አህመድ ሁሴን /ወልቂጤ ከተማ/
“ለወልቂጤ ከተማ የድል ግቦችን ማስቆጠሬ አስደስቶኛል”
“ከጌታነህ ከበደ አጠገብ በመጫወታችን እድለኞች ነን”
ወልቂጤ ከተማ በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ የዘጠነኛ ሳምንት ጨዋታው ተጋጣሚውን ሰበታ ከተማን በአህመድ ሁሴን ሁለት ግቦችና በጌታነህ ከበደ አንድ ግብ 3-2 ያሸነፈ ሲሆን ለሰበታ ከተማ ደግሞ ፍፁም ገብረማርያም እና ሳሙሄል ሳሊሶ አስቆጥረዋል፡፡
ወልቂጤ ከተማ ይህን ድሉን አስመልክቶም የደረጃ መሻሻልን ያሳየ ሲሆን አሁን ወደ 7ኛ ስፍራ መጥቷል፡፡ ከነበረበት ስፍራም ወደ መጥቷል፡፡
ወልቂጤ ከተማ በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ዘንድሮ እያደረገ ባለው ተሳትፎ ዙሪያና በሌሎች መሰል ጉዳዮች ላይ ሰበታ ከተማን ካሸነፉ በኋላ የቡድኑን የአጥቂ ስፍራ ተጨዋችና ሁለቱን የድል ግቦች ያስቆጠረውን አህመድ ሁሴንን ጠይቀነው ምላሹን በሚከተለው መልኩ ሰጥቶናል፤ ቃለ-ምልሱም እንደሚከተለው ይቀርባል፡፡
ሰበታ ከተማን ባሸነፉበት ጨዋታ ሁለት የድል ግቦችን ለቡድኑ ማስቆጠር ስለመቻሉ
“አጥቂ ሆነህ ከግብ ስትርቅ በጣም ይከብዳል፤ ይሄ ሁኔታም እኔንም አጋጥሞኝ ጭንቀት ውስጥ ከቶኝ ቆይቷል፤ አሁን ላይ ግን ግቦችን ለማስቆጠር በመቻሌ እና ቡድኔንም ለአሸናፊነት እንዲበቃ በማድረጌ በጣም ደስ ብሎኛል፤ በቀጣይ ጨዋታዎቼ ላይም ነገሮች ስለሚቀሉኝ ሌሎችን ጎሎች ስለማስቆጠርም አስባለው”፡፡
ስለ ወቅታዊ ብቃቱ
“በእግር ኳስ ጨዋታ አንድ አንዴ ትወርዳለህ በሌላ ጊዜ ደግሞ ጥሩም ትሆናለህ፤ እኔ ሁለቱንም ነገሮች በተጨዋችነት ዘመኔ አሳልፌያለሁ፡፡ አሁን ደግሞ ጎል ማስቆጠር መጀመሬ ከወቅታዊ ብቃት አኳያ ወደ ጥሩ አቋሜ እንድመለስ ብርታት ስለሚሆነኝ ጠንክሬ በመስራት ቡድኔን የምጠቅም ተጨዋች እንደምሆን አምናለሁ”፡፡
ሰበታ ከተማን ማሸነፍ ስለቻሉበት ሁኔታና ስለተጋጣሚያቸው
“ሰበታ ከተማ ጥሩ ቡድን ነው፤ በጨዋታው ላይ እኛ ያሸነፍናቸውም ፈትነውን ነው፤ ከእነሱ ጋር በነበረን ጨዋታ ልናሸንፋቸው የቻልነው ባለፈው ግጥሚያ በቡና ተሸንፈን ስለነበርና አሁን ደግሞ ከመሪዎቹ ክለቦች በነጥብ መራቅ እንደሌለብን ስላወቅን ውጤቱ በጣም ያስፈልገን ነበርና ጠንክረን ለግጥሚያው ስለመጣን ነው ልናሸንፋቸው የቻልነው”፡፡
ወልቂጤ ከተማ አሁን ላይ ጥሩ ቡድን ነው ማለት ይቻላል፤ እያስመዘገበ ያለው ውጤትስ የሚመጥነው ነው?
“ከውጤት አንፃር አሁን እያስመዘገብን ያለነውን ስመለከተው አዎን ጥሩ ውጤት ነው፤ ሁሉም ቡድን አንድ ጨዋታን ሲያሸንፍ በደረጃ ሰንጠረዡ ወደላይ ይወጣልና፤ በአቋም ደረጃም ቢሆን የእኛ ቡድን ጥሩ ነው፤ የሀገሪቱ ምርጥ አጥቂም እኛ ጋር ይገኛል፤ ከእዛ ውጪም ከኋላ ጀምሮ እስከፊት ድረስም ያሉት ተጨዋቾች አቅም ያላቸው ስለሆኑም ይሄ የእኛን ቡድን ጥሩነት ይገልፀዋል፤ ጥሩነታችንንም ውድድሩ ከተቋረጠበት መልስም የምናስቀጥለው ይሆናል”፡፡
ቤትኪንግ ዋንጫውን ማን ያነሳዋል
“ሁሉም ቡድን ዋንጫውን ለማንሳት እንደሚጫወት አሁን እየተመዘገበ ካለው ውጤት የምትረዳው ብዙ ነገር ስላለ አሁን ላይ ይሄ ቡድን አሸናፊ ይሆናል ብለህ መናገር አትችልም፤ የውድድሩ ሻምፒዮናም መጨረሻ ላይ ይታወቃል”፡፡
ዘንድሮ ሊያመጡ ስላሰቡት ውጤት
“ወደ ውድድሩ ስንገባ ጥሩ ነገር ሰርተን የደረጃ ተፎካካሪ ስለመሆን ነው ያሰብነው፤ አሁን በእዛ አካባቢም ላይ ነው የምንገኘው፤ ምንአልባትም ደግሞ ከዛ ከፍ ያለ ውጤት ሊገጥመንም ይችል ይሆናል”፡፡
በተጠባባቂ ስፍራ ላይ ስትቀመጥ የምታኮርፍ አይነት ተጨዋች ነህ ወይንስ…..
“በፍፁም አኩራፊ የሆንኩ ተጨዋች አይደለሁም፤ ወጣት ተጨዋች ነኝ፤ ለምንስ አኮርፋለው፤ ወደፊት እኮ ብዙ ተስፋ ያለኝና ብዙ መጥቀም የምችልም ተጨዋች ነኝ”፡፡
ጌታነህ ከበደ ወደ ወልቂጤ መጥቶ ስለመጫወቱ
“የእሱ ወደ እኛ ቡድን መምጣት በብዙ ነገሮች እየጠቀመን ነው የሚገኘው፤ ጌታነህ የሀገሪቱ ትልቅ አጥቂ ስለሆነም ከእሱ ብዙ ነገሮችንም እያገኘን ነው፡፡ በአጠቃላይ እሱ እየፈጠረልን ካለው ነገር አኳያም ስመለከተው ከአጠገቡ ጋር ሆነን መጫወት መቻላችን በራሱ እድለኞች ነን”፡፡
ስለ ቀጣይ ጊዜ የኳስ እልሙ
“በእግር ኳስ ማንኛውም ተጨዋች ተሳካለትም አልተሳካለትም ለብሄራዊ ቡድን ተመርጦ መጫወትን ያልማልና እኔም ጠንክሬ ሰርቼ ይህን እድል ማግኘትን እፈልጋለው፤ ይህን ለማሳካት ግን ትህግስትና ፅናት ያስፈልጋል”፡፡
ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉን ከአምናው ስታነፃፅረው
“በሁሉም ነገር ለእኔ አሁንም ተመሳሳይ ነው፤ ለየት ያለ ነገርን አልተመለከትኩም”፡፡
እናጠቃል
“ባሳለፍኩት የኳስ ህይወት በጣም ደስተኛ ነኝ፤ ለእዚህ እንድበቃ ያደረጉኝን ቅድሚያን ፈጣሪዬ ይውሰድና በመቀጠል ቤተሰቦቼን፣ አሰልጣኞቼን ለታን፣ አስራት ሄርጳን፣ ደረጄ በላይንና ደግአረግ ይግዛውን ላመሰግናቸው እፈልጋለው”፡፡