test
Google search engine

“በተደራቢ አጥቂነት የምጫወተው በአዲሱ የጨዋታ ሚናዬ በርካታ ግቦችን እንደማስቆጥር ታምኖብኝ ነው”

 

“የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ ለማንሳት ትላልቅ ቡድኖችንም ማሸነፍ ይኖርብናል”ታፈሰ ሰለሞን /ሐዋሳ ከነማ/

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የውድድር ተሳትፎው ላይ ለልደታው ኒያላ እና ለኤሌክትሪክ እንደዚሁም ደግሞ ለሐዋሳ ከነማ እንደ ቡድንም እንደ ግልም  ሲጫወት በሜዳ ላይ በሚያሳየው የጨዋታ ብቃት የበርካታዎቹን የስፖርት አፍቃሪዎች ቀልብ እና ስሜትን ሲገዛ የሚስተዋለው የሐዋሳ ከነማው የአማካይ ስፍራ ተጨዋች ታፈሰ ሰለሞን በሊጉ እያደረጓቸው በሚገኙት እያንዳንዱ ጨዋታዎች ዋንጫውን ለማንሳት ከፈለጉ ትላልቅ የሚባሉትንም ክለቦች ማሸነፍ እንደሚኖርባቸው አስተያየቱን ለሊግ ስፖርት ጋዜጣ ሰጥቷል፡፡

የሐዋሳ ከነማ እግር ክለብ ውስጥ በሊጉ የእስካሁን የጨዋታ ተሳትፎ ከክለቡ አጋር ተጨዋቾች ጋር እንደቡድንም በግልም ጥሩ እንቅስቃሴን ከማሳየት ባሻገር 7 ግቦችንም በማስቆጠር የፕሪምየር ሊጉ የኮከብ ግብ አግቢዎቹንም ፉክክር በመቀላቀል ከሲዳማ ቡናው አዲስ ግደይ እና ከአዳማ ከነማው ዳዋ ሁጤሳ በአንድ ግብ በማነስ ተከታዩን ስፍራ ይዞ የሚገኘው ይሄው ተጨዋች በቀጣይ የሊጉ ጨዋታዎች ለክለቡ ተጨማሪ ግቦችን የሚያስቆጥርበት ሰፊ ዕድል እንዳለውም እየተናገረ ይገኛል፡፡

የሐዋሳ ከነማ ክለብ ውስጥ የአሁን ሰዓት ላይ አዲስ በተሰጠው የጨዋታ ሚና ተደጋጋሚ ጎሎችን በማስቆጠር ጥሩ ብቃቱን እያሳየ የሚገኘው ታፈሰ ሰለሞን ስለ አዲሱ የጨዋታው ሚናና ተደጋጋሚ ጎሎችን እያስቆጠረ ስለሚገኝበት ሁኔታም አስተያየቱን በዚህ መልኩ ሊሰጥ ችሏል፡፡

“የሐዋሳ ከነማ ክለብ ውስጥ ከዚህ ቀደም እጫወት የነበረው በአማካይ ስፍራ ላይ ነበር፤ የክለቡን  የዋና አሰልጣኝነት ሚና አዲሴ ካሳ በዋና አሰልጣኝነት ዘንድሮ ሲረከብ ግን እኔን በተደራቢ አጥቂነት ብጫወት በርካታ ግቦችን እንደማስቆጥር ስላመነብኝ ነው በቦታው ላይ የተሰጠኝን አዲሱን የጨዋታ ሚና በአግባቡ ተጠቅምቤት ተደጋጋሚ ጎሎችን በማስቆጠር ላይ ያለሁት በማለት ሀሳቡን ለዝግጅት ክፍላችን አክሎ ሰጥቷል፡፡

የሐዋሳ ከነማ የአማካይ ስፍራ ተጨዋች የነበረው አሁን ደግሞ በተደራቢ አጥቂነት የሚጫወተው ታፈሰ ሰለሞን ደ/ፖሊስን በሳምንቱ አጋማሽ 3ለ1 በረቱበት ጨዋታ ሁለት የድል ግቦችን ያስቆጠረ ሲሆን  ተጨዋቹን በፕሪምየር ሊጉ የውድድር ተሳትፎአቸው ዙሪያ በወቅታዊ አቋሙና ሌሎችንም ጥያቄዎች ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ /G.BOYS/ አቅርቦለት የሰጠው ምላሽ እንደሚከተለው ይቀርባል፡፡

ሊግ፡- የሐዋሳ ከነማን ወቅታዊ አቋም እንዴት ነው የምትገልፀው?

ታፈሰ፡- የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የዘንድሮው የውድድር ዘመን ተሳትፎአችንን በሜዳችንም ሆነ ከሜዳችን ውጪ ስናደርግ ያለን አጠቃላይ አቋም እና የጨዋታ እንቅስቃሴያችን በአብዛኛው ጎኑ ሲታይ ጥሩ የሚባል እንጂ መጥፎ የሚባል አይደለም፤ በእስካሁኑ ጨዋታዎቻችንም ጥሩ ውጤት ያመጣንባቸው ፍልሚያዎች እንዳሉ ሁሉ ውጤት ያጣንባቸውም ግጥሚያዎች ይገኛሉ፤ ከእነዚህ ውስጥ ውጤት ያጣንባቸው ጨዋታዎች በተጋጣሚያችን ቡድኖች በጨዋታ እንቅስቃሴ የተበለጥንባቸው ስላልሆኑ የቡድናችንን ወቅታዊ አቋም አሁን ላይ የምገልፀው መልካም በሚባል መልኩ ነው፡፡

ሊግ፡- የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የውድድር ተሳትፎአችሁ ላይ የክለባችሁ ጠንካራ እና ደካማ ጎን ምንድነው?

ታፈሰ፡-  የዘንድሮው የውድድር ዘመን ተሳትፎአችን ላይ ክለባችን ያለው ጠንካራ ጎን ከዚህ በፊት ከሜዳችን ውጪ ስንጫወት ከግጥሚያው በፊት ተሸንፎ የመሄድ ነገር ነበር፤ ይሄ ችግር አሁን ላይ  ቡድናችን ጋር ጨርሶ የለም፤ እያንዳንዱን የሊጉን ጨዋታ ለማድረግ ስንጓዝ ጨዋታውን እናሸንፋለን ብለን ለውድድሩ ስለምናመራና ችግሩንም ስለቀረፍን ይሄ ጠንካራው ጎናችን ሆኗል፡፡ ሌላው ጥሩና ጠንካራው ጎናችን ቡድናችን በስኳዱ ያቀፋቸው የወጣት ተጨዋቾች ስብስባችንም ናቸው፤ እንደ እነ እስራኤል /ካቻ/ መሳይ እና ሌሎችም በርካታ ስማቸውን ያልጠቀስኳቸው ተጨዋቾች በጥሩ ብቃት ላይ ስለሚገኙም ለእኛ ያለንን ጥንካሬ ይበልጥ ሊጨምርልንም ችሏል፡፡

የውድድሩ ተሳትፎአችን ላይ እንደክፍተት የምመለከተው ሁኔታ ደግሞ በአንዳንድ ጨዋታዎቻችን ላይ ለምሳሌ ከባህር ዳር ከነማ ጋር ያደረግነውን ጨዋታ ጨምሮ በሌሎች ግጥሚያዎች ላይም ከተቃራኒ ቡድን ግብ ጠባቂዎች ጋር በተደጋጋሚ ጊዜ ፊት ለፊት እየተገናኘን ውጤታማ ሊያደርጉን የሚችሉና አንድአንዴም  ባስቆጠርናቸው ግቦች ላይ ተጨማሪ የሚሆኑ ግብ የማስቆጠር ችግሮችም የሚከሰትብን አጋጣሚዎችም ታይቶብናልና ይሄ እንደ ድክመት ሊቆጠርብን የሚችል እና በጣምም ልናሻሽለው የሚገባን ነው፡፡

ሊግ፡- በሐዋሳ ከነማ አዲስ የጨዋታ ሚና ተሰጥቶህ ተደጋጋሚ ጎሎችን እያስቆጠርክ ይገኛል፤ ጎሎቹን እንዴት ልታስቆጥር ቻልክ? የኮከብ ግብ አግቢነቱ ተፎካካሪም ሆነሃል፤ በዚህ ደረጃ ላይ በመገኘትህስ ምን ስሜት ተሰማህ?

ታፈሰ፡-  በፕሪምየር ሊጉ የሐዋሳ ከነማ የተጨዋችነት ቆይታዬ ላይ ከዚህ ቀደም እጫወትበት ከነበረው የአማካይ ስፍራ ቦታዬ በመቀየር በተደራቢ አጥቂነት እንድጫወት ተደርጎ ተደጋጋሚ ጎሎችን ላስቆጥር የቻልኩት በአሰልጣኜ አዲሴ ካሳ የተሰጠኝ አዲሱ የጨዋታ ሚና በጣም ስለተሰማማኝ ነው፤ በዚህ የተደራቢ አጥቂነት ሚና ውስጥ ሆኜ ስጫወትም ጎል ከማስቆጠሬ በተጨማሪ ራሴ ማስቆጠር የምችላቸውንም ሌሎች ጎሎች ለቡድኔ አጋር ተጨዋቾች ስለማቀብል እንጂ አሁን ካስቆጠርኳቸው የበለጠ ጎሎችም ላገባ እና የኮከብ ግብ አግቢ መሪነት ላይ የተቀመጡትንም ተጨዋቾች አልፌያቸው መሄድም እችል ነበር፤ ዘንድሮ በተሰጠኝ አዲሱ የጨዋታ ሚናዬ በጣም ደስተኛ ነኝ፤ የኮከብ ግብ አግቢ ፉክክር ውስጥ መገኘቴም ተጨማሪ እና  ልዩ የደስታ ስሜትም በውስጤ እየፈጠረብኝም ነው የሚገኘው እና ከዚህ በመነሳት ሌሎች በርካታ ጎሎችንም በቀጣይ ጨዋታዎቻችን ለማስቆጠርም ራሴን በበቂ ሁኔታ አዘጋጃለው፡፡

ሊግ፡- አሰልጣኝ አዲሴ ካሳ አንተን በብዙዎች ዘንድ ከምትታወቅበት የአማካይ ስፍራ እንዴት እና በምን መልኩ  ወደ አዲሱ የተደራቢ አጥቂነት የጨዋታ ሚና ሊያመጣህ ቻለ?

ታፈሰ፡- ሐዋሳ ከነማን በኃላፊነት እየመራ የሚገኘው አሰልጣኝ አዲሴ ካሳ በዘንድሮ የውድድር ዘመን እኔን ቀደም ሲል ከምጫወትበት የአማካይ ስፍራ በማምጣት በተደራቢ አጥቂነት እንድጫወት ያደረገው  የጨዋታ እንቅስቃሴዬን በሚገባ በማጥናት እና በሚገባም በመመልከት ነው፤ አዲሴ ሁሌም አንተ ሀገሪቱ ውስጥ ካሉት የሊጉ ተጨዋቾች የተለየ አይነት ብቃት እና ምርጥ ኳሊቲ ያለህ ተጨዋች ነህ ይለኝ ነበር፤ ከአማካይ ይልቅ በተደራቢ አጥቂነት ብትጫወት ደግሞ ክለቡን በብዙ ግልጋሎት ከመጥቀም አልፈህ ለኮከብ ግብ አግቢነትም መፎካከር ትችላለህም ብሎኝ ነበርና አዲሱን የጨዋታ ሚናዬን በአግባቡ እየተጠቀምኩበት ነው የምገኘው፡፡

ሊግ፡- በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የ12ኛ ሳምንት ጨዋታ ደ/ፖሊስን ማሸነፍ ችላችኋል፤ ጨዋታው ምን መልክ ነበረው? ውጤቱስ ምን ስሜት ፈጠረባችሁ?

ታፈሰ፡- ከደ/ፖሊስ ጋር የነበረን የሳምንቱ አጋማሽ  ፍልሚያ እኛ ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ተሸንፈን በመምጣት የምናደርገውና  እነሱ ደግሞ በወራጅ ቀጠናው ላይ በመገኘት የሚያከናውኑት ስለነበር ጨዋታው ከባድ ይሆናል ብለን ገምተን ነበርና ያንን ነው በሜዳ ላይ የተመለከትነው፤ ይሄን ስላወቅን  ለግጥሚያው በቂ ትኩረት ሰጥተን ነው ወደሜዳ የገባነው፤ ጨዋታው በሁለታችንም በኩል ጥሩ ፉክክር የተደረገበት ነበር፤ እኛ የመሪነቱን ጎል ለማስቆጠር ብንችልም ደቡብ ፖሊሶች በኳስ ቁጥጥሩ ከእኛ የተሻሉ ነበሩ፤ በኋላ ላይ የአቻነቱን ጎል ሲያስቆጥሩ ግን የበለጠ የተነሳሱበት ሁኔታን ተመልክቼያለውና ወዲያው ያደረግነው ባለን እንቅስቃሴያችን ላይ መግባባት እንዳለብን ተማምነን እና ስለ እንቅስቃሴያችንም  መነጋገር ስለቻልን ነው ጨዋታውን ለማሸነፍ የቻልነው፡፡

የደቡብ ፖሊስ ክለብን ለመርታት በመቻላችን እና ወደ አሸናፊነት መንፈሱም በመመለስ ከመሪው ክለብ ኢትዮጵያ ቡና ጋር በነጥብ  ብዙ ሳንርቅ በሁለት ነጥብ ብቻ አንሰን በመቀመጣችንም ያገኘነው ውጤት በጣም ሊያስደስተን ችሏል፡፡

ሊግ፡-  ደቡብ ፖሊስን 3ለ1 በረታችሁበት ጨዋታ ሁለት ጎሎችን ለማስቆጠር ችለሃል፤ በዚህስ ምን ስሜት ነው የተፈጠረብህ?

ታፈሰ፡-  ደቡብ ፖሊስን በተፋለምንበት ጨዋታ ለክለቤ ሁለት ጎሎችን ላስቆጠር እንጂ ስጫወት የነበረው  እያመመኝና እያነከስኩ ነበር፤ የህመሙ ስሜት የተፈጠረብኝም የመጀመሪያዬን ጎል ከማስቆጠሬ በፊት ነበር፤ ጎሉን ካስቆጠርኩ በኋላ ግን ህመሙን ረስቼ በመጫወቴ ሌላ ጎል ላስቆጥር ነው የቻልኩት ጨዋታውንም  ልጨርስ የቻልኩት አንክሼም ነው፤ በዛ መልኩ ተጫውቼ ጎል ማግባቴ በጣም ነው ያስደሰተኝ፤ በጨዋታው ሁለት ጎሎችን ላስቆጥር እንጂ ቡድናችን ከፈጠረው ተደጋጋሚ የጎል ማግባት ሙከራ አንፃር ሌላ ተጨማሪ ግብም ማስቆጠር እችል ነበር፡፡ ማግባት የምችለውን ኳስ ለጓደኞቼ ያቀበልኩበት አጋጣሚም ነበርና ከሁለት ጎል በላይም ጨዋታው ላይ አግብቼ የፕሪምየር ሊጉን የኮከብ ግብ አግቢ መሪዎችን መብለጥም እችል ነበር፡፡

ሊግ፡- የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዋንጫን ለማንሳት ክለባችሁን የት ድረስ ነው የምትጠብቀው?  ከተወዳዳሪ ክለቦች አንፃርስ ፉክክሩን እንዴት አገኘኸው?

ታፈሰ፡- የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የዘንድሮው ፉክክርን ስመለከተው ክለቦች ለእኛ በጣም ይከብዱናል ብዬ ጠብቄ የነበረ ቢሆንም ከውድድር አመቱ መጀመሪያ አንስቶ እስካሁን ሳገኛቸው ግን ብዙም እንደጠበቅኳቸው አላገኘኋቸውም፡፡ ውድድሩ ከባድ ሳይሆን በጣም ቀላል ነው ማለት ይቻላል፤ ክለባችንም ዘንድሮ ለዋንጫው ፉክክር ይጫወታል፤ የሊጉን ዋንጫ ለማንሳት ከፈለግን ደግሞ ከትላልቅ ቡድኖችም ጋር ስንጫወትም የሚኖረንን ጨዋታ መርታት ይኖርብናል፤ ቀጣዩ የመከላከያ ጨዋታችንንም ልናሸንፍ ይገባል፤ ይህን ውጤት ካገኘን ለወደፊቱ ጉዞአችን መልካም አጋጣሚ ይሆንልናልና ያን ለማሳካት ጠንክረን ልንሰራ ይገባል፤ ያለዚያ ሻምፒዮና ለመሆን ውድድሮቹ  አስቸጋሪ ይሆኑብናል፡፡

ሊግ፡- የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የኮከብ ግብ አግቢነት ፉክክሩን አንተን ጨምሮ በርከት ያሉ ተጨዋቾች ተቀራርበውበት ይገኛል? ዳዋ ሆጤሳ፣ አዲስ ግደይ፣ ምንይህሉ ወንድሙ በጥቂቱ ይገኛሉና የእነዚህን ተጨዋቾች ብቃት በጥቂቱ ብትጠቅስ….?

ታፈሰ፡- በጥያቄ ስማቸውን ከላይ የጠቀስካቸው ተጨዋቾች በብሄራዊ ቡድን ደረጃ አብሬያቸው ባልጫወትም በክለብ ደረጃ ሲጫወቱ የማውቃቸው ናቸው፤ በጥሩ ብቃት ላይም የሚገኙ ናቸው፤ የእያንዳንዳቸው ተጨዋቾች ብቃት እና እንቅስቃሴንም ስገልፅ ዳዋ በፊት እንዲህ አይነት ተጨዋች አይመስለኝም ነበር፤ በኋላ ላይ ግን በኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ በተጠራው የብሄራዊ ቡድን ውስጥ ሳየው  በጣም ትልቅ አቅም ያለው ተጨዋች ሆኖ ነው ያገኘሁት፤ ለአገራችን ወደፊት ብዙ ነገሮችን መስራት የሚችል አይነትም ተጨዋች ነው፤ ለእኔ ከሁሉም ተጨዋቾች በችሎታው የተለየ አይነት ተጨዋችም ነው፡፡ አዲስ ግደይንም ብትመለከት እንደ ዳዋ የኮከብ ግብ አግቢነቱን እየመራ ያለ ተጨዋች ሲሆን እሱም ጥሩ ችሉታ አለው፤ ምንይህሉም ጥሩ አጥቂ ነው፤ ዳዋ ግን ለእኔ የእውነቴን ነው የምለው በጣም ምርጡ አጥቂ ነው፡፡

ሊግ፡- በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አሁን ላይ ያለህን ወቅታዊ አቋም እንዴት ትገልፀዋለህ?

ታፈሰ፡- የሊጉ የውድድር ተሳትፎአችን ላይ አሁን ያለኝ አቋም በጣም ጥሩ የሚባል ነው፤ ለዛም ነው ለክለቤ ተደጋጋሚ የድል ጎሎችን ከማስቆጠር ባሻገር ለክለቤም ውጤት ማማር ከፍተኛ ግልጋሎትን እየሰጠሁ እና ራሴንም በኮከብ ግብ አግቢዎች ፉክክር ውስጥ ለመክተት የቻልኩትና በአቋሜ በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡

ሊግ፡-  የሊጉ ምርጥ ተጨዋች መሆንክን ብዙዎች ቢመሰክሩም  መዝናነትን ያበዛል በማለት ደግሞ የሚወቅሱክ አሉ? አሁንስ መዝናናቱ ላይ እንዴት ነህ…

ታፈሰ፡-  የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግን ላለፉት በርካታ ዓመታት ስጫወት አልዝናናም ነበር ብዬ ልዋሽክ አልችልም፤ በጣም ነው ስዝናና የነበረው፤ አሁን ላይ ግን ህይወትን ወደመመስረት ስታመራና ዕድሜህም እየበሰለም ስትመጣ ሁሉንም ነገር በፕሮግራም ተመርተህ ስለምትጓዝ አሁን ላይ መዝናናቱን ቀንሼ ነው የምገኘው፤ የተረጋጋ እና ጥሩ ህይወትንም ነው እየመራው የምገኘው እና በብዙ ነገሮች  በጣም ተለውጫለው፤ ለእዚህ እንድበቃ ያደረጉኝን ፍቅረኛዬን ጨምሮ አሰልጣኝ ውበቱ አባተን እንደዚሁም አሰልጣኝ አዲሴ ካሳና ሌሎችንም ጓደኞቼን ማመስገን እፈልጋለው፡፡

 

spot_img
ተመሳሳይ ጽሁፎች

አስተያይት ያስፍሩ

እባክዎን አስተያይትዎን ያስፍሩ
እባክዎን ስምዎን እዚህ ያስገቡ

ትኩስ ዜናዎች

P