Google search engine

በቆሙና የአየር ላይ ኳሶች ሁላችንም የሀገራችን ቡድኖች ደካሞች ነን”
በዛብህ መላዮ /ፋሲል ከነማ/

ፋሲል ከነማ ከዩ.ኤስ ሞናሲር
እሁድ 10፡00


የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጠንካራ ተፎካካሪ ክለብ የሆነው ፋሲል ከነማ ወደ ሰሜናዊቷ አፍሪካ ሀገር ቱኒዚያ በመጓዝ ከዩ. ኤስ ሞናሲር ጋር ያደረገውን ጨዋታ በ2-0 ሽንፈት ማጠናቀቁ ይታወሳል፤ በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ካፕ ጨዋታ አገራችንን በመወከል የተጫወተው ይኸው ክለብ የመልስ ግጥሚያውን በነገው ዕለት በአዲስ አበባ ስታድየም ከቀኑ 10 ሰዓት ጀምሮ የሚያደርግ ሲሆን ይህን ጨዋታም ሩዋንዳዊው አልቢትር በዋና ዳኝነት እንደሚመሩት ይታወቃል፤ ፋሲል ከነማ በመጀመሪያው ግጥሚያ 2-0 መሸነፉን ተከትሎ ወደተከታዩ ዙር ለማለፍ ከሁለት ግቦች ልዩነት በላይ ማስቆጠር የሚጠበቅበት ሲሆን ይህን ለማሳካትም ከፍተኛ ፍልሚያን እንደሚያደርግ ታውቋል፤ ይህን ጨዋታ በተመለከተ የቡድኑ የአማካይ ስፍራ ተጨዋች በዛብህ መላዮ በቱኒዝ ካደረጉት ጨዋታ በመነሳት “የተጋጣሚያችንን አቋምም ሆነ እኛን ያሸነፉበትን መንገድ አውቀነዋል፤ ለእዛም የሚረዳንን ዝግጅት በበቂ ሁኔታ አድርገናል፤ ይሄ ስለሆነም ውጤቱን ቀልብሰን ወደተከታዩ ዙር ለማለፍ ጨዋታው ብዙ ከባድ ይሆንብናል ብለን እያሰብን አይደለም፤ ስለዚህም ወደ ተከታዩ ዙር እናልፋለን ሲልም ከሊግ ስፖርት ጋዜጣ ለቀረበለት ጥያቄ ምላሹን ሰጥቷል፡
የፋሲል ከነማውን አማካይ ወደ ቱኒዚያ ተጉዘው ስላደረጉት የአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ጨዋታቸው፣ ነገ ስለሚያደርጉት የመልስ ጨዋታ እንደዚሁም ደግሞ ስለዘንድሮው የፕሪምየር ሊግ ተሳትፎአቸውና ከራሱም ጋር በተያያዙ ጉዳዮች በተለይ ደግሞ በቅርቡ የልጅ አባት ከመሆኑና ስለ ባለቤቱም ጥያቄዎችን አንስተንለት ምላሾቹን ሰጥቶናል፤ተከታተሉት፡፡


በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ካፕ የመጀመሪያው ጨዋታ በቱኒዚያው ክለብ ሽንፈትን አስተናግደው ስለመመለሳቸው


“በቱኒዝ ባደረግነው የመጀመሪያው ጨዋታችን ቡድናችን ምንም እንኳን የ2-0 ሽንፈትን ሊያስተናግድ ቢችልም በእንቅስቃሴ ደረጃ ግን መጥፎ የምንባል አልነበርንም፤ በጨዋታው ጥሩ ልንንቀሳቀስ ችለናል፤ ያም ሆኖ ግን የሰሜን አፍሪካም ሆኑ የምዕራብ አፍሪካ ቡድኖች ብዙ ጊዜ ከኢትዮጵያ ቡድኖች ጋር ሲጫወቱ በምን መልኩ ሊያሸንፉን እንደሚችሉዋናውን መንገዱን ያውቁበታልና በእዛም የተነሳ ነው ልንሸነፍ የቻልነው፤ ከእነዛም የሽንፈቶቻችን ምክንያቶች መካከል ብዙ ጊዜ እነሱ በሜዳቸው በሚጫወቱበት ሰዓት በዳኛ ላይ ጫና የሚያሳድሩበት እና ዳኛን የሚጫኑበት ሁኔታም አለ፤ ያን ስል አሁን የተሸነፍንበትን ምክንያት በዳኛ ነው ለማለት ፈልጌ እንዳልሆነ ሊታወቅልኝ ይገባል፤ ስለዚህም በመጀመሪያው ጨዋታችንየተሸነፍንበትን ምክንያት ልናውቅና ዋናው ነገር ደግሞ የሽንፈታችንን ክፍተት ጎኖችምመረዳት መቻላችን ነውና ከእዚሁ ተነስተን የነገው ግጥሚያችን ላይ በተሻለ መልኩ ለጨዋታው ለመቅረብና ግጥሚያውንም አሸንፈን ለመውጣት ጠንክረን እንቀርባለን”፡፡


ፋሲል ከነማን በመጀመሪያው ግጥሚያ ለሽንፈት ያበቃው ነገር


“ወደ ቱኒዚያ በተጓዝንበት ጊዜ ቡድናችን ያጋጠመው ሽንፈት ከእዚህ ቀደም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንንም ሆነ ክለቦቻችንን በተደጋጋሚ ጊዜ የሚያጋጥም አይነት ሽንፈት ነው፤ ፋሲልም ከቱኒዚያው ክለብ ዩ .ኤስ ሞናሲር ጋር ባደረገው ጨዋታ የተሸነፈው በቆሙና በአየር ላይ ኳሶች ግብ ተቆጥሮበት ነው፤ በእዚህ አጨዋወት ደግሞ እኛኢትዮጵያኖች ደካሞች ነን፤ ይሄ የሽንፈት ችግር ሁሌም የሚያጋጥመን ነው፤ ይሄ ስለሆነምበእዛ ስፍራ ላይ ጥቃት እንዳይደርስብንየመጫወቻ ቦታውን በመዝጋት በክፍተቶቻችን ላይ ስራዎችን ልንሰራ የሚገባው፤ ከዛ ውጪ ደግሞ እኛ ሁሌም እነሱ ወደሚጠቀሙበት የጨዋታ እንቅስቃሴ ውስጥ ስለምንገባም ነው ለጥቃት የምንዳረገው፤ ይሄ ስለሆነም ወደ እነሱ አጨዋወት ውስጥ ሳንገባ በራሳችን ይኸውም በአጭር እና ኳስን ተቆጣጥረን በምንጫወትበት የጨዋታ ታክቲክ ውስጥ በመግባት ከግጥሚያው የተሻለ ነገርን ከሜዳው ይዘንመውጣት እንችላለን”፡፡


ፋሲል ከነማ ለነገው የመልሱ ጨዋታ በምን መልኩ እንደተዘጋጀ እና ምን ውጤት እንደሚያመጣ


“በመጀመሪያው ጨዋታ ወደ እነሱ ሀገር ተጉዘን የ2-0 ሽንፈትን ማስተናገዳችን ይታወሳል፤ በሜዳው የሚጫወት ቡድን ደግሞ ብዙ ጊዜ ግጥሚያን የሚያሸንፍበት ሁኔታ አለ፤ለእዛም ከመጀመሪያው ጨዋታችን በመነሳት ተጋጣሚያችንን በምን መልኩ ማሸነፍ እንደምንችል በሚገባ ተዘጋጅተንበታል፤ በቱኒዝ ግጥሚያችን ቡድናችን 2-0 መሸነፉን ተከትሎ ውጤቱን ሰፊ አድርገው የሚያስቡ ሊኖሩ ይችላሉ፤ እኛ ግን ለእዚሁ የመልስ ጨዋታ ከተጋጣሚያችን ብቃት በመነሳትና ካደረግነው ዝግጅትም አንፃር የመጀመሪያውን ጨዋታ ውጤት ቀልብሰን ወደተከታዩ ዙር እንደምናልፍ እርግጠኛ ነኝ”፡፡


በቱኒዚያ ካደረጋችሁት ጨዋታ በመነሳት እነሱ እኛን በምን መልኩ እንደሚበልጡን


“የቱኒዚያው ቡድን እኛን ድል ባደረጉበት ጨዋታ በዋናነት ሊበልጡን የቻሉት ታክቲካል ዲስፒሊን ሆነው ስለተጫወቱ ነው፤ የሰሜን አፍሪካ ቡድኖች ደግሞ ብዙ ጊዜ በእዚህ አጨዋወት ይበልጡናል፤ በአጨዋወቱ ውጤታማም ናቸው፤ ከዛ ውጪ በረጅም እና የአየር ላይ ኳስ ጨዋታምከእኛ የተሻሉ ናቸው፤ የእኛ ቡድን ጥሩ የነበረው ኳስን ተቆጣጥሮ ለመጫወት ሲሞክር ብቻም ነው”፡፡


በኮቪድ ወረርሽኝ ለበርካታ ወራቶች ከኳስ ርቆ ዳግም ወደ ጨዋታ ስለመመለሱ


“በአገራችንም ሆነ በዓለም ደረጃ በተከሰተው በእዚሁ ወረርሽኝ ምክንያት ከኳሱ የራቅኩበት ጊዜ ለእኔ ብቻ ሳይሆን ለሁሉም እግር ኳስን ለሚጫወትም ሆነ ለሚመለከት አካል በጣም ከባድ ነበር፤ በተለይ እኔን በሚመለከት ከእዚህ ቀደም ክረምት መጥቶ እንኳን ማረፍ የማልወድ አይነት ተጨዋች ስለነበርኩ ያ ሲያጋጥመኝ ሊደብረኝ ቢችልም በሌላ ጎኑ ሳየው ደግሞ በጣም የተደሰትኩበትም ሁኔታ ነበር”፡፡


ከእግር ኳሱ በራቀበት ሰዓት የተደሰተው በምን እንደሆነ


“በኮቪድ ወረርሽኙ ወቅት ባለቤቴ ነፍሰ ጡር ነበረች፤ በእዚህን ጊዜም ኳስን ሳልጫወት በቀረሁበት ሰዓት ላይ እሷን በመንከባከብ እና የብቸኝነት ስሜትም እንዳይሰማት ሁሌም ከጎኗ በመሆኔ ነበር የተደሰትኩት፤ ከእዚህ በፊት ከባለቤቴ ጋር ለእንዲህን ያህል ጊዜ አሳልፌ አላውቅም ነበር፤ አሁን ግን አሳለፍኩ፤ ያ ልዩ የደስታ ስሜትን የሰጠኝ ጊዜያት ነበር”፡፡


ስለ ባለቤቱና ስለትውውቃቸው


“ባለቤቴ ቅድስት አመራ ነው የምትባለው፤ የመቐለ ዩንቨርስቲ ተማሪም ነበረች፤ ከሶስት ዓመት በፊትም ነው ለፋሲል ከነማ ስፈርም ቀድሞ ለወላይታ ድቻ አብረን በምንጫወትበት ሰዓት ጓደኛዬ በነበረው ሙባረክ ሽኩር አማካኝነት ሻይ ቡና እንል በነበርንበት ሰዓት ላይ ከእሷ ጋር ትውውቃችን የተጀመረው፤ ከእዛን ጊዜም አንስቶ ትውውቃችን በጣሙን ስለሰመረ ከጓደኝነት የተጀመረው ጉዞ ሰርግ ባይከናወንበትም ለትዳር ግን ልንበቃበት ችለናልና ባለቤቴን በተመለከተ ባለፉት ሶስት ዓመታት ትውውቃችን ከእኔ የኳስ ህይወት ጀርባ ትልቁን ስራ ስታከናውን የነበረች ናት፤ ከእዛ ውጪም ለእኔ ሀሳቢ ብሎም ደግሞ ስፖርተኛ ስትሆን አህምሮ ብዙ ቦታ ስለሚሆን በምንም ነገር እንዳልጨናነቅ እኔን ከመርዳት ባሻገር ቤተሰቦቼንም በስራ የምታግዝ በጣም ቅን ሰው ነችና በፈጣሪ ስም ደጋግሜ ላመሰግናት እፈልጋለውኝ”፡፡


የሰርግ ስነ-ስርዓትን ያለማድረግ ምክንያታቸው


“የሰርጉን ስነ-ስርዓት በተመለከተ በእኔም ሆነ በእሷ በኩል ፕሮግራሙ እንዲደረግ ከፍተኛ ፍላጎት የነበረ ቢኖርም በቤተሰቦቿ በኩል ግን ያልተስማሙበት እና ሰርጉንም ያልተቀበሉበት ሁኔታ ስለነበር ነው እስካሁን ሳናከናውን የቀረነው፤ ሁለታችን አሁንም ቢሆን ግን ሰርጉን የማድረግ ከፍተኛ ፍላጎት ነው ያለን”፡፡


በጓደኝነት በቆዩበት ጊዜ ስላሳለፉት የፍቅር ህይወት


“በጣም ጣፋጭ የሚባል ጊዜን ነበር በጋራ ያሳለፍነው፤ ባለቤቴ መልካም እና ጥሩም ሴት ነበረች፤ ለእዛም ነው ቆይታችን ምርጥ ስለነበርም ወደ ትዳር ዓለሙ ውስጥ የገባሁት”፡፡


ከባለቤቱ በቅርቡ ልጅ ስለማግኘቱ


“የልጅ አባት ስትሆን ሁልጊዜም ቢሆን በጣም ደስ ይልሃል፤ እኔም በቅርብ ጊዜ ውስጥ ማለትም ህዳር 8 ቀን 2013 ዓ/ም ላይ በጣም ከምወዳት እና ከማፈቅራት ውዷ ባለቤቴ የሴት ልጅ ከአብራኳ ተበርክቶልኝ ስላገኘው በቃላት ልገልፀው የማልችለው አይነት የደስታ ስሜት ነው የተሰማኝ፤ በእዚሁ አጋጣሚም ይህ እንዲሆን ላደረጉት ፈጣሪዬና ባለቤቴም ከፍተኛ ምስጋናን ነው ላቀርብላቸው የምፈልገው”፡፡


በፀሎት በሚል ለልጃቸው ስለወጣላት መጠሪያ


“ለልጃችን የወጣላት ይህ ስም የማንም ጣልቃ ገብነት ሳይኖር መብቱን ለባለቤቴ ሰጥቻት እሷ ናትስሙን ያወጣችላት፤ ይህ ስም ለመውጣቱ ምክንያትም ነበረው፤ እኔም ሆንኩ እሷ ልጅን በጣም ነበር እንፈልግ የነበርነው፤ ልጅቷም ተወለደች፤ ይህቺ ልጅ እንዴት እንደመጣች እና እንደተወለደች ሁለታችንም እናውቅ ነበር፤ በፀሎትና በፈጣሪ እርዳታ ጭምር ያገኘናትም ነበረችና ለእዛም ነው ባለቤቴ ያወጣችላትን ስም እኔም እፈልገው ነበርና በፀሎት በሚል ልንሰይማት የቻልነው”፡፡


የፕሪምየር ሊግ ውድድራችን ሊጀመር ስለመሆኑ


“ከበርካታ ወራቶች በኋላ ቀድሞ ወደነበርንበት እግር ኳስ ዳግም ልንመለስ አሁን ላይ የቀናት እድሜን እየተጠባበቅን መሆኑ ደስ የሚል ስሜትን ነው በሁሉም የስፖርት ቤተሰብም ሆነ በእኛ ስፖርተኞች ላይ ከፍተኛ ደስታን እየፈጠረልን ያለው፤ አሁን ላይ የኮቪድ ወረርሽኝ ረገብ በማለቱም ነው ኳሱ እንዲጀመርም ከውሳኔ ላይ የተደረሰው፤ ወደ ስራ ስትመለስ ሁሌም ቢሆን ደስ ይላል፤ ከናፈቁህ ሰዎች ጋር ትገናኛለህ፤ የምትወደውን ኳስም ትጫወታለህ፤ ለእዚህ ላበቃንም ፈጣሪ ምስጋናን አቀርባለው”፡፡


በፋሲል ከነማ የተጨዋችነት ዘመን ቆይታው ዘንድሮ ምንን እያለመ እንደሆነ


“በእዚህ ክለብ ቆይታዬ እስካሁን ጥሩ ጊዜን እያሳለፍኩ ነው፤ ያም ቢሆን ግን እንደ ግልም እንደ ቡድንም የሚጠበቅብን ይኸውም ከእዚህ ጠንካራ ከሆነ ክለብ ጋር የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ ማንሳት መቻልን የግድ እፈልጋለውና ከዕልሜና ከምኞቶቼ አንፃር ይሄን ድል ማሳካት ይጠብቅብኛል”፡፡
ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተመርጦ ስለመጫወት
“እንደ ማንኛውም የአገራችን ተጨዋቾች እኔም ይህን እድል አግኝቼ ለተደጋጋሚ ጊዜ መጫወትን እፈልጋለሁ፤ እስካሁን በነበረኝ የተጨዋችነት ዘመን ቆይታዬ ግን ለምን አልተመረጥኩም፤ ለምንስ አልተጫወትኩም በሚል የተቆጨሁበትና የተናደድኩበት ጊዜ የለምና ሁሉም ነገር ፈጣሪ ሲፈቅድ ተመርጬ መጫወቴ የማይቀር ነው”፡፡


በመጨረሻ


“በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ካፕ ኢትዮጵያን በመወከል እየተወዳደረ ያለው ፋሲል ከነማ ነገ በሚያደርገው ጨዋታ ሁላችንም የቡድኑ ተጨዋቾች እስከመጨረሻው ሰዓት ድረስ አቅማችን የሚችለውን ሁሉ በማድረግ ቡድናችንን ወደተከታዩ ዙር ለማሳለፍ ከፍተኛ ጥረትን እናደርጋለን፤ ፋሲል ይህን ጨዋታ ለማሸነፍ መጀመሪያ በተረጋጋ መልኩ ወደ ሜዳ ሊገባ ይገባል፤ እነሱን ልንበልጥ በምንችልበት የጨዋታ ታክቲክ ውስጥም ዘልቀን በመግባትም ነው ስኬቱን የምናገኘውና ይሄን ነው እያሰብን የምንገኘው፤ ለውጤቱም ፈጣሪ ይርዳን፤ ከዛ ውጪ ለመናገር የምፈልገው ፈጣሪ በቅርቡ የልጅ አባት ስላደረገኝ አመሰግነዋለው፤ እንደዚሁም ለእኔ ሁሉ ነገሬ የሆነችውንና በጣምም የማፈቅራትን ባለቤቴንና ቤተሰቦቼንም የማልረሳ ነኝና እነሱም የምስጋናው ተቋዳሽ ይሁኑልኝ”፡፡

spot_img
ተመሳሳይ ጽሁፎች

አስተያይት ያስፍሩ

እባክዎን አስተያይትዎን ያስፍሩ
እባክዎን ስምዎን እዚህ ያስገቡ

ትኩስ ዜናዎች

%d bloggers like this:
P