Google search engine

“በኢትዮጵያ ቡና መለያ እኔም እንደ ወንድሜ አቡበከር ናስር መንገስን እፈልጋለሁ”“የዘንድሮ ሻምፒዮና የሚለየው አስቀድሞ ሳይሆን ሊጉ ሲጠናቀቅ ነው”ሬድዋን ናስር /ኢትዮጵያ ቡና/

 

ኢትዮጵያ ቡና በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ የዓምናው የውድድር ተሳትፎው ሊጉን በሁለተኝነት በማጠናቀቅ በአፍሪካ ክለቦች የኮንፌዴሬሽን ካፕ ውድድር ላይ ሊሳተፍ ችሏል፤ ዘንድሮ ደግሞ ከዓምናው ውድድሩ በጨዋታ እንቅስቃሴም ሆነ በውጤት ደረጃ በጣም ተሻሽሎ በመቅረብ የፕሪምየር ሊግ ዋንጫውን ለመውሰድ እንደሚጫወትና የእሱም የዋንጫ ዋንኛ ተፎካካሪዎቹ አንድ እና ሁለት ክለቦች ሳይሆኑ ሁሉም ክለቦች መሆናቸውን የቡድኑ የአማካይ ስፍራ ተጨዋች ሬድዋን ናስር ከሊግ ስፖርት ጋዜጣ አዘጋጅ ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ /G.BOYS/ ጋር ባደረገው ቆይታ ገልጿል፡፡

ከአዲስ አበባ ከተማ መስተዳደር ክለብ ኢትዮጵያ ቡናን በቅርቡ ከተቀላቀለበት ጊዜ አንስቶ በሜዳ ላይ ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴን እያሳየ የሚገኘውና አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ ለሚከተለው የጨዋታ ታክቲክም ተመራጭ ተጨዋች መሆኑን እያስመሰከረ የሚገኘው ይኸው ተጨዋች የዘንድሮው የሊጉ ውድድርም ጠንካራ ፉክክር ተካሂዶበት አሸናፊውም ክለብ በመጨረሻዎቹ ግጥሚያዎች እንደሚታወቅም አስተያየቱን አክሎም ገልጿል፤ ሬድዋን ይህን አስመልክቶም ሲናገር አሁን ላይ ብዙ ቡድኖች ተጠናክረው ስለመጡም “የዘንድሮ ሻምፒዮና የሚለየው አስቀድሞ ሳይሆን ሊጉ ሲጠናቀቅ ነው” በሚልም በድጋሚ አስረግጦም ተናግሯል፡፡

ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ የመጀመሪያው ረድፍ ጨዋታዎች በሐዋሳ ከተማ አስተናጋጅነት በሐዋሳ ዩንቨርስቲ ሜዳ ላይ ነገ እሁድ በድምቀት የሚጀመር ሲሆን ኢትዮጵያ ቡና የመጀመሪያ ጨዋታውን የፊታችን ማክሰኞ ከሲዳማ ቡና ጋር ያደርጋል፤ የኢትዮጵያ ቡናን የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ የዘንድሮ ተሳትፎን አስመልክተንና ስለ ፕሪ-ሲዝን ዝግጅታቸው እንደዚሁም ደግሞ ሌሎችንም ተያያዥ የሆኑ ጥያቄዎችን ለሬድዋን ናስር አቅርበንለት ምላሹን በሚከተለው መልኩ ሰጥቶናል፡፡

ሊግ፡- ለኢትዮጵያ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ የውድድር ዘመን ተሳትፎሊግ ስፖርት እንኳን በሰላም አደረሳችሁ ትላለች?

ሬድዋን፡- እኛም እንኳን አደረሳችሁ ለማለት እንወዳለን፤ እናመሰግናለን፡፡

ሊግ፡- ለአዲሱ ዓመት ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ተሳትፎአችሁ በምን መልኩ ተዘጋጅቷችኋል? ከሲዳማ ቡና ጋር ስለምታደርጉት ጨዋታስ ምን ትላለህ…?

ሬድዋን፡- በፕሪ-ሲዝኑ የዝግጅታችን ወቅት ለዘንድሮው የውድድር ዘመን ለመቅረብ ስንዘጋጅና ልምምዳችንን ስንሰራ የነበርነው ከዓምናው አቋማችን በመነሳት ነው፤ ኢትዮጵያ ቡና ባለፈው ዓመት የነበረውን ጠንካራና ክፍተት ጎኑን በሚገባ ያውቋል፤ ብዙ ጥሩ ጎኖች ነበሩን፤ ጥሩ የውድድር ዘመንንም አሳልፈናል፤ ባመጣናው ውጤትም ለአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ካፕ ውድድር ለማለፍና ውድድራችንንም ምንም እንኳን ወደተከታዩ ዙር ባናልፍበትም ልናደርግ ችለናል፤ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉን በተመለከተ በአጨዋወት ደረጃ የሚያድግ ነገርን በሊጉ ተሳትፎአችን ከካቻምና አንስቶ ያስመለከትንበት አጋጣሚ አለ፤ ዘንድሮ ደግሞ ያን ይበልጥ በማሻሻል በውጤት ደረጃም ሆነ በሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ጠንካራ የሚባለውን ኢትዮጵያ ቡናን ይዘን እንቀርባለን፤ ከሲዳማ ቡና ጋር ስለሚኖረን ጨዋታም እኛ ለእዚህ ፍልሚያ ብቻ አይደለም የተዘጋጀነው በእያንዳንዱ ግጥሚያዎቻችን ላይ የድል ውጤትን እንፈልጋለን ያን ለማሳካትም ነው የምንጫወተው፡፡

ሊግ፡- በ15ኛው የአዲስ አበባ ሲቲ ካፕ ዋንጫ ላይ ለመሳተፍ ችላችሁ ነበር፤ በዛም ውድድር ላይ ከምድባችሁ ለማለፍ አልቻላችሁም፤ በውድድሩ ዙሪያ ምን የምትለው ነገር አለ?

ሬድዋን፡- የእዚህ ውድድር ዋንኛ ተሳትፎአችንና ግባችን የነበረው ክለቡ ከታዳጊና ወጣት ቡድኑ ያሳደጋቸውን ተጨዋቾች ወቅታዊ የኳስ ብቃት በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝና በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉም የትኞቹን ተጨዋቾች ለመጠቀም እንደሚችልና ከዛም ውጪ ደግሞ እንደ ቡድንም በእንቅስቃሴ ደረጃ ቡና ከዓምናው በተሻለ መልኩ በምን መልኩ ለመቅረብ እንደሚችል ራሱን በሚገባ ያዘጋጀበት የአቋም መለኪያ ጨዋታ በመሆኑ ለእኛ ይሄ ውድድር በሚገባ ጠቅሞናል፤ የእዚህ የውድድር ተሳትፎአችን ላይ በእርግጥ ደጋፊዎቻችን ክለባችን ጥሩ ውጤት እንዲያመጣ ይፈልጉ ነበር፤ ያን ብናሳካ እኛም ደስ ይለን ነበር፤ ያም ሆኖ ግን ግጥሚያው ለእኛ በብዙ ነገሮች የጠቀመን ስለሆነ በጥሩ ጎኑ ነው የምናየው፡፡

ሊግ፡- ኢትዮጵያ ቡና በአዲስ አበባ ሲቲ ካፑ ያስመለከተን ታዳጊና ወጣት ተጨዋቾች ለዋናው ቡድን ግብዓት የሚሆኑ ናቸው?

ሬድዋን፡- አዎን፤ ጥሩ ጥሩ ተጨዋቾችን አይተናል፤ አሰልጣኙም ከእነዛ ውስጥ የሚፈልጋቸው ተጨዋቾችም አሉ፡፡ እነዛ ልጆችም እኛን የሚጠቅሙን ናቸው፡፡

ሊግ፡- በኢትዮጵያ ቡና ቆይታህ ጥሩ እንቅስቃሴን ለማሳየት ችለሃል፤ አሁን ካለህ ወቅታዊ አቋም በመነሳት ዘንድሮም ያ ብቃትህ ይደገማል?

ሬድዋን፡- በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ተሳትፎዬ ዓምና ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴን ማሳየቴን አውቃለው፤ የሲቲ ካፑም ውድድር ላይ ጉዳት ኖሮብኝ በከፍተኛ ፍላጎት ኳስን ስለተጫወትን ጥሩ እንደተንቀሳቀስኩ ለመመልከት ችያለው፤ ከእዛም ተነስቼ ዘንድሮ ስለሚኖረኝ አቋም ለመናገር የምፈልገው በአሁን ሰዓት የፕሪ-ሲዝን ዝግጅታችንን በጥሩ ሁኔታ ስንሰራ የከረምንበት አጋጣሚው ስላለ በቡና ቆይታዬ እኔም እንደ ወንድሜ አቡበከር ናስር መንገስን እፈልጋለው፡፡

ሊግ፡- ኢትዮጵያ ቡና በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ የዘንድሮ ተሳትፎው ምን ውጤትን ማምጣት አልሟል?

ሬድዋን፡- የእኛ ክለብ ሁሌም ቢሆን ወደዚህ ታላቅ ወደሆነውውድድር ለመሳተፍ ሲመጣ የመጀመሪያው ዋንኛ ዓላማውና ግቡ ዋንጫውን ማንሳት ነው፤ ምክንያቱም ክለቡ ኢትዮጵያ ቡናና በብዙዎች ዘንድም የሚወደድ ኳስን ማራኪ በሆነ መልኩ የሚጫወት ክለብ ነውና፤ አልፎ አልፎ ካልሆነ በስተቀር ሌላ ውጤት እኛ ጋር ተቀባይነት የለውም፤ ስለዚህም ዘንድሮ ዋንጫውን ለማንሳት እንጫወታለን፡፡

ሊግ፡- ዋንጫውን እናነሳለን ነው? ወይንስ ዋንጫውን ለማንሳት እንጫወታለን?

ሬድዋን፡- አሁን ላይ ሆኜ ዋንጫውን እናነሳለን ማለትን አልደፍርም፤ ምክንያቱም ሊጉ ገና አልተጀመረምና እርግጠኛ ሆኜ የምነግርህ ግን እስከ መጨረሻው ሰዓት ድረስ ዋንጫውን ለማንሳት እንደምንጫወት ነው፡፡

ሊግ፡- ኢትዮጵያ ቡናን የትኞቹ ክለቦች ዘንድሮ ለዋንጫው ይፎካከሩታል?

ሬድዋን፡- በእዚህ ዓመት ላይ በርካታ ክለቦች ጠንክረው እንደሚመጡ በሚገባ አውቃለው፤ ከዓምናው የሚሻል የጨዋታ ፉክክርንም እንመለከታለን፤ ለእኛ ቡድንም በውድድር ዘመኑ ጉዞ የዋንጫው ተፎካካሪዎች የሚሆኑብን ክለቦች አንድና ሁለት ክለቦች ሳይሆኑ ሁሉም ቡድኖችም ናቸው፡፡

ሊግ፡- ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ ዓምና ፋሲል ከነማ ውድድሩ ሳይጠናቀቅአስቀድሞ አንስቷል፤ ይህን ዋንጫ ዘንድሮስ ቀሪ ግጥሚያዎች እየቀሩት የሚያነሳ ቡድን ይኖራል?

ሬድዋን፡- እንደዛ ይሆናል ብዬ ፈፅሞ አላስብም፤ ምክንያቱም ዘንድሮ ሁሉም ቡድኖች ተጠናክረው ነው ለውድድሩ የሚመጡት፤ ከዛ ውጪም ከዓምና ተሳትፎአቸው የተማሩትም ብዙ ነገር አለ፤ ሌላው ቡድኖቹ ወደዚህ ውድድር ሲመጡ እንደከዚህ ቀደሙ ሊጉ ላይ ለመቆየት ብቻ ሳይሆን ለዋንጫው ለመፎካከርም እንደሆነ ያስተዋልኩበት ሁኔታ ስላለ የእዚህ ዓመት ሻምፒዮናው ክለብ ወደ መጨረሻው ግጥሚያ የሚወሰን ነው የሚሆነው፡፡

ሊግ፡- ኢትዮጵያ ቡናን አዳዲስም ሆነ ከስር ያደጉም ተተኪ ተጨዋቾች በዝግጅት ወቅቱ ላይ ለመመልከት ችለናልና እነሱ ቡድኑን የቱን ያህል እየተላመዱት መጥተዋል፤ እነሱን በማላመድ በኩልስ እናንተ ጋር ያለው ሚናስ ምን ይመስላል?

ሬድዋን፡- ኢትዮጵያ ቡና አሁን ላይ በእንቅስቃሴ ደረጃ እንደ አዲስ እየተሻሻለ የመጣ ክለብ በመሆኑ ቡድኑን የሚቀላቀሉት ተጨዋቾች ከአሰልጣኝ ካሳዬ አራጌም ሆነ ከእኛም ነባር ተጨዋቾች ቡድኑን በፍጥነት እንዲላመዱት ብዙ የሚጠቀማቸውን ምክሮች እያገኙና ክለቡንም እየተላመዱት ነው፤ ኳስ ተጨዋቾች ደግሞ ለመግባባት ጊዜ አይወሰድባቸውምና አሁን ላይ ጥሩ ነገርን እየተመለከትኩባቸውም ነው፡፡

ሊግ፡- ወንድምህ ስለሆነ አይደለም የኢትዮጵያ ቡናውን አቡበከር ናስርን ዘንድሮስ እንዴት ትጠብቀዋለህ?

ሬድዋን፡- /እንደ መሳቅ ብሎ/ እሱ ወንድሜ ስለሆነ ሳይሆን ሁሉም ስለ እሱ ሜዳ ላይ አይቶ ነው የሚመሰክረው፤ አቡኪ ዓምና ጥሩ ነገር አሳልፏል፤ በኮከብነቱ የተለያዩ ሪከርዶችንም ለመስበር ችሏል፤ ዘንድሮ የምጠብቀው ደግሞ ከዓምናው በጣም ላቅ ያለውን አቡበከርን ስለሆነ ይሄን ገድሉን እንደሚያሳካው በጣም እርግጠኛ ነኝ፡፡

ሊግ፡- በመጨረሻ……?

ሬድዋን፡- ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጋችንዘንድሮ የአማረና የደመቀ እንዲሆን እመኛለው፤ ክለባችንም የእዚህ ውድድር ሻምፒዮና እንዲሆንም ሁላችንም ተጨዋቾች ከመክፈቻው ግጥሚያችን አንስቶ እስከመጨረሻዎቹ ጨዋታዎች ድረስ አቅማችንን ሳንሰስት በመጫወት ደጋፊዎቻችንን በውጤት ማስደሰት እንፈልጋለን፤ ይህን ካልኩ ሌላው ልጨምረው የምፈልገው ነገር ይሄ የውድድር ዓመት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በአፍሪካ ዋንጫ የሚሳተፍበት ጊዜ ስለሆነና ኳስ ማለት ደግሞ ብዙ ጥሩ ነገሮችን ይዞልን የሚመጣም በመሆኑ የሀገራችንን ህዝብ ከዳር እስከ ዳር የሚያስማማልን ዓመት እንዲሆንም ምኞቴ ነው፡፡

spot_img
ተመሳሳይ ጽሁፎች

አስተያይት ያስፍሩ

እባክዎን አስተያይትዎን ያስፍሩ
እባክዎን ስምዎን እዚህ ያስገቡ

ትኩስ ዜናዎች

%d bloggers like this:
P