በመሸሻ ወልዴ /G.BOYS/
የኢትዮጵያ ጥሎ ማለፍና የአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫን የዓመቱ ውድድር መጀመሪያ ላይ በማንሳቱ ዘንድሮ በሊጉ ስኬታማ ውጤትን ያስመዘግባል፤ የሊጉም አስፈሪ ቡድን ይሆናል በሚል ከፍተኛ ግምት ተሰጥቶት የነበረው የመከላከያ እግር ኳስ ክለብ የውድድር ጅማሬው ጥሩ ሳይሆን በመቅረቱ በበርካታ ጨዋታዎች ላይ ነጥቦችን የጣለ ሲሆን ከዛም አልፎ በርካታ ግቦችንም ሊያስተናግድ መቻሉ ብዙዎቹን አስገርሞ ነበር፤ አሁን ላ ግን ቡድኑ ወደ አሸናፊነት መንፈሱ ተመልሷል፤ የመከለከያ ክለብ ባጣው ውጤት ላይ ተንተርሶም ቡድኑ ውጤት ያጣው ተጨዋቾቹ በአሰልጣኙ ላይ ስላደሙ ነው፣ ተከፋፍለዋል የሚል ነገር ሲደመጥ ነበርና እነዚህን ጥያቄዎች ለቡድኑ ግብ ጠባቂ ይድነቃቸው ኪዳኔ አንስተንለት ተጨዋቹ ምላሹን ሊሰጠን ችሏል፤ ተከታተሉት፡፡
ሊግ፡- የኢትዮጵያ ጥሎ ማለፍ እንደዚሁም የአሸናፊዎች አሸናፊው ሻምፒዮና መከላከያ በፕሪምየር ሊጉ የዘንድሮ ጅማሬው ጥሩ ውጤት እያስመዘገበ አይደለም፤ በርካታ ግቦችም ተቆጥሮበታል፤ ይሄን እንዴት ተመለከትከው?
ይድነቃቸው፡- የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ውድድር ከመጀመሩ በፊት ዘንድሮ ስንዘጋጅ የነበረው ለጥሎ ማለፍ ዋንጫው ነበር፤ ለዚያም ተዘጋጅተን የአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫን ጨምሮ ባለድል ሆነናል፤ ይህን ድል ካሳካን በኋላ ግን ሊጉ ላይ በተደረጉት ውድድሮች ቡድናችን ጥሩ አጀማመር ስላልነበረው በበርካታ ግጥሚያዎች ላይ ነጥብን ጥሎ ውጤትን ለማምጣት አልቻለም፤ ለውጤት ማጣታችን በዋናነት መዘናጋታችን ጎድቶናል፡፡
ብዙ ጊዜ እኛ ሀገር የሲቲ ካፕ ዋንጫን ወይንም ደግሞ ሌላ የሚዘጋጅ ዋንጫን የሚያነሱ ክለቦች በቀጣይ ውድድሮቻቸው ላይ ይዘናጉና ላለመውረድ የሚጫወቱበትን ነገር ተመልክቻለውና በእኛም ላይ የተከሰተው ይሄ ነው፤ ዋንጫን ስትወስድ የሚሰማህ ስሜት አለህ፤ ያንን ጠብቆ ያለመሄድና የመዘናጋት ነገር ነበርና ቡድናችንን ይሄ አጋጥሞት ነጥቦችን ጥለናል፤ ከዛ ውጪ በ3 ጨዋታዎች ላይም በርካታ ግቦች ተቆጥሮብን ተሸንፈናል፡፡ አንዳንዴ እግር ኳስን እንደቀልድ ትጀምረውና እየሰፋ ይሄዳል፤ በዘንድሮ ውድድራችን ላይ አስቀድመን የጥሎ ማለፍ እና የአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫን ስላነሳን ብቻ ተጋጣሚዎቻችን ላይ አንድ ሁለት እናገባለን እንልና ቡድናችን ላይ ክፍተት እየተፈጠረ ይሄዳል፤ አንዱን ስንደፍን ሌላ ክፍተት ይከፈታልና ከሁለቱ ዋንጫዎች በኋላ የመዘናጋት ችግሮቻችን፣ በየጨዋታው ጥብቅ ያለመሆናችን እና የመላላት ችግሮቻችን ውጤትን አሳጥቶናል፡፡
ሊግ፡- የኢትዮጵያ ቡናን ቀደም ሲል ደግሞ ደደቢትን በተከታታይ ከመርታታችሁ አንፃር አሁን ላይ ሙሉ ለሙሉ ወደ አሸናፊነቱ መንፈስ ተመልሳችኋል ማለት ይቻላል?
ይድነቃቸው፡- የሊጉ ጨዋታዎች ላይ ክለባችን ውጤት ባጣ ሰአት የእኛ ዋና አላማ የነበረው ክለቡን ወደ አሸናፊነት መንፈስ መልሶ ጥንካሬውን ይዞ እንዲቀጥል ማድረግ እና መጣር ነበር፤ ያጣነውን ውጤትም ለመቀልበስ መላው የክለቡ ተጨዋቾች እና የኮቺንግ ስታፉ እንደዚሁም ደግሞ የክለቡ አመራሮች በጋራ ተገናኝተን ምንድን ነው ችግራችን በሚለው ዋናው እና አንኳር ነጥብ ላይ ተነጋግረንበታል፤ አመራሮቹም በእኛ በኩል ችግር አለ ብለው ጠየቁን እኛም በእናንተ በኩል ችግር የለም ችግሩ ያለው እኛው ተጨዋቾች ጋር ነው፤ ስለዚህም ይሄን ችግራችንን ራሳችን እናስተካክላለን በማለት ግልፅ የሆነ ውይይትን በማድረጋችን ነው ቡድኑ ወደ ድል የተመለሰው፤ የአሁን ሰአት ላይም ክለባችን በከፍተኛ ለውጥ ላይ ነው የሚገኘው፤ ያለፉትን ሁለት ጨዋታዎች አሸንፏል፤ ይሄን አሸናፊነታችንንም የምናስቀጥለው ይሆናል፡፡
ሊግ፡- የኢትዮጵያ ቡናን ያሸነፋችሁበት ጨዋታ ምን ስሜትን ፈጥሮባችኋል…. ግጥሚያውስ ምን መልክ ነበረው?
ይድነቃቸው፡- የኢትዮጵያ ቡና እና የመከላከያ ጨዋታ እነሱ ባለፉት ሶስት ግጥሚያዎቻቸው ከደረሰባቸው ሽንፈት አንፃር በጫና ውስጥ ሆነው ያደረጉት ሲሆን በእኛ በኩል ደግሞ ወደ አሸናፊነቱ መንፈስ በመምጣት ያከናወነው ስለነበር ጨዋታው ለቡድናችን መልካም አጋጣሚ የሆነልን ነበር፤ እነሱ ሽንፈት ውስጥ ስላሉና በርካታ ደጋፊዎችም ስላሏቸው አንድን ነገር ማሳየት ይፈልጉ ነበርና በጨዋታው ይሄን ጥረት አድርገው ሳይሳካላቸው ቀርቷል፤ ያገኙትንም አጋጣሚ ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል፤ የፍፁም ቅጣት ምት አለማስቆጠር በእግር ኳስ የሚያጋጥም ነው፤ ቡና ብዙ ደጋፊ ያለው ክለብ ከመሆኑ የተነሳ ጫና ውስጥ ያለ ክለብ ስለሆነ እኛን ማሸነፍ አልቻለም፤ ቡና ውስጥ ያለውን ጫና እኔ ተጫውቼ ስላሳለፍኩበት አውቀዋለው፤ ቡና በመጀመሪያው አጋማሽ ጥሩ ነበር፤ ያገኙትን እድል ስላልተጠቀሙ ዋጋ አስከፈላቸውና ተሸነፉ፤ እኛ ደግሞ በሁለተኛው አጋማሽ ቡድናችንን ጥሩ ቅርፅ አስያዝነውና ጥሩ ስለተጫወትን እነሱን አሸነፍናቸው፤ ቡናን ማሸነፋችን በጣም ነው ያስደሰተን ውጤትም ለቀጣዮቹ ጨዋታዎቻችን ከፍተኛ መነቃቃትንም ነው የሚፈጥርልን፡፡
ሊግ፡- የመከላከያ ተጨዋቾች በአሰልጣኝ ሰዩም ከበደ ላይ አድመዋል፤ እየተሸነፉ ያሉትም አወቀው ነው በሚል ስፖርቱ አካባቢ ስሞታ እየቀረበባችሁ ይገኛል፤ ከዛም ውጪ ቡድኑ ሁለት እና ሶስት ቦታ ተከፋፍሏልም ይባላል፤ ቡድናችሁ ውስጥ ክፍፍሉ አለ? በአሰልጣኙ ላይስ አድማው አለ?
ይድነቃቸው፡- /እንደ መሳቅ ካለ በኋላ/ የእግር ኳስ ማለት ውጤት ሲመጣ ፕሬዠሩ ከፍ እንደሚለው ሁሉ ስታጣም ጫናው ከፍ ይላል፤ ያኔም ውጤትን ባጣን ቁጥር ተጨዋቾቹ ተጣሉ፤ ተከፋፍለዋል፤ አሰልጣኙ እንዲህ ሆነ የሚባል ነገር አለ፤ ከውጪም አካባቢ የምሰማው ነገር አለ፤ ወደ ቡድናችን ስመጣ ግን ይሄን ነገር እኛ ጋር አላየሁም፤ የመከላከያ የውጤት ማጣት አስቀድሞ እንዳልኩክ መዘናጋት እንጂ አሰልጣኙ ላይ ስላደምን አይደለም፤ አሰልጣኝ ስዩም ከበደ ላይ ማናችንም አላደምንም፤ ማደምም አንችልም፤ መከላከያ ውስጥ ደግሞ በታሪክ አድማ የሚባል ነገር የለም፡፡ መከፋፈል የሚለውንም በወሬ ደረጃ ሰምቼዋለሁ፤ ቡድናችን ውስጥ ግን በመከፋፈሉ በኩል ያየሁት ነገር የለም፤ አንድ አንድ ሰው ግን ምንአልባት የየዕለት ውሎአችንን በማየት ሁሉም በየፊናው የየራሱ ግሩፕ ኖሮት ሻይ ቡና በሚባባልበት ጊዜ እንዴት ሁሉም በጋራ አብረው አይሆኑም በሚል ተከፋፍለዋል ሊልክ ይችላል፤ አዋዋል ደግሞ እንደ ስሜትክ ነውና ይሄ የተሳሳተ ሀሳብ ነው፤ ተከፋፍለዋል የሚሉት ነገሮችም ብዙ ጊዜ ውጤት ስታጣ የሚመጡ ወሬዎችም ናቸውና ይሄ አሁን በሂደት እየተቀረፈ ነው፡፡ ወሬ የሚቆመው ስታሸንፍ ነው፤ እንዲህ ያሉ ነገሮች ሊመጡ ይችላሉ አንተ ግን ነገሮችን ተረድተህ ወደ ስራህ ከገባክ ሁሉንም ነገሮች ማስቆም ትችላለክና ማደም የሚለውን ነገር ፈፅሞ የማላምንበት ነው፤ ክለባችንም ውስጥ የለም፡፡
ሊግ፡- በመከላከያ የግብ ጠባቂነት ዘመንህ በርካታ ግቦች ተቆጥሮብሃል፤ አሰልጣኝ ስዩም ከበደም ለቡድኑ ውጤት ማጣት የግብ ጠባቂ ችግርን አንዱ ምክንያት ነው ብሎ ጠቅሷል፤ ይሄን ትቀበላለህ?
ይድነቃቸው፡- የእግር ኳስ ጨዋታ የህብረት ስራ ነው፤ ግብ ጠባቂ ደግሞ አለም ላይ በአሁን ሰአት ጥቅሙ 50 ፐርሰንት ነው ይባላልና ይሄ ትክክል ነው፡፡ በእኛ ሀገር ደረጃ ስታየው ግን ያን ለማድረግ ብዙ ይቀረናል፤ ይከብደናል፤ ምክንያቱም አስራአንዱም ተጨዋች እንደ አንድ ካልሆነ በረኛ ብቻውን ምንም ነገር ሊያደርግ አይችልም፡፡ በመከላከያ ቆይታዬ ዘንድሮ እኔ ላይ እንዲህ ያለ ብዙ ግብ ተቆጥሮብኝም አያውቅም በዚህ አመት 3 ጨዋታዎች ላይ የአዳማውን ሁለት ሰው በቀይ ስለወጣብን እና እነሱም ጥሩ ስለነበሩ ብዙ ልልክ አልችልም፤ የቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታ ቀን ግን አጀማመራችን ጥሩ አልነበረም፡፡ በረኛ እኮ ሊሳሳት ይችላል፤ እዚህ ጋር ግን ህብረት ካለክና ቡድኑ ጥሩ ከሆነ የበረኛው ስህተት ተሸፍኖ ይወጣል፤ አለም ላይ በረኛ ተሳስቶ ቡድኑ የጨዋታውን ውጤት ይዞ የሚወጣበት ጊዜ አለ፤ ይሄን የምናየው ነገር ነው፡፡፡ እኛ ሃገር ላይ ግን በረኛ ተሳሳተ ማለት በረኛው አስበላን፤ በበረኛ ተሸነፍን ይባላል፤ ይሄ ችግራችን ሊቀረፍ ይገባል፤ አንድን ቡድን በረኛ ጥሩ ሆኖ ቡድኑን ከሜዳ ይዞት ሲወጣ ደግሞ በረኛው ነው ይዞን የወጣው ተብሎ አይወራምና እኛ ሀገር ብዙ ጊዜ እንደተመለከትኩት በረኞች ላይ ባለው አመለካከት የሚደብር ነገር አለ፡፡ በረኞች ጥሩ ሆነው ቡድናቸው አሸንፎ ሲወጣ እንደሚሞገሱት ሁሉ ቡድኑ ሲሸነፍም የውጪ ሀገር ግብ ጠባቂዎች በበዙበት ሀገራችን ላይ ሞራላቸውን መገንባት እንጂ መውቀስ ተገቢ ነው ብዬ አላምንም፤ የመከላከያ ውጤት ማጣት ላይ አሰልጣኝ ስዩም ከበደ በረኛን አስመልክቶ ከሙያው በመነሳት የሰጠው የራሱ የሆነ ሀሳብ አለ፤ እኔ ግን ሁሌ ውጤታማ ለመሆን ከፈለግን እንደ ቡድን ነው መንቀሳቀስ የሚኖርብን ነው የምለው፤ ክለባችን ሲያሸንፍ በረኛ አሸነፈ አይባልም፤ መከላከያ አሸነፈ ነው የሚባለው፤ ቡናን ፔናሊቲ አድኜ ስናሸንፍ ይድነቃቸው አሸነፈ አልተባለም፤ መከላከያ አሸነፈ ነው የተባለው፤ ስለዚህ ስንሸነፍም መከላከያ ወይንም ደግሞ ይድነቃቸው አልያም በዕለቱ የተሰለፈው ግብ ጠባቂ ተሸነፈ መባል ፈፅሞ የለበትም፡፡ በረኛን ከቨር ካላደረግከው ብዙ ጊዜ አስቸጋሪ ነው፤ በውጪው ዓለም በረኛን ከቨር ስለሚያደርጉ ነው እድገትን የሚያሳዩት፤ እኛ አገር በረኛ ትንሽ ሲሳሳት የማወርድ ነገር አለ፤ አሁን ፕሮፌሽናል በረኞች በዝተዋል፤ የእነሱ መብዛት የእኛዎቹን የመጫወት እድል ስላሳጣቸው አቋማቸውን እያወረደ መጥቷልና፤ የሚሰለፉትን በረኞች ማሞገስ እና ማነቃቃት እንጂ ከዛ በተቃራኒነት ከተጓዝክ ሀገሪቱ ውስጥ ወደፊት በረኛ ማግኘት አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል፤ በሊጉ ውድድር እኔ ብዙ ልምድ ያለኝ ግብ ጠባቂ ነኝ አንድ ነገር ብባል፤ ምንም ሳይመስለኝ ቶሎ ሪከቨር አድርጌ እመጣለው፤ ሌሎቹ ግን ልምዱ የሌላቸው በመደናገጥ በዛው ሊጠፉ እና ሊቀሩ ይችላሉ፤ በሊጉ ላይ በረኛን የሚያስደነግጥ አሰልጣኝ አለ፤ ደጋፊም እንደዛው ስለዚህም የበረኞችን ሁኔታ በተመለከተ ይሄን ችግር የምንቀርፈው ሁላችንም ነንና በጋራ ልንቀርፈው ይገባል፡፡
ሊግ፡- መከላከያ በሊጉ ላጣው ውጤት ተጠያቂው ተጨዋቾቹ ወይንስ አሰልጣኙ?
ይድነቃቸው፡- ድርሻው ሊያንስም ሊበዛም ይችላል እንጂ ሁሉም ተጠያቂነት አለው፤ በእኛ ቡድን አብዛኛው ተጠያቂ የምንሆነው እኛ ተጨዋቾች ነን፤ ተጨዋች ሜዳ ሲገባ እኮ ራሱ እንደ ኮች ነው፡፡ ራሱን አዘጋጅቶ መጫወት ካልቻለ ሊጠየቅ ይገባል፤ አሰልጣኝ ብዙ ነገርን የልምምድ ሜዳ ላይ ነው የሚሰጥህ፤ የራስክን ጨምረህ ነው ሜዳ ላይ የምታሳየው፤ ለአንድ ቡድን ውጤት ማጣት እንደየደረጃው ሁሉም አሰልጣኙን ጨምሮ ተጠያቂ ቢሆንም በዋናነት ግን እኛ ተጨዋቾች ነን ተጠያቂው፤ ስብሰባችን ላይም በዚህ ላይ ተነጋግረንበታል፤ ችግራችንን ለመቅረፍ እየጣርንም ነው፡፡
ሊግ፡- መከላከያን ብዙዎች ስብስብ ብቻ ብለው ይገልፁታል?
ይድነቃቸው፡- /ሳቅ ካለ በኋላ/ አይ ዶኖ! ምን አይነት አስተሳሰብ እንዳለ አላውቅም ክለባችን ስብስብ ብቻ ሳይሆን ምርጥ ቡድንም ነው ያለን፤ ልጆቹን ልምምድ ሜዳ ላይ መጥተህ ብታያቸው ቤስት እና ቤንች ለማውጣት ትቸገራለህ፤ ጥሩ ስብስብ ኖሮህ ውጤት ላይመጣልህ ይችላል፤ እኛ ቡድን ጋር የተቸገርነው ከተለያዩ ቡድኖች የመጡት ልጆች ቶሎ ሊቀናጁ ስላልቻሉ ነው፤ ይሄ ደግሞ ጊዜ ይፈልጋል፤ እኛ ስብስብ ብቻ አይደለም ያለን ስብስቡ ጥሩ ነው፤ ስብስብ ብቻ የተባለውን ነገር ሜዳ ላይ ካየከው ከሆነ ግን ልክ ነው፤ ያለብንን ችግር ቀርፈነው ምርጡን ስብስብ እናስመለክታለን፤ የሁለተኛው ዙር ላይም ከዋንጫው ፉክክር ስላልወጣን አስፈሪውን መከላከያ በማሳየት ውድድሩን በጥሩ ውጤት እናጠናቅቃለን፡፡