Google search engine

“በቅ/ጊዮርጊስ ክለብ ቆይታዬ ደማቅ የውጤት ታሪክ እንዲኖረኝ እፈልጋለው” በረከት ወልዴ /ቅ/ጊዮርጊስ/

 

ቅ/ጊዮርጊስ በሐዋሳ ዩንቨርስቲ ሜዳ ላይ የሸገር ደርቢ ጨዋታውን  ከኢትዮጵያ ቡና ጋር አድርጎ  4-1 ከረታ በኋላ የክለቡ የአማካይ ስፍራ ተጨዋች በረከት ወልዴ ስለ ዕለቱ ጨዋታና ስለ ቡድናቸው የዘንድሮ የፕሪምየር ሊግ ጉዞ እንደዚሁም ደግሞ ከራሱ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ከሊግ ስፖርት ጋዜጣ  ጋር  ቆይታን አድርጓል፡፡

ቅ/ጊዮርጊስ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ባደረገው የሸገር ደርቢ  ጨዋታ  የመጀመሪያውን ግብ በአበበ  ጥላሁን  ጉዳት ሳቢያ ራሱ ወደ  እጅ

ፎሪ  ያወጣውን  ኳስ በፌር ፕሌይ ቅ/ጊዮርጊሶች ይጫወቱታል ተብሎ ሲጠበቅ ሀይደር ወደ ቡና የግብ ክልል የመታውን ኳስ የቡድኑ አጥቂ ላግባት አላግባት በሚል የማመንታት ስሜት ተጫውቶ ግቧን ሊያስቆጥር የቻለ ሲሆን በእዚህም  የቡና ተጨዋቾች  ኳሷ ይሰጠናል  ብለው ሲጠብቁ ግቡ ስለተቆጠረ ስሜታቸውን መቆጣጠር አቅቷቸው  የቅ/ጊዮርጊስ ተጨዋቾችን ሲቃወሙና በጨዋታው ላይም ስሜታዊ ሆነው እንዲጫወቱም አድርጓቸዋል፡፡

በዕለቱ የሁለቱ ቡድኖች  ጨዋታ የፌር ፕሌይ ግብ መቆጠርን አስመልክቶ የከዚህ ቀደም ተመሳሳይ ግቦች እየተነሱ በሁለቱ ክለብ ደጋፊዎች መካከል ብዙ ነገሮች እየተባሉም ሲሆን ከጨዋታው በኋላም የቡናው አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ ግቧን አስመልክቶም ” ይህን አስተያየት ሲሰጥ የቅ/ጊዮርጊሱ አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ ደግሞ በተራው ” ይህን ብሏል፡፡

ቅ/ጊዮርጊስ ቡናን በረታበት ጨዋታ ቀሪዎቹን ግቦች ሁለቱን ሀይደር ሸረፋ ሲያስቆጥር አንዷን ቡልቻ ሹራ ሊያገባ ችሏል፤ ለቡና ደግሞ በባዶ ከመሸነፍ የዳኑበትን ግብ እንዳለ ደባልቄ ሊያስቆጥር ችሏል፡፡

ከቅ/ጊዮርጊስና ከኢትዮጵያ ቡና ጨዋታ በኃላ ሊግ ስፖርት ከቅ/ጊዮርጊሱ አማካይ በረከት ወልዴ ጋር በተለያዩ ጥያቄዎች ዙሪያ ያደረገው ቆይታ ይህን ይመስላል፡፡

ሊግ፦ በሸገር ደርቢ ለመጀመሪያ ጊዜ መጫወት ችለሃል፤ በአንተ አንደበት ስሜቱ እንዴት ይገለፃል?

በረከት፦ የሸገር ደርቢን በተመለከተ የማውቀው በታሪክ ነበር፤ በዛ ጨዋታ ላይም ተሰልፎ መጫወት የበፊት እልሜም ነበር፡፡  ዛሬ ላይ ግን ብዙዎቹ በሚጓጉለት የእዚህ ተጠባቂ ጨዋታ ላይ ከበፊት አንስቶ ልጫወትለት ለምፈልገው የቅ/ጊዮርጊስ ቡድን ተሰልፌ ስለተጫወትኩ በጣም ደስ ብሎኛል፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ ጨዋታውን ስላሸነፍም  ደስታዬ እጥፍ ድርብም ሊሆን ችሏል፡፡

ሊግ፦ የሸገር ደርቢ ጨዋታ ላይ መጫወት መቻል የሚፈጥረው የተለየ ስሜት አለ?

በረከት፦ በጣም፤ ሁለቱ ክለቦች የሀገሪቱ ትልቅና በብዙ ደጋፊዎችም የሚደገፉ ከመሆናቸው አንፃር ጨዋታቸው ሁሌም ተጠባቂ ነው፡፡ በዚህም ጨዋታ ላይ ከውጪ ሆነህ በምትመለከተው የደጋፊ ድባብ ለክለብህ አንድ ጥሩ ነገርን  ጠንክረህ እንድትሰራ ያደርግሃልና ይሄን ነው በዋናነት ለመመልከት የቻልኩት፡፡

ሊግ፦ ኢትዮጵያ ቡናን በሸገር ደርቢ ማሸነፍ ችላችኃል፤ የድል ስሜቱ ምን ይመስላል? መጀመሪያ ላይ ስላስቆጠራችሁት የፌር ፕሌይ ግብስ ምን ማለት ይቻላል?

በረከት፦ በቅ/ጊዮርጊስና በቡና ጨዋታ  ክለባችን ባሳካው ድል በጣም ነው የተደሰትኩት፡፡ ምክንያቱም በደርቢ ጨዋታ ላይ ግጥሚያን ማሸነፍ ለደጋፊዎቻችን የሚሰጠውን የተለየ ደስታ ከውጪ ሆኜም ሆነ ወደ ክለቡ ከገባው በኋላ በደንብ ላውቀው ስለቻልኩ ነው፡፡ ከዛ ውጪ ደግሞ በሊጉ የመጀመሪያ ሳምንት ጨዋታችን ከሰበታ ከተማ ስንጫወት ጥሩ ሆነን ነጥብን ጥለን ነበርና የደርቢው ጨዋታ ውጤት በጣም ያስፈልገን ስለነበር በእልህ ጭምር ስለተጫወትን ነው ኢትዮጵያ ቡናን ያሸነፍነው፡፡ መጀመሪያ ላይ ስላስቆጠርነው ግብ እኔ ተገቢ ነው ብዬ አላምንም፡፡ ያም ሆኖ ግን ሁኔታው ከተፈጠረ በኋላ በርካታ ደቂቃዎች ስለሚቀሩ ከዛ ተነስቶ መጫወት መቻል ለአንድ ቡድን ትልቅ ነገር ነውና ቡናዎች በዛ ደረጃ ሊጫወቱ ይገባቸው ነበር፡፡ እኛ ግን ይህን ጨዋታ ማሸነፍ በጣም ፈልገነው ስለነበር   እስከ መጨረሻው ሰዓት ድረስ በትጋት ስለተጫወትን ነው እነሱን ያሸነፍነው፡፡

ሊግ፦ ኢትዮጵያ ቡናን ለማሸነፍ  እንድትችሉ በዋናነት የረዳችሁ ነገር ምንድን ነው?

በረከት፦ በአጨዋወታቸው ጅማሬ  የእነሱን ስህተት ለመጠቀም ስለቻልን ነው ቡናን ለማሸነፍ የበቃነው፡፡ ቡናዎች ኳስን በመነካካት ነው የሚጫወቱት፡ ፡ ግን ይሳሳታሉ፡፡ ያን ስህተትም የእኛ ልምድ ያላቸውና እምቅ አቅምም ያላቸው ተጨዋቾቻችን በደንብ ስለሚያውቁት ያን አጋጣሚ ስለተጠቀምን ነው ውጤታማ የሆነው፡፡

ሊግ፦ በሶሰተኛው ሳምንት ጨዋታ ድሬዳዋ ከተማን ሰኞ ትፋለማላችሁ፤ ከግጥሚያው ምን ውጤትን ትጠብቃለህ?

በረከት፦ ቅ/ጊዮርጊስ በታሪኩ ሁሌም ቢሆን ግጥሚያዎችን ለማሸነፍ ወደ ሜዳ የሚገባ ክለብ ነው፤ የአቻ ውጤትና ሽንፈት በቡድኑ ውስጥ ተቀባይነት የለውም፡፡ ያን ሁሉም ተጨዋች ስለሚያውቅ ሁሌም ራሱን ዝግጁ አድርጎ ወደ ሜዳ ይገባልና ድሬዳዋ ከተማንም ከዚሁ መኀሻነት እኛ ልናሸንፋቸው እና ወደ መሪዎቹ ቡድኖችም በነጥም ለመ ጋት እየተዘጋጀን ይገኛል፡፡

ሊግ፦ ወደ ቅ/ጊዮርጊስ ቤት መጥተህ መጫወት ከጀመርክ በኋላ በውስጥህ እየተፈጠረብህ ያለው ስሜት ምን ይመስላል?

በረከት፦ ደስ የሚል ነገርን ነው እየተመለከትኩኝ ያለሁት፡፡ ለቡድኑ ስትጫወት ከአንተ ብዙ ነገሮች እንደሚጠበቁብህ ጠንቅቀህ ልታውቅ ይገባሃል፤ ይሄን ልረዳም ችያለው፡፡  ለቡድኑ መጫወት ሀላፊነቱ ከፍ ያለና ስሜቱም ደስ ስለሚል ጠንክረህ እንድትሰራም ሁኔታዎቹ ይገፋፉካል፡፡

ሊግ፦ ቅ/ጊዮርጊስ የመጀመሪያ ምርጫህ ሆኖ ወደ  ቡድኑ ያመራህበት ዋናው ምክንያት ምን ነበር?

በረከት፦ ወደዚህ ቡድን ስመጣ የቅድሚያ ጥሪውን ያቀረቡልኝ እነሱ ቢሆኑም የእኔም የመጫወት ፍላጎት እነሱ ጋር ስለነበር ነው ወደ ቡድኑ ላመራና ተስማምቼም በመፈረም እስከ መጫወት ደረጃ ልደርስ የቻልኩት፡፡

ሊግ፦ በወላይታ ዲቻ  ሆነህ  ቅ/ጊዮርጊስን በተቃራኒነት መግጠም ችለሃል፤ ከእነሱ ጋር ስትጫወት ግጥሚያው የተለየ ስሜት አለው?

በረከት፦ አዎን፤  ይኸውም ይሄ ክለብ ሀያል እና ብዙ ታሪኮች ያሉት ቡድን  እንደሆነ ስለምታውቅ ከእነሱ ጋር የምታደርገው ጨዋታ ሁሌም ቢሆን ድምቀትና የአማረ ስሜትን ይሰጥሃል፡፡ ከእነሱ ጋር የሚደረጉ ጨዋታዎችን የኳስ ተመልካች በነበርኩበት ጊዜ በሚገባ አይቻለሁ፤ አሁን ተጨዋች ከሆንኩ በኋላም ደግሞ እነሱን በተቃራኒነት ከመግጠም ባሻገር አብሬያቸውም ለመጫወት ችያለውና ቡድኑ ከሚይዛቸው ልምድ ያላቸው ተጨዋቾች አንፃር  ወደ ሜዳ ስትገባ ከእነሱ በልጠህ ለመገኘትና ተሽለህም ለመታየት ከመጣር አንፃር ሜዳ ላይ ያለህን አቅም ሁሉ ሰጥተህ ነው የምትጫወተውና ያለው ስሜት በጣም ደስ  ይላል፡፡

ሊግ፦ ቅ/ጊዮርጊስ እንደገባህ ማን ነው ስለ ክለቡ ታሪክ ብዙ ነገሮችን እንድታውቅና ቡድኑንም እንድትላመድ እያደረገ ያለው?

በረከት፦ በመጀመሪያ ደረጃ እኔ በተፈጥሮዬ ከሰዎች ጋር ብዙም የመግባባት ችሎታው  የለኝም፤ ዝምታን የምመርጥም ተጨዋች  ነኝ፡፡ ወደዚህ ቡድን በመጣሁበት ጊዜም ስለ ቡድኑ የማውቃቸው ነገሮች ቢኖሩም ይበልጥ ብዙ ነገሮችን እንዳውቅ እያደረጉኝ ያሉት የክለቡ የቦርድ አባላቶች ናቸው፡፡

ሊግ፦ በወላይታ ዲቻ ክለብ  ውስጥ ስትጫወት ወላጅ እናትህ እስኪ ወደ ሌላ ቡድን ውስጥ ገብተህም በመጫወት ራስህን ተመልከተው እንዳሉክም ሰማን ?

በረከት፦ የእውነት ነው እሷ በኳሱ ትልቅ ደረጃ ላይ እንድደርስላት በማሰብ የተናገረችው ነው፡፡

ወጥቼ  መጫወቱን እኔም እንደ እናቴ እፈልገው ነበርና  ልጫወትበት ወደም

ልገው ክለብ ላመራ ቻልኩ፡፡

ሊግ፦ በቤትኪንጉ ፕሪምየር ሊግ ለእናንተ የትኛው ቡድን የዋንጫ ተፎካካሪያችሁ ይሆናል?

በረከት፦ የዘንድሮ ውድድር  ሁሉም ቡድኖች ተጠናክረው የመጡበት ነው፡፡ ጥሩም ፉክክር በሊጉ ላይ እየተመለከትንበት ነው፡፡ ከዛም መነሻነት በሊጉ ለእኛ የዋንጫ ተፎካካሪ የሚሆኑ ክለቦችን እነዚህ ናቸው ለማለት አሁን ጊዜው አይደለም፡፡ ከስድስትና ከሰባት ሳምንት ጨዋታ በኃላ ግን ቡድኖቹን መለየት ይቻላል፡፡

ሊግ፦ በመጨረሻ ?

በረከት፦ ቅ/ጊዮርጊስ አሁንም ቢሆን ትልቅ ቡድን ነው፡፡  ወደ ነበረበት የውጤት ዝናው ልንመለሰው ዝግጁ ነን፡፡ ይህን ካልኩ በኳሱ እዚህ ደረጃ ላይ ያደረሰኝን ፈጣሪዬን እና ቤተሰቦቼን  ማመስገን እፈልጋለውኝ፡፡

spot_img
ተመሳሳይ ጽሁፎች

አስተያይት ያስፍሩ

እባክዎን አስተያይትዎን ያስፍሩ
እባክዎን ስምዎን እዚህ ያስገቡ

ትኩስ ዜናዎች

%d bloggers like this:
P