በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ደረጃ ለሙገር ሲሚንቶ፣ ለመከላከያ፣ ለሐዋሳ ከተማ፣ ለወልቂጤ ከተማ እና በብሔራዊ ቡድንም ደረጃ ተጫውቶ ያሳለፈው እና ባለው የኳስ ችሎታም ብዙዎች የሚያደንቁት ፍሬው ሰለሞን /ጣቁሩ/ በአዲሱ የውድድር ዘመን አሁን የተቀላቀለበትን የአሰልጣኝ ገብረ መድህን ሀይሌውን ሲዳማ ቡናን ከጓደኞቹ ጋር በመሆን ለስኬት እንደሚያበቃውና ይህ የስኬታማነት ውጤትም ቡድኑ አሁን ላይ እየተጠናከረ ከመሆኑ አንፃር እስከ ኢንተርናሽናል ተሳትፎ ድረስ በሚያበቃው መልኩም እንደሆነ ከሊግ ስፖርት ጋዜጠኛው መሸሻ ወልዴ /G.BOYS/ ጋር ባደረገው ቆይታ ገልጿል፡፡
የሲዳማ ቡናው አዲስ ፈራሚ ተጨዋች ከሆነው ፍሬው ጋር በተለያዩ ጥያቄዎች ዙሪያ ያደረግነው ቆይታም ይህን ይመስላል፤ ተከታተሉት፡፡
በዝውውር መስኮቱ ወደ ሲዳማ ቡና ስለ ማምራቱ
“ሲዳማ ቡናን በእዚሁ የክረምቱ የተጨዋቾች ዝውውር መስኮት የመጀመሪያ ምርጫዬ በማድረግ ለክለቡ ፊርማዬን ያኖርኩት አንደኛው ነገር ቡድኑ የሚገኝበት ቦታ የእኔ ቤተሰብ ለሚኖርበት ቦታ ሐዋሳ ከተማ በጣም ቅርብ በመሆኑና ሌላው ደግሞ በመከላከያ ቡድን በነበርኩበት ሰዓት አሰልጥኖኝ በነበረውና በጣም በማውቀው አሰልጣኝ ገብረ መድህን ሀይሌ ጋር ዳግም በመገናኘት መሰልጠንን ስለፈለግኩ ነውና ይሄ ሊሳካልኝ ችሏል”፡፡
በወልቂጤ ከተማ ቡድን ውስጥ በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ስለነበረው የውድድር ተሳትፎ
“ከእዚህ ቡድን ጋር የነበረኝ የጨዋታ ዘመን ቆይታዬ ጥሩ ነበር፤ መልካም የሊግ አጀማመርም ነበረን፤ በኋላ ላይና ወደ መጨረሻው አካባቢ ግን ከገንዘብ ችግር ጋር በተያያዘ ደመወዝ ባልተከፈለን ሰዓት ላይ ቡድኑ ውጤትንም እያጣ ሲመጣ እኔ ሁሌም ቢሆን ፊት ለፊት የመናገር ባህሪህ ስላለኝና ለተጨዋቾችም ክፍያ መፈፀም አለበት በሚልም እሳቤዬለመብታችን መቆም አለብን በሚል የከፈልኩት መስዋዕትነት ነገሮችን ስላጎላውና ብዙ ጫናዎችም ወደ እኔ እንዲመጡም ስላደረገ ያ ሊጎዳኝ ችሎ እግድ እንዲጣልብኝ አድርጓል፤ ከእገዳው በኋላም መልሰው ከጠሩኝ በኋላ ክፍያውን ሊፈፅሙልን ስላልቻሉና እኔም ከክለቡ ጋር መቀጠልን ስላልፈለግኩ ወደ አዲሱ ቡድን እንዳመራ አድርጎኛል”፡፡
በእግር ኳስ ተጨዋችነት ዘመኑ ምርጥ ጊዜን ስላሳለፈበት ክለብ
“በሐዋሳ ከተማ ያሳለፍኩት የተጨዋችነት ዘመን ቆይታዬ በውጤት ባይታጀብም ለእኔ ከሁሉም ይበልጣል፤ ይህን ስልም ያለ ምክንያት አይደለም፤ ሐዋሳ ሳለው ኳስን እንደ ቡድን በጥሩ መልኩ ተጫውቼና ተደስቼም ነው ያሳለፍኩት፤ በክለቡ ውስጥ የነበረው የኳስ ፍሰቱ ጥሩ ስለነበርም ነው ምርጡ የኳስ ጊዜዬ ልለውም የቻልኩት፤ ከዛ ቀጥሎ ደግሞ ልጠቅሰው የምፈልገው በጥሎ ማለፍ ደረጃ ሻምፒዮና ሆነንም ነበርና በመከላከያ የነበረኝን ቆይታዬ ነው”፡፡
በእግር ኳስ ጨዋታ ዘመን ጉዞው በምን እንደተደሰተና እንደተከፋ
“በኳስ ጨዋታ ዘመኔ ሁሌም ደስተኛ ነኝ፤ የተከፋሁበትን ጊዜ ምንአልባት የማስታውሰው የቡድኑ አባል ስለነበርኩ መከላከያ ከፕሪምየር ሊጉ በወረደ ሰዓትና ሌላው ደግሞ ለእኔ ብዙ ነገር የነበረው የሙገር ሲሚንቶ እግር ኳስ ቡድን በመፍረሱ ነው”፡፡
የቀድሞ ክለብህ መከላከያ ዳግም የፕሪምየር ሊጉን ስለመቀላቀሉ
“መከላከያ ከነበረበት ሊግ ተመልሶ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉን በመቀላቀሉ በጣም ነው ደስ ያለኝ፤ ይህ ቡድን በታችኛው ቶርናመንት ደረጃ በሚጫወትበት ጊዜም የመጨረሻ ጨዋታዎቹን እኔ በምገኝበት የሐዋሳ ከተማ አርቴፊሻል ሜዳ አካባቢ ያደርግ ነበርና በወቅቱ እረፍት ላይ ስለነበርኩና ጨዋታዎቹንም እመለከት ስለነበር በሚቻለኝ አቅም ከኮቪድ ወረርሽኝ ጋር በተያያዘና የሚጫወቱበት ሜዳም አርቴፊሻል በመሆኑም ይህን ጨምሮ በሌሎችም ጉዳዮች ላይ ከቡድኑ ጎን በመሆን ቡድኑን አግዝ ነበር፤ ከእነዛ መካከልም ለተጨዋቾች በረዶ በማቅረብ እንዲዘፈዘፉበትም ያደርግኩበት ሁኔታም አለና ይሄን በማድረጌ ደስ ይለኛል”፡፡
ከአዲሱ ቡድኑ ጋር ስለጀመሩት የፕሪ-ሲዝን ዝግጅት
“በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ለሚኖረን የመጪው ዘመን ውድድር ሲዳማ ቡናን ከተቀላቅልኩ በኋላ አሁን ላይ በቀን ሁለት ጊዜ እየሰራን ያለነው ልምምድ በጣም ጠንካራና በጥሩ መልኩም ዝግጅታችንን እየሰራንበት ያለ ነው፤ እኔን ጨምሮ ወደዚህ ቡድን የመጡት ሌሎች ተጨዋቾችና ነባሮቹም ይህን ልምምድ በትጋትም በመስራት በአዲሱ ዓመት ራሳቸውን ለማሳየትም እየተዘጋጁበት ነውና በምንሰራው ልምምድ ደስተኞች ነን”፡፡
በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ሲዳማ ቡና በአዲሱ የውድድር ዘመን ምን ውጤትን እንደሚያስመዘግብና እሱም እንደ አንድ ተጨዋች በቡድኑ ውስጥ ስለሚኖረው ቆይታ
“ሲዳማ ቡና በዘንድሮው የውድድር ዘመን ጥሩ ጅማሬ ባይኖረውም በኋላ ላይ የአሰልጣኝ ለውጥ ካደረገ በኋላ ከፍተኛ መሻሻሎችን ያሳየ ቡድን ነው፤ ከእዚሁ መነሻነትም የመጪው ዘመን ቡድኑ ምን መልክ ሊኖረው ይገባል በሚል አሰልጣኙ ገብረ መድህንና የክለቡ ሀላፊዎች በተነጋገሩበት መልኩ ቡድኑ በጠንካራ መልኩ መገንባት አለበት የሚል ውሳኔ ላይ ስለደረሱ አሁን ጥሩ ጥሩ ተጨዋቾችን ወደ ቡድኑ በማስመጣት ጭምር የፕሪ ሲዝን ልምምዱን ጀምሯልና በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ በሚኖረን ቆይታ ቡድኑን በአፍሪካ የክለቦች ውድድር ላይ እስከሚያሳትፈው የኢንተርናሽናል የውድድር መድረክ ላይ ለማቅረብ ነው የምንጫወተው፡፡ በእዚሁ ቡድን ውስጥ በሚኖረኝ ቆይታዬ እኔን በተመለከተ 2014 ላይ ከመቼውም ጊዜ በተሻለ በጥሩ ብቃት ለመቅረብ ዝግጁ ነኝ፤ አሁን ጊዜው የዲ. ኤስ. ቲቪ ነው፤ ከዛ ውጪ ግጥሚያዎቹ የሚደረጉበት ሁኔታም በቶርናመን ደረጃ በተመረጡ ሜዳዎች ላይ በመሆኑም ይሄ ለሁሉም ተጨዋች ይጠቅማልና እኔም በአዲሱ ክለቤ ሲዳማ ቡና መልካም ጊዜን እንደማሳለፍ እርግጠኛ ነኝ”፡፡