሪምየር ሊጉ ያሳለፈው ዋንኛው ጥንካሬው ምንድንነው?
አሰልጣኝ ደረጄ፡-ወደ ፕሪምየር ሊጉ ለመግባታችን ዋናው የስኬታማነታችን ምንጭ የነበረው የቡድናችን በማጥቃት ላይ ያተኮረ እግር ኳስን መጫወት መቻሉ ነው፤ በዚሁ አጨዋወት ውስጥም ካስቆጠርናቸው 42 ጎሎች ውስጥ 32ቱን ያስቆጠርነው ገና ጨዋታው በተጀመረ እስከ 20 ደቂቃ ባለው ጊዜ ውስጥ መሆኑ እኛን በጣም ስለጠቀመን ቡድናችን አብዛኛዎቹን ጨዋታዎች በዚሁ መልኩ እንዲያሸንፍና ዛሬ ላይም የፕሪምየር ሊጉን እንዲቀላቀልም ምክንያት ሆኖታልና ይሄ ነው ዋናው ጥንካሬያችን፡፡
ሊግ፡- ለፕሪምየር ሊጉ ተወዳዳሪነት እንድትበቁ ሌሎችስ የረዷችሁ ነገሮች የሉም?
አሰልጣኝ ደረጄ፡- አሉ እንጂ፤ ለውጤታማነታችን ማማር ደጋፊዎቻችን ልዩ እና ኩራታችንም ነበሩ፤ በተለይ ደግሞ በአብዛኛው ማለት ይቻላል የጉራጌ ብሄረሰብ ተከታዮች ኳሱን በጣምም ስለሚወዱት ያለስስትም ነበር ድጋፍን የሚሰጡን እና ይሄ ለክለባችን ስኬት ከፍተኛ አስተዋፅኦ አበርክቶልናልና ይሄ ድጋፋቸው በቀጣይነትም ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል፡፡
ወልቂጤን ወደ ፕሪምየር ሊግ ያሸጋገረው ሌላው ነገር ደግሞ ቡድኑ በየጨዋታው ከፍተኛ የሆነ የማሸነፍ መንፈስ ነበረው፤ ይሄን የአሸናፊነት መንፈስ ደግሞ የተጨዋችነት ዘመኔ ላይ ም/ጦር ሳለሁ ዋንጫ ያገኘሁበት ስለሆነ እና ይሄንንም ወደ ተጨዋቾቼም ስላስተላለፍኩት በሜዳ ላይ እነሱ ተግባራዊ አድርገውልኝ ቡድኑን ውጤታማ ሊያደርጉት ችለዋል፡፡
ሊግ፡- የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግን ከወዲሁ ብትቀላቀሉም ክፍተት ጎንም እኮ ነበረባችሁ?
አሰልጣኝ ደረጄ፡- ያ እማ ፈፅሞ አይዋሽም፤ አንድ ቡድን በፈለግከው መጠን ውጤታማ ቢሆን ከእነ ክፍተት ጎኑ ነው፤ የእኛንም ቡድን ዘንድሮ የገጠመው ክፍተት ጎን የቡድናችን ተጨዋቾች ብዙ የጨዋታ ልምድ የሌላቸው ከመሆኑ አኳያ አንዳንዴ ሲሸበሩ የምታይበት አጋጣሚዎች አሉ፤ ወዲያው ግን ያንን እኔ ስለማውቅ እና ያለባቸውንም ችግር በፍጥነት ስለምነግራቸው ወደራሳቸው ብቃት በመመለስ ጥሩ ጥሩ ነገሮችን ሲሰሩ እመለከታለሁና ይሄንን እኛ ቡድን ላይ ተመልክቻለሁ፡፡
ሊግ፡- ወልቂጤ ከተማን ከከፍተኛው ሊግ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ለማሳለፍ ቡድኑን በምን መልኩ ነበር ያዋቀርከው?
አሰልጣኝ ደረጄ፡- የእዚህ ዓመት የቡድኔ የተጨዋቾች ስብስብ በአብዛኛው እንደውም ሙሉ ለሙሉ ማለት ይቻላል የተዋቀረው ብዙም የጨዋታ ልምድ በሌላቸው ተጨዋቾች እና ካላቸው ችሎታም ተነስቼ በእግር ኳስ ብቃታቸው ወደፊት ሊያድጉ በሚችሉ አይነት ተጨዋቾች ነው፡፡ የተጨዋቾቹን ምልመላ ያደረግኩትም በድፍረት ነው፡፡
የኢትዮጵያ እግር ውስጥ ብዙ ጊዜ ተጨዋቾች ሲመረጡ ይሄ ተጨዋች ልምድ የለውም በሚል የመጫወት እድሉን ያጣል፤ እኔ ጋር ግን ይሄ አይነት ነገር እና አሰራር ፈፅሞ የለም፤ ሁሌም በወጣት ተጨዋቾችም ነው የማምነው፤ የጅማ አባቡናን ቡድን በያዝኩበት ጊዜ 5 እና 6 የሚደርሱ ተጨዋቾችም ለወጣት ቡድን እንዲመረጥ ያስቻልኩት ለወጣቶች ያለኝ አመለካከት ከፍተኛ በመሆኑም ነውና ወጣቶች ላይ መስራት ሁሌም ያስደስተኛል፡፡
ሊግ፡- ወደ ፕሪምየር ሊጉ ያለፋችሁበት የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ውድድሩ ምን መልክ ነበረው?
አሰልጣኝ ደረጄ፡- ሊጉ አመቱን ሙሉ ከባድ፣ ጠንካራ እና ከፍተኛ ፉክክርም የተደረገበት ነበር፤ በተለይ ደግሞ ውድድሩ ጉልበትን የሚጠይቅና ወጣት ተጨዋቾች ብቻ የሚጫወቱበት የሊግ ውድድር እንደሆነም በደንብ ያረጋገጥኩበት ስለሆነም ወደፊት በዚህ ሊግ ላይ የሚጫወቱ ሁሉም ክለቦች ቡድናቸውን በወጣቶች ቢገነቡት በጣም ተጠቃሚ ይሆናሉ ብዬም ነው ምክሬን የምለግሳቸው፤ በከፍተኛው ሊግ የዘንድሮ ተሳትፎአችን የደቡብ ዞን አካባቢ ያሉት እንደ እነ ወላይታ ሶዶና ዲላ ከተማን የመሳሰሉት ክለቦች የ2ኛው ዙር ላይ በጣም ፈትነውናል፤ የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳደር እግር ኳስ ክለብም በኋላ ላይ ከደረጃው ተንሸራተተ እንጂ ጥሩ ተፎካካሪ ነበር፡፡ ሃምበርቾ እና ኢትዮጵያ መድንም ጥሩ ተፎካካሪዎች ናቸው፤ በአጠቃላይ ውድድሩ በጣም ፈታኝ እና አስቸጋሪም ስለነበር እኛ ሊጉን በብልጠታችን ነው ልንቀላቀል የቻልነው፡፡
ሊግ፡- አሁን ላይ የፕሪምየር ሊጉን ተቀላቅላችኋል፤ በቀጣዩ ጊዜ ከቡድኑ ጋር ትቀጥላለህ? ወይንስ በአዲስ ቡድን እናይካለን?
አሰልጣኝ ደረጄ፡-ከወልቂጤ ከተማ ጋር ያለኝ የውል ጊዜ አሁን ላይ ቢጠናቀቅም የቡድኑ ፕሬዝዳንት በአዲሱ የፕሪምየር ሊግ የውድድር ተሳትፎ ከክለቡ ጋር እንድቀጥል ጥያቄ በማቅረባቸው እና እኔም ፈቃደኝነቴን ስለገለፅኩላቸው የመጪው አመት ላይ ወደ ሌላ ቡድን የመጓዝ ፍላጎቴ ያ
Hatricksport, [22.06.19 20:14]
ንን ያህል ስለሆነ ከወልቂጤ ከተማ ጋር ነው አብሬ የምሰራበት እድሌ በጣሙን ሰፊ ሆኖ የሚገኘው፡፡
ሊግ፡- የፕሪምየር ሊጉን ከወዲሁ እንደመቀላቀላችሁ ለመጪው ዓመት ጠንካራ ቡድንን ስለመስራት ምን እያሰባችሁ ነው?
አሰልጣኝ ደረጄ፡- ወልቂጤ ከተማ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በፕሪምየር ሊግ የሚሳተፍ በመሆኑ የውድድሩ ጠንካራ ቡድን እና ተፎካካሪ ለመሆን የመጀመሪያ ስራው ሊሆን የሚገባው የላይኛው ሊግ ተወዳዳሪ ከመሆኑ አንፃር እና ሊጉም የሚፈልገውን ነገር ከማወቅ አኳያ የፋይናንስ ችግሩ ላይ በጣም ሊያስብበት ይገባል፡፡
የወልቂጤ ከተማ ክለብ አመራሮችም የቡድኑን የፋይናንስ ችግር ስለሚያውቁትም አሁን ላይ በዛ ላይ በትኩረት ጠንክሮ ለመስራትም ተዘጋጅተዋልና ይሄ ከተሟላ ቡድኑን በሊጉ የተሻለ ደረጃ ላይ ማድረስ ይቻላል፡፡
ሊግ፡- የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ተሳታፊ መሆናችሁ ተረጋግጧል፤ በሜዳ ላይ ምን አይነት ቡድንን ለመገንባት ተዘጋጅታችኋል?
አሰልጣኝ ደረጄ፡- ወልቂጤ ከተማ በፕሪምየር ሊጉ ተሳትፎው በአብዛኛው ቡድኑን የሚገነባው ዘንድሮ የያዛቸውን ወጣት ተጨዋቾች ሊጉ ላይ በመጠቀም እና ሌሎችን የፕሪምየር ሊግ ልምድ ያላቸውን ጥቂት ተጨዋቾችንም ወደ ቡድኑ በማምጣት ነው፤ እነዚህ የሊጉ ልምድ ያላቸው ተጨዋቾችም የመጫወቻ ጊዜያቸው ያላለፈባቸው፣ የአሸናፊነት መንፈስ ያላቸው እና በተፈጥሮ ችሎታቸውም ለእኔ ክለብ አጨዋወት የሚመቹ ተጨዋቾችም ናቸው፡፡
ሊግ፡- በመጨረሻ…
አሰልጣኝ ደረጄ፡- የአሰልጣኝነት ሙያዬ ላይ ስሰራ ሁሌም ቢሆን የስራ ነፃነትን እፈልጋለሁ፡፡ ወደ ወልቂጤ ከተማ ሳመራም በዚህ ጉዳይ ላይ ከክለቡ አመራሮች ጋር መብቴን ጠይቄ በመነጋገር ስለተከበረልኝ በዚህ ውጤታማ ልሆን ችያለሁና ይሄን ውጤት ላሳካልኝ ፈጣሪዬ የቅድሚያ ምስጋናዬን አቀርባለሁ፡፡ ለወልቂጤ ከተማ ውጤት ማምጣት የክለቡ አመራሮች ከእኔ ጎን መሆን እንደዚሁም ደግሞ ረዳት አሰልጣኜ አብዱልሃኒ፣ የክለቡ ደጋፊዎች እና ባለቤቴም ሁሌም ከእኔ አጠገብ በመሆንና ትኩረቴንም ሰብስቤ ስራዬን እንድሰራ የጠቀመችኝ ነገር አለና በዚህ አጋጣሚ ለእነሱ እና የሚኒቴሪ ተራ የጤና ቡድን አባላቶችም ብዙዎቹ የጉራጌ ብሔረሰብ አባል ስለሆኑና ወልቂጤ ከተማም በእነሱ የሚደገፍ ስለሆነም ሁሌም ስለ ቡድኑ የውድድር ጉዞ በመከታተል እና እኔንም በማበረታታት ከጎናችን ቆመዋልና እነሱን ጭምር ነው የማመሰግነው፡፡