ጅማ አባቡና ከከፍተኛው ሊጉ ወደ ፕሪምየር ሊጉ በተሸጋገረበት ዓመት ላይ ለቡድኑ ውጤት ማማር ትልቁን ድርሻ ወስዶ የነበረው የክለቡ የአጥቂ ስፍራ ተጨዋች አሜ መሐመድ ነበር፤ የግብ አዳኙ አሜ በእዚያን የውድድር ዘመን ላይ ለክለቡ 24 ግቦችን በማስቆጠር ቡድኑ ፕሪምየር ሊጉን እንዲቀላቀል ያደረገ ሲሆን በወቅቱ የውድድር ዘመኑም ኮከብ ግብ አግቢ ተብሎም ተሸልሟል፡፡
አሜ መሐመድ በእዚያን የውድድር ዘመን ላይ ቅ/ጊዮርጊሶችን ለመቀላቀል ቢችልም በክለቡ ጅማሬም ጥሩ ለመጫወት ቢችልም በኋላ ላይ ግን በእግሩ ላይ የደረሰበት ጉዳት ከሜዳ ሊያርቀው በመቻሉና ቡድኑም የተለያዩ አሰልጣኞችን በየጊዜው መቀያየሩ ድኖ በመጣበት ወቅት ላይ የመሰለፍ እድልን ከማጣት ጋር በተያያዘና በፍጥነትም ወደሚታወቅበት ብቃቱ ላይም ሊገኝ ስላልቻለ በክለቡ ሊያሳካቸው ከፈለጋቸው ውጤቶች ጋር መራራቁ ከፍተኛ የቁጭት ስሜት እንደፈጠረበት ለሊግ ስፖርት ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡
የእግር ኳስን በመከላከያ ተስፋ ቡድን ውስጥ መጫወት ጀምሮ በጅማ አባቡና፣ በቅ/ጊዮርጊስና በወልቂጤ ከተማ ቡድኖች ውስጥ ያሳለፈው አሜ መሐመድ በአሁኑ የክረምቱ የተጨዋቾች ዝውውር መስኮት ለአዳማ ከተማ ፊርማውን ያኖረ ሲሆን ከእዚህ ተጨዋች ጋር በተያያዘ የሊግ ስፖርት ጋዜጣ አዘጋጅ ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ ከተጨዋቹ ጋር በአንድ አንድ ጥያቄዎች ዙሪያ ቆይታን አድርጎ ምላሽን አግኝቷል፤ ቃለ-ምልልሱም በሚከተለው መልኩ ቀርቧል፡፡
ሊግ፡- ከጅማ አባቡና ለቅ/ጊዮርጊስ ለመጫወት ወደ ፕሪምየር ሊጉ ስትመጣ የጎሉ አዳኝ ሆነህ ነበር፤ ይህን ግን ማስቀጠል አልቻልክም?
አሜ፡- የእውነት ነው፤ በኳስ ዓለም አንዴ ጥሩ ትሆናለህ፤ አንድአንዴ ደግሞ በምትፈልገው መልኩ ላትንቀሳቀስ ትችላለህ፤ እኔም ከጅማ አባቡና ወደ ቅ/ጊዮርጊስ በመጣሁበት ሰዓት ላይ በከፍተኛው ሊግ ላይ የነበረኝን ምርጥ ብቃትና የጎል ማስቆጠር ችሎታዬን በዚህ ክለብ ውስጥ አሳያለው፣ አሳካለው፤ ቡድኑንም ውጤታማ አደርጋለው ብዬ ለራሴ ቃል ገብቼና ብዙም ተጠብቆብኝ የነበረ ቢሆንም በምፈልገው መልኩ ቆይታዬን ላስኬደው ስላልቻልኩ በጣም ተቆጭቻለው፤ በእነዛ የውድደር ዓመታት ቆይታዎቼ ውስጥም የመጀመሪያው ዓመት ላይ የነበረኝ ብቃት ብቻም ነው ምንም እንኳን የሊጉን ዋንጫ ባለማንሳታችን ብቆጭም ለእኔ ግን እንደ ግል ጥሩ የሚባል ጊዜን ላሳልፍ የቻልኩት፡፡
ሊግ፡- በቅ/ጊዮርጊስ የተጨዋችነት ዘመን ቆይታህ ላይ በምትፈልገው መልኩ እንዳትንቀሳቀስና ከሜዳም እንድትርቅ አድርጎ የነበረው በእግርህ ላይ የደረሰብህ ጉዳት ብቻ ነው የሚል ነገርን ሰማን፤ ችግሩ ይህ ብቻ ነው?
አሜ፡- አይደለም፤ በጊዜው የደረሰብኝ ጉዳት ከሜዳ ሊያርቀኝ ቢችልም ያን ያህል ግን ጉዳቱ ከባድ የሚባል አልነበረም፤ ሆኖም ግን ጉዳት ደርሶብህ ከሜዳ ስትርቅ እንደ ቅ/ጊዮርጊስ ባሉ ትላልቅ ቡድኖች ውስጥ ለመሰለፍ የሚኖረው ፉክክር ከበድ የሚልና በፍጥነት ወደ ሜዳ ለመመለስም የሚቸግርህ ስለሆነ ከዛ ውጪ ደግሞ ቡድናችን በተለያዩ ጊዜያቶች አዳዲስ የውጪ ሀገር አሰልጣኞችን ስለሚቀያየርም እነዚህ ሁኔታዎችም ናቸው ከአጨዋወት ዘይቤ ጋር በተያያዘ ለአንዱ አሰልጣኝ ልትሆን ለአንዱ አሰልጣኝ ደግሞ ላትሆን ስለምትችል እነሱ በሚመርጡት አጨዋወት ጭምርም ነው የመጫወት እድልን ካለማግኘት ጋር ተያይዞም ከሜዳ ልርቅ የቻልኩት፡፡
ሊግ፡- በቅ/ጊዮርጊስ ክለብ ቆይታህ ላይ በምትፈልገው መልኩ እንድትጫወት ለአንተ የትኛው አሰልጣኝ ነበር ምቹ የሆነልህና የተስማማህ?
አሜ፡- በቫስ ፒንቶ ዘመን ነው አሰልፎ ስላጫወተኝ ሳይሆን በብዙ ነገር ጎበዝ አሰልጣኝ ስለሆነ ነው ለእኔ እንቅስቃሴ ምቹ ሆኖልኝ እሱ በነበረበት ሰዓት ላይ ጥሩ ልጫወት የቻልኩት፡፡
ሊግ፡- በቅ/ጊዮርጊስ የተጨዋችነት ቆይታህ ብዙ ተጠብቆብህ ስምህን ማግነንና ከፍ ማድረግ አልቻልክም፤ ለዚህ ለመዳረግህ ራስህን ወይንስ ሌላ አካላትን ትወቅሳለህ?
አሜ፡- በቅ/ጊዮርጊስ በነበረኝ የተጨዋችነት ዘመኔ ራሴንም ሆነ ሌላ የምወቅሰው አካል ማንም የለም፤ ክለቡ ውስጥ በነበረኝ ቆይታ ነገሮች ከስኬት ጋር ባይሄዱልኝም መልካምና ጥሩ ጊዜን ነበር ያሳለፍኩት፤ በተለይም ደግሞ ይህን ቡድን ከተቀላቀልኩበት ጊዜ ጀምሮ እነ ሳላህዲን ሰይድ፣ ደጉ ደበበ፣ አዳነ ግርማ እንደዚሁም ደግሞ እንደ እነ ምንተስኖት አዳነን የመሳሰሉት ተጨዋቾች እኔን ለቡድኑ አዲስ እንደመሆኔ በብዙ ነገሮች ይረዱኝ ነበር፤ በተለይ ስለ ቅ/ጊዮርጊስ ትልቅ ቡድንነት፣ ዋንጫ የለመደ ቡድን ስለመሆኑ፣ ሽንፈት በቡድኑ እንደማይወደድና ሌሎችም ነገሮችን ደጋግመው ይነግሩኝ ነበር፤ ከዛ ውጪ እኔ በመጣሁበት ሰዓት ላይም በአፍሪካ ክለቦች ቻምፒዮንስ ሊግ ላይ የሚሳተፍበት ዓመት ላይ ስለነበርና ቡድኑ በሊጉም ዋንጫ የለመደ ክለብ ስለሆነም አንድ ነገር መስራት እንዳለብኝም እንዳውቅ አድርገውኝ ነበርና ሁሌም ከጎኔ ለነበሩት ለእነሱ እንደዚሁም ደግሞ ለክለቡ አመራሮችና ደጋፊው ሁሉ ከፍተኛ ምስጋናዬን ማቅረብ እፈልጋለው፡፡
ሊግ፡- በቅ/ጊዮርጊስ ቆይታህ ላይ ስለ ክለቡ በደንብ ስታውቅ ከሁሉም በላይ የቆጨህ ነገር ምንድን ነው?
አሜ፡- የቅ/ጊዮርጊስ ቆይታዬ ላይ ስለ ክለቡ ትልቅ ቡድንነትና በሀገራችን ከሚገኙት ሁሉም ቡድኖች በተሻለም ታሪክና ውጤት ያለው መሆኑን ከተረዳሁበት ጊዜ ጀምሮ የእኔ የእዚህ ቡድን ትልቁ ቁጭቴ ከዚህ ክለብ ጋር አድርጌው በነበረው የአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታ ላይ ጥሩ ስኬትን ለማስመዝገብና የሊጉንም ዋንጫ ለማንሳት አለመቻሌ ነበር፤ ያ እልሜ ፈፅሞ ሊሳካልኝ ስላልቻለ በጣም ነው የተቆጨሁት፡፡
ሊግ፡- የቅ/ጊዮርጊስ ጨዋታ ዘመንህ እንዳበቃ ወደ ወልቂጤ ከተማ አምርተህ ነበር፤ ስለ ቡድናችሁ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ተሳትፎ ምን አልክ?
አሜ፡- በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ የነበረን አጀማመር እስከ ጅማ ከተማ ተሳትፎአችን ድረስ በጣም ጥሩ ነበር፤ ወደ ባህርዳር ካመራን ጊዜ ጀምሮ ግን ይደርስብን በነበረው ሽንፈት ክለቡ ውስጥ ጫናም ስለነበር ወደ ላይ መውጣት አቃተን፤ ሲዳማ ቡናም በተመሳሳይ እንደ እኛ ሁሉ ውድድሩ እየከበደው ሄዶ ነበር፣ እነሱ ግን ከጫና ወጥተው ወደ ውጤታማነት ሲሄዱ እኛ ግን በተለይም የሁለተኛው ዙር ላይ ፈፅሞ አልነበርንበትምና ውጤት ሊክደን ችሎ አስከፊ ውጤትን ልናስመዘግብ ቻለን፤ የእኛ ቡድን ከድሬ መልስ ያስመዘገበው ነጥብ አንድ ብቻ ነበር፤ ያ ከሊጉ ሊያወርደውም ችሏል፤ ሆኖም ግን ከትግራይ ክለቦች አለመሳተፍ ጋር በተያያዘ ሌላ በተገኘ እድል ተወዳደረና ተመልሶ ሊጉን ሊቀላቀል ችሏል፡፡
ሊግ፡- በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ የመጪው ዓመት ተሳትፎ ለአዳማ ከተማ ለመጫወት ፊርማህን አኑረሃል፤፤ ዝግጅታችሁ ምን ይመስላል? ከአንተና ከቡድናችሁስ ምን ነገር ይጠበቅ…
አሜ፡- እስካሁን እያደረግነው ያለው ዝግጅት በጣም ጥሩ ነው፤ አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ ከዚህ ቀደም እኔን በቅዱስ ጊዮርጊስ ቆይታዬ አሰልጥኖኝ ያለፈ በመሆኑም የእሱን ልምምድ የማውቀውና ሊለውጥህ የሚችልም በመሆኑም ጠንክሬ እየሰራውኝም ነው፤ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ሲጀመር ለአዳማ ከተማ ክለብ ከእኔ ሊጠበቅ የሚችለውን ነገር አውቃለው፤ ዘንድሮ በወልቂጤ አበረታች እንቅስቃሴው ነበረኝ፤ አዲሱ ዓመት ላይ ደግሞ የቀድሞ ማንነቴን ማለትም በተለይ በጅማ አባቡና በነበርኩበት ሰዓት የነበረኝን ግብ አዳኝነቴን መመለስ እፈልጋለውና በዛ መልኩም ነው እየተዘጋጀው የሚገኘው፤ ከአዳማ ከተማ ጋር በተያያዘ ይሄ ቡድን ትልቅ ነው፤ ጠንካራ የሊጉ ተፎካካሪም ነበር፤ ያን ሁኔታ አሁን ላይ አጥቷል፤በመጪው ዓመት በሚኖረን ተሳትፎ ቡድናችን ጥሩ ጥሩ ሲኒየርና ታዳጊና ወጣት ተጨዋቾችን ቢይዝም ዋንጫ ይበላል አልልህም፤ ግን ጠንካራ ተፎካካሪ እንሆናለን፤ የቡድኑን ስምና ዝናም እኛ የአሁኑ ጊዜ ተጨዋቾቹም እንመልሰዋለን፡፡
ሊግ፡- በመጨረሻ?
አሜ፡- በእግር ኳሱ ከጎኔ የነበሩትን ሁሉ አመሰግናለው፤ በወልቂጤ ከተማ ቆታዬም ደጋፊዎች ላደረጉልኝ ነገርም ምስጋናዬን አቀርባለው፡፡