Google search engine

“በአንድ ወቅት ህይወቱ አልፏል ተብሎ ተለቅሶልኛል”“ጉዳት ከዋልያዎቹ ስብስብ ውጪ ስላደረገኝም አስቆጭቶኛል”ሀብታሙ ተከስተ /ፋሲል ከነማ/

 

በስፖርት ቤተሰቡ አካባቢ ከዋናው ስሙ ይልቅ “ጎላ” በሚለው መጠሪያ ስሙ በብዙዎቹ ዘንድ ይታወቃል፤ ይኸው የፋሲል ከነማ የአማካይ ስፍራው ተጨዋች በዘንድሮው የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ሻምፒዮና ውድድር ላይ ለቡድኑ ስኬታማነት ትልቁን አስተዋፅኦ ካደረጉት ተጨዋቾች መካከል ስሙ የሚጠቀስ ሲሆን በሜዳ ላይ ባሳየው ምርጥ ብቃትም ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተመርጦም መልካምና ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴን ሲያሳይም ተመልክተነዋል፤ ያም ሆኖ ግን ሀብታሙ ተከስተ በዝግጅት ወቅት ላይ የደረሰበት ጉዳት ከዋልያዎቹ ስብስብ ውጪ እንዲሆን ያደረገው ሲሆን ይህን አስመልክቶም “ጉዳት ከዋልያዎቹ ስብስብ ውጪ ስላደረገኝና በተለይም ደግሞ በዓለም ዋንጫው የማጣሪያ ጨዋታ ላይ ልሳተፍበት ከፈለግኩት የጋናው ጨዋታ ውጪ ስለሆንኩኝ ቆጭቶኛል” ሲልም ከሊግ ስፖርት ጋዜጣ አዘጋጅ ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ /G.BOYS/ ጋር ባደረገው ቆይታ ገልጿል፡፡

ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን /ዋልያዎቹ/ እና ለፋሲል ከነማ ሲጫወት የምናውቀው ሀብታሙ ተከስተ /ጎላ/ አሁን ላይ ከጉዳቱ በማገገም በአፍሪካ ክለቦች ቻምፒዮንስ ሊግ ላይ የሚጫወተውን የክለቡን የፋሲል ከነማን ዝግጅት ተቀላቅሎ ልምምዱን እየሰራ ሲሆን ከዚህ ተጨዋች ጋር በተለያዩ ጥያቄዎች ዙሪያ ቆይታ አድርገን ተከታዩን ምላሽ ሰጥቶናል፤ ተከታተሉት፡፡

ሊግ፡- አስቀድሞ በደረሰብህ ጉዳት ከዋልያዎቹ ስብስብ ውጪ መሆንህ ይታወሳል፤ በዛን ወቅት የተሰማህ ስሜት ምን ይመስል ነበር?

ሀብታሙ፡- ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተመርጬና ተጫውቼም የኳስ ችሎታዬን በከፍተኛ ደረጃና ሁኔታ ላይ ለማሳደግ ጥረትን በማደርግበት ሰዓት የልምምድ ወቅት ላይ የደረሰብኝ ጉዳት ከዋልያዎቹ ስብስብ ውጪ ስላደረገኝና በተለይም ደግሞ አጥብቄ ልጫወትበት ከፈለግኩበት ከጋና ብሔራዊ ቡድን ጋር ላለብን የዓለም ዋንጫው የማጣሪያ ጨዋታ ውጪ ልሆን ስለቻልኩ በጣም ነው የቆጨኝ፤ በቃላት መግለፅ በማልችለው መልኩም ከፍተኛ የሀዘን ስሜትም ነው የተሰማኝ፡፡

ሊግ፡- እንደ አንድ ተጨዋች ብዙ ተስፋን ከሰነቅክበት የብሔራዊ ቡድን ተጨዋችነትህ ውጪ ከሆንክ በኋላ ከማዘን ውጪ ሌላ ያሰብከውስ ነገር ነበር….?

ሀብታሙ፡-  አዎን፤ ጉዳት በማንኛውም ጊዜና ሰዓት ላይ ሊያጋጥም እንደሚችልና ያንን ደግሞ አምነህ መቀበል እንዳለብህ ነው፤ እኔ ይህንን ነው ወዲያው ያሰብኩት፤ ፈጣሪን ይመስገነውና አሁን ላይ ወደ መልካም ጤንነቴ ልመለስ ችያለው፡፡

ሊግ፡- አሁን ላይ ግን ከጉዳትህ በማገገም ከክለብህ ፋሲል ከነማ ጋር የፕሪ-ሲዝን ልምምድህን ጀምረሃል፤ በዚህ ዙሪያስ ምን የምትለን ነገር አለ?

ሀብታሙ፡- አዎን፤ በጥሩ ጤንነት ላይ የምገኝ በመሆኑ ከክለቤ ፋሲል ከነማ ጋር ዝግጅቴን ጀምሬያለው፤ የሁለተኛ ቀን ልምምዴንም በጥሩ መልኩ ሰርቻለው፤ ለእዚህ ላበቃኝ ፈጣሪዬም በድጋሚ ከፍ ያለ ምስጋናዬንም አቀርባለው፡፡

ሊግ፡- ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለመጀመሪያ ጊዜ ስትመረጥና ስትጫወት የተሰማህ ስሜት ምን ይመስል ነበር?

ሀብታሙ፡- ለፋሲል ከነማ እየተጫወትኩ በነበረበት ሰዓት ለሀገሬ ብሔራዊ ቡድን ተመርጬ መጫወትን በጣም አልም ነበር፤ ያ እልሜ ተሳክቶም በሀገሪቱ ውስጥ ከሚገኙት ከዛ ሁሉ ተጨዋቾች ውስጥ ተመርጬ የእዚሁ ቡድን አባል ስሆንና ብሎም ደግሞ ታላላቅ ከሚባሉት የአፍሪካ ሀገራት ጋር ማለትም ከእነ ዛምቢያና ኮትዲቯርን ከመሳሰሉት ሀገሮች   ተቃራኒ ሆኜ ጨዋታዬን ሳደርግ የተሰማኝ ስሜት በጣም ደስ የሚል ነበር፤ ምክንያቱም ዋልያዎቹን ከዚህ ቀደም እከታተል የነበረው በአካል ጨዋታቸውን በማየትና በቴሌቪዥን መስኮት በመከታተል ነበር፤ አሁን ያ ጊዜ አልፎ እኔም በጣምለምወዳት ሀገሬ ልጫወት በቅቻለውና የደስታ ስሜቱን በቃላት ብቻ የምትገልፀውም አይደለም፡፡

ሊግ፡- ለካሜሩን የአፍሪካ ዋንጫ ዋልያዎቹ ከአስተናጋጇ ሀገር ካሜሩን፣ ቡርኪናፋሶና ኬፕቨርዴ ጋር መደልደሏ ይታወሳል፤ በእዛ የዕጣ ድልድል ዙሪያ የአንተ ስሜት ምን ይመስላል?

ሀብታሙ፡- የአፍሪካ ዋንጫውየዕጣ ድልድል ሲወጣ እኛን ስለደረሱን ቡድኖች ከወቅታዊ አቋም ተነስቼ እኔ ብዙም የማውቀው ነገር የለኝም፤ እኛ ወደዚህ ውድድር የገባነው ጥሩ ውጤት ለማስመዝገብና የከዚህ ቀደሙን የሀገራችንን ሪከርድ ለማሻሻል ነው፤ በዕጣ ማውጣቱ ስነ-ስርዓትም እኛን የደረሱንን ቡድኖች አክብደንም፤ አቅልለንም አናይም፤ የእኔ ስሜት አሰልጣኙ ከሚያሰራው ስራ ተነስቼ ጥሩ ውጤት እንደምናስመዘግብ ነው፡፡

ሊግ፡- ፋሲል ከነማ በአፍሪካ ክለቦች ላለበት የቻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታ ዝግጅቱን ጀምሯል፤ የእስካሁን ልምምዱ ምን ይመስላል? ምን ውጤትስ ያስመዘግባል?

ሀብታሙ፡- እኔ የእዚህ ቡድናችን ዝግጅትን ከተቀላቀልኩ ምንም እንኳን ገና ሁለት ቀኔ ቢሆንም ክለቡ ላለበት የኢንተርናሽናል ጨዋታ ተሳትፎው አስቀድሞ መዘጋጀት ስለጀመረ እስካሁን ጥሩ ልምምድን ነው እየሰራን የሚገኘው፤ ፋሲል ከነማ ወደዚህ ውድድር የሚያመራው ከከዚህ ቀደም የሁለት ጊዜ ኢንተርናሽናል  ተሳትፎው ብዙ ነገሮችን ተምሮ ነው፤ አሁን ልምድን አግኝቷል፤ ቡድኑን ሊያጠናክሩ የሚችሉ ልጆችንም በስኳዱ አካቷልና መልካም የሚባል ውጤትን የምናመጣ ይመስለኛል፡፡

ሊግ፡- ፋሲል ከነማ በእዚህ የውድድር ተሳትፎው እንደ ስጋት የሚመለከተውስ ነገር አለ?

ሀብታሙ፡-ብዙ የጎላ ባይሆንም ሊኖር ይችላል፤ አሁን ላይ ዝግጅታችንን እየሰራን የምንገኘው ከክለባችን ለብሔራዊ ቡድን የተመረጡትን ተጨዋቾች ሳንይዝ ነው፤ እነሱ ቢኖሩልንና አብረናቸው ልምምድን ብንሰራ ኖሮ የበለጠ ለመቀናጀት ጥሩ ይሆንልን ነበር፤ አሁን ግን እነዚህን ተጨዋቾች የምናገኛቸው ከብሔራዊ ቡድን ጨዋታ በኋላና ለሁለት ቀን ለሚሆን የልምምድ ጊዜም በመሆኑ ይሄ ሁኔታ ነው ምንአልባት መጠነኛ ችግርን ሊፈጥርብን የሚችለው፡፡

ሊግ፡- በአንድ ወቅት አንተን ለህልፈት ሊያበቃ ህመም አጋጥሞህ እንደነበር ሰማን፤ እውነት ነው? እስኪ በዛ ጉዳይ ዙሪያ አውራን?

ሀብታሙ፡- ይሄ ሁኔታ የተፈጠረው በ2011 ላይ ነበር፤ በጣም ያመኝና ወደ ግል ሆስፒታል ሄድኩ፤ እዛም እንደደረስኩ ታይፎይድና ወባም ተብዬ መድሃኒቶችን እንድወስድ ተደረግኩ፤ ወደቤት ስመጣም ህመሙ ጠንከር ስላለብኝ አልሻልም አለኝ፤ በኋላ ላይም በተኛሁበት ሆስፒታል ውስጥ ግሉኮስ ተደርጎልኝም እየታከምኩ ነበርና ራሴን ፈፅሞ አላውቀውምም ነበር፤ ይህ ሁኔታም ነው እንግዲህ በቤተሰቦቼ ዘንድም ህይወቴ ያለፈ መስሎአቸውም ሊለቀስልኝ የቻለውም፤ ያኔ ከደረሰብኝ ህመም እንደነቃው ቤተሰቦቼ እያለቀሱ ነበር፤ ቀና አልኩና ምን ሆናችሁ ነው የምታለቅሱት ስላቸው ደርሶብኝ ከነበረው ጠንከር ያለ ህመም አኳያ የሞትክ መስሎን ነበር ሲሉኝ ነው ሁሉንም ነገር ላውቅና በጌታዬም እናት ድንግል ማሪያምም ምክንያት ልድን የቻልኩትና እሷን ከፍ አድርጌ ማመስገን እፈልጋለውኝ፡፡

ሊግ፡- እናጠቃል..?

ሀብታሙ፡- እስካሁን በኳስ ለመጣሁበት መንገድ አሁንም ስሟን ከፍ አድርጌ መጥራት እፈልጋለውና ቅድሚያ እመቤቴ ማሪያምን ማመስገን እፈልጋለው፤ ከዛ በመቀጠል ያሰለጠኑኝን አሰልጣኞችና ቤተሰቦቼን እንደዚሁም ጓደኞቼንና የፋሲል ከነማ ደጋፊዎችም ይመስገኑልኝ፡፡

spot_img
ተመሳሳይ ጽሁፎች

አስተያይት ያስፍሩ

እባክዎን አስተያይትዎን ያስፍሩ
እባክዎን ስምዎን እዚህ ያስገቡ

ትኩስ ዜናዎች

%d bloggers like this:
P