Google search engine

“በኳስ ዘመኔ ጥሩ ጊዜን ባሳልፍም ሀገሬን ግን በምፈልገው ደረጃ አላገለገልኩም”
ታደለ መንገሻ /ሰበታ ከተማ/


የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የተጨዋችነት ዘመን ቆይታው ላይ ለቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ለኢትዮጵያ መድን፣ ለደደቢት፣ ለአርባምንጭ ከተማ በመጫወት አሳልፏል፤ ከአምና አንስቶ እና ዘንድሮ ደግሞ በሰበታ ከተማ ቡድን ውስጥ ይገኛል፤ በሊጉ የተጨዋችነት ዘመን ቆይታው በሜዳ ላይ በሚያሳየው ጥሩ ብቃት እንደዚሁም ደግሞ ለአጥቂ ስፍራ ተጨዋቾች በሚሰጣቸው ጣጣቸውን የጨረሱ የግብ ኳሶች በብዙዎች ዘንድ ይደነቅ የነበረው ታደለ መንገሻ ለብሔራዊ ቡድናችንም እስከመጫወት ደረጃ የደረሰ ሲሆን ስላሳለፋቸው የኳስ ጊዜያቶቹና ስለመጪው ጊዜ እንደዚሁም ሌሎችን ጥያቄዎች ጨምረን አነጋግረነው የሰጠንን ምላሽ እናቀርብላችኋለን፡፡
የአርባምንጭ ከተማ ውስጥ በመወለድ ያደገው ታደለ መንገሻ በቤተሰባቸው ውስት ከሚገኙት 5 ወንድሞቹና አንድ እህቱ ውስጥ በአሁን ሰዓት ብቸኛው የእግር ኳስ ተጨዋች ሲሆን ከእዚህ ቀደም በተለያዩ ቡድኖች ውስጥ በጥሩ ብቃት ላይ ኳስን ይጫወት የነበረው ታላቅ ወንድሙ አለማየሁ መንገሻ /ክሪዝ/ የሚጠቀስ ተጨዋችም ነበር፤ ከታደለ መንገሻ ጋር ያደረግነው ቆይታ ይሄንን ይመስላል፡፡
ሊግ፡- በእግር ኳስ ጨዋታ ዘመንህ በተለያዩ ክለቦች ውስጥ ተጫውተህ አሳልፈሃል፤ እነዛ ጊዜያቶችህ ለአንተ ምርጦች ነበሩ?
ታደለ፡- አዎን፤ በኳስ የሚያጋጥሙ ጥሩም ሆኑ ጥሩ ያልሆኑ ነገሮች ቢኖሩም እስካሁን ባሳለፍኩት የኳስ ህይወቴ በጣም ደስተኛ ነኝ፤ በየተጫወትኩባቸው ክለቦች ውስጥም ጥሩና ምርጥ የሚባል ጊዜንም ነው ለማሳለፍ ችያለሁ፤ በተለይ ደግሞ ኳስን ስጫወት እንደ መዝናኛ /ኢንጆይመንት/ ተዝናንቼበት የምጫወተው እንጂ ተጨናንቄበት የማሳልፈው ነገር ስላልሆነ ለዛም ጭምርነው ጠንክሬ በመስራት የዛሬው ደረጃ ላይ ለመድረስ የቻልኩት፡፡
ሊግ፡- በእግር ኳስ ጨዋታ ዘመንህ የተቆጨህበት ጊዜስ የለም?
ታደለ፡-ደስታው የሚበዛ ቢሆንም አለ እንጂ፤ከቁጭቴ ውስጥ ግን መቼም ቢሆን የማልረሳው የሀገሪቱ ትልቅ ቡድን የሆነው የኢትዮጵያ መድን እግር ኳስ ክለብ በእኛ ጨዋታ ዘመን ሊወርድ በመቻሉ ነው፤ መድን ጥሩ ቡድን ነበር፤ ከሊጉ በጎል ልዩነት ነበር ተበልጦ የወረደው፤ ካለው ስምና ዝና አንፃር መውረድ አልነበረበትም ነበርና ያኔ በጣም አዝኛለው፡፡
ሊግ፡- በእግር ኳስ ጨዋታ ዘመንህ ለሁለት ጊዜያት ያህል የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ ለማንሳት ችለሃል፤ ሶስተኛ ዋንጫስ አይናፍቅም?
ታደለ፡-ይናፍቃል እንጂ፤ እነዚህን ስኬቶች ከእዚህ ቀደም በቅ/ጊዮርጊስ እና በደደቢት ክለብ የተጨዋችነት ዘመን ቆይታዬ ለማሳካት ችያለሁ፤ እነዚህን የሊግ ዋንጫ ክብሮችን ለመቀዳጀት የቻልኩትም ቡድኖቹ ጥሩ የተጨዋቾች ስብስብ ስለነበራቸው እና የዋንጫ ተፎካካሪ ቡድን ስለሆኑም ነው፤ ስለዚህም በቀጣዩ ጊዜ የኳስ ህይወቴም ይህንን ዋንጫ ለሶስተኛ ጊዜ ጥሩ ስብስብን ከሚይዘው እና ጠንካራም የሊጉ ተወዳዳሪ ከሚሆነው ቡድኔ ጋር ማንሳቴ የማይቀር ነው፡፡
ሊግ፡- በብሔራዊ ቡድን እና በክለብ ደረጃ የእግር ኳስን ተጫውተህ ባሳለፍክባቸው ያለፉት ጊዜያቶች የእኔ ምርጥ የጨዋታ ዘመኖቼ ብለህ የምትጠቅሳቸው የትኞቹን ነው?
ታደለ፡- በክለብ ደረጃ ደደቢት እያለው የነበረበትን ጊዜ ነው የምጠቅሰው፤ ያኔ ቡድናችን ምርጥ ነበር፤ ዓመቱን ሙሉ በጥሩ ብቃታችን ተጫውተናል፤ የኳስ ፍሰታችን የሚያምርም ነበር፤ ከዛም ውጪ አሳማኝ በሆነ መልኩም ከሁሉም ቡድኖች ተሽለን የሊጉን ዋንጫ በክለቡ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜም የወሰድንበትና እኔም ምርጡን የውድድር ዘመን እንደ ቡድን ብቻ ሳይሆን እንደ ግልም ያሳለፍኩበት ጊዜ ስለነበር ያ የሚረሳ አይደለም፤ ከክለብ ባሻገር በብሔራዊ ቡድን ደረጃ ለእኔ ምርጡ ጊዜ የምለው ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በተመረጥኩበት ዓመት ላይ ከአልጄሪያ ጋር ተደርጎ በነበረው ጨዋታ 7 ግብ ተቆጥሮብን ስንሸነፍም ሆነ የመልሱ ጨዋታ ላይ 3-3 ስንለያይ ጥሩ ከመጫወቴ በተጨማሪ ጌታነህ ከበደ ላስቆጠራቸው ሶስት ግቦች የተመቻቹ የግብ ኳሶችን ሰጥቼው ነበርና እነዛ ጨዋታዎቼ የሚታወሱ ናቸው፡፡
ሊግ፡-ከእዚህ ቀደም ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተመርጠህ ያሳለፍክባቸው ጊዜያቶች ነበሩ፤ አሁንስ ይህን ቡድን በድጋሚ ለመቀላቀል የምታደርገው ጥረት አለ?
ታደለ፡- አዎን፤ እንዴት አይኖርም፤ በኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ የኃላፊነት ዘመን የመመረጡን ዕድል ከማግኘት አንስቶ የ23ቱ የተጨዋቾች ዝርዝር ውስጥ እስከመግባት ደረጃ ላይ ደርሼ ነበር፤ እነዛን የመመረጥ ዕድሎች የምታገኘው ደግሞ በክለብ ውስጥ በምታሳየው ወቅታዊ አቋምና ብቃትም ላይ ነበርና ያን እድል በጊዜው ለማግኘት ችያለሁ፤ ስለዚህም የአሁኑ ብሔራዊ ቡድን ላይም ዳግም የቡድኑን ስኳድ ለመቀላቀል በቀጣይ ጊዜ በሚኖረኝ የውድድር ዘመን የራሴን ችሎታ ከሌሎች ተጨዋቾች በላይ /አሁት ሻይን/ በማድረግ ለመመረጥ ከፍተኛ ጥረትን አደርጋለው፡፡
ሊግ፡- ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከእዚህ ቀደም ተመርጠህ ከመጫወትህ አንፃር ሀገሬን በሚገባ አገልግያለው ብለህ ታስባለህ?
ታደለ፡- በፍፁም፤ ለሀገር ብሔራዊ ቡድን መጫወት መቻል በጣም ደስ የሚል እና ማንኛውም ተጨዋችም የሚመኘው ነገር ቢሆንም ካለኝ ብቃት አንፃር እንደዚሁም ደግሞ በተለያዩ ክለቦች ውስጥ ኳስን ስጫወት ጥሩ ጊዜን ባሳልፍም ሀገሬን ግን እኔ በምፈልገው ደረጃ አላገለገልኩም፤ ስለዚህም በቀጣይ ጊዜ የኳስ ቆይታዬ ጠንክሬ በመስራት እና ለብሔራዊ ቡድን በመመረጥ ሀገሬን ለአንዴ ብቻ ሳይሆን ለተደጋጋሚ ጊዜም የታላቅ የውድድር መድረክ ላይ ማብቃት ስችል ነው በጣም ጠቅሜያታለው ብዬም የማስበው፡፡
ሊግ፡- ከማን አጠገብ ስትጫወት ነው የእግር ኳስ ጨዋታ ዘመኔ ምርጡ ጥምረቴ የምትለው?
ታደለ፡- ከሽመልስ በቀለ ጋር ነዋ! ከእሱ ጋር በብሔራዊ ቡድን ደረጃ ከአጠገቡ ሆኜ ተጫውቻለው፤ ምርጥ ችሎታ አለው፤ ከእሱ አጠገብ ስትሆን ኳስ ቀሎህ እንድትጫወት ያደርግሃል፡፡
ሊግ፡- እንደ መሀል ሜዳ ተጨዋችነትህ የሚመችህ ምርጡ አጥቂስ?
ታደለ፡- በእዚህ ደረጃ ሁሌም ስሙን መጥቀስ የምፈልገው ተጨዋች ቢኖር ጌታነህ ከበደን ነው፤ ከጌታነህ ጋር በደደቢት እና በብሔራዊ ቡድን ደረጃ አብረን ተጫውተናል፤ የእሱ የቦታ አያያዝ /ፖዚሽን/ በጣም አመች እና በየቱም ስፍራና መልኩም ኳስን እንድታቀብለው ያስገድድሃልና ከእሱ ጋር በእዚህ የእንቅሰቃሴ ደረጃ ሁሌም ስለምንግባባ እና ኳስን ለመስጠት ስለማይከብደኝ እንደዚሁም ደግሞ ምን እንደሚፈልግም ስለማውቅ እሱ የእኔ ቀዳሚ ምርጫዬ ነው፡፡
ሊግ፡- ከአንተ አጠገብ እንዲጫወት የምትመኘው ተጨዋችስ?
ታደለ፡- ይህ ተጨዋች የኢትዮጵያ ቡናውና የብሔራዊ ቡድናችን አጥቂ አቡበከር ናስር ነው፤ ወጣቱን ተጨዋች በጣም ነው የማደንቀው፤በችሎታው ባለፉት ሁለት ዓመታት በፕሪምየር ሊጉ እያንፀባረቀ የመጣና ተስፋ የሚጣልበትም ተጨዋች ነው፤ ወደፊት ትልቅ ደረጃም ላይ ይደርሳል፡፡
ሊግ፡- ለዘንድሮው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሻምፒዮና ውድድር ክለባችሁ ሰበታ ከተማ እስካሁን ዝግጅት አልጀመረም፤ አንተስ ጀመርክ?
ታደለ፡- አዎን፤ ከጀመርኩኝም ቆይቻለሁኝ፤ ምክንያቱም ክለቤ አልጀመረም ብለህ አንተ ቁጭ የምትል ከሆነ ስራህን እያከበርክ አይደለህም ማለት ነውና በብዙ ነገሮች ልትጎዳ ትችላለህ፤ ልክ ነህ የአሁን ሰዓት ላይ አብዛኛው ቡድኖች የፕሪ-ሲዝን ዝግጅታቸውን መስራት በጀመሩበት ሰዓት የእኛ ቡድን ግን ዝግጅቱን አልጀመረም፤ ስለዚህም የእኛ ሀገር ተጨዋቾች ላይ የመዘናጋት ነገርን ብዙ ጊዜ ታያለህና ቡድንህ ባይጀምር እንኳን አንተ ልምምድህን በግል ልትሰራ ይገባል፤ ባለፉት በርካታ ወራቶች ራሱ በኮቪድወረርሽኝ ምክንያት ምንም አይነት እንቅስቃሴዎች እንዳይኖሩ በተደረገበት ጊዜ ራሱ ከበሽታው ራስህን በመጠበቅ ተደብቀህ ልምምድ መስራት በራሱ ጥቅም ነበረውና በዛ መልኩ ነው ዝግጅቴን ሳላቋርጥ ስሰራ የነበረውና እንደ ግል ለአዲሱ የውድድር ዘመን ራሴን በሚገባ ከወዲሁ አዘጋጅቻለው፡፡
ሊግ፡- ሰበታ ከተማ ዝግጅቱን እስካሁን አለመጀመሩ በሊጉ የውድድር ተሳትፎው ላይ ምንም አይነት ተፅህኖን አይፈጥርበትም?
ታደለ፡- ሌሎች ቡድኖች ዝግጅታቸውን ከአንድ ወር በፊት ከመጀመራቸው አንፃር ሲታይማ ተፅህኖ ማጋጠሙ አይቀርም፤ እኛን በጣምም ነው የሚጎዳን፤ ከእዚህ በኋላ የአንድ ወር ጊዜ ነው ያለን፤ ማን በምን አቋም ላይ እንዳለ አይታወቅም፤ የሚያሳስበን ነገር አለ፤ ይሄ ሁሉ ሲሆን ግን ክለባችንን የሚያጋጥመውን ነገር ሳያስቡ ቀርተው አይመስልም፤ አሁን ላይ የፋይናንስ ችግራችንን እያስተካከሉ በመምጣት የሊጉን ዝግጅት በምን መልኩ መጀመር እንዳለብን ነው እያሰቡ ያሉትና አሁንም ቢሆን በፍጥነት ወደዝግጅታችን ብንገባ የከፋ ነገር ከሚያጋጥመን መልካም ነው፡፡
ሊግ፡- ሰበታ ከተማ ያሳለፍነውን ዓመት የውድድር ዘመን በምን መልኩ አሳለፈ?
ታደለ፡-ሰበታ የፕሪምየር ሊጉን ውድድር የተቀላቀለው ከከፍተኛ ሊግ በመምጣት ነበር፤ ከዛም በአዲስ አበባ ሲቲ ካፕ ውድድር ላይ በመሳተፍ እስከፍፃሜ ደረጃ ላይ ሊዘልቅም ችሏል፤ ክለቡ ከስር እንደመምጣቱ፣ አብዛኛዎቹ ተጨዋቾችም አዲስ እንደመሆናቸውና በአዲስ አሰልጣኝም እንደመመራቱ ጠንካራ የሚባል ቡድንን ለመገንባት ጊዜ ያስፈልጋልና የኮቪድ ወረርሽኝ የሊጉንውድድር እስካቋረጠበት ጊዜ ድረስ ቡድናችን ያስመዘገበውን ውጤት ስመለከተው ምንም እንኳን የአንድ ቡድን ውጤት የሚለካው የዓመቱ መጨረሻ ላይ ቢሆንም ለእኛ ግን የተመዘገበው ውጤት በጣም የሚያበረታታ ነበር፤ በተለይ ደግሞ በአንደኛው ዙር ላይ ከነበረን ጥሩ ያልሆነ አጀማመር አኳያም ከሰባተኛው ሳምንት አንስቶ ራሳችንን እያስተካክልን የመጣንበትና ከሁሉም በላይ ደግሞ የሁለተኛው ዙር የሁለት ሳምንት ጨዋታዎቻችን ላይ ያስመዘገብነውን ውጤት ስንመለከት ከወልዋሎ ጋር ነጥብ ተጋርተን የመጣንበት እና ቅ/ጊዮርጊስን ደግሞ በሜዳው እና በደጋፊዎቹ ፊት አሸንፈን የወጣንበትም ስለነበር ውድድሩ ባይቋረጥ ኖሮ ጉዞአችን ከእዚህም በላይ በጣም የሰመረም ይሆን ነበር፡፡
ሊግ፡- ሰበታ ከተማ ዘንድሮስ ምን አይነት ቡድንን ይዞ ይቀርባል፤ ምን ውጤትስ ያስመዘግባል?
ታደለ፡- በክለቡ ውስጥ ልምድ ያለን /ሲኒየር/ ተጨዋቾች አለን፤ ጥሩ አቅምም አለን፤ የእኛ በቡድኑ ውስጥ መኖር መቻልም ቡድኑን በጣም ይጠቅመዋል፤ ወደ ቡድኑ ከሚመጡት ሌሎች ተጨዋቾች ጋርም ሆነ ነባር ከሆኑት ጋርም ስንቀናጅ ጠንካራ ቡድንን ለመስራት የሚቻለንም ይመስለኛል፤ ውጤትን በተመለከተ አሁን ላይ ዝግጅትን ሳንጀምር ይሄ ይገጥመናል ብዬ ለመናገር አልፈልግም ዋናው ነገር ጠንክሮ መስራትና አህምሮህን ማሳመን ነው ያኔም ጥሩ ነገር ይገጥምሃል፡፡
ሊግ፡- የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በዲ.ኤስቲ.ቪ ዘንድሮ ይተላለፋል፤ በእዚህ ዙሪያ ምን አልክ?
ታደለ፡- በዲ.ኤስ.ቲቪ እነዚህ ጨዋታዎች መተላለፋቸው ለብዙ ተጨዋቾቻችን ከፍተኛ ጠቀሜታ ነው ያለው፤ እስከዛሬ ባለመተላለፉም ተጎድተናል፤ ምክንያቱም እነዚህን ግጥሚያዎቻችን ዓለም ነው የሚያያቸው፤ አሰልጣኞች፣ የተጨዋቾች ኤጀንቶች እና ሌሎችም አካላቶች ይህን ግጥሚያ ተመለከቱ ማለትም በርካታ ተጨዋቾቻችን ራሳቸውን በብቃት በማዘጋጀትና ወደ ባህር ማዶም በቀጥታ ሄደው የሚጫወቱበት እድል ስለሚኖር ይሄ ለኢትዮጵያ ትልቁና መልካሙም ዜና ነው፡፡
ሊግ፡- በአሁን ሰዓት የእግር ኳስን ከመጫወት ውጪ የአንተ የተለየ መዋያ ወይንም ደግሞ ሆቢህ ምንድን ነው?
ታደለ፡- ወደ ቤተክርስቲያን እና ገዳማቶች መሄድን እና መጎብኘትን አዘወትራለው፤ ከዛ ውጪ ደግሞ ፊልም ማየትም ዋንኛ ምርጫዎቼ ስለሆኑ እነዚህ ነገሮች ናቸው የእኔ ጊዜ ማሳለፊያዎች፡፡
ሊግ፡- የታዴ ጋብቻ መች ነው የሚል ጥያቄ እየተነሳ ይገኛል፤ ይህን መች እንጠብቅ?
ታደለ፡- ጓደኛዬ በባህር ማዶ ከመኖሯ አኳያ ከፈጣሪ እርዳታ ጋር በእዚህ ሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ይህ ጋብቻ ቀን ተቆጥሮለት እውን ይሆናል፡፡
ሊግ፡- በባህሪህ መልካም ሰው ነህ ማለት ይቻላል?
ታደለ፡- በጣም፤ ከእኔ ይልቅ ግን ሰው ስለ እኔ ቢያወራ ይሻላል፤ መልካምነት ብቻ እኔን አይገልፀኝም፤ ከዛም በላይ ነኝ፤ ኳሱ ላይ እንድቆይ ያደረገኝም ይህ ባህሪዬም ነው፤ በተለይ ደግሞ በጣም ዲስፕሊን ሆኜ መምጣቴና ለምወደው ሙያዬም ተገዥ መሆኔም ብዙ ነገሮችንም ተቋቁሜ እንድጫወትም አድርጎኛልና በዛ መልኩ ማለፌ ደስተኛ እንድሆንም ነው ያደረገኝ፡፡
ሊግ፡- የአገራችንን ሰላም እና አንድነት በሚጠብቅልን የመከላከያ ሰራዊታችን ላይ ሰሞኑን በራሳችን ወገን ጥቃት ተፈፅሞበታል፤ እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ይህን መረጃ ስትሰማ ምን አይነት ስሜትን በውስጥህ ፈጠረብህ?
ታደለ፡-በእውነቱ መጀመሪያ ወንድም በወንድሙ ላይ እንዴት ይጨክናል ነው ያልኩት፤ ድርጊቱ በጣም አሳዛኝ እና የሚያሳፍርም ነው፤ ስለ አገራችን ሁኔታ ካለፉት ሁለት ዓመታት አንስቶ የምንሰማቸው ነገሮች በጣም ደስ አይሉም፤ የምትሰማቸው ነገሮች ሁሉም በጣም ይከብዱሃል፤ ብዙ ችግሮችን እያስተናገድን ባለንበት የአሁን ሰዓት ላይ እኛ ኢትዮጵያኖችን በመጠበቅ ላይ ባለው ሰራዊታችን ላይ በገዛ ወንድሞቻችን ይሄ የጥቃት አደጋ ለመድረስ መቻሉም ለሰሚም በጣም የሚከብድ ስለሆነ ድርጊቱ ሊኮነን ይገባል፤ እኛ ኢትዮጵያኖች ሁሌም ሰላምን ነው የምንፈልገው፤ ስለዚህም አሁን በተፈጠረው ድርጊት ያዘንኩ ቢሆንም ከእዚህ በኋላ ለሚኖረው ነገር 90 በመቶ የሚሆነው የአገራችን ህዝብ የየእምነቱ ተከታይ በመሆኑ ፈጣሪን በፀሎት በማሰብ ጥሩ ነገር እንዲመጣልን ነው ምኞቴን የምገልፀው፤ በሞት ላጣናቸውም ፈጣሪ ነፍሳቸውን ይማርም እላለሁ፡፡
ሊግ፡- ጨረስኩ ማለት የምትፈልገው ነገር ካለ?
ታደለ፡- በእግር ኳስ ጨዋታ ዘመኔ በሜዳ ላይ ጥሩ ነገር እንዳለኝ ሁሉ የሚጎሉኝም ነገሮች አሉ፤ ኳስን ዲስፕሊን ሆኜ መጫወቴ በጣም ነው የጠቀመኝ፤ ከብዙ ሰዎች ጋር እንድግባባና ስራዬንም አክብሬ እንድሰራም ነው ያደረገኝና በእዚህ ውስጥ አልፌ እንድጫወት ላደረጉኝ ሁሉ ትልቅ ምስጋናን ማቅረብ ነው የምፈልገው፤ በኳስ ህይወቴ በተለይ ደግሞ እዚህ ደረጃ ላይ እንድጓዝ ዋናው እና የመጀመሪያው ተጠቃሽ ፈጣሪ ነው፤ በመቀጠል ደግሞ ቤተሰቦቼን መግለፅ ለእኔ ከባድ ቢሆንም የእነሱ አስተዋፅኦም ይጠቀሳል፤ ሌላው አባቴን በሞት ያጣሁት በመሆኑ እንደ አባት ሆኖ ብዙ ነገሮችን ያደረገልን ግርማ መንገሻ እና ከእሱ ውጪም ለእኔ የኳስ አርአያዬ የነበረው የቀድሞው እግር ኳስ ተጨዋች ወንድሜ አለማየው መንገሻም /ክሪዝ/ የሚጠቀስ ነውና እሱን እና ከእኔ አጠገብ የነበሩትን በሙሉ ላመሰግናቸው እፈልጋለው፡፡

spot_img
ተመሳሳይ ጽሁፎች

አስተያይት ያስፍሩ

እባክዎን አስተያይትዎን ያስፍሩ
እባክዎን ስምዎን እዚህ ያስገቡ

ትኩስ ዜናዎች

%d bloggers like this:
P