Google search engine

“በብሔራዊ ቡድን ደረጃ ሀገርህን አገልግላት፣ ጥቀማት ተብለህ ስትጠራ እርካታ ይሰማሀል” መሳይ ጳውሎስ /ሐዋሳ ከተማ/

በመሸሻ ወልዴ /G.BOYS/


የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን /ዋልያዎቹን/ ከሐዋሳ ከተማ ክለብ በመመረጥ የተቀላቀለው ጠንካራው የመሀል ተከላካይ መሳይ ጳውሎስ በነገው ዕለት ከሩዋንዳ ብሔራዊ ቡድን ጋር በመቐለ ኢንተርናሽናል ስታዲየም የሚያደርጉትን የቻን 2020 የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ አሸንፈው እንደሚወጡ ለዝግጅት ክፍላችን ተናግሯል፤ ከእዚህ ግጥሚያ ጋር ተያይዞና ሌሎችን ጉዳዮች በማንሳት ተጨዋቹ የሚከተለውን ምላሽ ሰጥቷል፡፡
ሊግ፡- ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የተመረጥክ አዲሱ ተጨዋች ሆነሃል፤ በእዚህ ምን ተሰማህ?
መሳይ፡- የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ተመራጭ ተጨዋች ለመሆን መቻል ሁሌም ቢሆን መታደልና አስደሳችም ነገር ነው፤ ሃገርህን አገልግል፣ ሃገርህን ጥቀማት ተብለህ ስትጠራ የሚኖርህ የደስታ ስሜት ከፍ ያለ ነውና እኔ ይህንኑ እድል ሳገኝ ውስጤን ከፍተኛ እርካታ ተሰምቶታል፤ በእዚህ አጋጣሚም ለእዚህ ያበቃኝን ፈጣሪዬን አመሰግነዋለሁ፡፡
ሊግ፡- የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ተመራጭ ተጨዋች እሆናለሁ ብለህ ጠብቀህ ነበር?
መሳይ፡- ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የምመረጥበት ወቅትና ጊዜ መች እንደሚሆን አላውቅም እንጂ ይሄንን እድል እንደማገኝ አስብ ነበር፤ የእግር ኳስን የምጫወተው እኮ ክለቤን ካገለገልኩ በኋላ በሜዳ ላይ በምሰጠው አበረታች የሆነ ግልጋሎት ለሃገሬ ብሄራዊ ቡድን ለመመረጥ ነው፤ በእዚህም የሃዋሳ ከተማ ክለብ ውስጥ በነበረኝ የተጨዋችነት ዘመን ቆይታዬም በራሴ ላይ አበረታች የሆኑ ነገሮችን ስለተመለከትኩ አንድ ቀን የመመረጥ እድሉን እንደማገኝ እገምት ነበር፤ እንደውም እኮ መጀመሪያ የተመረጥኩት እድሜያቸው ከ23 አመት በታች ለሆናቸው የኦሎምፒክ ብሄራዊ ቡድን ነበር፤ ያኔ ከተጠራሁ በኋላ ክለባችን ወሳኝ የሊግ ግጥሚያዎች ስለነበሩትና እኔም ወደ ብሄራዊ ቡድን ስላልሄድኩ ያኔ ነበር የመጀመሪያውን የመመረጥ እድል ያገኘሁት፡፡
ሊግ፡- 2012 ለአንተ የተለየ አመት ይሆንልሃል?
መሳይ፡- ብዬ አስባለሁ፤ ምክንያቱም ለኢትዮጵያየቻን ብሄራዊ ቡድን በመመረጥ አዲሱን አመት በደስታና በጥሩ መልኩ ልቀበለው ችያለሁናከእዚህ በኋላ የሚኖሩትን ጊዜያቶች ደግሞ ከፈጣሪዬ እርዳታ ጋር ጠንክሬ እየሰራሁ ስለሆነ ለክለቤም ሆነ ለሃገሬ ውጤት ማማር የሚቻለኝን ግልጋሎት ሁሉ እሰጣለሁ፡፡
ሊግ፡- አሁን ላይ ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን እስከመመረጥደረጃ ደርሰሃል፤ በኳሱ የመጣህበት መንገድ ምን ይመስላል?
መሳይ፡- ወደ እግር ኳስ ተጨዋችነቱ የመጣሁት በተወለድኩበት የሃዋሳ ከተማ ውቅሮ አካባቢ ልጅ ሆኜ ኳሱን እያንከባለልኩ በመጫወት ነው፤ ትንሽ አደግ ካልኩ በኋላ ደግሞ በማሳደጊያ ውስጥ ነበር ያደግኩትና በፕሮጀክት ደረጃ መጫወት ጀመርኩ፤ ያኔ የፕሮጀክታችንም ስም መሰረት ክርስቶስ ይባል ነበር፤ በኋላ ላይ ደግሞ ለሃዋሳ ከተማ የወጣትና የዋናው ቡድን በመጫወት ነው የኳስ ጅማሬዬን የአሁን ደረጃ ላይ ያደረስኩት፡፡
ሊግ፡- ከቤተሰባችሁ ውስጥ የእግር ኳስን የምትጫወተው አንተ ብቻ ነህ? ስንተኛ ልጅስ ነህ? ስንት ወንድምና እህትስ አለህ?
መሳይ፡- ከቤተሰባችን ኳሱን የምጫወተው እኔ ብቻ ነኝ፤የቤቱም 3ተኛ ልጅ ነኝ፤ 3 ወንድሞችና 2 እህቶች ያሉኝ ሲሆን እነሱም ተማሪና ሰራተኞች ናቸው፡፡
ሊግ፡- የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ሩዋንዳን ለሚፋለምበት የነገው ጨዋታ ዝግጅቱን እየሰራ ይገኛል፤ የእስካሁኑ ልምምድ ምን ይመስላል?
መሳይ፡- የዋልያዎቹ ዝግጅት ጥሩ እና ደስ የሚልነው፤ሁሉም የቡድኑ አባላት በከፍተኛ ፍላጎትና ጥሩም የቡድን መንፈስ ላይ ሆነው እየተለማመዱ ይገኛልና ይሄን በመልካምነቱ የምጠቅሰው ነው፡፡
ሊግ፡- ዋልያዎቹ ምርጥ የተጨዋቾች ስብስብ ነው ያላቸው?
መሳይ፡- አዎን፤ ከዛ ባሻገርም ልምምዳቸውን ደስ በሚልና በፍላጎትም የሚሰሩ ጥሩ ብቃት ያላቸውን ተጨዋቾች ያካተተ እንደዚሁም ደግሞ በወጣቶች የተገነባንም ቡድን የያዘ ስለሆነ ይሄ ቡድን በቀጣይነት ጥሩ ነገር ይሰራል ብዬ ነው ተስፋ የማደርገው፡፡
ሊግ፡- ቤተሰባችሁ አሁን ሳይሆን በፊት ኳስን እንድትጫወት ይፈልጉ ነበር?
መሳይ፡- አይፈልጉም፤ ያን ጊዜ በትምህርቴ ላይ እንዳትኩር ነበር የዘወትር ምክራቸውን የሚሰጡኝ፤ በኋላ ላይ ግን የእኔን ከኳስ ሜዳ ያለመጥፋት ሲያዩና ወደኳስም ሳዘነብል ጊዜ ሲያዩኝ እኔን ማበረታታት ጀመሩና በእዚሁ ነው ኳሱ ላይ በርትቼ በመስራት የዛሬው ደረጃ ላይ የደረስኩት፡፡
ሊግ፡- የእግር ኳስን መጫወት በጀመርክበት ሰአት ማንን አድንቀህ ነበር ያደግከው?
መሳይ፡- የኢትዮጵያ እግር ኳስን በፊት አላይም ነበር፤ በኋላ ላይ ግን መመልከት ከጀመርኩበት ጊዜ አንስቶ የሐዋሳ ከተማ ተከላካይ የነበረውን ግርማ በቀለን ነው በማድነቅ ያደግኩት፤ ግርማ ጥሩ ችሎታ የነበረውና ጠንካራ ተጨዋች ከዛ ውጪ ደግሞ ሜዳ ከገባ አልሸነፍ ባይም ስለሆነ ለእኔ ተምሳሌቴ ተጨዋች ነበር፤ ከባህር ማዶ ተጨዋቾች ደግሞ እኔ የማደንቀው ተጨዋች ኮስልይኒን ነው፤ እሱን ምርጫዬ ያደርግኩትም የአርሰናል ደጋፊ ስለሆንኩ ሳይሆን ችሎታውን ስለምወደው ነው፡፡
ሊግ፡- ተከላካይ የሆንከው ከበፊት ጀምሮ ነው?
መሳይ፡- አዎን፤ በአንድ ወቅት ግን ለትምህርት ቤት ስጫወት የመሃል ሜዳ ስፍራ ተጨዋች በመሆን አሳልፌያለሁ፡፡
ሊግ፡- የሐዋሳ ከተማ ክለብ ውስጥ የነበረህን ቆይታ በምን መልኩ ትገልፀዋለህ? ሃዋሳንስ?
መሳይ፡- የሐዋሳ ከተማ ክለብ ውስጥ ያለኝ ቆይታ ጥሩ የሚባል ነው፤ ከወጣት ቡድኑ አንስቶ እስከዋናው ቡድን ደረጃም እየተጫወትኩበት የሚገኝ አሳዳጊዬ ቡድኔም ነው፤ አሁን ላይ በፕሪምየር ሊግ ደረጃም ለመጫወት 3ተኛ አመቴንም የያዝኩበት ቡድኔ ስለሆነ በጣም ነው የምወደው፤ ሐዋሳ ከተማን በተመለከተ ደግሞ ይህች የትውልድ ስፍራዬ በቃላት ብቻ የምትገለፅ አይደለችም፡፡ ለብዙዎች በመስብዕነቷና በመዝናኛነቷም የምትታወቅ ውብ ሃገርም ነችና እኔን ላፈራችኝ ለእዚህች ከተማዬ ታላቅ ምስጋናም ነው የማቀርብላት፡፡
ሊግ፡- ሐዋሳ ከተማ ለሁለት ጊዜያት ያህል የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ እንደዚሁም ደግሞ የጥሎ ማለፉንም ዋንጫ አንስቷል፤ ያ ድል አሁን ላይ ከራቀው ግን አመታቶች አልፎታል፤ በእዚህ ዙሪያ ምን የምትለው ነገር አለ?
መሳይ፡- የእውነት ነው፤ የሃዋሳ ከተማ ቡድን ከውጤት ጋር ከተጣላ ረጅም ጊዜን አስቆጥሯል፤ ኳስ ላይ ደግሞ ጎል ማግባት ካልቻልክ እንዲህ ያሉ ነገሮች ያጋጥምሃል፤ ከዛ ውጪም አሸናፊ መሆንም አትችልም፤ የእኛ ቡድን ብዙ ጊዜ ጥሩ ኳስ ቢጫወትም ጎል የማስቆጠር ችግር ስላለበት በእዚህ ውጤትን ያጣል፡፡
ሊግ፡- ጎል የማስቆጠር ችግሮቻችሁን ለመቅረፍ እና ውጤታማ ለመሆን ምን እየሰራችሁ ይገኛል?
መሳይ፡- የሐዋሳ ከተማ ክለብ በሌላ ቡድኖች ሁሌም የሚበለጠው በጨዋታ ሳይሆን የሚያገኛቸውን የግብ እድሎች ሊጠቀም ባለመቻሉ ነው፤ ይሄ ደግሞ በኳሱ ላይ ያጋጥማልና ችግሩን ለመቅረፍ እዚያ ላይ በርትተን ልንሰራ ይገባል፤ በተለይ ደግሞ ቡድናችን አሁን የያዛቸው ተጨዋቾች ወጣቶች ስለሆኑም ጥሩ ነገርን ይሰራሉ ብዬ ነው ተስፋ የማደርግባቸው፡፡ በአሁን ሰዓት የአጥቂው ስፍራም ላይ ጥሩ ችሎታ ያላቸውን ልጆች ይዘናል፤ ሃዋሳ ከእዚህ ቀደም የሊጉን ዋንጫ ሲያነሳ በአጥቂውም ሆነ በሌላ ስፍራ ላይ ያሉ ተጨዋቾች ነበር ለስኬት ያበቁትና ይሄን ድል የምንደግምበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም፡፡
ሊግ፡- ሐዋሳ ከተማ ውጤት ሲያጣና ሲያገኝ ያለህ ስሜት ምን ይመስላል?
መሳይ፡- ሐዋሳ ከተማ በሚያደርጋቸው ማናቸውም ጨዋታዎች ውጤት ስናጣ በኳስ ማሸነፍና መሸነፍን እንደዚሁም ደግሞ አቻ መውጣትን በሚገባ ስለማውቀው ለራሴ የሚሰማኝ ስሜት ቢኖርም ያ ስሜቴ ግን ነገ ውጤት ማግኘት እና ማሸነፍ እንዳለ ስለምረዳ በጣም የወረደ አይደለም፡፡ ውጤት ስናገኝ ደግሞ በጣም ነው ደስ የሚለኝ፡፡
ሊግ፡- የእግር ኳስን ተጫውተህ ከጨረስክ በኋላ የእረፍት ጊዜ መዝናኛ ምንድን ነው?
መሳይ፡- ከኳስ ውጪ መዝናኛዬ በስልኬ ላይ የኳስ ጌም አለና እሱን ማየት፤ ነው ከዛ ውጪ ሌሎች ነገሮች ላይ ብዙ ትኩረትን አላደርግም፡፡
ሊግ፡- በባህርይ እንዴት ትገለፃለህ?
መሳይ፡- ሰዎች ስለእኔ ቢናገሩ ብመርጥም እኔም ስለራሴ አንድ አንድ ነገር ብል ምንም አይደለም፤ በተፈጥሮዬ ከሰዎች ጋር ተግባቢ ነኝ፤ ከሰዎች ጋር ካልሆንኩም የሚደብረኝ አይነት ሰውም ነኝ፡፡
ሊግ፡- በመጨረሻ….?
መሳይ፡- የኢትዮጵያ እግር ኳስ ላይ በመጣሁበት የአጭር ጊዜ ውስጥ ለእዚህ ደረጃ በመብቃቴ በቅድሚያ ፈጣሪዬን አመሰግናለሁ፡፡ ከዛ በመቀጠል ከህፃንነት ጀምሮ ያሰለጠኑኝ አሉ፤ መልካሙ /ባዬ/፣ እስራኤል እንደዚሁም ደግሞ ለሐዋሳ ከተማ ዋናው ቡድን እኔን ከስር በማሳደግ ለጥሩ ደረጃ እንድበቃ ያደረገኝ እና በወጣት ተጨዋቾች ከፍተኛ እምነት ያለው አሰልጣኝ ውበቱ አባተን አመሰግናለው፤ ውበቱን የማመሰግነው ያለምክንያት አይደለም፤ እሱ ከኢትዮጵያ ብዙዋን አሰልጣኞች ይለያል፤ እኛ ሀገር ያሉ ብዙዎቹ አሰልጣኞች ሲኒየር ተጨዋቾችን በማምጣት የራሳቸውን ስም መጠበቅ ስለሚፈልጉ፤ ከዛ ውጪም በወጣቶች ላይ መስራት የማይፈልጉና እምነቱም የሌላቸው ስለሆኑ ለውበቱ የተለየ ቦታ አለኝ፡፡
የአጥቂው ስፍራም ላይ ጥሩ ችሎታ ያላቸውን ይዘናል ሃዋሳ ከእዚህ ቀደም የሊጉን ዋንጫ ሲያነሳ በአጥቂውም ሆነ በሌላ ስፍራ ላይ ያሉ ተጨዋቾች ነበር ለስኬት ያበቁትና ይሄን ድል የምንደግምበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም፡፡
ሊግ፡- ሃዋሶ ከነማ ውጤት ሲያጣና ሲያገኝ ያለህ ስሜት ምን ይመስላል?
መሳይ፡- ሃዋሳ ከነማ በሚያደርጋቸው ማናቸውም ጨዋዎች ውጤት ስናጣ በኳስ ማሸነፍና መሸነፍን አቻ መውጣትን በሚገባ ስለማውቀው ለራሴ የሚሰማኝ ስሜት ቢኖርም ያ ስሜቴ ነገ ውጤት ማግኘት እና ማሸነፍ እንዳለ ስለምረዳ የወረደ አይደለም፡፡ ውጤት ስናገኝ ደግሞ በጣም ነው ደስ የሚለኝ፡፡

spot_img
ተመሳሳይ ጽሁፎች

አስተያይት ያስፍሩ

እባክዎን አስተያይትዎን ያስፍሩ
እባክዎን ስምዎን እዚህ ያስገቡ

ትኩስ ዜናዎች

%d bloggers like this:
P