የኢትዮጵያ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ሻምፒዮና ፍፃሜውን እንዳገኘ አብዛኛዎቹ የአገራችን እግር ኳስ ተጨዋቾች የእረፍት ጊዜያቸውን ከቤተሰቦቻቸው ጋር በማሳለፍ ላይ ይገኛሉ። ከእነዚህ ተጨዋቾች መካከልም የሚጠቀሱት የአቶ ጉግሳ ልጆች የሆኑት ሶስቱ እግር ኳስ ተጨዋቾች ሽመክት ጉግሳ፣ አንተነህ ጉግሳና ቸርነት ጉግሳ በውድድር ዘመኑ ጥሩ ጊዜን ካሳለፉ በኋላ ወደ ሶዶ ከተማ ወደሚገኙት ወላጅ አባታቸውና ወላጅ እናታቸው ጋር በማምራት የእረፍት ጊዜያቸውን እየኮመኮሙና ስለ ቀጣይ ጊዜ ህይወታቸውም እየተወያዩና እያቀዱም ይገኛሉ።
በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ሻምፒዮና የዘንድሮ ተሳትፎው የሊጉን ዋንጫ ከፍ አድርጎ ማንሳት ከቻለው ከዚህ ቤተሰብ ውስጥ አንዱ የሆነው ሽመክት ጉግሳ ፋሲል ከነማ የዘንድሮን የሊግ ዋንጫ እንዲቀዳጅ ትልቁን አስተዋፅኦ ያበረከተ ሲሆን ይህን ተጨዋች የሊግ ስፖርቱ ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ /G.BOYS/ የተለያዩ ጥያቄዎችን እያነሳለት አውግቶት የሚከተለውን ቆይታ ከተጨዋቹ ጋር አድርገዋል፤ መልካም ንባብ።
ስለ ሻምፒዮናነታቸው ሚስጥር
“ፋሲል ከነማን ለቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ሻምፒዮናነት ሊያበቃው የቻለው ዋንኛው ሚስጥር ለሁሉም ክለቦች እኩል የሆነ ግምትን ሰጥተን ወደ ሜዳ ስለምንገባና ለእያንዳንዱም ጨዋታዎቻችን ከፍተኛ ትኩረትን ሰጥተን በመምጣት ግጥሚያዎቻችንን ልናሸንፍ በመቻላችን ነው”።
ወደ ውድድሩ ማጠናቀቂያ ላይ ግን የትኩረት ማጣት ችግር ይስተዋልባችሁ ነበር
“አዎን፤ ይሄ ችግር የጎላ ባይሆንም በመጠኑም ቢሆን ቡድናችን ላይ ተመልክተንበታል፤ ይሄ የሆነው ደግሞ ሻምፒዮናነታችን ካረጋገጥን በኋላ ነው”።
ሻምፒዮናው ክለባቸው ላይ ስለተመለከተው ክፍተት ጎን
“በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ብዙ ጠንካራ ጎን ስለነበረን የክፍተታችንን ጎን ለይቶ ማውጣት በጣም ይከብዳል። ዘንድሮ እያንዳንዱን ጨዋታዎቻችንን በአብዛኛው ስናደርግ የነበርነው በጥንቃቄ እየተጫወትን ነበር። ለዛም ነው ተጋጣሚዎቻችንንም እናሸንፍ የነበርነው። ከዛም ውጪ ኳሱን በስርዓትም እንደ ቡድን እንጫወት ስለነበርን ስለ ጥንካሬያችን ብቻ ማውራቴ ተገቢ ይመስለኛል”።
ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ በኳስ ታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ስለማንሳቱ
“አዲስ ስያሜ የተሰጠውንና በፊት ደግሞ የፕሪምየር ሊግ ዋንጫ በሚል መጠሪያ የሚታወቀውን ይህን ዋንጫ በእግር ኳስ ተጨዋችነት ታሪኬ በጣም ከወደድኩት ክለቤ ፋሲል ከነማ ጋር ለሁለታችንም የመጀመሪያችን በሆነ መልኩ ድሉን ለመጎናፀፍ ስለቻልን በጣም ነው ደስ ያለኝ። የሊጉን ዋንጫ ከዚ በፊት የእዚሁ ቡድንም ሆነ የሌላ ክለብ ተጨዋች በመሆን ስኬቱን ለማግኘት ብዙ ሙከራ አድርጌ አጥቻለው። በ2013 ግን በህይወትህ አጋጣሚ ምንአልባት አንዴም ላታገኘው የምትችለው የስኬት አጋጣሚ ሊኖር ስለሚችል ለእኔ ቡድናችን ሁሉንም ባሳመነ መልኩ ይህን ዋንጫ ሊያገኝ በመቻሉ ጭምርም ነው ልደሰት የቻልኩት”።
ከፋሲል ከነማ ጋር ዋንጫ ከማንሳትህ ጎን ለጎን በ2013 ዓ/ም ለዋልያዎቹም ተጫውተህ እኮ ወደ አፍሪካ ዋንጫው ካለፉት ተጨዋቾች ውስጥ አንዱም ሆነሃል
“አዎ፤ ይሄ ዓመት ለእኔ ብቻ ሳይሆን በቡድናችን ውስጥ ለሚገኙት ሌሎች ተጨዋቾችም ጭምር ነው ድሉ ያማረላቸው ሊሆን የቻለው። ከኛ ቡድን ውስጥ ወደ አፍሪካ ዋንጫው ካለፈው ቡድን ጋር የሚገኙ ተጨዋቾችም ስለነበሩ የክለቡን ድል ጨምሮ ለአፍሪካ ዋንጫም ያለፍንበት አጋጣሚም ስለተፈጠረልን ከሌሎች ክለብ ተጨዋቾች በተሻለ መልኩም ነው ሁለቱንም ድል በማሳካት ደስታችን እጥፍ ድርብም ሊሆንልን የቻለው”።
ፋሲል ከነማ በየቱ የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ጨዋታ ዘንድሮ ተፈትኗል? በጣም ተደስቶ የወጣበትስ ግጥሚያ…?
“ፈታኝ ብዬ የምገልፀው ከሲዳማ ቡና ጋር ያደረግነውን ነው፤ የተደሰትንበት ጨዋታም ባለቀ ሰዓት ላይ ጎል አስቆጥረን አሸነፍናቸው እንጂ በዋናነት እሱ ነበር። ከዚህ ግጥሚያ ውጪ ደግሞ ከቡና ጋር ብዙ የግብ ዕድሎችን ፈጥረን ያሸነፍንበትና ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋርም በነበረን ጨዋታ የመጨረሻው ደቂቃ ላይ ግብ አስቆጥረን አቻ የተለያየንበት የሚጠቀሱ ናቸው። ከሁለቱ ጨዋታ በተለይ ቡናን ያሸነፍንበት እነሱን በነጥብ ለመራቅ መንደርደሪያ የሆነንና ከዛ ውጪም የመጀመሪያው ዙር ላይ በጎዶሎ ተጨዋች አሸንፈውን ስለነበር ያ ጨዋታም ለእኛ በቁጭት ስሜት ኳሱን እንድንጫወት ጥሩ መነሳሻ ስለሆነልንም በሁለተኛው ዙር ላይ አግኝተን ስንረታቸው በጣም ነበር ልንደሰት የቻልነው”።
ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉን በተለያዩ ሜዳዎች ላይ ስታደርጉ በየቱ ከተማ ላይ ስትጫወቱ ነው ዋንጫውን እንደምታነሱ እርግጠኛ ለመሆን የቻላችሁት
“በባህርዳር ከተማ ላይ ስንጫወት የነበረውን ነው ለእኔ እንደቀዳሚነት የማነሳው። ምክንያቱም በዘንድሮው የውድድር ተሳትፎአችን አዲስ አበባ ላይ ስንጫወት ውጤታችን ሙሉ ካለመሆን ጋር ተያይዞ ትንሽ መንገጫገጭ ነበር። ከቡና ጋር ያደረግነውና የተሸነፍንበት ጨዋታ ግን እኛን ብዙ አስቆጭቶንና አስከፍቶን ስለነበር ከዛ ግጥሚያ ነው ብዙ ነገሮችን ተምረንና ከቁጭት ስሜትም ተነስተን በጥንቃቄ በመጫወት ውጤታችን እየተስተካከለና እያማረ ሊሄድ የቻለው። በተለይ በጅማ ከተማ ላይ ያደረግነውን አራት ያህል ጨዋታን ስናሸንፍ ደግሞ ይበልጥ ወደ ዋንጫው ማለም ጀመርን። ወደ ባህርዳር ስናመራ ደግሞ እያንዳንዱ ጨዋታ በጣም ከባድና ከተጋጣሚዎችህ የምታገኘው ሶስት ነጥብም የስድስት ነጥብ ያህል ይቆጠርልህ ስለነበር የእዚህ ከተማ ላይ ጨዋታዎቻችን ናቸው ለእኛ ለሁሉም ክለቦች እኩል ትኩረትን እንሰጥ ለነበርነው ፋሲሎች የውድድር ዘመኑ ሻምፒዮና እንደምንሆን እርግጠኞች ለመሆን ያስቻለን”።
ፋሲል ከነማ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ያገኘው የሻምፒዮናነት ዋንጫ በአንድ ድል ይቆማል ወይንስ?
“ይሄን ድል ማስቀጠል ካልቻልንማ ጠንካራዎች ነን ማለት አንችልም። ምክንያቱም ቡድኑ ትልቅ አቅም አለውና ከዚህ በኋላ እኛ ፋሲሎች ጋር ወደኋላ መመለስ ፈፅሞ አይታሰብም። የዘንድሮ ድል ታሪክ ሆኖም አልፏል። ለሁለተኛ ለሶስተኛ ጊዜም እያልን ነው ዋንጫን ለማንሳት የምንጫወተው ከዛ ጎን ለጎንም በአፍሪካ የውድድር መድረክም ባለፉት ሁለት ዓመታት ጥሩ ልምድን ስላገኘንና በተለይም ደግሞ ዓምና በጥቃቅን ስህተት ከውድድሩ ስለተሰናበትን ያ ትምህርት ሆኖንም ነው በአሁኑ የውድድር ተሳትፎአችን ለክለባችንም ሆነ ለአገራችን እግር ኳስ ሪከርድ ሊሆን የሚችል ውጤት ለማስመዝገብ ጭምር የምንዘጋጀው”።
በቤትኪንጉ የኢትዮጵያ ቡናው አቡበከር ናስር የኮከብ ተጨዋችነቱን ክብር ሊቀዳጅ ችሏል፤ ከፋክ? ወይንስ?
“በፍፁም፤ ለምንስ ይከፋኛል። ከአቡበከር ውጪ ዘንድሮ እኔና ያሬድ ባየህን የመሰሉ ተጨዋቾችም ጥሩ የውድድር ዓመትን ለማሳለፍ ችለን ነበር። የኮከብ ተጨዋችነት ሽልማትን ለማግኘት ደግሞ ይሄ ነው የሚባል መስፈርት ጭምር የተቀመጠ ስላልሆነ አቡኪ ዘንድሮ ቡናን እዚህ ደረጃ ላይ ለማድረስ ብዙ ጥረትን ከማድረግ ባሻገር በርካታ ግቦችንም አስቆጥሯልና ሽልማቱን ሊወስድ ችሏል። ይሄ በመሆኑም ጥሩ የውድድር ጊዜያቶችን ባሳለፈው በአቡበከር ኮከብነት ፈፅሞ አልተከፋሁም፤ እኔ ሀዝን የነበረው ደስተኛ ያደረገኝ ፋሲል ከነማ ሻምፒዮና ባይሆንም ነበር”።
በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ሻምፒዮና ሲሆኑ የመጀመሪያዎቹን የደስታ መግለጫ ማን እንደላከለት
“እነዚህ መልዕክቶች ከሁለቱ እግር ኳስ ተጨዋቾች ወንድሞቼ አንተነህ እና ቸርነት ጉግሳ የመጡ ነበሩ። መጀመሪያ ላይ ሲደውሉልኝ በደስታ እየጨፈርኩ ስለነበር አላነሳውም ነበር። ከዛም ነው እኔም ተደዋውዬላቸው በእንኳን ደስ ያለህ ስሜቶች መልዕክትን የተለዋወጥነው”።
በፋሲል ከነማ ቆይታህ ደስተኛ ሆነህ ነው የእግር ኳስ ጊዜህን እያሳለፍክ ያለኸው?
“አዎን፤ በጣም። ምክንያቱም ይሄ ቡድን ለእኔ ብዙ ነገሮችን እያደረገልኝም ጭምር በመሆኑ ነው። በዚህ ቡድን ቆይታዬ ብዙ ጓደኞችን ላፈራ ችያለው። ከጥሩ አመራሮችም ጋር ተዋውቄበታለው። ከዛም በተጨማሪ የእግር ኳሱን በነፃነት ሆኜም የተጫወትኩበትና አጥብቄ የምፈልገውንም የሊግ ዋንጫን ስላገኘሁበት እንዴትስ ነው ደስተኛ የማልሆነው። ከዚህ በኋላም ቢሆን ብዙ ደስታዎችን ከዚህ ቡድን ጋር እንደሚኖረኝም አስባለው”።
ስለ ቀጣይ ጊዜ እልሙ
“የፋሲል ከነማ የተጨዋችነት ዘመን ቆይታዬ በዚህ ድል ብቻ እንዲቆም አልፈልግም። ሌሎች ተጨማሪ ስኬቶች ያስፈልጉኛል። ከዛ በተጨማሪም ለአፍሪካ ዋንጫ ካለፈው የዋልያዎቹ ስብስብ ጋርም ሀገሬን የሚያስጠራ አንድ ነገርንም መስራት እፈልጋለውና ራሴን ጠብቄና ጎዶሎ ነገሮቼንም በመሙላት ወደፊት የኳስ ጊዜያቴን በመልካም ሁኔታ ነው ለማጠናቀቅ የምፈልገው”።
ለወላይታ ዲቻ ስለሚጫወቱት ስለ ሁለቱ ወንድሞቹ
“ቸርነትና አንተነህ ጉግሳ ወንድሞቼ ስለሆኑ ሳይሆን ጥሩ የውድድር ጊዜያቶችን ነው በዚህ የውድድር ዓመት ተሳትፎአቸው ላይ ያሳለፉት። ጠንካራና ጎበዝ ተጨዋቾችም ናቸው። በተሻለ ብቃት ላይ ሆነው የውድድር ጊዜያቸውን ስላጠናቀቁም በጣም ነው ደስ ያለኝ። እነዚህ ወንድሞቼ በተለይም ደግሞ እኔን አርአያ አድርገውም ስለመጡ ኳስ መጫወት በራሱ አርአያ መሆንም ነው ብዬ እንዳስብም ነው ያደረገኝ”።
እግር ኳሳችን በዲ ኤስ ቲቪ ሊተላለፍ በመቻሉ
“የዘንድሮ የሊጉ ጨዋታዎች የቀጥታ ስርጭትን አግኝተው ሊተላለፉ በመቻላቸው ጥሩ የውድድር ዘመንን እና ጥሩ እግር ኳስን እንድንመለከት አድርጎናል። ብዙ ሰውም ጋር ዲ ኤስ ቲቪ ስለነበርም በነበረው ኳስም ህዝቡ ተዝናንቷል። እኛ የሀገሪቱ እግር ኳስ ተጨዋቾች በሚተላለፈው የእግር ኳስ ጨዋታ ገንዘብ ማምጣት እንደምንችልም ለማሳየት ችለናል። ከዚህ በፊት በነበረው እግር ኳስ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ተጨዋቾች ከሊጉ ውድድር ገንዘብን ያስወጣሉ እንጂ ገንዘብን አያስገኙም በሚል እስከመተቸትና እስከመሰደብ ደረጃ የደረስንበት አጋጣሚም ነበርና ያ ሁኔታ አሁን ላይ እየቀረና ዶላርም እያስመጣን በመሆኑ የጨዋታዎቹ በዚህ ደረጃ መተላለፋቸው ለአገራችን እግር ኳስ እድገት ብቻ ሳይሆን ለተጨዋቾቻችንም ወደ ውጪ ወጥተው ለመጫወት እንዲችሉም እድልን ስለሚፈጥርላቸው ይሄን ሁኔታ በመልካምነቱ ነው የማነሳው ለአዘጋጅ አካሎችም ምስጋናዬ የላቀ ነው”።
እናጠቃል
“በእግር ኳስ ተጨዋችነቴ እዚህ ደረጃ ላይ ለመገኘት እንድችልና በችሎታዬም ላይ ለውጦችን ከዓመት ዓመት በማሳየት ዛሬ ለበቃሁበት የስኬት ስፍራ ላይ እንድደርስ ያደረጉኝን ቅድሚያ ፈጣሪዬን በመቀጠል ደግሞ ቤተሰቦቼንና ከትንሽ አንስቶ ሰፊ ምክሮችን የሰጡኝ ብዙ ሰዎች እና እንደዚሁም ደግሞ ያሰለጠኑኝ አካላቶችም አሉና ኤነሱን ላመሰግናቸው እፈልጋለውኝ”።