ኢትዮጵያ ቡናን በእዚህ ዓመት ተቀላቅሎ ነው ክለቡን እያገለገለ የሚገኘው፤ በቡድኑ የዘንድሮ የተጨዋችነት ዘመን ቆይታውም አበረታች የሚባል እንቅስቃሴን ካሳዩ ተጨዋቾች መካከል ስሙ የሚጠቀስ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ቡና የተከላካይ አማካይ ስፍራ ቦታ ላይ የሚጫወተው አለምአንተ ካሳ ከሊግ ስፖርት ጋዜጣ ጋር በተለያዩ ጥያቄዎች ዙሪያ ቆይታን አድርጎ ምላሹን በሚከተለው መልኩ ሰጥቷል፡፡
ሊግ፡- አለምአንተ ወይንስ ማሪዬ… በየትኛው ስምህ ነው በብዛት የምትታወቀው? ስሙስ እንዴት ሊወጣልህ ቻለ?
አለምአንተ፡- በመዝገብ ስሜ አለምአንተ ካሳ ተብዬ ልጠራ ብችልም ከልጅነት ዕድሜዬ አንስቶ ግን እኔ የምታወቅበት መጠሪያ ስም ማሪዬ ነው፤ በዛም ስምም ነው በብዙዎች ዘንድም የምጠራው፤ ይህ ስያሜ የወጣልኝም ልጅ ሳለው በጣም አጭር ነበርኩና ማሪዬ የሚባል የጌም ጨዋታ ነበርና የአካባቢዬ ልጆች ነው ሊያወጡልኝ የቻሉት፡፡
ሊግ፡- አለምአንተ የሚለው የመዝገብ ስምህስ አሁን ላይ በደንብ እየታወቀ ነው?
አለምአንተ፡- በሚገባ፤ አሰልጣኜ ካሳዬ አራጌ ጭምር በእዚህ ስሜ እየጠራኝ ነው፤ ከእሱ ውጪም ሌሎች የክለባችን ደጋፊዎችና እኔን የሚያውቁኝ ሌሎች ጓደኞቼም በስሙ እየጠሩኝ ነው፡፡
ሊግ፡- ወደ እግር ኳሱ መንደር የመጣኸው በኳስ ሜዳ አካባቢ በመወለድ ነው፤ በዛ ዙሪያ ምን የምትለው ነገር አለ?
አለምአንተ፡- ኳስ ሜዳ ለተለያዩ ክለቦች ብቻ ሳይሆን ለሀገር ጭምር ትልቅ ግልጋሎትን ሰጥተው ያለፉ ተጨዋቾችን ያፈራ አካባቢ ነው፤ ዛሬ ላይ ይሄ ሰፈር የስፖርት ማዘወተሪያ ቦታ አጥቶ እንደበፊቱ ብዙ ተጨዋቾችን ላያወጣ ቢችልም እኔም ከእዚሁ አካባቢ የተገኘው ነኝ፤ ከእዚህ ሰፈር በኳስ ተጨዋችነቱ በመውጣቴም በጣም ደስተኛም ነኝ፤ ይሄ ሰፈራችን ዛሬ ላይ ከሜዳ እጦት የተነሳ እንደበፊቱ ብዙ ተጨዋቾች ባይወጡበትም ወደሌላ ሙያ እና አላስፈላጊ ወደሆኑ ነገሮች ሊያመሩ ቢችሉም አሁንም ቢሆን ከእኔ የሚሻሉ ብዙ እምቅ ችሎታ ያላቸውን ተጨዋቾች ለእግር ኳሱ ማስገኘት ይችላልና የሚመለከተው አካል ለእዚህ አካባቢ አንድ ጥሩ ሜዳን ቢሰራ መልካም ነው፡፡
ሊግ፡- ኳስ ሜዳ የትውልድህ ቦታ ነው፤ አካባቢህን ምን ይለየዋል?
አለምአንተ፡- ብዙ ነገር ነዋ! ከእነዛም መካከል ዋና ዋናዎቹ ኳስ ጨዋታ በጣም የሚወደድበት ስፍራ መሆኑና ኳስን የሚችሉ ተጨዋቾችም የሚወጡበት ቦታ መሆኑ ነው፤ ሌላው ቀልደኛ እና ጨዋታ የሚችሉ ልጆች ይበዙበታል፤ ቁምነገርን በቀልድ ጭምርም ያወሩታልና ይሄ ይለያቸዋል፡፡
ሊግ፡- የእግር ኳስን በልጅነት ዕድሜ መጫወት ስትጀምር ለአንተ አርአያ ወይንም ደግሞ ሞዴልህ የሆነው ተጨዋች ማን ነበር?
አለምአንተ፡- የመጀመሪያው አርአያዬ የሆነው ተጨዋች ታላቅ ወንድሜ እስከዳር ካሳ ነበር፤ ያኔ እሱ ምንም እንኳን በክለብ ደረጃ ገብቶ ባይጫወትም ኳስ ሲጫወት በጣም ጎበዝ ነበር፤ ለመጫወት በሚሄድበት ስፍራ ሁሉ እሽኮኮ እያደረገም ይወስደኝ ነበር፤ በወቅቱ ሲጫወትም ተመለከትኩትና ስለ ኳስ ጨዋታ ማሰብ ጀመርኩ፤ በኋላም ላይ ትንሽ አደግ ስል እሱን ተመለከትኩና ራሴም ኳስን በሚገባ መጫወት ጀመርኩ፡፡
ሊግ፡- የእግር ኳስን ሲጫወቱ ተመልክተህ ሌሎች ያደነቅካቸው ተጨዋቾችስ ነበሩ?
አለምአንተ፡- አዎን፤ ከላይ ወንድሜን ገልጬልህ ነበር፤ ከእሱ ሌላ ደግሞ በሰፈር ደረጃም ሆነ በክለብ ውስጥ ሲጫወቱ ተመልክቼ ያደነቅኳቸው ተጨዋቾች ቢኖሩ ሙሉዓለም ረጋሳንና ቢኒያም ታዬን ነው፤ አጨዋወታቸው እኔ የምፈልገው አይነትም ነው፤ እነሱን በኳሱ ለረጅም ጊዜ ሲጫወቱ ባያቸው ብዬም ነበር የተመኘሁት፤ ሌላው ሲጫወት ያደነቅኩት ተጨዋች ደግሞ በደደቢት ክለብ ውስጥ አብሮኝ የተጫወተውን ሳምሶን ጥላሁንን ነው፤ ይሄ ተጨዋች አስገራሚ ክህሎት ያለውም ነው፡፡
ሊግ፡- የእግር ኳስን መጫወት ስትጀምር የቤተሰብ ተፅህኖ ነበረብህ? ከአንተ ውጪስ ሌሎች ተጨዋቾች አሉ?
አለምአንተ፡- በቤተሰባችን ውስጥ እግር ኳስን በክለብ ደረጃ እየተጫወትኩ ያለሁት እኔ ብቻ ነኝ፤ ሌሎቹ 3 እህቶቼና 2 ወንድሞቼ በተለያየ ስራ ላይ ነው የተሰማሩት፤ በተለይ አንዷ እህቴ በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል በላብራቶሪ ቴክኒሺያን እየሰራች ትገኛለች፡፡ ኳስን ልጅ ሆኜ ጀምሮ ስጫወት የቤተሰብ ተፅህኖ አልነበረብኝም፤ ለትምህርትህም ትኩረት ስጥ እንጂ አትጫወት ብሎም የሚጫነኝም ማንም አልነበረም፤ ኳሱን እንድጫወት በተለይ ቤተሰቦቼ ትጥቆችን ይገዙልኝ ነበር፤ እናቴም ኳስ የምጫወትበት ካልሲ የቆሸሸ እንዳይሆን ሁሉ እያጠበች ታቀርብልኝም ነበርና የእነሱን ውለታ ፈፅሞ አልረሳውም፡፡
ሊግ፡- ኢትዮጵያ ቡናን ከደደቢት በመምጣት ነው ዘንድሮ ክለቡን የተቀላቀልከው፤ በእዚህ ዓመት የነበረህ ቆይታህ የተሳካ ነው ወይንስ ያልተሳካ?
አለምአንተ፡- ለእኔ የተሳካ ነው እንጂ፤ ምክንያቱም በአዲሱ ቡድን ቆይታዬ በአዲሱ የክለቡ አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ የተሰጠኝን አዲስ የጨዋታ ታክቲክ በሜዳ ላይ እየተገበርኩ የነበርኩበት ሁኔታ ከሞላ ጎደል በጣም ጥሩ እና ሰፊ ስለነበርም ነው፡፡ ከዛ በተጨማሪ ደግሞ አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ በእኔ ላይ ያለው እምነትም ጥሩ እና ተደጋጋሚ የመጫወት እድሉን የሰጠኝም በመሆኑ ይህን ስመለከት በቡና ያሳለፍኩትን ቆይታዬ በጣም ነው ጥሩ የምለው፡፡
ሊግ፡- ኢትዮጵያ ቡና የቅድሚያ ምርጫህ ለአንተ እንዴት ሆነህ?
አለምአንተ፡- ምክንያቶቹ ሁለት ናቸው፤ የመጀመሪያው ክለቡን ልጅ ሆኜ እደግፈው ስለነበር ነው፤ ከዛ ውጪ ያለው ደግሞ ቡድኑ የሚከተለው አጨዋወት የምወደው አይነት እና የሚማርከኝ ስለነበርም ወደ ቡድኑ እንድገባ አስችሎኛል፤ ለቡና ገብቼ በመጫወቴም እድለኛ እና ደስተኛም እንድሆን አድርጎኛል፡፡
ሊግ፡- ለኢትዮጵያ ቡና መጫወት መቻልህ ያስገኘልህ ጥቅም አለ?
አለምአንተ፡- አዎን፤ በመጀመሪያ ደረጃ ለቡና መጫወት መቻል መመረጥ ነው፤ ከዛ በተጨማሪም በኢትዮጵያ ቡና ብቻ ሳይሆን በአሰልጣኝ ካሳዬ አራጌም ተፈላጊ እና ከፍተኛ እምነት የሚጣልብህ ተጨዋች ለመሆን መቻልህ እግር ኳስን በአህምሮ እንድትጫወት ስለሚያደርግህ እና እሱ በሚሰጥህ ስልጠናም ለውጦችን በራስህ ላይ ለመመልከት ስለምትችል ይህን ማግኘት መቻል ዕድለኝነትም ጭምር ስለሆነ ነው፡፡ ወደ ክለቡ ሳመራና ስጫወት ደግሞ ለእኔ ያስገኘልኝ ዋናው እና ሌላው ጥቅም የደጋፊውን እና የሰውን ፍቅር ማግኘት መቻልም ነውና ይሄ ደግሞ ከምንም ነገር በላይ ይበልጣል፡፡
ሊግ፡- ወደ ኢትዮጵያ ቡና ገብቶ መጫወት ከገንዘብ ጭምር ነው የሚበልጠው?
አለምአንተ፡- ለእኔ አዎን፤ ይህን የምልበትም የራሴ የሆነ ምክንያት አለኝ፤ ገንዘብ ነገ የሚገኝ ነገር ነው፤ ይሄን ገንዘብ የምታገኘውም መጀመሪያ ክለብህን በደንብ ማገልገል ስትችል ነው፤ በተለይ ደግሞ ለእንደዚህ አይነት ትላልቅ ቡድኖች እና የሀገሪቱም ታዋቂ የነበሩ ተጨዋቾች ተጫውተው ላለፉበት ክለብ ውስጥ ገብተህ ስትጫወት ትልቅ ስምና ክብርንም ስለሚያስገኝልህ ይሄን አገኘህ ማለት ደግሞ በተለይ ጥሩ የምትጫወት ከሆነ በራስህም ሆነ በሌሎች ቡድኖች የምትፈለግበት ዕድልህም በጣም ሰፊ ስለሆነ ለቡና መጫወት ተመራጭ ነው፤ ወደ ቡድኑ ስገባ ካገኘሁት ጥቅም አንዱም ለእዚህ ትልቅ ክለብ ለመጫወት መቻሌም ነው፡፡
ሊግ፡- በኢትዮጵያ ቡና የእዚህ ዓመት የተጨዋችነት ቆይታህ በሜዳ ላይ ከምታሳየው እንቅስቃሴ በመነሳት አንተን የሚያደንቁህም የሚቃወሙክም ደጋፊዎች አሉ? በእዚህ ዙሪያ ምን የምትለው ነገር አለ?
አለምአንተ፡- በመጀመሪያ ለሁለቱም ለሚያደንቁኝም ለሚቃወሙኝም ደጋፊዎች ትልቅ አክብሮት እንዳለኝ ብቻ ነው ለመናገር የምፈልገው፤ ምክንያቱም እነዚህ ደጋፊዎች በራሳቸው አመለካከት እና እይታም ነው ያደነቁኝም የተቃወሙኝም፤ የቡድኑ አሰልጣኝ ስላልሆኑም ምንም ነገርንም ሊሉ ይችላሉ፤ በቡና የዘንድሮ ቆይታዬ እኔ የምችለውን ብቻ ሳይሆን አሰልጣኜ ያዘዘኝንና በእኔ ልክ የሰራውን ነገር ነው በሜዳ ላይ ለመተግበር ጥረትን ሳደርግ የነበርኩት፤ ቡና አዲስ አይነት አጨዋወትን ነው ሲከተል የነበረው፤ በእዚህ አጨዋወት ውስጥ ደግሞ እስክትላመድ ድረስ ጊዜ ይፈልጋል፤ አሰልጣኙም ይህን ጠንቅቆ ያውቃል፤ ሁሉም ነገር የሚለመደው በመሳሳት ውስጥም ነው ብሎም ስለሚያምን እኔንም በዛ ደረጃ ጭምር ነው እያጫወተኝ እንድሻሻል እና መልካም የሆነ ጊዜንም ከክለቡ ጋር እንዳሳልፍ እያደረገኝ የሚገኘው፡፡
ሊግ፡- የኢትዮጵያ ቡናን የእዚህ ዓመት የሊግ ተሳትፎን በተመለከተ ምን የምትለው ነገር አለ? በመጪው ዓመት ውድድራችሁስ ምን ውጤትን ታስመዘግባላችሁ?
አለምአንተ፡- በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት የእዚህ ዓመት ውድድር እስከተቋረጠበት ጊዜ ድረስ ክለባችን ያስመዘገበውን ውጤት ስመለከት ለእኔ በጣም ጥሩ ነው፤ ምክንያቱም ቡና በዘንድሮው ውድድር አዲስ አሰልጣኝን በማምጣቱ፣ የተለያዩ ተጨዋቾችንም ከተለያዩ ክለቦች አስመጥቶ አዲስ ቡድንን በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ በመገንባቱ እና የክለቡም ተጨዋቾች አዲስ የጨዋታ ታክቲክን እየተላመዱ ከመምጣታቸው አኳያ የተመዘገበው ውጤት የሚያበረታታ ነው፤ ይሄን በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ከጥሩ ጨዋታ ጋር ለማየት ከተቻለ በመጪው ዓመት ላይ ደግሞ ክለቡ ይበልጥ ሊጠናከር የሚችልበት እና የሚከተለውንም የጨዋታ ታክቲክ በደንብ በሜዳ ላይ የሚተገብርበት ሁኔታ ስለሚኖር የሊጉ ሻምፒዮና እስከመሆን ድረስ የውድድር ዓመቱን እናጠናቅቃለን፡፡
ሊግ፡- በኮቪድ 19 ከእግር ኳሱ ከራቅህ በኋላ በጣም የናፈቀህ ማን ነው?
አለምአንተ፡- ብዙዎቹን ተጨዋቾች በስልክ አገኛቸዋለሁ፤ በአካል ያገኘዋቸውም አሉ፤ ለእኔ ግን በዋናነት የናፈቀኝ ሰው ቢኖር አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌን ነው፤ ካሳዬን ባገኘው ደስ ነው የሚለኝ፡፡
ሊግ፡- በኢትዮጵያ ቡና ቆይታህ አንተን በመጪው ዓመት እንዴት እንጠብቅህ?
አለምአንተ፡- የኢትዮጵያ ቡና ቆይታዬ ላይ ዘንድሮ በአሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ የተሰጠኝን አዲስ የጨዋታ ታክቲክ እየተላመድኩ በመጣሁበት ሰዓት ነው ውድድሩ ሊቋረጥ የቻለው፤ በአጨዋወቴ እሱም ቢሆን በእኔ ላይ ከፍተኛ እምነቱ አለው፤ ከዛ በመነሳት የመጪው የውድድር ዘመን ላይ ፈጣሪ ብሎ እግር ኳሳችን ሲጀመር ለቡና ሜዳ ላይ የምቅርብለት በጣም ምርጥ የሚባለውን ብቃቴን ከዘንድሮ የውድድር ዘመን በተሻለ መልኩ ይዤ በመምጣት ነው፡፡
ሊግ፡- ኢትዮጵያ ቡናን ከቋሚ ተሰላፊዎቹ ውስጥ አማኑሄል ዩሃንስ፣ ፈቱዲን ጀማል እና አህመድ ረሺድ /ሺሪላ/ ክለቡን ለቅቀዋል፤ ይሄን እንዴት ተመለከትከው?
አለምአንተ፡- እነዚህ ሶስት ተጨዋቾች የክለቡን አዲስ አጨዋወት ከመላመዳቸው እና ካላቸውም ጥሩ ችሎታ አንፃር ከእኛ ጋር ሊቀጥሉልን ቢችሉና ቢኖሩልን ኖሮ በጣም ደስተኛ ነበርኩ ምክንያቱም አዲስ ተጨዋች ወደ ቡድኑ ሲመጣ ገና አጨዋወቱን እንደ አዲስ ነው የሚላመደውና ያ ግን ሊሆን አልቻለም ስለዚህም ክለቡ በእነሱ ምትክ ለእንቅስቃሴው ምቹ የሆኑና አጨዋወቱንም ቶሎ ሊላመዱ የሚችሉ ተጨዋቾችን ወደ ቡድኑ በማምጣት የእነሱን ቦታ በፍጥነት ሊሸፍን ይገባዋል፡፡
ሊግ፡- ለኢትዮጵያ ቡና ስትጫወትም ሆነ ከዛ በፊት በነበረህ የተጨዋችነት ዘመን ቆይታህ ለጓደኞችህ ኳስን የምታቀብልበት መንገድ ብዙዎቹ ባላሰቡበት ነው፤ ለእዚህኛው ተጨዋች ትሰጣለህ ተብሎ ሲጠበቅ ላልታሰበው ተጨዋች ትሰጣለህ፤ በእዚህ ዙሪያ የምትለው ነገር ካለ?
አለምአንተ፡- አዎን፤ ከላይ የተገለፀው አይነት አጨዋወትን ብዙ ጊዜ የምጠቀምበት ነው፤ በተለይ ደግሞ ወደ ኢትዮጵያ ቡና አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ ከመጣ በኋላ የሚታይ ተጨዋች ሳይሆን የማይታይ ተጨዋች ፈልጉ፤ እዛ ላይም ትኩረት አድርጉ ስለሚል ያ የጨዋታ ዘይቤ ሊጠቅመኝ ችሏል፤ ብዙ ጊዜ አጥቂዎች በተከላካዮች ማርክ ተደርገው ነው ኳስ ሲሰጣቸው የሚታየው፤ ይሄ አጨዋወት ደግሞ የሚያዋጣ አይነት ስላልሆነ ነው የማይታይ ተጨዋች ፈልጋችሁ ኳስን አቀብሉ ስለሚል ያንን ነው ተግባራዊ የማደርገው፡፡
ሊግ፡- የኢትዮጵያ ቡና ተጨዋችነት ቆይታህ ላይ ማሻሻል አለብኝ የምትለው ነገር?
አለምአንተ፡- በእግር ኳስ ተጨዋችነቴ አሁን ከምገኝበት ደረጃ ከፍ ባለ ስፍራ ተገኝቼ ኳሽን ለመጫወት እንድችል ፍጥነቴን ማሻሻል እና የአካል ብቃቴንም /ፊትነስ/ መጨመር እንዳለብኝ ብዙዎች እየነገሩኝ ነው፤ እኔም የተረዳሁት ነገር አለ፤ ለዛም ስል አሁን ላይ ጠንክሬ እነዚህን ልምምዶች እየሰራሁ ነው የምገኘው፡፡
ሊግ፡- ኳስ ሜዳ ላይ ሲበላሽብህ ብዙ ጊዜ አትናደድም፤ ምክንያት አለህ?
አለምአንተ፡- አዎን፤ ኳስ ሲበላሽብኝ ምንም የማይመስለኝ ተናድጄ የምፈጥረው ነገር ስለሌለ ነው፤ ስለዚህም በቀጣዩ ስቴፕ የተበላሸብኝን ነገር አስተካክለዋለው ብዬ ስለማስብ ለዛ ስል አልናደድም፡፡
ሊግ፡- ከኢትዮጵያ ቡና ክለብ ውጪ በደደቢት እና በወልዋሎ አዲግራት ዩንቨርስቲ ክለቦች ውስጥ ተጫውተህ አሳልፈሃል፤ በእነሱ ቡድን የነበረህ ቆይታስ?
አለምአንተ፡- የደደቢት ክለብ ውስጥ የነበረኝ የተጨዋችነት ዘመን ቆይታዬ ገና ወጣት ተጨዋች እና የተካበተም የጨዋታ ልምድን ያልያዝኩበት ጊዜ ስለነበር የመሰለፍ ዕድልን ብዙ ካለማግኘት ጋር ያሳለፍኩበት ነው፤ በወልዋሎ አዲግራት ግን ከደደቢት በውሰት ተሰጥቼ ምርጥ የጨዋታ ጊዜን ያሳለፍኩበት እና ክለቡንም ወደ ፕሪምየር ሊጉ እንዲሸጋገር ትልቁን አስተዋፅኦ ያበረከትኩበት በአጠቃላይ ቆይታዬም የተሳካን የውድድር ጊዜን ያሳለፍኩበት ስለነበር ያን ፈፅሞ የምረሳው አይደለም፡፡
ሊግ፡- በወልዋሎ አዲግራት በአሰልጣኝ ብርሃኔ ገ/እግዚአብሄር ነው ለመሰልጠን የቻልከው፤ እሱን እንዴት አገኘኸው?
አለምአንተ፡- አሰልጣኝ ብርሃኔን መግለፅ በጣም ይከብዳል፤ በጣም ቅንና እንደ አባቴም የምገልፀው አይነት ነው፤ በችሎታዬ ላይ የጨመረልኝ ነገር አለ፤ ብዙ ጊዜ ልምምድ ላይ ነው ምን ማድረግ እንዳለብኝ የሚነግረኝ፤ በጨዋታ ላይ ግን በችሎታዬ በጣም ስለሚተማመን የሚያወራኝ ነገር ፈፅሞ የለም፤ የራሱ የሆነ ኳሊቲ ያለው አሰልጣኝም ነው፤ ለወልዋሎ አዲግራትም ትልቅ ቦታ መድረስ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደረገ ባለሙያተኛም በመሆኑ እሱን ላደንቀው ነው የምፈልገው፡፡
ሊግ፡- በዓለም እግር ኳስ የየትኛው ተጨዋች አድናቂ ነህ?
አለምአንተ፡- የባርሴሎና ደጋፊ ነን፤ ዣቪና ኤኔዬስታን ነው ሳደንቃቸው የነበርኩት፡፡
ሊግ፡- የእግር ኳስን ከመጫወት ውጪ የእረፍት ጊዜህን የምታሳልፍበት የተለየ ነገር አለ?
አለምአንተ፡- አዎን፤ ብዙ ጊዜ በቀጥታ የሚተላለፉ የባህር ማዶ እና የተቀዱ የቆዩ ኳሶችን ነው በመከታተል የማሳልፈው፤ በተለይ ደግሞ እኔ የምደግፈውን የባርሴሎናን ጨዋታ እና የሪያል ማድሪድን ኳሶች ስከታተል በጣምም ነው ደስ የሚለኝ፤ ሌላው ጊዜ ማሳለፊያዬ ፕሮግራም ደግሞ ሙዚቃን መስማት መቻል ነው፡፡
ሊግ፡- በሙዚቃው የምታደንቀው አርቲስት ማንን ነው? ምን አይነት ሙዚቃዎችስ ይመቹሃል?
አለምአንተ፡- በጣም የሚመቹኝ ሙዚቃዎች የቴዲ አፍሮ ናቸው፤ የእሱም አድናቂ ነኝ፤ ሌላው የምወደው ዘፈን ደግሞ የትግርኛን ነው፡፡
ሊግ፡- ባለህ ባህሪህ በምን መልኩ እና እንዴት ተደርገህ የምትገለፅ አይነት ሰው ነህ?
አለምአንተ፡- በባህሪዬ እኔ ሁሌም ቢሆን እንደ አካባቢው ሁኔታ ነው የምገለፀው፤ የሚጫወት ሰው ካለ እጫወታለው፤ ዝም የሚልም ካለ ዝም እላለው፡፡
ሊግ፡- በኢትዮጵያ ቡና ካምፕ ውስጥ በተለየ ባህሪው የምትጠቅሰው ተጨዋችስ አለ?
አለምአንተ፡- በቡና ክለብ የዘንድሮ ቆይታዬ በካምፕ ደረጃ ብዙም ባልኖርም አልፎ አልፎ በገባሁበት ሰዓት እና ቡድኑ አካባቢ ከተመለከትኩት ነገር በመነሳት በባህሪው ለእኔ ለየት ያለብኝ ተጨዋች ቢኖር እንዳለ ደባልቄ /ካክሽ/ ነው፡፡ ካክሽ በራሱ ዓለም የሚኖር እና የሚዝናናም አይነት ተጨዋች ነው፤ የሚያወራቸው ነገሮች በጣም ያስቃሉ፤ ለባሽ እና ዘናጭም የሆነ ተጨዋች ነው፤ በዛ ላይ ደስተኛም ነውና እሱን ነው በልዩ ባህሪው ልጠቅሰው የምችለው ተጨዋች፡፡
ሊግ፡- የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎችን ስትገልፃቸው?
አለምአንተ፡- እነሱን በምን አይነት ቃላት እንደምገልፃቸው አላውቅም፤ ያም ሆኖ ግን ሁሌም ቢሆን ለክለባቸው እና ለለበሱት 12 ቁጥር ማልያ ልዩ ፍቅር ያላቸውና ለቡድኑም ሟች የሆኑም ናቸው፤ ከዛ ውጪ ቡድናቸው ጥሩ እግር ኳስን ሁሌም ቢሆን እንዲጫወትም ያልማሉና ይሄ ዋንኛ መለያቸው ነው፡፡
ሊግ፡- የእግር ኳስን መጫወት መጨረሻ ለአንተ በክለብ ተጫውቶ ማሳለፍ ብቻ ነው?
አለምአንተ፡- አይደለም፤ ለብሔራዊ ቡድን ተመርጬ ሀገሬን ማገልገል እፈልጋለው፤ ለብሔራዊ ቡድን ተመርጬ ከተጫወትኩ በኋላም ነው ፕሮፌሽናል ተጨዋች መሆንን አጥብቄ የምፈልገው፤ ያን ነው የኳስ መጨረሻዬ ብዬም ልጠቅሰው የምፈልገው፤ ያለዚያ ለክለብ ብቻ ተጫውቼ በማሳለፍ ሳልታይ ፕሮፌሽናል ተጨዋችነትን ማለም ብዙም ስሜትን የሚሰጥ አይደለም፡፡ ስለዚህም በቡና የተጨዋችነት ዘመን ቆይታዬ ለክለቤ ምርጥ የሚባል ግልጋሎትን በቀጣይነት በመስጠት እነዚህን እድሎች ማግኘትን እፈልጋለውኝ፡፡
ሊግ፡- ወደ ትዳር ህይወቱ አምርተሃልና እንዴት እያስጓዝከው ነው? ስለ ባለቤትህስ ምን ትላለህ?
አለምአንተ፡- የትዳር ህይወት በጣም አሪፍ እና ከፍተኛ ኃላፊነትም እንዲሰማህ ያደርግሃልና እስካሁን ባለኝ ጉዞዬ ኑሮዬን በጥሩ መልኩ እያስኬድኩት ነው፤ ያን ካልኩ ስለ ባለቤቴ ሜሮን ብርሃኔ የምለው ነገር ቢኖር ደግሞ ሜሮን በኳሱ አሁን ላይ ለምገኝበት ስፍራ ከጎኔ በመሆን ብዙ ነገሮችን እያደረገችልኝ ያለች እና የምትደግፈኝ ናት፤ ከዛ በተጨማሪ አሁን ላይ በኮቪድ ሩ ለእዚህ ውለታዋም ልትመሰገን ይገባታልና አመሰግናታለሁ፡፡
ሊግ፡- ሜሮንን አጠር ባለ ቃላት አወድሳት ወይንም ደግሞ ግለፃት ብትባል?
አለምአንተ፡- በጣም እወድሻለሁ፤ አፈቅርሻለሁ፤ አከብርሻለሁም ነው የምላት፡፡
ሊግ፡- ኮቪድ 19 ወደ አገራችን ከገባበት ጊዜ አንስቶ ከኳሱ ርቅሃል፤ ስሜቱ እንዴት ይገለፃል? ወቅቱንስ በምን መልኩ እያሳለፍክ ነው?
አለምአንተ፡- በኮቪድ ወረርሽኝ ለበርካታ ወራቶች ከእግር ኳሱ የራቅንበት ሁኔታ ፈፅሞ ያልተለመደ እና በተጨዋችነት ዘመናችንም አጋጥሞን የማያውቅ ስለሆነ ነገሮችን ሁሉ ለእኔ ብቻ ሳይሆን ለሁሉም የእግር ኳስ ተጨዋቾች ከባድ አድርጎባቸዋል፤ ኮቪድ ከምንወደው እግር ኳስና ከሚወዱን ደጋፊዎቻችን ጭምርም ነው ሊያርቀን የቻለውና ይሄ መሆን መቻሉ ጥሩ ስሜት እንዳይሰማን አድርጓል፡፡ ስለዚህም በፈጣሪ እርዳታ ወደምንወደው እና የብዙ ሰዎችም የደስታ ምንጭ ወደ ሆነው ኳሳችን በፍጥነት እንድንመለስ እሱ ይርዳንም ነው የምለው፡፡
በኮቪድ የእግር ኳስን መጫወት ካቆምኩ በኋላ አብዛኛውን ጊዜዬን ሳሳልፍ የነበረው ከባለቤቴ ጋር በመሆን በቤት ውስጥ ነበር፤ አሁን ላይ ደግሞ አልፎ አልፎ ራሳችንን ከወረርሽኙ በምንጠብቅበት ሁኔታ የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎችን በማድረግና መሀል ባልገባም በመጫወት ጊዜውን እያሳለፍን ይገኛል፡፡
ሊግ፡- በመጨረሻ….. ?
አለምአንተ፡- በእግር ኳስ ዛሬ ላይ ለደረስኩበት ስፍራ ከጎኔ ሆነው ከፍተኛ አስተዋፅኦ ላበረከቱልኝ አካላቶች ሁሉ ምስጋና አለኝ፤ ቤተሰቦቼ፣ ባለቤቴ ሜሮን፣ ለወልዋሎ አዲግራት ስጫወት በክለቡ አመራሮች አሰልጣኞች እና ደጋፊዎች ልብ ውስጥ ገብቼ ነበርና እነሱን እንደዚሁም ደግሞ የቡና ደጋፊዎችን እና የኳስ ሜዳ አካባቢ ጓደኞቼን ላመሰግናቸው እፈልጋለው፡፡