በመሸሻ ወልዴ (ጂ.ቦይስ)
የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ተወዳዳሪው
አዳማ ከተማ የአገራችን የተጨዋቾች
ዝውውር መስኮት ተጧጡፎ በቀጠለበት
የአሁን ሰዓት ላይ የተከላካይ አማካይ ስፍራ
ተጨዋች የሆነውን ዮናስ በርታን ከደቡብ
ፖሊስ ክለብ አስፈርሟል፤ አዲሱ የአዳማ
ከተማ ተጨዋችም የዘንድሮ ውድድር
ሲጀመር በሚኖረውየቡድኑ ቆይታ የተሳካና
ጥሩ ጊዜያትንም እንደሚያሳልፍ ለዝግጅት
ክፍላችን ሀሳቡን ገልጿል፡፡
የአዳማ ከተማ ክለብን በዝውውር መስኮቱ
የተቀላቀለውን ይህን ተጨዋች በተለያዩ
ጥያቄዎች ዙሪያ ያወራነው ሲሆን ምላሹንም
በሚከተለው መልኩ ሰጥቷል፡፡
ሊግ፡- ለአዳማ ከተማ ለመጫወት
ፊርማህን አኑረሃል፤ ክለቡን እንዴት ነው
ለመቀላቀል የቻልከው? ምን ውጤትንስ
ከቡድኑ ትጠብቃለህ?
ዮናስ፡- የአዳማ ከተማ እግር ኳስ ክለብን
ልቀላቀል የቻልኩት በደቡብ ፖሊስ ውስጥ
የነበረኝ የውል ጊዜ መጠናቀቁን ተከትሎ
በቡድኑ ልፈለግ በመቻሌ ነው፤ ያኔም
ጥያቄው ሲቀርብልኝ ከድሬዳዋ ከተማ፣
ከጅማ አባጅፋርና ከወልቂጤ ከተማም
ክለቦች የተጫወትልን ጥያቄዎች መጥቶልኝ
የነበረ ቢሆንም በተለያዩ ነገሮች ልስማማ
ስላልቻልኩና አዳማም እኔ ለምኖርበት የአዲስ
አበባ ከተማ በጣም ቅርብ በመሆኑ ክለቡን
ምርጫዬ አድርጌዋለሁ፡፡
አዳማ ከተማ ዘንድሮ ስለሚያመጣው
ውጤት ክለቡ በሊጉ ጥሩ ልምድ ያለውና
ጥሩ የተጨዋቾች ስብስብንም የያዘ ነው፤ ከዛ
ውጪም አሰልጣኙ በሙያው የረጅም ጊዜ
የተካበተ ልምድ ያለው ስለሆነ በእዚህ ዓመት
ጠንካራ የውድድሩ ተፎካካሪ ከመሆን ባሻገር
ዋንጫውን ለማንሳትም አቅም ያለው ቡድን
ነውና ይሄን ለማሳካት ጠንክረን እንሰራለን፡፡
ሊግ፡- ለአዳማ ከተማ አዲስ ተጨዋች
ከመሆንህ አኳያ በዘንድሮው የውድድር ዘመን
የተሳካ ጊዜያትን ታሳልፋለህ?
ዮናስ፡- አዎን፤ ከፈጣሪ እርዳታ ጋር ብዬ
አስባለሁ፡፡
ሊግ፡- ወደ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ
ገብተህ መጫወት ከጀመርክበት ሰዓት አንስቶ
ያለህን ችሎታና ብቃት በምን ደረጃ ላይ
ታስቀምጠዋለህ?
ዮናስ፡- በፕሪምየር ሊግ ደረጃ መጫወት
የጀመርኩት በቅርብ ነው፤ ደቡብ ፖሊስ
ክለብ ውስጥም ነው ገብቼ የተጫወትኩት፤
በዚህን ጊዜ ራሴን የተመለከትኩትም ገና
ብዙ የሚቀረኝ ወጣት ተጨዋች እንደሆንኩም
ያህል ነው፤ ኳስን በአግባቡና በምፈልገው
አይነት መልኩም እየተጫወትኩ አይደለሁም፤
ብዙ መስራት ይጠበቅብኛል፤ አሁን ላይ
ትኩረት እያደረግኩ ያለሁትም ያለኝን ብቃት
ከጊዜ ወደ ጊዜ በማሻሻል ሃገሬን መጥቀም
በምችልበት ደረጃ ላይ መጫወት መቻልን
ነውና ያንን እድል ጠንክሬ በመስራት
ማግኘትን እፈልጋለሁኝ፡፡
ሊግ፡- በእግር ኳስ ተጨዋችነቱ
ከልጅነትህ እድሜ አንስቶ ተጫውተህ
ያሳለፍክባቸው ክለቦች የትኞቹ ናቸው?
እንዴትስ ትገልፃቸዋለህ?
ዮናስ፡- የእግር ኳስን ልጅ ሆኜ
በመጀመሪያ የተጫወትኩበት ክለብ ፓሪስ
የሚባል የቸርች ቡድን ነው፤ በኤፍሬምና
በጥሩሰው አማካኝነትም ይመራና ይሰለጥን
የነበረ ቡድን ነው፤ ከዛም አክረም የሚባል
ኳስ ወዳድ ላቋቋመውና ብዙ መስዋዕትነትንም
ለከፈለበት የራሱ ቡድን ለሆነው አክረምና
ልጆቹ አመራሁና እዛ ሄጄ ተጫወትኩ፤
ይሄ ቡድን ብዙ ልጆችን ያፈራና ጥሩም
ይጫወት የነበረ ነውና የሁለቱን የአካባቢዬቼን
የልጅነት ቡድኖቼን መቼም ቢሆን የምረሳቸው
አይደለሁም፤የክለብ ደረጃ ላይ ሆኜ ደግሞ
በቅድሚያ የተጫወትኩት ለኢትዮጵያ
ንግድ ባንክ ዋናው ቡድን ከታዳጊው በአንድ
ዓመት ውስጥ የማደግ እድሉን ባገኝም
የተጫወትኩት ለተስፋው ቡድን ነው፤ ከዛም
ለለገጣፎ ለገዳዲ፣ ለባህር ዳር ከተማ እና
ለደቡብ ፖሊስ ቡድኖች ልጫወት ችያለሁ፤
የእነዚህ ክለብ ቆይታዎቼንም የማስታውሰው
ባንክ እያለው በአሰልጣኝ አለም ሰገድአንቼና
አለባቸው በሚመራው የተስፋ ቡድን ውስጥ
ጥሩ እጫወትና መልካም የሚባል ቆይታም
እንደነበረኝ ነው፤ በአሰልጣኝ ያሬድ ቶሌራ
/ድሬ/ እና ዳዊት ሃብታሙ በሚመራው
የለገጣፎ ለገዳዲ ክለብ ውስጥስጫወት ደግሞ
በጊዜው ጥሩ የውድድር ዓመትን ያሳለፍኩበት
ሰአት ነበር፤ ያኔ የክለቡ የአመቱም ኮከብ
ተጨዋች ተብዬ የ3ሺህ 500 ብር ገንዘብ
ልሸለምም ችያለው፤ በተጨዋችነቴ ሌላው
ጥሩ ጊዜን ያሳለፍኩበት ቡድን የአምናው
በደቡብ ፖሊስ ቡድን ውስጥ በነበረኝ ቆይታዬ
ነው፤ ክለባችን ምንም እንኳን የመውረድ
እጣ ፈንታው ቢገጥመውም በግሌ ጥሩ
በመጫወት ያሳለፍኩበት ነበር፤ በእዛ ቡድን
የነበረኝ አበረታች ብቃትም ሰሞኑን ለብሄራዊ
ቡድን እንድመረጥም ያስቻለኝና በኳሱበራሴ
ላይእያየሁት ያለ ለውጥ አለና ጥሩና መልካም
የሚባል ነው፡፡
ሊግ፡- የእግር ኳስን ስትጫወት ጥሩ
ጊዜን አላሳለፍኩበትም ብለህ የምትጠቅሰውስ
የትኛውን ነው?
ዮናስ፡- በእዚህ በኩል የምጠቅሰው
የባህር ዳር ከተማ ክለብ ውስጥ የነበረኝን
የተጨዋችነት ቆይታዬን ነው፤ ይሄ ክለብ
ያኔ የከፍተኛው ሊግ ተወዳዳሪና ሻምፒዮናም
በመሆን ወደፕሪምየር ሊጉ የገባ ቡድን
ነበር፤ በጊዜው ፕሪምየር ሊግ ሊገባ ቢችልም
በከፍተኛው ሊግ የውድድር ተሳትፎው ላይ
አሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸው /ማንጎ/ የክለቡ
ደጋፊዎችም ሆኑ አንዳንድ ተጨዋቾች እኔን
ተሰልፌ እንድጫወት በመፈለግ አስተያየት
ቢሰጡም እሱ የመጫወት
እድሉን ብዙ ስላልሰጠኝ ጥሩ
የሚባል ጊዜን አላሳለፍኩም፡፡ያም
ሆኖ ግን በጊዜው እኔ የመጫወት
እድሉ ባይሰጠኝም የአሰልጣኞችን
ውሳኔ ከመቀበልና ከማክበር
ውጪ ሌላ የኩሪፊያንም ሆነ
አንዳችንም ነገር ያላደረግኩ
ተጨዋች በመሆኔ ይሄ ባህሪዬ
በጣም ነው የሚያስደስተኝ፡፡
ሊግ፡- የእግር ኳስን
በመሃል ተከላካይ ሊብሮ ሆነህ
ነበር የምትጫወተው፤ አሁን
ላይ ደግሞ የተከላካይ አማካይ
ስኪመር ሆነህ እየተጫወትክ
ይገኛል፤ እንዴት የቦታ ለውጥን
አደረግክ?
ዮናስ፡- ከመሃል ተከላካይ
ስፍራ ቦታ ቀይሬ በአሁን ሰአት
ስኪመር ሆኜእየተጫወትኩ
ያለሁት ወደ ደ/ፖሊስ ክለብ
ባመራሁበት ሰሞን አሰልጣኝ
ዘላለም ሽፈራው /ሞውሪንሆ/ነው
ሁለተኛው ጨዋታ ላይ አሰልፎኝ
ጥሩ ልጫወት ስለቻልኩ
በእዚያው ስፍራ የቀጠልኩት፤
በእዚህም ቦታ ላይ ዘላለም
ክለቡን ለቅቆ ከሄደ በኋላም
አሰልጣኝ ገ/ክርስቶስ ቢራራ
ክለቡን ተረክቦ ነበርና በእዛው
ቦታ አስቀጥሎኝ ጥሩ ልጫወት
የቻልኩት፡፡
ሊግ፡- የደ/ፖሊስ እግር ኳስ
ክለብን በአሰልጣኝነት ይመራ
የነበረው ገ/ክርስቶስ ቢራራ
በብዙዎች ዘንድ ጥሩ አሰልጣኝ
እንደሆነ እየተነገረለት ነው፤
አንተስ እንዴት አገኘኸው?
ዮናስ፡- አዎን፤ እሱ ጥሩ
አሰልጣኝ ነው፤ በዛ ላይ
ደግሞ በጣም ሃቀኛ፤ ይሄን
በተመለከተ ደግሞ እኔ ብቻ
ሳልሆን የኢትዮጵያ ህዝብ ሁሉ
ያውቀዋል፤ በአንድ ወቅት
እንደውም እሱ የሚያሰለጥነው
ቡድን ወደ ጎል የመታት ኳስ
የውጪው መረብ ላይ ባረፈበት
ሰዓትና ዳኛውም ጎል ብሎ
ኳሷን ባፀደቀበት ሰአት እሱ ጎሏ
አልገባችም ልፀድቅም አይገባም
በማለት እንዲሻር ያደረገበት
አጋጣሚ ነበርና ይሄን ማድረጉ
እንዲወደድም አድርጎታልና
በአጠቃላይ ስለእሱ ለመናገር
ቃላቶች ያጥሩሃል፡፡
ሊግ፡- ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን
መመረጥ ችለሃል፤ ስሜቱ ምን ይመስላል?
ዮናስ፡- ለሃገር ብሄራዊ ቡድን መመረጥ
መቻል በጣም ደስ ያሰኛል፤ በቀጣይነት ደግሞ
ከመመረጥ አልፎ ተሰልፈህ ስትጫወትም
የሚኖርህ የደስታ ስሜት ከፍ ያለ ስለሚሆን
ያን እድል ለማግኘትና ሃገሬንም መጥቀም
ስለምፈልግ ለእዛ ጠንክሬ እሰራለሁ፡፡
ሊግ፡- እንደ እግር ኳስ
ተጨዋችነትህ ምንን ማሻሻል
ትፈልጋለህ?
ዮናስ፡- ብዙ ነገርን፤ ከላይ
የገለፅኩልህ ነገር አለ፤ እኔ ገና
ብዙ የሚቀረኝ ተጨዋች ነኝ ብዬ፤
ስለዚህ ሙሉ ተጨዋች መሆንን
ስለምፈልግ ያለብኝ ክፍተት
ቦታዎች ላይ ተሻሽዬ እመጣለሁ፡፡
ሊግ፡- ደ/ፖሊስ ከሊጉ ሲወርድ
እንደተጨዋችነትህ ምን አይነት
ስሜት ተፈጠረብህ?
ዮናስ፡- በጣም ነው ያዘንኩት፤
ክለቡ እንደ እነ ጌታነህ ከበደ እና
ሽመክት ጉግሳን የመሳሰሉ ጥሩ
ችሎታ ያላቸውን ተጨዋቾች
ከማፍራቱ አኳያናበእዚህ ክለብ
ውስጥ እኔም ጥሩ ጊዜን በመጫወት
ያሳለፍኩበትም ስለሆነ መውረዱ
ጥሩ ያልሆነ ስሜት እንዲሰማኝ
አድርጓልና ምንአልባት የፎርማቱ
ሁኔታ ተቀይሮ አልያም ደግሞ
በሌላ ውድድር ደ/ፖሊስ ሊጉ ላይ
ቢቆይ በጣም ደስ ይለኛል፡፡
ሊግ፡- ወደ እግር ኳስ ሜዳው
ከገባህ በኋላ የማትወደው ነገር
ምንድነው?
ዮናስ፡- በእንቅስቃሴ ጥሩ ሆነህ
ሳለህ ስትሸነፍ በጣም ያናድዳል፤
ይሄን ሁሌ አልወደውም፡፡
ሊግ፡- በመጨረሻ…..?
ዮናስ፡- የእግር ኳስ ተጨዋች
ሆነህ ሁሌም ከአንተ ጎን ሆነው
የሚያበረታቱህ፣ የሚመክሩህና
እንደዚሁም ደግሞ ጥሩ
ተጨዋችነትህን መስክረው ወደተሻለ
ጎዳና እንድታመራ የሚያደርጉ
አሰልጣኞችም ሆኑ ከእዛ ውጪ
ያሉ አካላቶች አሉና በእኔ ህይወት
ውስጥ ጥሩ ነገርን ስላደረጉልኝ
ከልብ አመሰግናቸዋለሁ፤ በእዚህ
በኩል የምጠቅሳቸውም ቅድሚያ
ለፈጣሪ ምስጋና ይግባውና አምላኬን
ማመስገን እፈልጋለው፤ከዛም
ቤተሰቦቼን በተለይ ደግሞ ነፍሱን
ይማረውና አባቴን፣ የሰፈር
አብሮ አደግ ጓደኞቼን ሳሙኤል
ወንድሙን፣ ቴዎድሮስ ሸዋአማረን
አንዳርጋቸው ይላቅን/ማቲ/ ዮሴፍ
ወንድሙን እንደዚሁም ደግሞ ደ/
ፖሊስ በገባሁበት ሰአት እንደጥሩ
ተጨዋችነቴ አንዳንድ ነገሮችን
በማድረግ ብዙ ውለታ የዋሉልኝን
ጌታቸው ካሳ /ቡቡ/ ግዛቸውንና
አሰልጣኝ ዳዊት ሃብታሙን
በመጨረሻም የሰፈሬ ቄራ ይመስገን
ጋራዥ አካባቢ ያሉ ጓደኛቼን ከልብ
ለማመስገን እፈልጋለሁ፡፡