Google search engine

“በአንድ ጨዋታ ምክንያት አጠቃላይ ፕሪምየር ሊጉ መቋረጡ እኛን ፋሲሎች አስቆጥቷል” አምሳሉ ጥላሁን /ሳኛ/ /ፋሲል ከነማ/


መሸሻ ወልዴ /G.BOYS


የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሊጠናቀቅ የሶስት ሳምንታት ጨዋታዎች እየቀሩትና ውድድሩንም ፋሲል ከነማ እየመራ ባለበት
የአሁን ሰዓት ላይ ሊጉ ላልተወሰነ ጊዜ የመቋረጥ አደጋ ያጋጠመው ሲሆን ይህን አስመልክቶ ከተለያዩ ክለብ ተጨዋቾች
ጋር አጠር ያለ ቃለ-ምልልስን አድርገን ምላሻቸውን እንደሰጡን ሁሉ ሊጉን በመምራት ላይ ከሚገኘው የፋሲል ከነማ
እግር ኳስ ቡድን ተጨዋቾች መካከል ደግሞ በጠንካራ ተከላካይነቱ ቡድኑን በከፍተኛ ሁኔታ እየጠቀሙ ከሚገኙት
ተጨዋቾች ውስጥ አንዱ የሆነውን አምሳሉ ጥላሁንን ሊጉን እየመሩ ባለበት የአሁን ሰዓት ውድድሩ ስለመቋረጡና
ቡድናቸው በእዚህ ዓመት በሊጉ ተሳትፎው ስላደረገው ስኬታማ ጉዞው እንደዚሁም ደግሞ በራሱ አቋም ዙሪያ የተለያዩ

ጥያቄዎችን ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ /G.BOYS/ ጥያቄዎችን አቅርቦለት የሚከተሉትን ምላሾቹን ሰጥቷል፡፡


ሊግ፡- የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግን በመምራት ላይ እያላችሁ ውድድሩ ላልተወሰነ ጊዜ ተቋርጧል፤ ይህን ስትሰሙ ምን
አላችሁ?
አምሳሉ፡- የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የዘንድሮ ውድድር በመርሃ ግብሩ መሰረት እስካሁን ተካሂዶ በዚህ ሰዓት ላይ ጥቂት
ጨዋታዎች ሲቀሩ ላልተወሰነ ጊዜ ይቋረጣል ብለን ፈፅሞ አልገመትንም፤ መረጃውን ስንሰማም እኛ ብቻ ሳንሆን
መላው የጎንደር ህዝብም በጣም ነው ያዘነው፤ በሊጉ ጥሩ በነበርንበት እና ውድድሩንም እየመራን ባለንበት ሰዓት ይህ
ጨዋታ መቋረጡም ቡድናችንን የሚጎዳው ነገር አለና በዚህ ሁኔታ ውስጥ በእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ ላይ ከፍተኛ ቅሬታም
ነው ያለን፡፡
ሊግ፡- የፕሪምየር ሊጉ ላልተወሰነ ጊዜ ይቋረጥ የሚለው የእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ ውሳኔ በፋሲል ከነማ ክለብም ሆነ
በእናንተ ተጨዋቾች ዘንድ ከፍተኛ ተቋውሞን እያስነሳ መሆኑን ሰምተናል፤ በዛ ላይ ቡድናችሁ ሊጎዳ እንደሚችልም
እየገለፃችሁ ይገኛልና፤ በዚህ ዙሪያስ ምን የምትለው ነገር አለ?
አምሳሉ፡- የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ላልተወሰነ ጊዜ ይቋረጥ የሚለው የእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ ውሳኔው የመጣው
በኢትዮጵያ ቡናና በመቐለ 70 እንደርታ ክለቦች መካከል ሊደረግ በነበረው ጨዋታ ምክንያት ነው፤ ይሄን ጨዋታም
በመተዳደሪያ ደንቡ መሰረት የእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ ትክክለኛና ፍትሃዊ በሆነ መልኩ ከአንድም ሁለት ጊዜ ማካሄድ
ሲገባው ሳያከናውን ቀርቷል፤ ታዲያ የእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ የዘንድሮውን ውድድር እስካሁን እዚህ ደረጃ ላይ አድርሶት አሁን
ላይ የሁለቱን ክለቦች ጨዋታ ማካሄድ ሲያቅተው ጊዜ አጠቃላይ የሊጉን ውድድር ላልተወሰነ ጊዜ ብሎ ማቆሙ ምን
የሚሉት ውሳኔ ነው? እንደ እኔ አመለካከት የእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ ውስጥ ቆራጥ አመራር ቢኖር የኢትዮጵያ ቡናና
የመቐለ 70 እንደርታ ጨዋታ በፍፁም አይቋረጥም ነበር፤ በሁለቱ ጨዋታ የተነሳ የሊጉ ውድድር ላልተወሰነ ጊዜ
መቋረጡ ውድድሩን ለምንመራው እንደእኛ ላለነው ክለብ ከሞራልም ከአቅም ማጣትም ጋር የሚጎዳን ነገር አለ፤
ለምሳሌ የሊጉ ውድድር ሲቋረጥ ቡድናችን በሜዳ ላይ ውድድሩ ዳግም ከቆይታዎች በኋላ ቢቀጥል እንኳን አቅምን
ያጣል፣ የአሸናፊነት ተነሳሽነቱም ይቀንሳል፣ ከዛ ውጪ ደግሞ እንደ አዲስ ሆነን ስንመጣም ከበጀት የተነሳም በክለቡ
ውስጥ የሚፈጥረው ነገር ስለሚኖር በቡድናችን ላይ ከፍተኛ ተፅህኖንም ይፈጥርብናልና በአንድ ጨዋታ ምክንያት የሊጉ
ውድድር መታመስ ስለሌለበት የሊጉ ውድድር በፍፁም መቋረጥ የለበትም፡፡
ሊግ፡- የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የፕሪምየር ሊግ ውድድሩን አሁን ላይ ላልተወሰነ ጊዜ እንዲቋረጥ ወስኗል፤
እንደዚህ አይነት ውሳኔዎች በእግር ኳሱ ላይ ዳግም እንዳይከሰቱና ውድድሮች ደግሞ በሰላም ተጀምረው በሰላም
ሊቀጥሉ የሚችሉበት የመፍትሄ ሀሳብ ካለህ…..?
አምሳሉ፡- በዚህ ዙሪያ የራሴን ሀሳብ ለማስቀመጥ አሁንም ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አልወጣም፤ በቅድሚያ
ውድድሩን በጥሩ ሁኔታ ለመምራት ፍትሃዊ መንገድን የተከተለ ቆራጥ የሆነ አመራር ያስፈልጋል፤ በመቀጠል ከዳኝነት

ምድባ አንስቶ እግር ኳስ ፌዴሬሽናችን ውስጥ ከቀድሞ ጊዜ አንስቶ ያሉት ነገሮች መፅዳት አለባቸው፤ ሁሉም ለክለብ
ሳይሆን ለሀገር መስራት ይኖርበታል፤ በእግር ኳስ ጥሩ ብሔራዊ ቡድን የሚኖረን ጥሩ ጥሩ ክለቦች ሲኖሩ ነውና
የክለቦቹን ውድድር በጥሩ መልኩ መምራት ያስፈልጋል፤ ሁላችንም የእግር ኳሱ ባለድርሻ አካላት በእግር ኳሱ የተሻለ
ደረጃ ላይ እንደደረሱት ሀገራት ማለትም እንደ ትላልቆቹ በማሰብ የየድርሻችንን ከቆፍጠን ያለ የፌዴሬሽን ፍትሃዊ የሆነ
አመራር ሃላፊነታችንን ልንወጣ ይገባናልና ይሄን ነው ለማለት የምፈልገው፡፡
ሊግ፡- ፋሲል ከነማ የሊጉ መሪ ሆኖ ነው ውድድሩ የተቋረጠው፤ ለእናንተ ዓመቱ እንዴት እያለፈ ነበር?
አምሳሉ፡- የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የዘንድሮ ውድድር አሁን ላይ ባይጠናቀቅም ሊጉ ቢቋረጥም እስካሁን ስናሳልፍ
የነበረው ጊዜ በጣም ደስ የሚል እና ለሁላችንም ጥሩ የሆነልንም ነበር፤ ፋሲል ከነማ በሊጉ ተሳትፎው በሜዳ ላይ
ካለው ጥንካሬ በተጨማሪ አሁን ላይ በደመወዝ ክፍያም ሆነ ተጨዋቾችን በጥሩ እንክብካቤም በመያዝ ከብዙዎቹ
ክለቦች የተሻለ በሚባል ደረጃም ላይ ይገኛልና ይሄ ዘንድሮ ላሳካነው ውጤት ከፍተኛ አስተዋፅኦ አበርክቶልናል፤ ፋሲል
ከደመወዝ ክፍያ እና ከሌሎች እንክብካቤዎች ጋር በተያያዘ ዘንድሮ ለቡድኑ እያደረገ ያለው ድጋፍ ይበል የሚያሰኝ ነው፤
ከዚህ ቀደም በዚህ ደረጃ ላይ ይገኝ የነበረው ቡድን ቅዱስ ጊዮርጊስ ነበር አሁን ላይ ግን እኛም አለንና ይሄ ድጋፍ ቡድናችን
ውስጥ መኖሩ ጠቅሞናል፡፡


ሊግ፡- የፕሪምየር ሊግ የውድድር ተሳትፎአችሁ ላይ ፋሲል ከነማን ስኬታማና ውጤታማ ያደረጉት ዋና ዋና እውነታዎች
የትኞቹ ናቸው?
አምሳሉ፡- የፋሲል ከነማ የዘንድሮ የስኬታማነት ምንጭ ወደ ክለቡ ማንም ተጨዋች ቢመጣ ማንም ተጨዋች ቢሄድ
ክለባችንን ይሄ ነገር ብዙም ሳያስጨንቀው ከአሰልጣኝ አንስቶ እስከ ተጨዋቾች ድረስ ሌላ ተባብሮና ተጋግዞ የሚጓዝ
ቡድንን ዳግም መገንባት ይችላልና ይሄ ቡድኑን በሚገባ እየጠቀመው ይገኛል፡፡
የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የዘንድሮ የውድድር ዘመን ጉዞአችንን በሚመለከት ክለቡን በውጤታማነት ማማ ላይ
ልናስቀምጠው የቻልንበት ዋንኛው ምክንያታችን ክለባችን የያዘው የተጨዋቾች ስብስብ ከአጥቂው አንስቶ
እስከተከላካዩ ድረስ ጥሩ ስለሆነና እከሌ ቢጎዳ ሌላ ተጨዋች የለኝም ብለህ የምትሰጋበት ክለብ ስላልሆነ እንደዚሁም
ያለው ህብረትና መከባበርም ከፍ ያለ መሆኑ ነው፤ ሌላው ውበቱ አባተ የተባለ ጥሩ የእግር ኳስ ስልጠናን የሚሰጠን
ምርጥ አሰልጣኝ አለን፤ ተጨዋቾቹ ደግሞ የአሰልጣኙን የታክቲክ ስልጠና በፍጥነት በመተግበር የሚታወቁ እንደሆኑ
በሜዳ ላይ ካሳዩት ነገር በመነሳት መመልከት ተችሏል፤ አሰልጣኛችንንም ከሚያስተምረን ትምህርቶች አኳያም እኛ
እንደ ት/ቤትም ነው የምንቆጥረውና ይሄን በጥሞና መከታተላችን ጠቅሞናል፤ የፋሲል ከነማ ክለብ ውስጥ ኳስን ብቻ
አይደለም የምትማረው፤ ከኳስ ውጪ ስላለህ ህይወትህ /ላይፍም/ ትማራለህ፤ ሁለቱን በማጣመር በክፍል ውስጥ
በሳምንት ሶስት እና አራት ቀናት በአሰልጣኛችን ውበቱ አባተ የሚሰጠን ትምህርትም ለቡድናችንን ተጨዋቾች በጣም
የጠቀመም ሁኔታ አለና የእነዚህ ድምር ውጤቶች ፋሲልን ስኬታማ አድርጎታል፡፡
ሊግ፡- ፋሲል ከነማ የሊጉ መሪ እንደሆነ ይታወቃል፤ በውድድሩ ተሳትፎአችሁ ከዚ በላይ እንዳትጓዙ ያጣችሁት ነገር
የለም….?
አምሳሉ፡- አለ እንጂ! ይሄ ግን የመጀመሪያው ዙር የሊጉ ተሳትፎአችን ላይ እንጂ አሁን አይደለም፤ አሁን ግን ቡድናችን
በጥሩ ብቃቱና ጥንካሬው ላይ ስለሚገኝ ያጣው ነገር ምንም የለም፡፡
ሊግ፡- የፕሪምየር ሊግ የመጀመሪያው ዙር ላይ ምን ነበር ያጣችሁት?
አምሳሉ፡- ፋሲል ከነማ በውድድሩ ተሳትፎው በጊዜው አጥቶት የነበረው ነገር የቡድናችን ተጨዋቾች በሚገባ
ስላልተዋወቁ ከመዋህድ ችግር ጋር በተያያዘ በተደጋጋሚ ጨዋታዎች ላይ ነጥቦችን ይጥል ስለነበር ነው ያኔ ተዋህደን
ቢሆን ኖሮ የሁለተኛው ዙር ላይ ካለን ብቃት አንፃር አሁን ላይ ተከታዮቻችንን በ15 እና በ16 ነጥብ በልጠን የሊጉን
ሻምፒዮናነታችንን ከወዲሁ እናረጋግጥ ነበር፡፡
ሊግ፡- ፋሲል ከነማ ባህርዳር ከተማን በሰፊ የግብ ልዩነት ማሸነፉ አሁን ላይ በነጥብም በግብ ክፍያ ልዩነትም መሪነቱን
ለብቻው እንዲጨብጥ አድርጎታል፤ የጨዋታውን ሂደት እና ውጤቱን በሚመለከት ምን የምትለው ነገር አለ?
አምሳሉ፡- ፋሲል ከነማ ባህር ዳር ከተማን በሰፊ የጎል ልዩነት ድል በማድረግ ያሸነፈበት ጨዋታ ለአንድአንዶች
ሊዋጥላቸው ባይችልም ይህን ጨዋታ እኛ የረታነው ተጋጣሚያችን የአቅማቸውን አውጥተው በመጫወት እኛን
ለመፎካከር ጥረት ባደረጉበት መልኩ በመሆኑ እና ከዛ አልፎ ደግሞ በሁለተኛው ዙር ላይ እያደረግን ካለናቸው የሜዳችን
ውጪ ጨዋታዎች መካከል ደግሞ እንደ እነ መከላከያና ደደቢትን የመሳሰሉት ክለቦችን በሰፊ የጎል ልዩነት እያሸነፍናቸው
ስለሆነም ከቡድናችን ጥንካሬ አንፃር ባህርዳርን ማሸነፋችንም አይገርምም፤ ባህርዳርን ያሸነፍነው ከእነሱ በተሻለ
መልኩ ለመቅረብ ስለቻልን ነው፤ ያ ግጥሚያም መሪነታችንንም ያጠናከረልን ስለሆነ በድሉ በጣም ተደስተናል፡፡
ሊግ፡- ፋሲል ከነማ የሊጉ ውድድር ዳግም ሲቀጥል ዋንጫውን ያነሳል?
አምሳሉ፡- በእርግጠኝነት ከአዳማ ከተማ ጋር ያለንን ጨዋታ በማሸነፍ አዳማ ላይ ዋንጫውን እናነሳለን፤ ፋሲል ከነማ
በስርዓት የሚያጫውት ዳኛ ካለና የተሻለም ሜዳ ካገኘ ቡድናችን አሁን ላይ ካለው ወቅታዊ ጥሩ አቋሙ የተነሳ
የትኛውንም ቡድን ማሸነፍ ይችላልና ዘንድሮ ባለድል እንሆናለን፡፡
ሊግ፡- የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ፉክክርን እንዴት አገኘኸው?
አምሳሉ፡- የፕሪምየር ሊጉ የዘንድሮ ውድድር ከወትሮው በጣም ይለያል፤ ውድድሩን ስትመለከትም የአንተን ቡድን
ማሸነፍ ብቻ ሳይሆን የሌላውን ክለብም ነጥብ መጣል የምትመለከትበትም ስለሆነ ሊጉ አጓጊም ሆኗል፤ የሊጉ
የውድድር ቆይታዬ ላይ ላለፉት አራት ዓመታት ስጫወትም እንዲህ ያለ ፉክክርን ተመልክቼም አላውቅምና ይሄ የአማረ
ሊግ ከተቋረጠበት ቀጥሎ ፍፃሜውን ቢያገኝ በጣምም ነው ደስ የሚለኝ፡፡
ሊግ፡- የፋሲል ከነማ እግር ኳስ ክለብ ውስጥ በጥሩ ብቃት በመጫወት በደጋፊዎቻችሁ ዘንድ ከፍተኛ አድናቆትን
እያተረፍክ ትገኛለህ፤ ስለ ወቅታዊ አቋምህ ምን ትላለህ?

አምሳሉ፡- የፋሲል ከነማ ክለብ ውስጥ በጥሩ ብቃት ላይ በመገኘት አድናቆት እያገኘሁ ያለሁት እኔ ብቻ ሳልሆን
ብዙዎቻችን የቡድኑ ተጨዋቾች ነን፤ እንደ ህብረት ስለምንጫወትም ነው በጥሩ ብቃት ላይ ልንገኝ የቻልነው፤ ለዚህ
ጥሩነታችን ደግሞ የአሰልጣኛችን ውበቱ አባተ ስልጠናና በክፍል ውስጥ የሚሰጠን ትምህርት ለችሎታችን መሻሻል
በጣሙን ጠቅሞናል፤ አንድ ቡድን ጥሩ መምህር ካለው ጥሩ ተማሪን ያፈራል፤ እኛ ጋርም ውበቱ አባተ ጥሩ አስተማሪ
ስለሆነ ጥሩ ተማሪዎችን እያፈራ ይገኛልና በክለቡ ውስጥ እኔም ከእስከዛሬው የፕሪምየር ሊግ የውድድር ተሳትፎዎቼ
መካከል ከሁሉም ጊዜ በተሻለ በምርጥ ብቃት ላይ የተገኘሁት ዘንድሮ በመሆኑ ይሄ የወቅታዊ አቋሜ ጥሩ መሆን
በጣሙን አስደስቶኛል፡፡
ሊግ፡- የፋሲል ከነማ ዋንኛው ዕልም የሊጉን ዋንጫ ማንሳት ብቻ ነው ወይንስ….?
አምሳሉ፡- አይደለም፤ የፋሲል ከነማ ዕልም የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ ማንሳት ብቻ ሳይሆን በአፍሪካ ክለቦች ደረጃም
ተሳትፎ በኢንተርናሽናል ውድድር ላይ ጥሩ ውጤትን በማምጣት ራሱን ለእውቅና ማብቃትና ሀገርንም ማስጠራት መቻል
ነው፤ ይሄን ማሳካት ነው የምንፈልገው፡፡
ሊግ፡- የፋሲል ከነማ ደጋፊዎች በአንተ እይታ እንዴት ይገለፃሉ?
አምሳሉ፡- የፋሲል ከነማ ደጋፊዎች አዛውንቶችን፣ ጎልማሳዎችን፣ ወጣቶችን፣ ህፃናቶችን እና ሴቶችን ጭምር
በማካተት ቡድኑን በሜዳ ላይ በመገኘት የሚያበረታቱ ሲሆኑ ከዛ ውጪም ስለ ቡድኑ አጠቃላይ ጉዳዮችና ውጤቶችም
እናቶች ቡና አፍልተው በጉጉት የሚጠብቁ ህፃናቶችም ሁሉን ነገር በጉጉት በማየት የሚያድጉ አይነት ደጋፊዎችም ያሉት
ስለሆነ አጠቃላይ ደጋፊዎቻችን በሚገኙበት ቦታ ሆነው ከሚሰጡን ድጋፍ በመነሳት በምን ቋንቋ እና እንዴት ብለን
እንደምንገልፃቸው አንድአንዴ ቃላቶች ነው የሚያጥሩን፤ እነሱ እየሞቱም የሚከተሉን ደጋፊዎች ስለሆኑ ያ ልዩ ክብር
እንድትሰጣቸው ነው የሚያደርግህና ለሁልጊዜም ድጋፋቸው እናመሰግናቸዋለን፡፡

photo – kebera z gonder (KZG)

spot_img
ተመሳሳይ ጽሁፎች

አስተያይት ያስፍሩ

እባክዎን አስተያይትዎን ያስፍሩ
እባክዎን ስምዎን እዚህ ያስገቡ

ትኩስ ዜናዎች

%d bloggers like this:
P