Google search engine

“በዝውውሩ በርካታ ክለቦች ጠይቀውኝ የነበረ ቢሆንም ቅ/ጊዮርጊስን ያስቀደምኩት የምወደው ክለብ በመሆኑ ነው” የአብስራ ተስፋዬ /ቅ/ጊዮርጊስ/

በመሸሻ ወልዴ /G.BOYS/

ቅ/ጊዮርጊስ በክረምቱ የተጨዋቾች ዝውውር መስኮት ወጣቱን የደደቢት የአማካይ ስፍራ ተጨዋች የአብስራ ተስፋዬን ወደ ቡድኑ ማስመጣቱ በመሀል ሜዳ ላይ ያለበትን ችግር ይቀርፍለታል ተብሎ በመነገር ላይ ሲሆን ተጨዋቹም ክለቡ የሚጥልበትን አደራ በመወጣት ከጓደኞቹ ጋር ላለፉት ሁለት ዓመታት ከዋንጫ የራቀውን ቡድን ወደ ስኬታማነት እንደሚያመጡም አስተያየቱን ለሊግ ስፖርት ጋዜጣ ሰጥቷል፡፡
ቅ/ጊዮርጊሶች የአብስራ ተስፋዬን የክለባቸው ንብረት ሊያደርጉት የቻሉት በርካታ ቡድኖች የተጨዋቹ ፈላጊ ከሆኑበት ጊዜ አንስቶ እነሱ በቅድሚያ ሊያናግሩት በመቻላቸው ሲሆን የአብስራም ለክለቡ ለመጫወት ከነበረው ከፍተኛ ፍላጎት አንፃርም ወደ ቡድኑ እንደመጣ ተናግሯል፡፡
የአብስራ ወደ አዲሱ ቡድኑ ከመጣ በኋላም ከሊግ ስፖርት ጋዜጣ የተለያዩ ጥያቄዎች ተነስቶለት ምላሹን በሚከተለው መልኩ ሰጥቷል፡፡
ቅ/ጊዮርጊስን በክረምቱ የተጨዋቾች ዝውውር መስኮት በመቀላቀሉ ስለተሰማው ስሜት
“ቅ/ጊዮርጊስን የመጀመሪያና የቅድሚያ ምርጫዬ በማድረግ በክረምቱ የተጨዋቾች ዝውውር መስኮት ስቀላቀል እንደ ተጨዋችነቴ የተሰማኝ የደስታ ስሜት በጣም ከፍተኛ ነው፤ በእዚህ የወጣትነት ዕድሜዬ ይህን የሀገሪቱን ትልቅ ቡድን አገልግል ተብለህና ተፈልገህ ስትጠራ የሚፈጠርብህም ደስታ በአቻነቱ ወደር የማታገኝለትም ነው፤ ከዛ ውጪም የቅ/ጊዮርጊስ ክለብ ጠርቶት እምቢ የሚል ተጨዋችም እስካሁን ያለም ስለማይመስለኝ የእዚሁ አዲሱ ቡድኔ አባልና ተጨዋች ስለሆንኩ ልዩ ስሜትም እንዲሰማኝ አድርጓል”፡፡
ቅ/ጊዮርጊስን በዝውውር መስኮቱ የመጀመሪያ ምርጫው እንዴት እንዳደረገ
“ቅዱስ ጊዮርጊስን የመጀመሪያ ምርጫዬ በማድረግ ፊርማዬን ላኖር የቻልኩት ለቡድኑ ያለኝ ፍቅርና ክብር ላቅ ያለ በመሆኑ ነው፤ በዝውውር መስኮቱ እኔና ለመውሰድ መቐለ 70 እንደርታ፣ ፋሲል ከነማ እና ሲዳማ ቡናን የመሳሰሉት ቡድኖች ጥሪ አቅርበውልኝ ነበር፤ ያም ሆኖ ግን እኔን ለመውሰድ የመጀመሪያ ጥያቄን ያቀረበልኝ ቅዱስ ጊዮርጊስ ስለሆነ እና እኔም ደግሞ መጫወት የምፈልገው ለእዚሁ ታሪካዊና ውጤታማም ቡድን ስለሆነ ክለቡን ለእዛ ነው የቅድሚያ ምርጫዬ ላደርገው የቻልኩት”
ለቅዱስ ጊዮርጊስ ፊርማውን ሲያኖር ስለተደረገለት አቀባበል
“ቅዱስ ጊዮርጊሶች በእውነቱ ከጠበቅኩት በላይ ጥሩ የሆነና ደስ የሚል አቀባበልን ነው ያደረጉልኝ፤ እነሱ ለተጨዋቾች ከፍተኛ ክብር እንዳላቸውም ፊርማዬን ባኖርኩበት ጊዜም ተረድቻለሁና እነሱን እንደምፈልገው አይነት ሆነው ስላገኘኋቸው በእዚህ በጣም ደስ ብሎኛል”፡፡


በቅዱስ ጊዮርጊስ የመጪው ጊዜ ቆይታ ምን አይነት የውድድር ጊዜን እንደሚያሳልፍ
“የቅ/ጊዮርጊስ ክለብ ውስጥ በሚኖረኝ ቆይታ በደደቢት አምናና ካቻምና ከነበረኝ አቋም በጣም በተሻለ መልኩ በመቅረብ በአዲሱ ቡድኔ የተሳካና ምርጥ የሆነን የውድድር ጊዜ እንደማሳልፍ እርግጠኛ ነኝ፤ በእዚሁ ቡድን ተጨዋችነቴ ከክለቡ ጋር ዋንጫን ማንሳትም እፈልጋለው፤ ቅ/ጊዮርጊስ ባለፉት ሁለት ዓመታት ከዋንጫ ርቋል፤ ይሄ ቡድን ድል የለመደ ክለብ ሆኖ አሁን ላይ በእዚህ ደረጃ ላይ መቀመጡም የማይመጥነው ሆኖ ስላገኘሁትና የእኔ ዋናው ህልሜ ደግሞ ከቡድን አጋር ጋደኞቼ ጋር የክለቡን ስምና ዝና መመለስና ወደሚታወቅበትም ውጤታማነት እንዲመጣ ጥሩ ግልጋሎትን መስጠት ነውና በአዲሱ ቡድኔ ጥሩ ነገር እንደሚገጥመኝ በጣም እርግጠኛ ነኝ”፡፡
በቅዱስ ጊዮርጊስ ለመሰለፍ ስለሚኖረው ፉክክር
“ለቅ/ጊዮርጊስ በቋሚነት ተሰልፎ መጫወት ሁሌም ቀላል አይሆንልህም፤ እኔም ይህንን አውቄና አምኜም ነው ወደ ቡድኑ የመጣሁት፤ ያ ስለሆነም የመጪው የውድድር ዘመን ላይ ለአዲሱ ቡድኔ በቋሚነት ተሰልፌ ለመጫወት ከፍተኛ ጥረትን አደርጋለሁ፤ ካለኝ ወቅታዊ የሆነ ጥሩ ብቃቴ አንፃርም በክለቡ ተሰልፎ የመጫወት እድሉ ይኖረኛል ብዬ አስባለሁ”፡፡
የቅ/ጊዮርጊስን የመሀል ሜዳ ችግር ትቀርፋለህ ተብሎ ወደ ቡድኑ ስለመምጣቱ
“ቅዱስ ጊዮርጊሶች በደደቢት የነበረኝን የውል ጊዜ መጠናቀቅን ተንተርሰው እኔን ወደ ቡድናቸው ያስመጡኝ ጠንካራ አጥቂዎችና ተከላካዮች እንዳላቸው ሙሉ ለሙሉ ካመኑ በኋላ የመሃል ሜዳው ላይ ኳስን ከተከላካይ ክፍል በመቀበል አጥቂዎችን ከግብ ጋር የሚያገናኝ የተጨዋች ክፍተት አለብን በሚል ነው ያን ስፍራ እንድሸፍንላቸው በእኔ ላይ እምነትን የጣሉትና ይህንን ፍላጎታቸውን ላሟላላቸው ተዘጋጅቻለው”፡፡


በእግር ኳስ ተጨዋችነት ስላሳለፋቸው ያለፉት ጊዜያቶች
“የእግር ኳስ ተጨዋች ሆኜ ስመጣም ሆነ ወደ ደደቢት ቡድን ካመራሁበት ጊዜ አንስቶ ጥሩም ጥሩ ያልሆኑም ጊዜያቶችን አሳልፍያለው፤ በደደቢት ቆይታዬ ለእኔ ጥሩ የሚባሉት ወቅቶች ለክለቡ ተሰልፌ በተጫወትኩባቸው ጨዋታዎች መልካም የሚባሉ እንቅስቃሴዎችን ማድረጌ ነው፤ በተለይ ዘንድሮ ክለባችን ከፍተኛ የፋይናንስ ችግር ኖሮበት እንኳን ከቡድኑ ጎን ቆሜና እንደራሴም ቆጥሬው ከሊጉ እንዳይወርድ በሜዳ ላይ ያደረግኩት ከፍተኛ ጥረት ዛሬ ላይ እኔን ወደ ታላቁ ቡድን ቅ/ጊዮርጊስ እንዳመራ የጥርጊያውን በር የከፈተልኝም ነበርና ፈፅሞ ይህን አልረሳውም”፡፡
በመጨረሻ…
“ለቅዱስ ጊዮርጊስ ለመጫወት ፊርማዬን ባኖርኩበት የአሁን ሰአት በቅድሚያ እያሰብኩ ያለሁት የቡድናችን ደጋፊዎችም ሆኑ አመራሮች ባለፉት ሁለት አመታት ያጡትን ዋንጫ እንደምናመጣላቸውና እንደምናስደስታቸው ነው፤ እንደ ክለቡ አዲስ ተጨዋችነቴ በእነ የአብስራ ተስፋዬ ጊዜ ይሄ ቡድን ዋንጫን አመጣም የሚል ታሪክን ማስፃፍ ስለምፈልግ ይህን ለማሳካት ጠንክሬ እሰራለሁ”፡፡

spot_img
ተመሳሳይ ጽሁፎች

አስተያይት ያስፍሩ

እባክዎን አስተያይትዎን ያስፍሩ
እባክዎን ስምዎን እዚህ ያስገቡ

ትኩስ ዜናዎች

%d bloggers like this:
P