በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ስፖርት ታሪክ ውስጥ እጅግ ትልቅ ስፍራ የነበራቸው አንጋፋው እና ሰመጥሩ የስፖርት ሳይንስ አባት በጥቂት ቀናት ህመም በድንገት ዛሬ ሐሙስ ነሃሴ 19/2014 ዓ.ም ከዚህ አለም በሞት ተለይተዋል!
ኢትዮጵያ አንድ ትልቅ የአትሌቲክስ ስፖርት አባት አጥታለች!
ዶ/ር በዛብህ ወልዴ በቀድሞው የኮተቤ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ (በአሁኑ አጠራር የኮቴቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ) እና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በስፖርት ሳይንስ ትምህርት ክፍል ከመምህርነት እስከ ከፍተኛ የሌክቸረርነት ማዕረግ የደረሱና እስከ ህልፈተ ህይወታቸው ድረስ በአትሌቲክስ ስፖርት ሳይንስ ስፔሻላይዝ ያደረጉ ባለሙያዎችን ያፈሩ፣ በስፖርት አስተዳደር ኢንተርናሽናል ኢንስትራክተርነት፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ልዩ ልዩ አካዳሚያዊ ጽሑፎችን በማዘጋጀት፣ በበርካታ ሚዲያዎች ለስፖርት ጠቃሚ ምክረ ሃሳቦችን በማቅረብ በሙያቸው ‹‹አንቱ›› ከተባሉ ምሁራን ጎራ ቀድመው የሚጠሩ ሰው ነበሩ፡፡
ዶ/ር በዛብህ በኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ውስጥ ከ12 አመታት በላይ ከዋና ጸሐፊነት ጀምሮ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ታሪክ በመጽሔት መልክ እንዲዘጋጅ በማስተባበርና በመምራት፣
በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በዋና ጸሐፊነት፣ እንዲሁም ከ10 አመት በላይ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል በመሆንና በአቃቢ ነዋይነት፣ በቴክኒክ እና ህክምና ኮሚቴ ሰብሳቢነት፣
በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስትና በአዲስ አበባ ከተ/አስተዳደር የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንትነት ለበርካታ አመታት ኢትዮጵያንና ህዝቧን ከልባቸው አገልግለዋል፡፡
… ዝርዝር ታሪካቸውን እንመለስበታለን፡፡ …
ፈጣሪ የዶ/ር በዛብህ ወልዴን ነፍስ ይማርልን! ለዶ/ር በዛብህ ወልዴ ቤተሰቦች፣ ዘመድ አዝማዶችና ጓደኞች መጽናናቱን እንዲሰጥ ከልብ እንመኛለን!
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን፤