Google search engine

“በአሁን ሰዓት ካለኝ ብቃት አኳያ በብሔራዊ ቡድን ውስጥ የምቀር እንጂ የምቀነስ ተጨዋች በፍፁም አልሆንም” በረከት ደስታ /ፋሲል ከነማ/


የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከኒጀር አቻው ጋር ላለበት ወሳኙ የአፍሪካ ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታው ልምምዱን በእዚህ ሳምንት ጀምሯል፤ ዋልያዎቹ ይህን ልምምድ እየሰሩ ያሉት ካፍ
በሰራው አካዳሚ ሲሆን በአሰልጣኝ ውበቱ አባተ የተመረጠው ይኸው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የተጨዋቾች ስብስብም በኮቪድ የተያዙትን ተጨዋቾች ሳይጨምርም ነው በቀን
ሁለት ጊዜ ለወሳኙ ጨዋታ እየተዘጋጀ የሚገኘው፤ ይህን የብሔራዊ ቡድን ልምምድ አስመልክቶም ለብሔራዊ ቡድናችን ለመጀመሪያ ጊዜ የተመረጠው በረከት ደስታም በጥሩ
መልኩ ለወሳኙ ጨዋታ እየተዘጋጁ እንደሆነና በአካል ብቃቱም በኩል ሁሉም ተጨዋቾች ላይ ብቁነትም እየታየ መሆኑንም ሊገልፅልን ችሏል፡፡
በአሰልጣኝ ውበቱ አባተ አማካኝነት ለዋልያዎቹ ለመጀመሪያ ጊዜ በመጠራቱ ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማው የሚናገረው በረከት ደስታ ከእዚህ በኋላ በሚኖረው ቆይታም እስከ
መጨረሻው ድረስ በመታገልና ጠንክሮም በመስራት በቡድኑ ውስጥ ቀርቶ ሀገሩን ለማገልገልም መዘጋጀቱንም ይናገራል፤ በክለብ ደረጃ አዳማ ከተማን በዝውውር መስኮቱ ለቅቆ
አሁን ለፋሲል ከነማ ፊርማውን ያኖረው በረከት ከሊግ ስፖርት ጋዜጣ ጋር በተለያዩ ጥያቄዎች ዙሪያ ቆይታን አድርጓል፤ ተከታተሉት፡፡
ሊግ፡- ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለመጀመሪያ ጊዜ ተመረጥክ፤ በጣም ተደሰትክ?
በረከት፡- አዎን፤ ከምነግርህ በላይ ነዋ! ለመደሰቴም የመጀመሪያው ምክንያት የሆነኝ የሀገሬን ብሔራዊ ቡድን በዋናው ቡድን ደረጃ ወክሎ መጫወት በጣም የምጓጓለትና
ከልጅነቴም አንስቶም ስመኘው የነበረ ነገር በመሆኑ ነው፤ ከዛም ውጪ በጣም በምወደው አሰልጣኝ ውበቱ አባተም ተመርጬ የእዚህ ቡድን አባል ስለሆንኩም ደስታዬን እጥፍ
ድርብም ነው ሊያደርግልኝ የቻለው፡፡
ሊግ፡- በዋልያዎቹ ስብስብ ውስጥ በእዚህን ወቅት እካተታለው ብለህ ጠብቀህ ነበር?

በረከት፡- ይህ ይሆናል ብዬ በፍፁም አልጠበቅኩም ነበር፤ ከዛ ይልቅ ግን እኔ የማውቀው ነገር ቢኖር የብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ለእኔ ጥሩ ነገር እንዳለው ብቻ ነው፤
ለዛም መሰለኝ ለብሔራዊ ቡድን የመረጠኝ፡፡
ሊግ፡- አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ለአንተ ጥሩ ነገር እንዳለው በምን አወቅክ? በእሱስ ስር ለመጀመሪያ ጊዜ ለመሰልጠን በመቻልህስ ምን ስሜት አደረብህ?
በረከት፡- በእግር ኳስ ተጨዋችነት ዘመኔ እስካሁን በአሰልጣኝ ውበቱ አባተ ስር ሆኜ በክለብ ደረጃ ሰልጥኜ አላውቅም፤ አሁን ላይ ግን በብሔራዊ ቡድን ደረጃ በእሱ ለመጀመሪያ
ጊዜ ተመርጬ እየሰለጠንኩ መሆኑ ከፍተኛ የደስታ ስሜት ነው እየተሰማኝ የሚገኘው፤ ውበቱ አገራችን ውስጥ ከሚገኙት አሰልጣኞች በችሎታው እና በሚሰራው ጥሩ ቡድን በጣም
የማደንቀው ባለሙያ ነው፤ ዘንድሮ እሱ ወደ ብሔራዊ ቡድን ለማምራት ቻለ እንጂ በክለብ ደረጃም ቢሆን በእሱ ስር ሆኜ ለመሰልጠን ከውሳኔ ላይም ደርሼ ነበር፤ ውበቱ የሰበታ
ከተማ አሰልጣኝ ሆኖ ቢቀጥልና ወደሌላ ቡድን ቢያመራ በእዚህ ዓመት የእሱ ተጨዋችም ነበር የምሆነው፤ እሱም ቢሆን በእኔ ችሎታ እምነት ያለው ብቁ ባለሙያ ስለሆነ እኔን
ማሰልጠን እንደሚፈልግ ከሰዎች ነው የሰማሁት፤ ከዛም ለራሴም የነገረኝ ነገር ስላለም በእዚህ ደረጃ እኔና እሱ መፈላለግ በመቻላችንና ለብሔራዊ ቡድንም የመረጠኝ በመሆኑም
እንድደሰት ነው ያደረገኝ፡፡
ሊግ፡- ለኢትዮጵያ u-23 ብሔራዊ ቡድን ግን ከእዚህ ቀደም ተመርጠህም ተጫውተህም ነበር፤ ያን ዕድል በጊዜው ስታገኝስ ለየት ያለ የደስታ ስሜት ነበር የተሰማህ?
በረከት፡- አዎን ማለት ይቻላል፤ ምክንያቱም ከዚህ ቀደም ለእንደዚህ አይነት ብሔራዊ ቡድንም ሆነ ለዋናው ብሔራዊ ቡድን ተጨዋቾች ሲመረጡ አንድ አይነት እና ተመሳሳይ የሆኑ
ልጆች የሚጠሩ በመሆኑ ነው፤ እኔ በነበርኩበት ቡድን ውስጥ ግን በየቦታቸው የተለያየ ችሎታ ያላቸው ተጨዋቾች ስለተጠሩና ከዛም ውጪ ከእነ ከነዓን ማርክነህ፣ አስቻለው
ታመነ እንደዚሁም ደግሞ ከእነ ተመስገን ካስትሮ ከመሳሰሉ ተጨዋቾች ጋርም የመጫወት ዕድሉን ያገኘሁበት ጊዜም በመሆኑ ያኔ ባላሰብኩበት ሁኔታ የተሰማኝ ጥሩ የሆነውና
የሚገርመው አይነት የደስታ ስሜት አሁንም ለብሔራዊ ቡድን ለመጀመሪያ ጊዜ ስመረጥ ዳግም እየተሰማኝ ነው፡፡
ሊግ፡- የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን ከእዚህ ቀደም ተመልካች ሆነህ ነበር ስትከታተል የነበረው፤ አሁን ደግሞ የቡድኑ ተጨዋች ሆነሃል፤ ያኔ ተመልካች በነበርክበት ሰዓት ማንን
ነበር አድንቀህ ያደግከው?
በረከት፡- ሳላህዲን ሰይድን ነዋ! ጊዜው የብሔራዊ ቡድናችን በኢንስትራክተር ሰውነት ቢሻው የሚመራበት ወቅት ነበር፤ የሚገርምም ቡድን ነበር ያለን፤ ያኔ እኔ ኳስን በክለብ
ደረጃ ሳይሆን በሰፈር ደረጃ የምጫወትበትም ጊዜ ነበርና ልክ ሳላዲንን እንደተመለከትኩት በችሎታው በጣም ወደድኩት፤ የኳስ ብቃቱ ስቦኝ እሱን ላደንቀውም ቻልኩኝ፡፡
ሊግ፡- የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከኒጀር አቻው ላለበት የአፍሪካ ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታ ልምምዱን ጀምሯል፤ እያደረጋችሁት ያለው ዝግጅት ምን ይመስላል?
በረከት፡- እኛ የዋልያዎቹ የተጨዋቾች ስብስብ ከእዚህ ሳምንት የመጀመሪያ ቀናቶች አንስቶ እየሰራን ያለነው የዝግጅት ልምምድ በጣም ጥሩ ነው፤ በተለይ ደግሞ ሁሉም
ተጨዋቾች በአካል ብቃቱ /ፊትነስ/ በኩል ብቁ ሆነው የተመለከትኩበት ሁኔታ በጣምም ነው ሊያስገርመኝ እና ሊያስደስተኝም የቻለውና ይሄ መሆን መቻሉ ብዙ ነገሮችንም ነው
ሊያቀልልን የሚችለው፡፡
ሊግ፡- ይሄ ይሆናል ብለህ አልጠበቅክም ነበር?
በረከት፡- አዎን፤ ምክንያቱም ብዙዎቻችን ተጨዋቾች በኮቪድ የተነሳ ከኳሱ ከራቅን ብዙ ወራቶችን አስቆጥረን ስለነበርና አሁን ግን ወደ ልምምድ ስንመለስ በአካል ብቃት በኩል
ሊከብደን ይችላል ብለን ነበር፤ ያም ሆኖ ግን ተጨዋቾቻችን በኮቪድ ጊዜው ሁሉ ልምምዳቸውን እየሰሩ እንዳሉ ያስመለከተን ነገር ስላለ ይሄ በጥሩነቱ የሚነሳ ነገር ነው፡፡
ሊግ፡- የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በርካታ ተጨዋቾችን በስብስቡ ውስጥ ይዟል፤ አንተም የስኳዱ አባል ነህ፤ ከእዚህ በኋላ የመጨረሻዎቹ እጩ ተጨዋች ለመሆንና ሀገርህን
ለማገልገል ራስህን የት ድረስ ነው ያዘጋጀኸው?
በረከት፡- የብሔራዊ ቡድን ተመራጭ ስትሆን ብዙ ጊዜ የምታስበው እንደ ክለብ ተጨዋችነትህ አይደለም፤ ሀገርህንና አጠቃላይ ህዝብህን ወክለህ ነው የምትጫወተውና
የተጣለብህን ከፍተኛ አደራ ለመወጣት ስትል ያለህን አቅም ሁሉ አውጥተህ ትጫወታለህ፤ ከዛ ባሻገር ደግሞ በእዚህ ደረጃ ላይ ተመርጠህ ስትገኝም በአንተ ላይ እምነት ጥሎ
የመረጠህን አሰልጣኝም ማሳጣት ስለሌለብህም ለእሱም ጭምር ስትል ነው የምትጫወተውና በእዚህ በኩል ራሴን በደንብ አዘጋጅቼዋለው፡፡
ሊግ፡- የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የአፍሪካ ዋንጫ የመጨረሻዎቹን ተጨዋቾች ሲያሳውቅ እጩ ተጨዋች ወይንስ ተቀናሽ ተጨዋች የምትሆን ይመስልሃል?
በረከት፡- ካለኝ ወቅታዊ ብቃት አኳያ የብሔራዊ ቡድኑ ውስጥ ከሚቀሩት ተመራጭ ተጨዋቾች መካከል አንዱ እንደምሆን ነው የሚሰማኝ፤ ምን እሱ ብቻ ለብሔራዊ ቡድኑ ፈጣሪ
ከፈቀደም የመጀመሪያ ተሰላፊ ተጨዋች እሆናለው ብዬም አስባለሁ፡፡
ሊግ፡- የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከኒጀር፣ ከማዳጋስካርና ከኮትዲቭዋር ጋር ተደልድሎ የማጣሪያ ጨዋታዎቹን ጀምሯል፤ ለአፍሪካ ዋንጫው የምናልፍ ይመስልሃል?
በረከት፡- አዎን፤ ይሄ ብሔራዊ ቡድን ለእኔ የመጀመሪያዬ ቢሆንም ካለን ጥሩ የተጨዋቾች ስብስብ አንፃር ለአፍሪካ ዋንጫው የማለፍ ከፍተኛ ፍላጎቱ ስላለን ከፈጣሪ እርዳታ ጋር
ይህን እልማችን የምናሳካው ይመስለኛል፡፡
ሊግ፡- በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የዝውውር መስኮት አዳማ ከተማን ለቅቀህ ወደ ፋሲል ከነማ አመራህ፤ ከዛ በፊት ደግሞ የዝውውር መስኮቱ ሳይከፈት ሀድያ ሆሳህናን ተቀላቅለህ
ነበር፤ ስላደረግካቸው የዝውውር ሂደቶች አንድ ነገር ብትለን?
በረከት፡- በመጀመሪያ ደረጃ አንድ ማለት የምፈልገው ነገር ቢኖር አዳማ ከተማን ለቅቄ ወደየትኛውም ቡድን ባላመራ በጣም ነበር ደስ የሚለኝ፤ ያም ሆኖ ግን እንደ አንድ እግር
ኳስ ተጨዋች እኔም በዘመኔ መጠቀም ስላለብኝ እና አሁን ላይ ደግሞ ከምትመራው ህይወት አኳያም ከአንድ ውሳኔ ላይ እንድትደርስ የሚያስገድዱ ብዙ ሁኔታዎች ስላሉ
በመጨረሻ እየተሰማኝ ቢሆንም አቅም እያጣ የመጣሁን፣ ለእዚህ ደረጃ ያደረሰኝን፣ እንደዚሁም ደግሞ አሳዳጊዬ የሆነውን አዳማ ከተማን ለቅቄ ወደ ፋሲል ከነማ ለማምራት
የቻልኩት ከላይ በገለፅኩት መልኩ ነው፤ ወደ ሀድያም ካመራው በኋላ ደግሞ መልሼ ለፋሲል ከነማም ልፈርም የቻልኩት አሁንም ከጥቅማ ጥቅም ጋር በተያያዘ ነውና በፋሲል
የተሻለ ነገር ስላጋጠመኝ እና ክለቡም በጣም ጠንካራ ስለሆነ በመጨረሻ ቡድኑን ምርጫዬ አድርጌዋለሁ፡፡
ሊግ፡- ፋሲል ከነማን ምርጫህ ካደረግህ በኋላ በውሳኔህ ተደሰትክ?
በረከት፡- በጣም፤ ምክንያቱም ፋሲል ከነማ ጥሩ ቡድንና ጥሩ የተጨዋቾችን ስብስብ የያዘ በመሆኑ ችሎታዬን አሳድግበታለው ብዬም ስላሰብኩ ነው፤ ከዛም በተጨማሪም ጥሩ
ደጋፊዎች ያሉትና በአቅም ደረጃም ትልቅ ክለብ ስለሆነ ያ ምርጫዬ እንዲሆን አድርጎታል፡፡
ሊግ፡- ፋሲል ከነማ በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ካፕ ውድድር ላይ ዘንድሮ ይሳተፋል፤ ወደ ክለቡ ከማምራትህ አንፃር ይሄ ለአንተም እንደ ጥሩ አጋጣሚ ይመስለኛል?
በረከት፡- ልክ ነህ፤ በኢንተርናሽናል ጨዋታዎች ላይ መሳተፍ መቻል በጣም ጥሩ ነገር ነው፤ ያለህን ችሎታና አቅምም በሚገባ ታጎለብትበታለህ፤ ስለዚህም ፋሲል ከነማ
በሚያደርገው የእዚህ የኢንተርናሽናል ጨዋታ ተሳትፎ ላይ በክለብ ደረጃ እኔም የመጀመሪያ ግጥሚያዬን የማደርግበት ዕድሉ ስለሚኖረኝ ይሄ ለእኔ መልካም ዜናና ጥሩም አጋጣሚ
ነው፡፡
ሊግ፡- ፋሲል ከነማን በኮንፌዴሬሽን ካፕ የውድድር ተሳትፎው የት ድረስ ለማስጓዝ ተዘጋጅታችኋል?
በረከት፡- የእኛ የመጀመሪያው ዋናው ዓላማ ይሄን ክለብ ከእዚህ ቀደም ቅዱስ ጊዮርጊስ ካስመዘገበው የሩብ ፍፃሜ ውጤት በተሻለ የሚጓዝበትን ደረጃ እንዲያገኝ ማድረግ መቻል
ነው፤ ፈጣሪ ካለ ደግሞ እስከ ዋንጫው ድረስ መጓዝንም ቀጥሎ እናልማለን፡፡
ሊግ፡- የፋሲል ከነማ የተጨዋቾች ስብስብ በጣም የተዋጣለት ነው ማለት ይቻላል?
በረከት፡- በሚገባ! ይኸው ስብስባችንም ብዙ አይነት ኳሊቲ እና ብቃት ያላቸውን ተጨዋቾችንም የያዘ ነው፤ እኔም ወደ ቡድኑ ያመራሁበት አንደኛው ምክንያትም የተጨዋቾቹና
የክለቡም እንቅስቃሴ እኔ ከምፈልገው አይነት አጨዋወትም ጋር አብሮ ይሄዳልም ብዬ ስላሰብኩኝ ያለን ስብስብ ከሁሉም የፕሪምየር ሊግ ክለቦች የመጀመሪያው ደረጃና ረድፍ
ላይም የሚያስቀምጠንም ጭምር ነው፡፡
ሊግ፡- የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ታህሳስ 3 ቀን እንዲጀመር ከውሳኔ ላይ ተደርሷል፤ ፋሲል ከነማን በእዚህ ዓመት እንዴት እንጠብቀው?
በረከት፡- ምንም ጥርጥር አያስፈልገውም፤ ፋሲል ከነማ ለዋንጫ የሚጫወት ቡድን ነው፤ ጥሩ ቡድን ስላለውም ይሄን ድል 100 ፐርሰንት ያሳካል፡፡
ሊግ፡- የእግር ኳሱ መጀመር በጣም ናፍቆሃል?
በረከት፡- አዎን፤ የኮቪድ ወረርሽኝ እስካሁን ከቤታችን አስቀምጦን ነበር፤ አሁን ደግሞ ፈጣሪ ብሎ በጊዜ ወደ ውድድር ለመግባት እየተዘጋጀን ይገኛልና ለዛ አምላካችንን በጣም
ልናመሰግነው ይገባናል፡፡
ሊግ፡- በመጨረሻ… ?
በረከት፡- ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለመጀመሪያ ጊዜ የመመረጥ እድሉን ስላገኘው በጣም ደስተኛ ነኝ፤ ለእዚህ ቡድን ማንም ተመረጠ ማን ቅድሚያ መስጠት ያለብን ሀገራችን
ጥሩ ውጤትን በምታመጣበት ነገር ላይ በማሰብ ለዛም ነው ልንታገል እና አዲሱ አሰልጣኝም ሀገሪቷን ወደ አንድ ከፍ ወዳለ ደረጃም እንዲያሸጋግራት ሁላችንም ከጎኑ መሆን
የሚገባን፡፡

spot_img
ተመሳሳይ ጽሁፎች

አስተያይት ያስፍሩ

እባክዎን አስተያይትዎን ያስፍሩ
እባክዎን ስምዎን እዚህ ያስገቡ

ትኩስ ዜናዎች

%d bloggers like this:
P