አዳማ ከተማ ባለሜዳው ድሬዳዋ ከተማን 2-0 ያሸነፈበትን ውጤት ጣፋጭ ነው ሲል የክለቡ ተጨዋች አማኑሄል ጎበና ለሊግ ስፖርት ጋዜጣ አስተያየቱን ሰጥቷል።
በሊጉ የእዚህ ሳምንት ጨዋታ ቡድኑ ድል ሲያደርግ ዊሊያም ሰለሞን ግቦቹን ያስቆጠሩ ሲሆን ከክለቡ የሊጉ የውድድር ጉዞ ጋር በተያያዘ የአማካይ ስፍራ ተጨዋቹን አማኑሄል ጎበናን አነጋግረነው ምላሹን በሚከተለው መልኩ ሰጥቶናል፤ ተከታተሉት።
ባለሜዳውን ድሬዳዋ ከተማን ስለማሸነፋቸው
“ወደ ድሬዳዋ ከመጣን በኋላ በተከታታይ ጨዋታዎች ላይ ተሸንፈን ነበር፤ ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ደግሞ ነጥብ ይዘን ነበር። በእዚሁም መሰረት ድሬዳዋን ስንገጥም ከጨዋታው በፊት በጫና ውስጥ ሆነን ነበር። ከእዚህ ግጥሚያ ለእኛ ቡድኑ በሜዳውና በደጋፊው ፊት ስለሚጫወትና ጠንካራም ቡድን ስለሆነ ነጥብ መያዙ አስፈላጊ ስለነበር ያን ውጤት በጠንካራ በነበረው ጨዋታ አሸንፈናል፤ በድሉም ጣፋጭነት ተደስተናል”።
ስለ ሊጉ የእስካሁኑ ጨዋታዎቻቸው
“ሁለት አይነት መልክ ያለው ነው። በባህርዳር ቆይታችን ጠንካራ የነበርንበትና ነጥቦችንም የያዝንበት ነበር። ጥሩም ለመጫወት ችለናል። ድሬዳዋ ላይ ግን የሜዳው ምቹ አለመሆንን ጨምሮ ከእኛ ቡድን አጨዋወት አኳያ ነገሮች በተቃራኒው ሊሄዱልን ችለዋል፤ ውጤቶችም በፈለግነው መልኩ አልተሳኩልንም፤ በመጨረሻዎቹ ግጥሚያዎቻችን ደግሞ መልሶ ወደ ማንሰራራቱ የመጣንበትና የባህርዳር ቆይታችንንም እያስታወሰን ነው”።
የእዚህ ዓመት ግባቸው
“ሊጉ ገና በርካታ ጨዋታዎች አሉት፤ የእኛ ቡድን እንደ አምናው ላለመውረድ ከመጫወት ይልቅ ለተፎካካሪነት ይጫወታል”።
በሊጉ ሰርፕራይዝ የሆነበት ክለብ
“ኢትዮጵያ መድን ነዋ! ይሄ ክለብ ከታች መጥቶ ነው ውድድሩን እየመራ ያለው። በእርግጥ አሰልጣኙ ልምድ ያለው ነው። ልምድ ያላቸው ተጨዋቾችንም ይዟል። ባልተጠበቀ ሁኔታ ጥሩ ነጥብ መያዛቸውም ነው እንዲደነቁ ያደረጋቸው”።
ያስቆጫችሁ ጨዋታ
“ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ጋር ባለቀ ሰዓት እየመራን 2-2 የወጣንበትና ከወላይታ ዲቻ ጋር ደግሞ እየመራን የተሸነፍንባቸው ጨዋታዎች ያስቆጩናል”።
ያስደሰተክ ግጥሚያስ
“የምናሸንፋቸው ጨዋታዎች ሁሉ የተለየ ደስታን ይሰጡኛል”።
ለአዳማ ከተማ ስለሚሰጠው ግልጋሎትና ስላሳለፈው የኳስ ህይወት
“ፈጣሪ ይመስገን የኳስ ህይወቴ እስካሁን ያላሳካዋቸው ነገሮች ቢኖሩም በጥሩ መልኩ እየሄደልኝ ነው። ለአዳማም ቤቴ ስለሆነ ጥሩ ግልጋሎቴን ወደፊት መስጠቴንም አላቋርጥም።