test
Google search engine

“በጎዶሎም ይሁን በሙሉ ልጅ ቢጫወቱ ቅ/ጊዮርጊስን ማሸነፋችን አይቀርም ነበር”
ታፈሰ ሰለሞን /ኢትዮጵያ ቡና/

#በመሸሻ_ወልዴ

ኢትዮጵያ ቡና በቤትኪንጉ ፕሪምየር ሊግ የደርቢው ጨዋታ በአቡበከር ናስር ሶስት ግቦች ቅ/ጊዮርጊስን ከ2009 በኋላ 3-2 በማሸነፍ ባለድል ሆኗል፤ ኢትዮጵያ ቡና በጨዋታው ከተጋጣሚው ተሽሎ በቀረበበት በእዚህ ጨዋታም ያገኘው ውጤት ግጥሚያውን በአካል ተገኝተውም ሆነ በዲ.ኤስ.ቲቪ የተከታተሉትን የቡድኑን ደጋፊዎች በጣሙን ሊያስደስትም ችሏል፡፡

ኢትዮጵያ ቡና ሸገር ደርቢውን በበላይነት ባጠናቀቀበት ጨዋታ የቅ/ጊዮርጊሱ ግብ ጠባቂ ማታሲ በቀይ ካርድ ከሜዳ የወጣ ሲሆን ቅ/ጊዮርጊሶች ያስቆጠሩትን ሁለት ግቦች ደግሞ የመጀመሪያውን የቡናው የአማካይ ስፍራ ተጨዋች ሬድዋን ናስር ከግብ ጠባቂው ተክለማሪያም ሻንቆ ጋር በእይታ ሳይግባቡ ቀርተው ወደ ኋላ ሲመልስ በራሱ ላይ ያስቆጠረ ሲሆን ሌላኛውን የቡድኑን ግብ ደግሞ ጋዲሳ መብራቴ ሊያስቆጥር በቅቷል፡፡

ኢትዮጵያ ቡና ሸገር ደርቢውን በድል መወጣቱን ተከትሎም አሁን ላይ ከሀድያ ሆሳዕና እና ከፋሲል ከነማ ቡድኖች ጋር በእኩል 13 ነጥብ ላይ በመቀመጥና በግብ ክፍያ ብቻ በመበለጥ በሶስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ሲሆን ቡድኑ ቅ/ጊዮርጊስን  በሸገር ደርቢው ጨዋታ ላይ ካሸነፈ በኋላ በአሁን ሰዓት ቡድኑ በሚያደርጋቸው አብዛኛው ጨዋታዎች ላይ ጥሩ እንቅስቃሴ የሚያሳየውን ታፈሰ ሰለሞንን አናግረነው የሰጠን ምላሽ በሚከተለው መልኩ ቀርቧል፡፡

ሊግ፡- ቅ/ጊዮርጊስን በቤትኪንጉ ፕሪምየር ሊግ የደርቢ ጨዋታ ማሸነፍ ችላችኋል፤ የሁለታችሁ ፉክክር ምን መልክ ነበረው? ግጥሚያውን በማሸነፋችሁስ ምን አይነት ደስታ ተሰማህ?
ታፈሰ፡- ጨዋታው በጣም ከባድ ነበር፤ ተጋጣሚያችንም ትልቅ ቡድን ስለሆነና ሁለታችንም ደግሞ ከአሸናፊነት በመምጣትም የምናደርገው ጨዋታ ስለነበር ከእነሱ በተሻለ ነው እኛ ለግጥሚያው ከፍተኛ ትኩረትን ሰጥተናቸው ወደ ሜዳ በመግባት የተጫወትነው፤ በጨዋታው ላይ ቅዱስ ጊዮርጊሶች ግብ ጠባቂያቸው በቀይ ካርድ ሲወጣባቸው ተነሳስተዋል፤ የእኛም ቡድን ጥሩ ሊንቀሳቀስ ቢችልም በራሳችን ችግሮች ነበር ግብ ሊቆጠርብን የቻለውና በአጠቃላይ የጨዋታ እንቅስቃሴው ግን ጥሩ የነበረው ቡድን ጨዋታውን አሸንፎ ወጥቷል፤ በማሸነፋችንም ከፍተኛ ደስታ ተሰምቶኛል፡፡

ሊግ፡- ቅ/ጊዮርጊስን በሸገር ደርቢው ለማሸነፋችሁ የጨዋታው ልዩነት የነበረው ምንድን ነው? ምንአልባት አንድ ተጨዋች ከእነሱ በቀይ ካርድ ባይወጣስ ኖሮ?
ታፈሰ፡- ለማሸነፋችን ምንም ልዩነት አይኖረውም ነበር፤ እነሱ በሙሉ ልጅ ተጫወቱ አልተጫወቱ የእኛ ቡድን በጥሩ አቋም እና በከፍተኛ የተነሳሽነት ስሜት ላይም ስለነበር ማሸነፋችን አይቀርም ነበር፤ እንደውም በረኛው በቀይ ካርድ ባይወጣ ኖሮ እኛ ከዛ በላይም እንጫወትም ነበር፤  በግጥሚያው ላይ ትልቁ ልዩነት የነበረውና እኛን ለድል ያበቃንም በኳስ ቁጥጥር ላይ ያተኮረን እንቅስቃሴ ልክ ከፋሲል ከነማ ጋር ስንጫወት ከእኛ ቡድን አንድ ተጨዋች /ተመስገን ካስትሮ/ በቀይ ካርድ ወጥቶብን እንደተጫወትነው በመንቀሳቀሳችንም ነው ቅ/ጊዮርጊሶችን በጨዋታ ጭምር በልጠን ልናሸንፋቸው የቻልነውም፡፡

ሊግ፡- በቅ/ጊዮርጊስ ላይ የመሪነቱን ግብ ካስቆጠራችሁ በኋላ ራሳችሁ ላይ በሬድዋን ናስር አማካኝነት ባስቆጠራችሁት ግብ አቻ ለመሆን ችላችሁ ነበር፤ያኔ ምን አይነት ስሜትበውስጣችሁ ተፈጠረባችሁ?
ታፈሰ፡- እንደ እውነት ለመናገር መጀመሪያ ላይ ትንሽ ተደናግጠን ነበር፤ ግጥሚያውን ለማሸነፍ እንደምንችል ግን በጣም እርግጠኛ ነበርኩ፤ እንደውም በጥሩ የግብ ልዩነት ማሸነፍ የምንችልበት እድሉም ነበረን፡፡

ሊግ፡- ኢትዮጵያ ቡና ቅ/ጊዮርጊስን ለማሸነፍ የቻለው የመጨረሻ ደቂቃዎች አካባቢ ባስቆጠረው ግብ ነው? እዛ ሰዓት ድረስ እንሄዳለን ብለህስ ጠብቀህ ነበር?
ታፈሰ፡- ይሄ ኳስ ጨዋታ ነው፤ በየቱ ደቂቃ ላይ ጎል አስቆጥረህ ግጥሚያህን እንደምታሸንፍ አታውቀውም፤ በእዚህ መልኩ መጓዝም የኳሱ አንዱ አካል ስለሆነ ይሄ ያጋጥማል፡፡

ሊግ፡- ኢትዮጵያ ቡና በቤትኪንጉ የፕሪምየር ሊግ ተሳትፎው ያለው ጠንካራ ጎን ምንድን ነው?
ታፈሰ፡- ዋንኛው ጥንካሬያችን በእኛ እና እስከ ኮቺንግ ስታፉ ድረስ መካከል ያለን ህብረት ጥሩ መሆኑና እንደ ቡድን መጫወታችንም ነው፤ ይሄ ቡድን ከአምናው በጣም ተሻሽሎም መጥቷል፤ በኮቪድ ወደ አገራችን መግባት ምክንያት ከካምፕ ሳንወጣም ነው ልምምዳችንን የምንሰራው፤ በካምፕ ውስጥም የተለየ ፍቅርም ነው ያለንና ይሄ ቡድን ዘንድሮ ለየት ብሎም ቀርቧል፡፡

ሊግ፡- ኢትዮጵያ ቡና በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ የት ድረስ ይጓዛል?
ታፈሰ፡- አሁን ላይ ያለን ህብረት፣ አካሄድና ጅማሬያችን በጣም ጥሩ ነው፤ የኳስ አያያዛችንና ጎል ጋር የምንደርስበት መንገድም የተዋጣለት ነው፤ ሁሉም ተጨዋች አግቢም ስለሆነ ዘንድሮም እንደሌላው ጊዜ ሁሉ ለሻምፒዮናነት ነው የምንጫወተው፡፡

ሊግ፡- ቅ/ጊዮርጊስን ማሸነፍ የተለየ እና ልዩ የደስታ ስሜትን ይሰጣል?
ታፈሰ፡- እንደ እኔ ማንኛውንም ጨዋታዎች በእኩል ሁኔታ የምመለከት ስለሆንኩ እነዛን ግጥሚያዎች  ስናሸነፍ ደስ ይለኛል፤ ሸገር ደርቢ ሲሆን ደግሞ ተጋጣሚያችን ትልቅ ቡድን ከመሆኑ አንፃርና ከግጥሚው በኋላ ደግሞ ከሁለቱም ቡድን ደጋፊዎች የሚጠበቅ ነገር ስላለ እነሱን ማሸነፍ የበለጠ ያስደስታል፡፡

ሊግ፡- ቅዱስ ጊዮርጊስን በጨዋታው በምን መልኩ አገኘኀቸው?
ታፈሰ፡- እነሱ ግብ ጠባቂያቸው ማታሲ በቀይ ካርድ ወጥቶባቸው በጎዶሎ ልጅ የተጫወቱ ቢሆኑም ኳስ ለመጫወት ይሞክሩ ነበርና እንደ እኔ ምልከታ ምንም እንኳን እኛ የኳስ ብልጫን ብንወስድባቸውም ከእዚህ ቀደም ቡድናቸው  አኳያ ጥሩ ነበሩ፤ ባለፈው የወዳጅነት ጨዋታም ላይ እኛን ሲያሸንፉን አይቻቸውም ነበር፤ እኛ ኳስን ስንይዝባቸው እነሱ ግን ወደጎላችን ይደርሱ ነበር፤ የአሁኑም ጨዋታ ላይ ኳስን አደራጅተው ለመውጣትና ለመጫወትም ይሞክሩ ስለነበሩ ጥሩ ሆነው አግኝቻቸዋለው፡፡

ሊግ፡-  ኢትዮጵያ ቡናን እንደ ቡድን በምን መልኩ አገኘኸው? ቅ/ጊዮርጊስ ላይ ሀትሪክ የሰራውን አቡበከርንስ?
ታፈሰ፡- አቡበከርን በአሁን ሰዓት በመመልከት ላይ ያለሁት በጣም ምርጥ ተጨዋች እና ከሊጉ በላይም እንደሆነ አድርጌ ነው፤ በባህር ማዶ ኳስ እኔ የአርሰናል ደጋፊ ነኝ፤ በዛ ሊግ ደረጃ ለማጋነነ ሳይሆን እድሉን ቢያገኝ ፊት አድርጎም መጫወትን ይችላል፤ ለእሱ ቃላት የለኝም፤ በጣም የማደንቀው ተጨዋች ነው፤ ከእዚህ በፊት በሌላ ክለብ ውስጥ እያለው እንዲህ ያለ ተጨዋች አይመስለኝም ነበር፤ ዘንድሮ ግን በአጥቂ ስፍራ ላይ የእሱ የቦታ አጠባበቅ /ፖዚሽኑ/ ተመቻቸልህም አልተመቻቸልህም ኳስን እንድትሰጠው ያስገድድሃል ከቅ/ጊዮርጊስ ጋር በነበረን ጨዋታም የመጀመሪያዋን ግብ ሲያስቆጥር እንድሰጠው ስላስገደደኝም ነው ጎል ያስቆጠረውና እሱ ልዩ ተጨዋች ነው፤ የእሱ ጥሩ መሆንም ነው ግቦችን እንድናስቆጥር እያደረገን የሚገኘው፤ ቡድናችንን በተመለከተ ቡና ጠንካራ ቡድን ነው፤ በእንቅስቃሴም ሆነ በስብስቡም በጥሩ አቋም ላይ ነው የሚገኘው፡፡

ሊግ፡- ለኢትዮጵያ ቡና አንተስ ምን አይነት ግልጋሎትን ለቡድንህ ለመስጠት ቆርጠህ ተነስተሃል?
ታፈሰ፡- በኢትዮጵያ ቡና ውስጥ ባለኝ የተጨዋችነት ቆይታ ክለቡን ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ለማገልገል ቆርጬ ተነስቻለው፤ ባለፈው ጊዜ ግን እኔ አስቤው ሳይሆን ባላሰብኩት ሁኔታ ባሳየሁትና ነገሮችም ወደሌላ አቅጣጫ በሄዱበት ሁኔታ የቪ ምልክትን በማሳየቴ ብዙ ክርክሮች ተነስተውብኝ የነበረ ቢሆንም እኔ ግን ቡናን የምወድ ተጨዋች እና የተሻለ ነገርንም አግኝቼ ወደ ቡድኑ የመጣሁበት ሁኔታ ስለነበር ከእዚህ ቡድን ደጋፊዎች ጋር ሻምፒዮና የምሆንበትንና አብሬም የምጨፍርበትን ሁኔታ ነው በመጠባበቅ ላይ የምገኘው፡፡

ሊግ፡- ከድሬዳዋ ከተማ ጋር በነበረው ጨዋታ የፍፁም ቅጣት ምት አግኝተህ ስተህ ነበር…ያን ግብ ያኔ ብታስቆጥር ኖሮ ባለፈው የቪ ምልክት ከማሳየትህ ከተፈጠረው ነገር ጋር አያይዘህ ለይቅርታ ወደ ደጋፊዎቹ ልትሄድ ነበር….
ታፈሰ፡- በፍፁም፤ እንደዛ የማስብ አይነት ተጨዋችም አይደለውም፤ ፍፁም ቅጣት ምቱን የሳትኩት ጎል የማግባት ጉጉት ስለነበረብኝ፤ ነው አቡበከርም በቅ/ጊዮርጊሱ ጨዋታ ጉጉት ኖሮት የፍፁም ቅጣት ምትን ስቷል፡፡

ሊግ፡- የኢትዮጵያ ቡና አጨዋወት ተመችቶሃል፤ አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌንስ በምን መልኩ ትመለከተዋለህ?
ታፈሰ፡- የቡና አጨዋወትማ በጣም ስለሚመችም ነው ቡድኑን አምና የተቀላቀልኩት፤ አሰልጣኙን ካሳዬን በሚመለከት ደግሞ በኳስ ህይወቴ ብዙ አሰልጣኞችን አይቻለው፤ እሱ ግን ቤተሰብ ጭምር ነው፤ ብዙ ነገርን ጠርቶህ የሚያማክርና ነገሮችን ከብዙ አንግል የሚያይም ነው፤ እንደ ወንድምና አባትም ነው፤ በተለይ ደግሞ ከእኔ ጋር ትልቁ የመለወጤ ሚስጥር በኳሱም በህይወትም እሱ ነው ፤ ለብቻው ከልምምድ ውጪ ሁሉ ቀጥሮም ይመክረኛል፤ ለእሱ ትልቅ ክብር አለኝ አመሰግነዋለው፡፡

ሊግ፡- በማንኛውም ግጥሚያ የእግር ኳስን ስትጫወት አቅልለህ ነው፤ የተቃራኒ ቡድን ተጨዋቾችም አያስፈሩህም፤ ብዙ ኳሶችም አይበላሽብህም፤ ሚስጥሩ ምንድን ነው?
ታፈሰ፡- ኳሱን አቅልዬ በፈለግኩበት መልኩ የምጫወተው ፈፅሞ ስለማልጨነቅ ነው፤ አንድ አንድ ተጨዋቾች ወደ ትላልቅ ግጥሚያ ላይ ሲገቡ ለጨዋታው ከሚሰጡት ግምት አኳያ ይጨናቃሉና እኔ ጋር ስትመጣ ይሄ ችግር ከበፊት አንስቶ እኔ ጋር የለም፤ ኳሱን ስለምችል፣ በራሴ ስለምተማመንና ኳስ ላይም መሰረት አድርጌ እና ተረጋግቼም ስለምጫወት ነው ጥሩ ለመጫወት የቻልኩት፡፡

ሊግ፡- እንደ ዊሊያም እና ሬድዋንን የመሳሰሉ ወጣት ተጨዋቾች ጥሩ እንቅስቃሴን እያሳዩ ይገኛል፤ እንዴት ተመለከትካቸው?
ታፈሰ፡- ዊሊያም ብዙ ነገሩ ጥሩ ነው፤ ሲጫወት ደስ ይላል፤ ገና ልጅም ነው፤ ዘንድሮም ነው የመጣው፤ ቡድናችን ጥሩ ስለሆነም ነው እሱ ብቻ ሳይሆን ሁላችንም ጥሩ እየሆንን ያለነው፤ ሌሎችም ብዙ ወጣቶች አሉ እነ ሬድዋንና አዲስንም የመሳሰሉ ተጨዋቾች፤ ይሄ ሁሉ የሆነው አሰልጣኙ ካሳዬ ስለሆነ ነው፤ ካሳዬ በኳስ ነው የሚያምነው፤ ለእዛም ነው ለተጨዋቾቹ እድልን እየሰጠ የሚገኘው፡፡

ሊግ፡- በመጨረሻ…?
ታፈሰ፡-  ኢትዮጵያ ቡና ዘንድሮ እስከ ሻምፒዮናነት ነው የሚጓዘው፤ ቡድናችንን እና እኔን በተመለከተ በእዚህ ቡድን ቆይታዬ በቅርቡ ለተፈጠረው ነገር አሁንም በድጋሚ ክለቡንና ደጋፊዎቹን ይቅርታ እጠይቃለው፤ ደጋፊውም እኔን ቶሎ ተረድቶኝ ይቅርታዬን ስለተቀበለኝም አመሰግናቸዋለው፤ ቡና በውጤት ደረጃ አይደለም በደጋፊው አሁን ላይ እንደሚጫወተው ያለ ደጋፊውም ከእዚህ በላይ ብዙ የሚጓዝ ቡድንም ነው

https://t.me/Leaguesport

spot_img
ተመሳሳይ ጽሁፎች

አስተያይት ያስፍሩ

እባክዎን አስተያይትዎን ያስፍሩ
እባክዎን ስምዎን እዚህ ያስገቡ

ትኩስ ዜናዎች

P