ቅ/ጊዮርጊስ ወደ ናዝሬት ተጉዞ አዳማ ከተማን በተፋለመበት የአበበ ቢቂላው ስታዲየም ጨዋታ ሁለቱም ክለቦች ግጥሚያቸውን ያለ ግብ በአቻ ውጤት ያጠናቀቁ ሲሆን በጨዋታውም ከአዳማ ከተማ ወገን በረከት ከግብ ጠባቂው ጋር ፊት ለፊት ተፋጦ ያገኛት ኳስ ወደ ውጪ ስትወጣበት ቴዎድሮስ በቀለም ወደ ግብ የመታት ኳስ የውስጥ ብረት ሲመልስበት ከቅ/ጊዮርጊስ በኩል ደግሞ አሜ መሐመድ ወደጎል የመታት ኳስ በአዳማ ከነማ ተከላካይ ክንድ እና ሆድ መሀል ሊመለስ በመቻሉ ጎል የማስቆጠር ዕድላቸው ሳይሳካላቸው ቀርተዋል፤፡፡
የቅ/ጊዮርጊስ እና የአዳማ ከተማ ክለቦች ረቡዕ ዕለት ያደረጉት የሊጉ የተስተካካይ ጨዋታ ሁለቱም ቡድኖች ግጥሚያውን ለማሸነፍ ከፍተኛ ፉክክር ያደረጉበት ሲሆን ጨዋታውም በብዙ ደጋፊዎች ታጅቦ የተከናወነ መሆኑም ስሜትን ሊሰጥ ችሏል፡፡
የቅ.ጊዮርጊስ እና የአዳማ ከነማ ክለቦች የረቡዕ ዕለት ጨዋታቸውን ከማድረጋቸው በፊትም የአዳማ ከነማ ክለብ ደጋፊዎች የቀድሞ ተጨዋቻቸው ለሆነው እና ለወልዲያ በሚጫወትበት ጊዜም በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ቅጣት ተጥሎበት የነበረውን እና አሁን ቅጣቱን የጨረሰውን ብሩክ ቃልቦሬን ለሁለተኛው ዙር ማስፈረማቸውን ተከትሎ የቡድኑን ማልያ እንዲለብስ አድርገው እና ማስታወሻ አዘጋጅተው በመስጠት መልካምና ጥሩ አቀባበል ያደረጉለት ሲሆን ተጨዋቹም ምስጋናውን ገልፆላቸዋል፡፡
የቅ/ጊዮርጊስ እና የአዳማ ከነማ ጨዋታ ከተጠናቀቀ በኋላ ከሁለቱም ቡድን ተጨዋቾች ውስጥ ግጥሚያውን አስመልክቶ እና በክለቦቻቸው ዙሪያ ጥሩ እንቅስቃሴ እያሳዩ ካሉ ተጨዋቾች መካከል የቅ/ጊዮርጊሱን ሄኖክ አዱኛን እንደዚሁም ደግሞ የአዳማ ከተማውን ኤፍሬም ዘካሪያስን አናግረናቸው የሚከተለውን ምላሽ ለሊግ ስፖርት ጋዜጣ ሰጥተዋል፤ ተከታተሏቸው፡፡
የአዳማ ከነማን ከሜዳቸው ውጪ ተፋልመው አቻ ስለተለያዩበት የተስተካካይ ጨዋታ
“ቅዱስ ጊዮርጊስ እና የአዳማ ከነማ ረቡዕ ዕለት ያደረጉት ጨዋታ በጣም አሪፍ ነበር፤ የደርቢ ያህል ፉክክር የተደረገበትም ነው፤ በሁለታችን ፍልሚያ እኛ ተደጋጋሚ የሆኑ የጎል እድሎችን ብንፈጥርም ጎል ማስቆጠር ሳንችል ስለቀረን የማሸነፍ እድላችንን ሳንጠቀምበት ቀርተናል”፡፡
የተጋጣሚያቸው የአዳማ ከነማን አቋም አስመልክቶ
“አዳማ ከነማ ትልቅ ቡድን ነው፤ በሜዳ ላይ እንቅስቃሴያቸውም እንደ ቡድንም እንደግልም ጥሩ ብቃትን የሚያሳዩ ተጨዋቾች አሏቸው ናቸው፡፡ ያም ሆኖ ግን ረቡዕ ዕለት በነበረው የሁለታችን የእርስ በርስ ጨዋታ እኛ ከእነሱ የተሻልን እና ጥሩ የነበርን ቢሆንም እነሱም ጠንካራ ነበሩ ደግሞም የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብን በተቃራኒነት የሚገጥሙ አጠቃላይ የሃገሪቱ ቡድኖች ሁሌም ጠንካራ ሆኖው የሚቀርቡበት ሁኔታ ስላለም ይሄ ለቡድናችን ብዙም አዲስ የሚባል ሆኖ አላገኘሁትም፡፡”
ከወላይታ ድቻ ጋር ወደ ቡድቲ በመጓዝ ስለምታደርጉት ጨዋታ
“የወላይታ ድቻ ጋር የሚኖረን የነገው የእሁድ ጨዋታ ከሜዳችን ውጪ የምናደርገው ነው፡፡ ይህ ጨዋታም የአንደኛው ዙር የመጨረሻችን ግጥሚያ እና ምንአልባትም የያዝነውን መሪነት አጠናክረን በማስጓዝ ውድድሩን በመሪነት ልንጨርስ የምንችልበት እድሉን ሊፈጥርልን ስለሚችል ጨዋታውን አሸንፈን ለመውጣት በሙሉ ዝግጅት ላይ እንገኛለን፤ ግጥሚያውንም እናሸንፋለን”፡፡
ቅዱስ ጊዮርጊስን ከወቅታዊ ብቃቱ በመነሳት አቋሙ ላይ መሻሻልን እየተመለከታችሁበት ነው?
“አዎን፤ ቡድናችን ላይ ከበፊቱ የውድድሩ ጅማሬያችን አንፃር ጨዋታዎችን በተከታታይ እያሸነፍንበት የመጣንበት አጋጣሚ ስለነበር ከፍተኛ መሻሻል አለን፡፡ ከዛ ውጪም ከዓምናው የተሻለ የሜዳ ውጪ ጨዋታዎችን ከማሸነፋችን በተጨማሪ ጎሎችም እየተቆጠሩብን አይደለምና ይሄ ጥንካሬያችን ነው፤ አሁን ላይ በጥሩ ብቃት ላይም ነው የምንገኘው፡፡”
የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ፉክክር ክለቦች በተቀራረበ ነጥብ ላይ ይገኛሉና ውድድሩን እንዴት ተመለከትከው
“የዘንድሮው የፕሪምየር ሊግ ፉክክር በርካታ ክለቦች ተደራራቢ ግጥሚያዎችን እያደረጉ ያሉበት ሁኔታ ቢኖርም ከነጥብ መቀራረብ አኳያ ስትመለከተው ያለው ፉክክር ትኩረትን የሚስብ ነው፡፡ በሻምፒዮንነት ፉክክሩ የእኛ ክለብ መሻሻልን አሳይቷል፤ ከሜዳው ውጪም ጥሩ የሚባሉ ድሎችንም አግኝቶበት የተመለሰበት እና በመሪነትም የተቀመጠበት ሁኔታ ስላለ እንዲህ ያለ ፉክክር ሁሌም ቢኖር መልካም ነው፤ እኛም የሻምፒዮናነቱን ዋንጫ ለማንሳት ጠንክረን እየሰራን ነው”፡፡
ቅዱስ ጊዮርጊስ የሁለተኛው ዙር ላይ የተለየ ቡድን ይዞ ይቀርባል? ወይንስ በአሁኑ ጉዞው ይቀጥላል…?
“የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የውድድር ተሳትፎአችን ላይ ክለባችን አሁንም ጠንካራ ነው፤ የሁለተኛው ዙር ላይ ደግሞ የበለጠውን ጠንካራ እና የሻምፒዮና ቡድኑን ነው ይዞ ነው የሚቀርበው፤ ለደጋፊዎቻችንም መናገር የምፈልገው ዋንጫውን አንስተን በድል እንደምናስጨፍራቸው ነው”፡፡
የቅዱስ ጊዮርጊስ የመጀመሪያው ዙር ጥንካሬዎቹ እና ክፍተቶች ምን ምን ነበሩ?
“የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የአንደኛው ዙር ተሳትፎአችን ላይ በክፍተት ደረጃ እንደ ቡድኑ ተጨዋችነቴ ብዙም ችግሮች ነበሩብን ብዬ አላስብም፤ ለእኔ የሜዳችን ውጪ ተከታታይ የሆኑ ግጥሚያዎችን አሸንፈን የመጣንበት ሁኔታ ስለነበርና ጠንካራ ጎኖችም ስለሚበዙብን ደካማ ጎን ነበረን ለማለት እና ለመናገር አልደፍርም፡፡ ለአንድ ቡድን ክፍተት ወይንም ደግሞ ደካማ ጎን ሁሌም አለ ያ ካለም የሁለተኛው ዘር ጨዋታዎች ሲጀመሩ የኮቺንግ ስታፋችን ብዙ ነገሮችን ስለሚያውቁ እና የሚነግሩንም ስለሆነ በእዛ ላይ ትኩረትን አድርገን እንሰራለን”፡፡
የጅማ አባጅፋሩ እና የቅዱስ ጊዮርጊሱ ሄኖክ አዱኛ የሜዳ ላይ ብቃት አምና እና ዘንድሮ ሲነፃፀር
“የእኔ የሜዳ ላይ አቋም አምና በጅማ አባጅፋርም ሆነ ዘንድሮ በቅዱስ ጊዮርጊስ ተመሳሳይ እና አንድ አይነት ነው፡፡ በውጪ ሀገር አሰልጣኝ በሚሰለጥነው የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ውስጥም አበረታች ብቃት እያሳየውም እገኛለው፤ ለቅ/ጊዮርጊስ ስትጫወት እንደሌላው ቡድን አይደለም፤ በቦታዬ ያለቦታዬ የሚባል ነገር የለም፤ በውጪው አሰልጣኝ በሚሰጠኝ የጨዋታ ሚናም ክለቤን በግራ ላይም በቀኝ ላይም በመጫወት የተሰጠኝን ሃላፊነት በቀጣይ ጊዜም ጠንክሬ ሰርቼ በመምጣት ክለቤን ለውጤት ለማብቃት እንደምችልም ካለኝ ጥሩ አቋም አንፃር ለመናገርም እፈልጋለው፡፡”
በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከክለባችሁም ከክለባችሁም ውጪ ጥሩ አቋምን አሳይተዋል ብለህ የምትጠቅሳቸው ተጨዋቾች
“የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጨዋቾች ውስጥ ሊጉ ላይ ጥሩ ብቃትን እያሳዩ የሚገኙት ተጨዋቾች ሁሉም ናቸው፤ በእነሱ እንቅስቃሴም ደስተኛ ነኝ፤ ከእኛ ክለብ ውጪ ደግሞ በሚዲያ ደረጃ ከምሰማውም ሆነ ካየኋቸው ተጨዋቾች መካከል የመቐሌ 70 እንደርታው አማኑኤል ወ/ሚካኤል የመከላከያው ምን ይህሉ ወንድሙ እና የሲዳማ ቡናው አዲስ ግደይ በብሄራዊ ቡድኑ ደረጃም ስለማውቃቸው ጥሩ ነገርን እየሰሩ ነው፤ ወደፊትም ከዚህ በላይ ምርጥ የሚባል ብቃታቸውንም ያሳያሉ”፡፡
የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎችን በተመለከተ
“በቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች ፊት ሆነህ ኳስን መጫወት በጣም ነው የሚያስደስተው፤ በቃ ኳስን ገና የጀመርኩኝ ያህልም ነው የምቆጥረው፤ ከዛ ውጪም በእነዚህ ደጋፊዎች ፊት ለመጫወት መቻሌም እድለኛ ነኝና ይሄ በመሆኑም እነዚህን ደጋፊዎቻችንን ለማስደሰት ሁላችንም ጠንክረን መስራት አለብንና ይህንንም ተግባራዊ እናደርጋለን”፡፡