Google search engine

ቴዎድሮስ በቀለ /ኢትዮጵያ ቡና/

ቴዎድሮስ በቀለ /ኢትዮጵያ ቡና/
በኢትዮጵያ እግር ኳስ የተጨዋችነት ታሪክ ቆይታው ከታችኛው ሊግ ተሳታፊው አርሲ ነገሌ ቡድን አንስቶ እስከ ፕሪምየር ሊግ ተወዳዳሪዎቹ አዳማ ከተማ፣ መከላከያና ሀድያ ሆሳዕና ክለቦች ድረስ ተጫውቷል። በኳስ ዘመን የተጫወተበት ቦታም የመሀል ተከላካይና የግራ መስመር ተከላካይ ሆኖም ነበር። ይህ ተጨዋች ቴዎድሮስ በቀለ ሲሆን በአሁኑ የተጨዋቾች ዝውውር መስኮት ከሀድያ ሆሳዕና ጋር የነበረውን የውል ጊዜ በማጠናቀቅ ወደተፈለገበት ኢትዮጵያ ቡና አምርቶ ለክለቡ ለመጫወት ለሶስት ዓመታት ፊርማውን አኑሯል።
ኢትዮጵያ ቡናን የተቀላቀለውን ይኸውን ተጨዋች የሊግ ስፖርቱ ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ ወደ ቡድኑ ስላደረገው ዝውውርና በተለያዩ ክለቦች ውስጥ ስላሳለፈው የኳስ ህይወት እንደዚሁም ደግሞ በኢትዮጵያ ቡና ስለሚጠብቀው የኳስ ቆይታው በማናገር የሰጠን ምላሽ በሚከተለው መልኩ ቀርቧል።
ሊግ፦ በክረምቱ ወራት የተጨዋቾች ዝውውር መስኮት ኢትዮጵያ ቡናን የተቀላቀልክ አዲስ ተጨዋች ሆነሃል፤ ይሄ ቡድን የቅድሚያ ምርጫህ ነበር ማለት ነው?
ቴዎድሮስ፦ አዎን፤ በዝውውር መስኮቱ ከአራትና አምስት ከሚደርሱ ክለቦች የተጫወትልን ጥሪ ደርሶኝ እንድፈርምላቸው አናግረውኝ ነበር። በኳስ ጨዋታ ዘመኔም እንዲህ ያለ ጥሪም ደርሶኝና ኖሮኝ አያውቅምም ነበር። በመጨረሻ ላይ ግን ኢትዮጵያ ቡናን የቅድሚያ ምርጫዬ አድርጌ ለሶስት ዓመታት ለመጫወት ፊርማዬን አኖርኩ።
ሊግ፦ ለኢትዮጵያ ቡና ቅድሚያ ሰጥተህ እንድትጫወት ያደረገህ ዋናው ነገር ምንድን ነው? የተሻለ ጥቅምና ገንዘብ ስለሰጡ ነው ወይንስ በሌላ ምክንያት…?
ቴዎድሮስ፦ በጥቅም ደረጃማ ከቡና የተሻለ በሚባል ደረጃ ገንዘብን ያቀረቡልኝ ክለቦች ነበሩ። አጋነንከው እንዳትለኝ እንጂ አንተ ፈርምልን እንጂ እስከ 4 ሚሊዮን ብር ድረስም በእጄ ጭምር ሊሰጡኝ የተዘጋጁና የደወሉልኝ ቡድኖችም ነበሩ። ያም ሆነ ይህ ግን እኔ ገንዘብን ብቻ ማየት የለብኝም ከሚል ውሳኔ ላይ ደርሼ ከቡና ክለብ አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ የቀረበልኝን ለቡድኑ የተጫወትልን ጥያቄ እኔኑ በጣም ስላስደሰተኝና አስቀድሜም በዚህ አሰልጣኝ ለሚመራው ቡድንም የመጫወት ፍላጎቱም ስለነበረኝ ለዛ ነው ክለቡን ከሌሎች አንፃር ላስቀድምና ወደ እነሱ ጋርም ለመጫወት ላመራ የቻልኩት”።
ሊግ፦ ወደ ኢትዮጵያ ቡና ገብቶ ለመጫወት ሌላስ ያስመኘ ነገር አለ?
ቴዎድሮስ፦ አዎን፤ ለዛም ነው እኮ የቡድኑን ጥሪ ተቀብዬም በቅድሚያ ልፈርም የቻልኩት። ቡና ከበፊት አንስቶ ልጫወትበት የምፈልገውና የምመኘው ቡድን ነበር። ክለቡ ጥሩ አደረጃጀት ና መሰረት ያለውም ነው። በዛ ላይ ክለቡን ከልብ የሚወዱ ምርጥ ደጋፊዎችንም ያሰባሰበም ስለሆነና በቀድሞ ተጨዋቹና በአሁኑ አሰልጣኝ ስር ሆኜም መስራትን ስለፈለግኩ ወደ ወደድኩት አዲሱ ቡድኔ በማምራት ለመጫወት ተዘጋጅቼያለው።
ሊግ፦ በአሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ ስር መስራትን በመፈለግ ጭምር ነው ወደ ቡና የመጣሁት የሚል ቃልንም ተንፍሰሃልና እስኪ ስለ እሱ ያወቅከውን ነገር አሰማን? ካሳዬ ሲጫወትስ ተመልክተከዋል…..?
ቴዎድሮስ፦ ካሳዬ አራጌ ሲጫወት ስላልደረስኩ አልተመለከትኩትም፤ ወደ አሰልጣኝነት ህይወት በድጋሚ ወደ ቡና ከመጣ በኋላ ግን ስለ እሱ የሌላ ቡድን ተጨዋች ሆኜ ከምሰማቸው ነገሮች በመነሳት ብዙ ነገሮችን በደንብ አወቅኩኝ። ከሁሉ በላይ በእሱ የተደሰትኩት ነገር ቢኖር ለተጨዋቾች ባለው ከበሬታ /ሪስፔክት/ ነው። ከዛ ሌላም የአንድን በተለያዩ ችግሮችም ሊሆን ይችላል ደከም ያለ ተጨዋችን አቅም በደንብ አይቶና አውቆም ከወደቀበት የማንሳት ጉልበትም አለውና ይሄ ነገሩ ለየት እንዲል ያደርገዋልና እኔንም ወደ ቡድኑ እንድመጣ በፈለገበት ሰዓት ላይ ሲያናግረኝ ይህን ሁኔታ በድጋሚ በደንብ አስተውዬበታለውና በእሱ ስር ወደ ሚሰለጥነው ኢትዮጵያ ቡና በማምራቴ እና በዚሁ ክለብ ውስጥም በችሎታዬም ላይ በጣሙን እቀየራለው ብዬም ስላሰብኩ ከወዲሁ በጣም ደስተኛ ነኝ።
ሊግ፦ በኢትዮጵያ ቡና የመጪዎቹ ዘመናት የተጨዋችነት ቆይታህ የተሳካ የኳስ ጊዜን የምታሳልፍ ይመስልሃል?
ቴዎድሮስ፦ በዚህ ረገድ መቶ ፐርሰንት ነው የምልህ ምንም አይነት ጥርጣሬው የለኝም። ወደ ቡና የመጣሁት በኳሱ አስቀድሞ የነበረኝንና ጠፍቶና ተውጦም የነበረውን የመጀመሪያዬን ማንነቴን ለማደስ ነው። ይሄ የሚሳካው ደግሞ በቡና ተጨዋችነቴ ነውና በዚሁ ቡድን ቆይታዬ ጥሩ ጊዜያትን እንደማሳልፍ በጣም እርግጠኛ ነኝ።
ሊግ፦ ኢትዮጵያ ቡና በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ የመጪው ዘመን ቆይታው ምን ውጤት ይገጥመዋል….. በኮንፌዴሬሽን ካፕ ተሳትፎውስ?
ቴዎድሮስ፦ ወደ ቡና ከመጣሁበት ምክንያቶች መካከል በቀዳሚነት የማነሳው ከዚህ ታላቅ ቡድን ጋር የሀገሪቱን የሊግ ዋንጫ ማንሳት መቻል ነውና ለዚህ እቅዴ በርትቼ ነው የምሰራው። ሌላው ቡድኑ ላለበት የኮንፌዴሬሽን ካፕ ተሳትፎውም የያዘውን የአጨዋወት ባህሪ ባለቀቀ መልኩ የከዚህ ቀደሙን ውጤት ከፍ ባደረገ መልኩ ማስቀመጥም ነውና ይሄን ከፈጣሪ እርዳታ ጋር ለማሳካት ከፍተኛ ጥረትን እናደርጋለን።
ሊግ፦ በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የተጨዋችነት ዘመን ቆይታህ ለአንተ ምርጡ የነበረው ጊዜ የቱ ነው?
ቴዎድሮስ፦ በመከላከያ የነበረኝ ቆይታ ነው ለእኔ ምርጡ። ጥሩ የኳስ ጊዜን በማሳለፍም ነው ለክለቡ ልጫወት የቻልኩት። በዚህ ቡድን በነበርኩበት ሰዓት ላይም ለክለቡ በስቶፐር ስፍራ እየተጫወትኩ በአራት ተከታታይ ጨዋታዎች ላይም አራት ግቦችን አስቆጥሬ ቡድኔን ከወራጅ ቀጠናው እንዲወጣም ያደረግኩበት ወቅትም ነበርና ይሄ ከሁሉም በላይ ያስደሰተኝ ነው።
ሊግ፦ በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ በሀድያ ሆሳዕና የነበረህ የዘንድሮ ቆይታስ?
ቴዎድሮስ፦ መጀመሪያ ላይ እንደ ግል ጥሩና ደስ የሚል ጊዜን ነው ለማሳለፍ የቻልኩት፤ በቆይታዬ ራሴን በጥሩ መልኩም ገልጬበታለው። ከዛ ግን እንደ ቡድንም እንደ ግልም አጀማመራችን ያማረ የነበረልን ቢሆንም በኋላ ላይ ግን በክለቡ አመራሮች ችግር ለቡድኑ ተጨዋቾች ደመወዝ ሊከፈል ባለመቻሉና እኛ ተጨዋቾችም ከገንዘብ ችግር ጋር በተያያዘ ልምምድን ለሶስትና ለአራት ቀናት እያቆምን ድጋሚ የምንጀምርበት ሁኔታም በመፈጠሩ ይሄ ሁኔታ ክለቡን ውጤት እያሳጣው ሄዶ ለዋንጫ ካልሆነ ደግሞ በሁለተኛ ደረጃ ላይ ሆነን የሊጉን ውድድር ልናጠናቅቅ እንዳንችል ከማድረጉ ባሻገር ያለው ጫና ከነበረኝ ጥሩ ብቃት አኳያ እኔንም ይበልጥ እንዳልጎላ ስላደረገኝ ያ ሊያስከፋኝ ችሏል።
ሊግ፦ የሀድያ ሆሳዕና ክለብን በኋላ ላይ ውጤት ያሳጣው ለተጨዋቾች ደመወዝን አለመክፈሉ ብቻ ነው?
ቴዎድሮስ፦ አዎን፤ ጠንካራና ጥሩ ቡድን ነበረን። እስከ ዋንጫው ካልሆነ ደግሞ ከላይም ገልጬዋለው ሁለተኛ ሆነን ማጠናቀቅና በኢንተርናሽናል የውድድር መድረክ ላይ መሳተፍም እንችል ነበር። ከወጪ አንፃር ይህ እንዲሆን በክለቡ ስላልተፈለገ ግን እኛን በመበተን ውጤትን እንድናጣ አድርገውናል።
ሊግ፦ በፋሲል ከነማ የሊጉን ዋንጫ በማንሳት ዙሪያና ስለ አቡበከር ናስር የዘንድሮ ኮከብነትስ ምን የምትለው ነገር አለ?
ቴዎድሮስ፦ ፋሲሎች መሰረት ባለው መልኩ ቡድናቸውን በደንብ ስለሰሩት እና አመራሮቻቸውም ተጨዋቾቻቸው ምን እንደሚፈልጉም ስለተረዱና የሚያስፈልጋቸውንም ነገር ስለሚያሟሉላቸው የዚህ ዘመን ዋንጫ ካላቸው ጠንካራ ቡድን አኳያ የሚገባቸው ነው። ወደ አቡኪ ሳመራ ደስ የሚል ችሎታና አቅም ያለው ተጨዋች ነው። በእኛ ሀገር ደረጃም በዚህ መልኩ ጎልቶ መውጣትም ያልተለመደም ስለሆነ ወደፊት ይህ ልጅ ካለው ከፍተኛ አቅም በመነሳት ለጥሩ ደረጃ ይደርሳል። በተለይም ደግሞ ያለው አጨራረስና ድፍረቱም የብዙ ኳሊቲ ባለቤት እንዲሆን ስላደረገውም እስከ ፕሮፌሽናል ተጨዋችነት ስፍራም የሚጓዝ ይመስለኛል።
ሊግ፡- የእግር ኳስ ተጨዋችነት ቀጣይ እልምህና ግብህ የት ድረስ መጓዝ ነው?
ቴዎድሮስ፡- በእግር ኳስ ተጨዋችነት ዘመኔ ወደፊት ብዙ ነገሮችን ሰርቼ በማለፍ የተሻለ ደረጃ ላይ እንደምደርስ በሚገባ አውቃለው፤ አሁን ላይ በተለይ ለቡና ብቻ ሳይሆን ለሀገሬ ብሔራዊ ቡድንም ተመርጬ ሀገሬን በጥሩ ሁኔታ ለማገልገል የተነሳሁበትና የኳስ ህይወቴንም እስከ ፕሮፌሽናል ተጨዋችነት ደረጃም መጓዝን አልማለውና ይህን ለማሳካት ከፍተኛ ጥረትን አደርጋለው፡፡
ሊግ፡- ለኢትዮጵያ ቡና ለመጫወት ፊርማህን አኑረሃል፤ ከዛ በፊት ደግሞ ክለቡን በተቃራኒነት ገጥመሃል፤ ቡናን ያኔ በተቃራኒነት ስትገጥም የተለየ ግምትን ትሰጣቸው ነበር? ካልሆነስ በምን መልኩ ተመለከትካቸው?
ቴዎድሮስ፡- ወደ ኢትዮጵያ ቡና ከማምራቴ በፊት እነሱን በተቃራኒ ሆኜ ስገጥም ሁሌም ቢሆን የተለየ ግምትን ሰጥቼያቸው አላውቅም፤ ከእነሱ ጋር ስንጫወትም ራሴን ለማሳየትም ጠንክሬ እሰራም ነበር፤ የአሁኑ አጨዋወታቸው ግን ለማንም ቡድን ከባድ እንደሆነ በሚገባ ተመልክቻለው፤ ቡናን ስትፋለም የእነሱ ተጨዋቾች የሰው ቁጥርን አብዝተው በትርፍ ሰው ወደ ጎል እንደ ቡድን ስለሚመጡብህ ይህ አጨዋወታቸው የሚማርክ ነው፡፡
ሊግ፡- ወደ ግል ህይወትህ እናምራ፤ የትዳር ዓለሙን የተቀላቀልክ ይመስለኛል?
ቴዎድሮስ፡- አልተሳሳትክም ልክ ነህ፤ ገና ወደ ኳሱ ዓለም ሳልገባ የ19 ዓመት ልጅ ሳለውም ነበር የልጅነት ጓደኛዬ ከነበረችውና በቀድሞ ጊዜ አባባልም ዕቃ ዕቃ አብረን በመጫወት አብሬያት ካደግኩት ፍቅረኛዬ ህይወት ሲሳይ ጋር ትዳርን መስርቼ አብሬ እየኖርኩ ያለሁት፤ በዚህ ህይወት ቆይታችንም በመሰረትነው ጋብቻ አራት ልጆችን ማለትም ሀናን፣ ቬሮኒካን፣ ሳሙሄልንና በፀሎትን ከማፍራታችን በተጨማሪ አምስተኛ ልጅም እየመጣ በመሆኑ ይሄ እያስደሰተን ያለ ነገር ነው፤ በትዳራችንም በጣም ደስተኛም ነን፡፡
ሊግ፡- ባለቤትህን ግለፃት ብትባል በምን ሁኔታ ነው ስለ እሷ የምታወራው?
ቴዎድሮስ፡- አብሮ አደጌ እንደመሆኗ በብዙ ነገሮች ተግባብተንና ተረዳድተን ነው የመጣነው፤ እሷ በህይወት ዘመን ቆይታችንም ጎበዝና ታታሪ ከመሆኗ ባሻገር የፀሎት ሰውም ሆና ቤተክርስቲያንን በማገልገል እንደዚሁም ደግሞ ልጆቼንም እኔ ስራ ላይ በመሆኔ የተነሳ ተንከባክባ በማሳደግ የአንበሳውን ድርሻም የምትወስድ ስለሆነች በዚሁ አጋጣሚ በጣም እንደምወዳት፣ እንደማከብራትና እንደማመሰግናትም ለመግለፅ እወዳለው፡፡
ሊግ፡- በእግር ኳሱ ከፍቶህ ያውቃል?
ቴዎድሮስ፡- በአንድ ወቅት የሰበታ ከተማ ተጨዋች በነበርኩበት ዘመን አዎን በጣም ነበር የከፋኝ፤ ያን ጊዜ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ለማለፍ በነበረው የመጨረሻ ውድድር ላይ ነው እኛና ዳሽን ቢራ ስንጫወት 5-0 በመሸነፋችን ሳናልፍ የቀረነው፤ ያኔ ይህን ጨዋታ ካሸነፋችሁ በሚል ክለቡ ቦታ አሳይቶን መሬት ሊሰጠን አስቦ ነበር፤ ግን በመሸነፋችን ደጋፊውን ጭምር አስከፍተን ወደከተማው እንዳንገባ ሁሉ ጥረት አድርጎ ነበርና ያኔ የተነካው ሞራላችን የማይረሳኝ ነበር፤ በዛን ወቅት በተለይ እኔ ለ15 ቀን ያህል ራሴን ሳላገኝ የቆየሁበት ጊዜም ስለነበር ሁኔታውን መቼም ቢሆን አልረሳውም፡፡
ሊግ፡- በመጨረሻ….?
ቴዎድሮስ፡- ወደ ኢትዮጵያ ቡና እንዳመራ አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ የእኔን ችሎታ ተረድቶ ስላመጣኝ ለእሱ ከፍተኛ ምስጋናን ላቀርብለት እፈልጋለው፤ ከዛ በፊት ደግሞ ፈጣሪ ነው የሚቀድመውና ለዚህ ላበቃኝ አምላክ ክብርና ምስጋና ይግባው እላለው፤ ይህን ካልኩ ቤተሰቦቼንና ሁሌም ከጎኔ የሆነችውን ባለቤቴን አመስግኜ በቡና በሚኖረኝ ቆይታ ደግሞ በኳሱ አስቀድሞ ከነበረኝ ብቃት አኳያ ተደብቄ ነበርና በዚህ አዲሱ ቡድኔ ውስጥ ጎልቼ እንደምወጣ አስባለው፡፡

spot_img
ተመሳሳይ ጽሁፎች

አስተያይት ያስፍሩ

እባክዎን አስተያይትዎን ያስፍሩ
እባክዎን ስምዎን እዚህ ያስገቡ

ትኩስ ዜናዎች

%d bloggers like this:
P