በመሸሻ ወልዴ /G.boys/
የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግን ዘንድሮ ለተቀላቀለው የባህር ዳር ከነማ እግር ኳስ ክለብ በአጥቂ ስፍራ እየተጫወተ የሚገኘው ወሰኑ ዓሊ ቡድናቸው በእዚህ ዓመት የሊግ ውድድር ጥሩ ተፎካካሪ በመሆን ከ1-4ኛ ባለው ደረጃ እንደሚፈፅም አስተያየቱን ለሊግ ስፖርት ጋዜጣ ሰጥቷል፤ የኢትዮጵያ መድን የቀድሞው ተጨዋች የእግር ኳስን መጫወት የጀመረው በልጅነት ዕድሜው ቃሊቲ በሚገኘው የሰፈራቸው ሜዳ ላይ ሲሆን ያኔ የጋራዥ ስራውን ትቶና የቤተሰቦቹንም ኳስ አትጫወት ጥያቄ ባለመቀበል እና ጥያቄያቸውንም ወደ ኋላ በማለት ነው የኳስ ስሜቱ አሸንፎት ትልቅ ደረጃ ለመድረስ እየተጫወተ የሚገኘው፤ የባህር ዳር ከነማ እና ይሄን የቀድሞ የመድን ተጨዋች በተለያዩ ጥያቄዎች ዙሪያ ያናግረነው ሲሆን ምላሹንም እንደሚከተለው ሰጥቷል፤ ተከታተሉት፡፡
ሊግ፡- በአሰልጣኝ አስራት ኃይሌ የመድን ቡድን ውስጥ ጥሩ ብቃታቸውን ከሚያሳዩ ተጨዋቾች መካከል አንዱ አንተ ነበርክ፤ ከዛ ጠፋህ፤ ስለስምክም ብዙ አይነሳም፤ አሁን ደግሞ ዳግም የተወለድክ አይነትን እንቅስቃሴ ማሳየት ጀምረሃልና በእነዚህ ጉዳዮች ዙሪያ ምን የምትለው ነገር አለ?
ወሰኑ፡- አዎን፤ የእውነት ነው የመድን ክለብ ውስጥ በነበረኝ የተጨዋችነት ዘመን ቆይታዬ ለክለቡ ጥሩ እንቅስቃሴን ከማሳየት በተጨማሪ ቡድኑንም ለውጤት ከጓደኞቼ ጋር አበቃው ነበር፤ ያም ሆኖ ግን ከጊዜያቶች በኋላ በእኔ ላይ የደረሰብኝ ጉዳት በብቃቴ እንዳልቀጥልና ስለእኔም ብዙ እንዳይወራ ስላደረገኝ ጉዳት ነው እኔን አጥፍቶኝ የነበረው፤ ያም ሆኖ ግን አሁን ላይ የባህር ዳር ከነማ ክለብን ከተቀላቀልኩበት ያለፉት ሁለት አመታት ጊዜ አንስቶ ከጨዋታ ወደ ጨዋታ ጠንክሬ በመስራቴና ራሴንም እያሻሻልኩ ስለተጓዝኩ ወደራሴው የቀድሞ አቋም በአዲስ መልክ ልመለስ ችያለሁ፤ ለእዚህ ላበቃኝ አምላኬም ታላቅ ምስጋናዬን ማቅረብም እፈልጋለሁ፡፡
ሊግ፡- በመድን ክለብ ውስጥ የነበረህን የጨዋታ ብቃት ወደኋላ መለስ ብለህ ስታስታውስ በአቋምህ ብዙ አለመጓዝህ እና ለከፍተኛም እውቅና አለመብቃትህ አይቆጭህም?
ወሰኑ፡- በጣም ነው እንጂ የሚቆጨኝ፤ ያኔ በነበረኝ ብቃት ወደተሻሉ እና ወደ ትልልቅ ክለቦች የመሄድ እድሉ ነበረኝ፤ ሆኖም ግን ምን ታደርገዋለህ ጉዳቱ ነው ብዙ እንዳልጓዝ ያስቀረኝ፡፡
ሊግ፡- ኢትዮጵያ መድን የቀድሞ ቡድንህ ነው፤ በአንተ አንደበት እንዴት ይገለፃል?
ወሰኑ፡- መድን ልጅ ሆኜ ኳስን በሰፈር ደረጃ ስጫወት የደገፍኩት ቡድን ነው፤ ያኔ የእነሱን እንቅስቃሴም በመመልከት ነው አድናቂያቸው ልሆን የቻልኩት፤ ሳድግ ደግሞ የቡድኑም ተጨዋች ሆንኩና ስለዚህ ክለብ ማለት የምፈልገው ለእኔ የዛሬ ደረጃ ላይ መድረስ በጣም ባለውለተኛዬም የሆነ ቡድን ነውና ከምነግርህ በላይ ቡድኑን መቼም ቢሆን የማልረሳው ነው፡፡
ሊግ፡- የመድን ክለብን ልጅ ሆነህ ስትደግፍ ከተጨዋቾች ማንን ነበር የምታደንቀው?
ወሰኑ፡- ያኔ መድኖች ልምምድ ይሰሩ የነበሩት በሰፈራችን በሚገኘው የቃሊቲው ካምፕ ሜዳቸው ላይ ስለነበር በጊዜው ከተመለከትኳቸው ተጨዋቾች መካከል በቀዳሚ ደረጃ ያደነቅኩት ሀሰን በሽርን ነው፤ እሱ አሁን ላይ የእኔ ሞዴሌም ተጨዋች ነው፤ ችሎታው ይለያል፤ እኔን የቡድን የታዳጊ ቡድን ውስጥም አሰልጥኖኝ አልፏል፤ ሲያሰለጥነኝም ወደፊት የተሻለ ደረጃ ላይ እንድደርስ የወንድሙን ያህል ብዙ ነገሮችን ይመክረኝም ነበርና እሱን ፈፅሞ የማልረሳው ነው፡፡
ሊግ፡- የባህር ዳር ከነማ ክለብ ውስጥ በሊጉ እየተጫወትክ ትገኛለህ፤ ዘንድሮ ከአንተ ምን ይጠበቅ?
ወሰኑ፡- የባህር ዳር ከነማ ክለብ ውስጥ አሁን ሶስተኛ አመቴን ይዣለሁ፤ በከፍተኛ ሊጉ ውድድር ከአመት ወደ አመት ስጓዝ ራሴ ላይ ከፍተኛ መሻሻሎችን አሳይቻለሁ፤ አሁን የምጫወትበት ሊግ ደግሞ ፕሪምየር ሊግ ስለሆነ ከእኔ ብዙ ነገር ይጠበቃል፡፡ ስለሆነም የቡድኑ ቆይታዬ ላይ ዘንድሮ ቡድኔን ለጥሩ ውጤት ከማብቃት ባሻገር ኮከብ ግብ አግቢ የመሆንም እቅዱ አለኝና ራሴን ለእነዚህ ስኬቶች ለማብቃት አዘጋጅቻለሁ፡፡
ሊግ፡- የኢትዮጵያን ፕሪምየር ሊግ ስትቀላቀሉ በውስጥህ ምን አይነት ስሜት ነበር ያደረብህ? ማለፋችሁስ ተገቢ ነበር?
ወሰኑ፡- አዎን፤ እኛ ባህር ዳሮች ከነበረን እቅድና ህልም አንፃር የእዚህ አመቱን የፕሪምየር ሊግ ውድድር እንደምንቀላቀል እናውቅና እርግጠኛም ነበርን፤ ለዛም ነው ቀሪ ጨዋታዎች እየቀሩን ማለፋችንን ያረጋገጥነው፤ ያኔ የማለፋችን ህልምም ሲሳካ የነበረኝ የደስታ መጠን ተነግሮ የማያበቃ ነው፤ እንደዛ አይነት ደስታን ተመልክቼም አላውቅምና ድሉ የሚገባን ሆኖ ነው ያገኘሁት፡፡
ሊግ፡- የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመክፈቻ ጨዋታ ላይ ቅዱስ ጊዮርጊስን 1ለ0 ድል ስታደርጉ አንተ የአሸናፊነቷን ግብ አስቆጥረሃል፤ ስለጨዋታው እና ስለድሉ ምን አለክ? ግቡን ስለማስቆጠርህስ?
ወሰኑ፡- ከቅዱስ ጊዮርጊሶች ጋር የነበረን ጨዋታ ከሜዳችን ውጪ እንደመጫወታችንና ከክለቡም ትልቅነት አንፃር እኛ ወደ አዲስ አበባ የመጣነው ነጥብ ተጋርተን ለመሄድ ቢሆንም ያን እለት ፈፅሞ ባልጠብቀነው መልኩ በጨዋታው ፍላጎት ከእነሱ ተሽለን እና ጥሩም ሆነን በመቅረባችን ግጥሚያውን ልናሸንፍ እና በድሉም በጣም ልንደሰት ችለናል፡፡ ከቅ/ጊዮርጊስ ላይ ያገኘው ሶስት ነጥብ ወርቃማ የሚባል ነው፤ በእዛም ጨዋታ ቡድናችን አሸናፊ ሲሆን የድሉን ግብ ያስቆጠርኩትም እኔ ስለሆንኩ ተደራራቢ የደስታ ስሜትም ነው ተሰምቶኝ የነበረው፤ ከእዛ ውጪም ግቧ ለቀጣይ ጊዜ ግጥሚያዎቻችን ትልቅ የሞራል ስንቅም ሆናልኛለች፤ ከሐዋሳ እና ከሲዳማ ቡና ጋር ባደረግናቸው ጨዋታዎች ምንም እንኳን ጎል አላስቆጠር እንጂ በተደጋጋሚ ጊዜ የግብ ሙከራን እንዳደርግም የጥርጊያ በር የከፈተልኝ ስለሆነ በወደፊት ግጥሚያዎች ላይ በርካታ ግቦች እንደሚኖረኝ ነው ምልክትን ሰጥቶኝ ሊያልፍ የቻለው፡፡
ሊግ፡- የባህር ዳር ከነማ ጠንካራ ጎን በአንተ እይታ ምንድነው? ማሻሻል ያለበትስ?
ወሰኑ፡- የሊጉ የውድድር ጅማሬያችን ላይ ቡድናችንን እንደተመለከትኩት ያለን ጠንካራ ጎን ሁሉም የቡድናችን ተጨዋቾች ዲሲፕሊን ያላቸው ከመሆኑ ባሻገር የምንከባበርና አንድነት ያለን መሆኑም ነው ይሄ ያበረታታናል፤ ማሻሻል ያለብን ብዬ የማስበው ደግሞ ኳስን ስንጫወት ዝም ብለና እና ሳናወራ ነው፤ በእግር ኳስ ደግሞ አንተ እንዲህ አድርግ አንተም እንዲህ ሁን እያልክ መነጋገር ይኖርብሃልና ይሄ ሊሻሻል ይገባዋል፡፡
ሊግ፡- የባህር ዳር ከነማ ክለብ ውስጥ ካለህ የጨዋታ ሚና ራሴን ማሻሻል አለብኝ የምትለው ምን ላይ ነው?
ወሰኑ፡- ብዙ ጊዜ ኳስን ወደ መስመር ይዤ ብወጣም የመሃል ተጨዋቾቻችን ማገዙ ላይ እምብዛም ነኝና ይሄን ብቃቴን ማሻሻል እፈልጋለሁ፤ ለዚህም በግሌ ጭምር ጠንክሬም እየሰራሁ ነው፡፡
ሊግ፡- የኢትዮጵያ እግር ኳስ ውስጥ በጣም የተደሰትክበትና የተከፋህበት አጋጣሚ?
ወሰኑ፡- የተጨዋችነት ዘመኔ ላይ ምርጡ የደስታዬ ጊዜ ብዬ የማስበው ክለባችን ኢትዮጵያ መድን በአሰልጣኝ አስራት ኃይሌ በሚመራበት ዘመን ኒያላን አሸንፎ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ሲገባ እና ባህር ዳር ከነማም ሊጉን ዘንድሮ ሲቀላቀል ነው፤ ያዘንኩት እና የተከፋሁበት አጋጣሚ ደግሞ መድን ከሊጉ ሲወርድ ነው፤ ያኔ የማልረሳው ከፍተኛ የሀዘን ስሜት ነው የተሰማኝ፡፡
ሊግ፡- የኢትዮጵያ እግር ኳስ ውስጥ የአንተ ምርጡ አሰልጣኝ እና ተጨዋች እነማን ናቸው?
ወሰኑ፡- በእግር ኳስ ህይወቴ ቀዳሚውን ቦታ በመስጠት ለእኔ ምርጡ አሰልጣኝ ብዬ ስሙን የማነሳው አሰልጣኝ አስራት ኃይሌን ነው፤ እሱ ከሁሉም ይለያል፤ ጥሩ አባትና እውነተኛም ሰው ነው፤ ከእዛ ባሻገር የዋህም ነው፤ ሲቆጣህ ፊት ለፊት ነው፤ ጥፋትህን እዛው ይነግርሃል፤ ብዙ ጊዜ ሲቆጣም ለክፋት አይደለም፤ አንተ እንድትሻሻልና በሁሉም ነገር እንድትለወጥም ስለሚፈልግ ነው፤ እሱ ለእኔ እዚህ ደረጃ ላይ መድረስም ብዙ ነገር አድርጎልኛልና ምርጤ የምለው ባለሙያ ነው፤ በተጨዋቾች ደረጃ ደግሞ የእኔ ምርጡ ተጨዋች በመሀል ሜዳ ብቃቱ ሁሌም የሚደነቀው ሙሉአለም ረጋሳ ነው፤ ኳስን የሚያቀብልበት መንገድ ይገርማል፤ እሱ ከስኬታማ ተጨዋችነቱ በዘለለ አራትና አምስት አይን ያለውም ተጨዋች ነው፡፡
ሊግ፡- የባህር ዳር ከነማ ክለብ ተስማምቶሀል? ደጋፊዎቹ በአንተ አንደበት ሲገለፁ?
ወሰኑ፡- የባህር ዳር ከነማ ክለብም ሆነ ከተማዋ ለእኔ በጣም የተስማሙኝ ሆነው ነው ያገኘኋቸው፤ ባህር ዳር ልዩ ሀገርም ሆናብኛለች፤ ደጋፊዎቹን በተመለከተ በጣም ፍቅር ናቸው፤ ሲደግፉን ያምራሉ፤ አሁን ላይ ለእኔ ችሎታም መሻሻል ብርታት እየሆኑልኝ ስለመጡ እነሱን በዚሁ አጋጣሚ አመሰግናቸዋለሁ፡፡
ሊግ፡- የኢትዮጵያ ቡና ጋር የቀጣይ ሳምንት ላይ ጨዋታ ታደርጋለችሁ፤ ከወዲሁ ስለግጥሚያው ምን እያሰብክ ነው?
ወሰኑ፡- ከኢትዮጵያ ቡና ጋር በመጪው ሳምንት የምናደርገው ጨዋታ በጣም ጥሩና ጠንካራም ነው የሚሆነው፤ ግጥሚያውንም ከወዲሁ በጉጉት እየጠብቀነው ነው የምንገኘውና ከጨዋታው 3 ነጥብን ከሜዳ ይዘን ለመውጣት ተዘጋጅተናል፡፡
ሊግ፡- በመጨረሻ….
ወሰኑ፡- የኢትዮጵያ እግር ኳስ ውስጥ በተጨዋችነት አሁን ለደረስኩበት ደረጃ እኔን በመምከርም ሆነ በማሰልጠን ከፍተኛ አስተዋፅኦ ላበረከቱልኝ በቅድሚያ ፈጣሪዬን እና ቤተሰቦቼን በመቀጠል ደግሞ አሰልጣኝ አስራት ኃይሌን፤ አሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸውን /ማንጎ/ አሰልጣኝ ሀሰን በሽር፣ አሰልጣኝ አባይነህ እና አሰልጣኝ ፀጋዬ ወንድሙን እና የባህርዳር ከነማ ክለብ አመራሮችና ደጋፊውን ማመስገን እፈልጋለው፡፡