Google search engine

“በአንድ ጨዋታ ተደጋጋሚ ጎሎችን ማስቆጠር ለእኔ ብርቄ አይደለም” ፍፁም ጥላሁን /አዲስ አበባ ከተማ/

 

በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ  የዘንድሮ ውድድር  ከፍተኛ ግቦች  ከተቆጠሩበት  ግጥሚያዎች መካከል በአዲስ አበባ ከተማና በሰበታ ከተማ መሀከል የተደረገው ጨዋታ አንዱ ሲሆን አዲስ አበባም ፍልሚያውን 5-1 አሸንፏል፤ ለአዲስ አበባ ከተቆጠሩት ግቦች መካከልም የግብ አዳኙ ፍፁም ጥላሁንም  ሁለቱን አስቆጥሯል፤ ለፍፁም  እነዚህ ግቦቹ ቁጥሩን ወደ አምስት ያደረሰለት ሲሆን የኮከብ ግብ አግቢዎቹንም ተቀላቅሏል፤ ከአዲስ አበባ ከተማው  አጥቂ ፍፁም ጥላሁን ጋር የሊግ ስፖርቱ ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ አጠር ያለ ቆይታን አድርጓል፤ ተከታተሉት፡፡

ሊግ፦ ሰበታ ከተማን  በሰፊ  ግብ አሸንፋቸዋል፤  ግጥሚያው ምን መልክ ነበረው? ውጤቱንስ ጠብቃችሁ ነበር?

ፍፁም፦ ከጫና ውስጥ ከመምጣታችን አኳያ ግጥሚያው ጥሩ ነበር፤  ወደ ሜዳ የገባነውም እርግጠኛ ሆነን ጨዋታውን እንደምናሸንፍ ነበር፤  ያም ተሳክቶልናል፤  ለጨዋታው ትኩረት ስለሰጠንና  በደንብ ስለሰራንም ነው ያሸነፍነው።

ሊግ፦  ጨዋታውን እንድታሸንፉ የረዳችሁ ዋንኛው ጥንካሬያችሁ ምን ነበር?

ፍፁም፦  የመጀመሪያው ህብረታችን ነው፤  ለአንድ ቡድን  አስፈሪነት  ደግሞ  ትብብር  በጣም ወሳኝ ስለሆነ ያ እኛን  ላሳካነው ውጤት ጠቅሞናል።

ሊግ፦  አዲስ አበባ ተጋጣሚውን ሰበታ ከተማ በሰፊ የግብ ልዩነት ነበር  ያሸነፈው፤ በጨዋታው  ክፍተት የለበትም ነበር ማለት ነው?

ፍፁም፦ እንዴት አይኖርበትም፤ በእግር  ኳስ  የሚሸነፍ ቡድን ብቻ ሳይሆን የሚያሸንፍ  ቡድንም ክፍተት ይኖርበታል፤ በማሸነፍ ውስጥ ክፍተት አለ፤ ያንንም አሰልጣኞች ተመልክተው ችግሩን ያስተካክሉታል፡፡

ሊግ፦  በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ የእዚህ ሳምንት ጨዋታችሁ ሰበታን በመግጠም ነበር ያሸነፋችሁት፤ እነሱ ስለነበራቸው አቋም ምን አልክ?

ፍፁም፦  አብዛኛው  ሰው ጨዋታውን እንደተመለከተው እኛ ለግጥሚያው ከፍተኛ ትኩረት ሰጥተን ወደ ሜዳ እንደገባነው ሁሉ እነሱም ትኩረት ሰጥተው ነበር፤ ያም ሆኖ ግን  ቶሎ ቶሎ በእነሱ መረብ ላይ ጎል መግባት መቻሉ እነሱን ሊያወርዳቸው ስለቻለ በእዛ ነው እኛን ሊቋቋሙን ያልቻሉት፡፡

ሊግ፦  በኢትዮጵያ ቡና  ከሰበታ ከተማ ጨዋታ በፊት ተሸንፋችሁ ነበር፤ ስለእዛ ግጥሚያ የምትለን ይኖራል?

ፍፁም፦ አዎን፤ ከቡና ጋር ባደረግነው ጨዋታ ከባድ ግጥሚያ ነበር ያጋጠመን፤  መሸነፍ ደግሞ የሞራል ውድቀትን ያመጣል፣ የራስ መተማመንን ያጠፋል፤ አንገትንም ያስደፋል። እኛ ላይ ይህ ደርሶብንም ነበር፡፡

ሊግ፦  በኢትዮጵያ ቡና  መሸነፋችሁ  ተገቢ ነበር?

ፍፁም፦ በጣም፤ ቡና  በጨዋታም በሁሉም ነገር አሳማኝ  በሆነ መልኩ ነበር እኛን ያሸነፈን፤ ያን ዕለት እነሱ ለጨዋታው እንደሰጡት ትኩረት እኛ አለመስጠታችን ጎድቶናል፡፡

ሊግ፦  አዲስ አበባ ከተማ በቀጣይነት ስለሚያደርጋቸው ጨዋታዎች ምን ያስባል?

ፍፁም፦  ከፊት ፊት ያሉንን  ግጥሚያዎች ለማሸነፍ እንሄዳለን፡፡

ሊግ፦  በሰበታ ከተማ ላይ  ያገባከውን ሁለት ጎል ጨምሮ  አሁን ለቡድንህ ያስቆጠርከው ግብ አምስት ደርሶልሃል፤  ለኮከብ ግብ አግቢነቱም እየተፎካከርክ ነው፤ በእዚህ ዙሪያ የምትለው ነገር አለ?

ፍፁም፦  አዎን፤ ግቦችን ማስቆጠር ለእኔ ብርቄ አይደለም፤ ከእዚህ በፊትም  በአንድ ጨዋታ ሁለትና ከዛ በላይ ያስቆጠርኩባቸው ጊዜያቶችም ሆነ  በእዛ ደረጃ የሚገኙ የግብ እድሎችን አገኝም ነበር፤ የኮከብ ግብ አግቢነቱን በተመለከተ እየተፎካከርኩ ነው፤  የራሴ አንዳንድ ክፍተቶችና  የሜዳዎች አለመመቻቸት ካልሆነ በስተቀር   የራሴ  የሆነ  እቅድ ስላለኝ  ይህን  የኮከብ ግብ አግቢነት ክብር ለማግኘት ከፍተኛ ጥረትን አደርጋለሁ፡፡

ሊግ፦  በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ መጨረሻ አዲስ አበባ ሊጉ ላይ ይቀራል? ወይንስ አናገኘውም?

ፍፁም፦  በእርግጠኝነት እንኖራለን፡፡ የመጪው ዘመን ተሳታፊም እንሆናለን፡፡

ሊግ፦  አንድ ነገር በልና እንሰነባበት?

ፍፁም፦ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ከአምናው ጠንከር ብሏል፤  ክለቦች ብዙ ትምህርትም ወስደዋል፤ ጨዋታው እየከበደም መጥቷል። ይህን ካልኩ ልጨምር የምፈልገው ቡድናችን አሁን በያዘው የአሸናፊነት መንፈሱ ቀጥሎ እና ፍቅሩንና አንድነቱንም አጠናክሮ ጥሩ ስራ በመስራት ቡድኑን በሊጉ እንዲቆይ ማድረግ ዋናው ጉዳይ ነው፡፡

spot_img
ተመሳሳይ ጽሁፎች

አስተያይት ያስፍሩ

እባክዎን አስተያይትዎን ያስፍሩ
እባክዎን ስምዎን እዚህ ያስገቡ

ትኩስ ዜናዎች

%d bloggers like this:
P