Google search engine

በረከት ደስታ /ፋሲል ከነማ/ “ግብ ከማስቆጠር  ይልቅ የግብ ኳስ  መስጠት ደስታን ይፈጥርልኛል”

 

ፋሲል ከነማ  ሲዳማ ቡናን 4-0 ካሸነፈ በኋላ በቀጣዩ  የአማራ ደርቢ ግጥሚያ  ባህርዳር ከተማን ገጥሞ  ያለ ግብ አቻ የተለያየ ሲሆን ቤትኪንግ መሪነቱንም  ትናንት የተደረጉትን ጨዋታዎች ውጤት ሳይጨምር  አሁንም በቀዳሚነት ይዞ ይገኛል፡፡

ለፋሲል ከነማ እግር ኳስ ክለብ በዘንድሮው የውድድር ዘመን የቡድኑ ቁልፍ ተጨዋችነትን በሜዳ ላይ እያስመለከተን የሚገኘው በረከት ደስታ ከሊግ ስፖርት ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ ጋር  በቡድናቸው አቋም እና ከራሱ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ  አጠር ያለ ቆይታን አድርጎ መመለስ ባለበት ጥያቄዎች ዙሪያ ምላሹን ሰጥቶናል፤ ቃለ-ምልልሱም እንደሚከተለው ይቀርባል፡፡

ከባህርዳር ከተማ ጋር ስላደረጉት የአማራ ደርቢ ጨዋታ

“ይህ የደርቢ ጨዋታ  በሁለታችንም  መካከል እስካሁን ከተደረጉት በጣም የላቀው፣ ምርጥ የነበረ፣  ጥሩም ፉክክር  የታየበት እንደዚሁም ደግሞ እልህ የተጋባንበትና  በጨዋታው ላለመሸነፍም ጉሽሚያዎችም የታየበት ሲሆን ተመልካቹም ጥሩ ነገርን ሊመለከት ችሏል”፡፡

ስለ አቻ ውጤቱና  በተመዘገበው ውጤት ስለተሰማቸው ስሜት

“ወደ ሜዳ የገባነው ማሸነፍን ፈልገን ነበር፤ ማሸነፍም ይገባን ነበር፤  ያም ሆኖ ግን የባህርዳሮች የመከላከል ጥንካሬና  ብቃት ብዙም ወደ እነሱ የግብ ክልል በተደጋጋሚ ጊዜ እንዳንደርስ ስላደረገንና ሲከላከሉም እንደ ቡድን በጣም  ከፍተኛ ስለነበር  ነጥብ ተጋርተን ልንወጣ ችለናል፤ ባስመዘገብነው የአቻ ውጤትም ተከፍተናል”፡፡

ከባህርዳር ጨዋታቸው በፊት ሲዳማ ቡናን በሰፊ ግብ ስለማሸነፋቸው

“ይህን ጨዋታ ከመርታታችን በፊት በ3 ግጥሚያዎች ላይ ነጥብ ጥለን ነበር፤  ያም የቁጭት ስሜት ስለፈጠረብን ለመነሳሳት ቻልን፤ ራሳችንንም በሞራል ልንገነባም ቻልን፡፡ ከዛም ግጥሚያውን አሸነፍን፡፡

ሲዳማን በሰፊ ግብ እናሸንፋለን ብለው ጠብቀው እንደነበር

“በፍፁም፤ ምክንያቱም ተጋጣሚያችን ጠንካራ  ቡድን  ከመሆኑ አንፃር  በሜዳ ላይ  ጥሩ  ፉክክር ይገጥመናል ብለን አሰብን  እንጂ በዛን ያህል የጎል ልዩነት ስለማሸነፍ በጭራሽ  አላሰብንም፡፡ ወደ ሜዳ ስንገባ ግን ፕሬስ አድርገን በመጫወትና  ግብ  በማስቆጠርም ስለቀደምናቸው  እነሱን ልናሸንፍ ቻልን”፡፡

ወደ መሪነት መምጣታቸው ስለፈጠረላቸው ነገር

“ይሄ ለእኛ  የቀጣይ  ግጥሚያዎቻችን ላይ  ትልቅ ሞራል  ሆኖን ወደ ሜዳ እንድንገባና በአሸናፊነት መንፈሱም እንድንቀጥልበት የሚያደርገን ነው”፡፡

ሲዳማ ቡናን በረቱበት ጨዋታ ስለነበራቸው ጥንካሬና ክፍተት

“ያን ዕለትም ሆነ  እኛ  በምንታወቅበት ሁኔታ ኳስን ስንጫወት ተግባብተንና ወደፊትም አጥቅተን  ስለሆነ  ግቦችን የምናስቆጥርበት እድሉ በጣም  አለን፤   ጎል በማስቆጠሩ ላይም ሁሌ  ከአንድ ተጨዋች ብቻ የሚጠበቅ ስላልሆነም ይሄ ጥንካሬያችንን የሚገልፀው ነው፤ ክፍተት ጎንን በተመለከተ በማሸነፍ ውስጥ እንዳለ ብናምንም ያን ዕለት ግን እነሱ ወደ እኛ የሜዳ ክልል ለመምጣት ብዙም ስላልደፈሩ ልናገር አልችልም”፡፡

በምርጥ ብቃታቸው ላይ ይገኙ እንደሆነ

“እንደዛ ለማለት ጊዜው ገና ይመስለኛል፤ በእስካሁኑ ጨዋታ ግን ቡድናችንን  እንደተመለከትኩት  ዛሬ ጥሩ ይሆንና ነገ ደግሞ ያን አንደግመውም፤ ከእዚህ በኋላ ግን በጣም እየተሻሻልን የምንሄድ ይመስለኛል”፡፡

ስለ ወቅታዊ የራሱ አቋም

“ዘንድሮ በተለየ መልኩ ጥሩ ነኝ ብዬ አስባለው፤ በብዙ ነገሮችም ተሻሽዬ ቀርቤያለው፡፡ ጎል ማስቆጠር መጀመሬም ለእኔ ብርታት ስለሚሆነኝ በቀጣይ ጊዜም ከፈጣሪ እርዳታ ጋር ሌሎች ጎሎች እንደሚኖሩኝ እምነቴ ነው”፡፡

ከጎል ማስቆጠር ይልቅ ኳሶችን ለቡድን ጓደኞቹ እያቀበለ ስለመሆኑና የግብ እድሎችንም ስለመፍጠሩ

“ይሄ ከእግር ኳስ ችሎታዬ አንዱ ኳሊቲዬ ነው፤ ብዙ ግቦችን በተደጋጋሚ ለማስቆጠር ባልችልም ቅድሚያ የምሰጠው ለቡድን ውጤት ስለሆነ ያን ማደረግ መቻሌ ደግሞ ለእኔ ከፍተኛ ደስታን ይፈጥርልኛል”፡፡

በሲዳማ ቡና  ላይ ጎል ካገባ በኃላ የተጠባባቂ ግብ ጠባቂያቸውን ሄዶ ስለማቀፉ

“እሱ ወደ ጨዋታው ልገባ ስል ለእኔ ካለው ጥሩነት  ዛሬ ግብ እንደማገባ ነግሮኝ ነበር፤ ለእዛም ነው ደስታዬን ላጋራው ብዬ ያቀፍኩት”፡፡

ስለ ሻምፒዮናነት እቅዳቸው

“ወደ አሸናፊነት መንፈሱ መመለሳችን በጣም አስደስቶናል፤ ለሻምፒዮንነት እንደምንጫወትም ይታወቃል፡፡ ዋንጫውን ማንሳትም ስለምንፈልግ ያ እልማችንም ይሳካል”፡፡

በመጨረሻ

“ከባህርዳር  ጋር የነበረንን ጨዋታ በአቻ ውጤት ብናጠናቅቅም መልሰን ወደ አሸናፊነት መንፈሱ መመለሳችን አይቀርም፡፡ በቀጣይ ግጥሚያዎቻችን ላይም በጣም ጠንካራውን ፋሲል ከነማን የምንመለከትበት ጊዜም ሩቅ ስላልሆነም ደጋፊዎቻችንንም በውጤት ማስደሰታችን አይቀርም”፡፡

spot_img
ተመሳሳይ ጽሁፎች

አስተያይት ያስፍሩ

እባክዎን አስተያይትዎን ያስፍሩ
እባክዎን ስምዎን እዚህ ያስገቡ

ትኩስ ዜናዎች

%d bloggers like this:
P