Google search engine

አሰልጣኝ እስማሄል አቡበከር /አዲስ አበባ ከተማ እግር ኳስ ክለብ/ “አንድ ጎል በአንድ ሚሊዮን ብር ከሚተመንበት ፈታኝና ጠንካራ ሊግ መጥተን ነው ፕሪምየር ሊጉን የተቀላቀልነው”

አዲስ አበባ ከተማ፣ መከላከያ እና አርባምንጭ ከተማ በመጪው ዘመን ለሚካሄደው የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ውድድር ከወዲሁ ከነበሩበት ከፍተኛ ሊግ ማለፋቸውን ያረጋገጡ ሲሆን ከእነዚህ ቡድኖች መካከልም አዲስ አበበባ ከተማን በማሰልጠን ቡድኑን ወደ ፕሪምየር ሊጉ እንዲሸጋገር ያስቻለውን አሰልጣኝ አስማሄል አቡበከርን በስኬታቸው እና ከራሱ ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ዙሪያ ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ አናግሮት ምላሽን ሰጥቶታል፡፡

ሊግ፡- በቅድሚያ እንኳን ደስ አለህ?

አሰልጣኝ እስማሄል፡- እንኳን አብሮ ደስ አለን፤ አመሰግናለሁ፡፡

ሊግ፡- ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉን ለመቀላቀል ችላችኋል፤ ለእዚህ ክብር የበቃችሁበት ትልቁ ጥንካሬያችሁ ምንድን ነው?

አሰልጣኝ እስማሄል፡- የመጀመሪያው ቡድናችን ምንም እንኳን ጥቂት ሲኒየር ተጨዋቾች ቢኖሩትም አብዛኛውን ስኳዳችንን በወጣት ተጨዋቾች ለመገንባት መቻላችን በጣም ጠቅሞናል፤ ውድድሩ በአንድ ቦታ ላይ በቶርናመንት ደረጃም ሊከናወን መቻሉም ሌላው የረዳን ነገር ነው፤ በተለይ የሊግ ውድድሩ በዚህ መልኩ መደረጉ ዳኞችን አልፎ አልፎ ሊሳሳቱ የቻሉበት አጋጣሚ ቢኖርም በብዙ ጎኑ ግን በነፃነት እንዲያጫውቱም አድርጓቸዋልና እነዚህ ነገሮች ለእኛ ሊጠቅመን ችሏል፤ አዲስ አበባ ከተማን ወደ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ እንዲያልፍ ሌላው የጠቀመው ነገር የአጠቃላይ የስታፉ የስራ መረዳዳትና ጥንካሬው ከፍ ያለና የቡድናችን ተጨዋቾችም ከእኔ የሚሰጣቸውን የጨዋታ ስትራቴጂ በአግባቡ በመቀበል ሜዳ ላይ የሚተገብሩት መሆኑና ከፍተኛም የአሸናፊነት ስነ-ልቦናው ስለነበራቸው የእነዚህ ድምር ውጤቶች ነው ለክብሩ ያበቃን፡፡

ሊግ፡- ወደ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ያለፋችሁት ፈታኝ የውድድር ዘመንን አሳልፋችሁ ነው?

አሰልጣኝ እስማሄል፡- አዎን፤ የከፍተኛው ሊግ ውድድር ሁሌም ቢሆን ፈታኝና ከፍተኛ ትግልን የሚጠይቅ ነው፤ እዛ ተወዳድረህም ፕሪምየር ሊጉን በቀላሉ አትቀላቀልም፤ እኛ በነበርንበት ምድብ እንደ እነ ሀምበርቾ፣ ሀላባ ከተማ፣ ነቀምት ከተማና ጋሞ ጪንቻን የመሳሰሉት ጠንካራ ቡድኖችም ነበሩና ብዙ ተፈትነን እንደዚሁም ደግሞ “አንድ ጎል በአንድ ሚሊዮን ብር ከሚተመንበት ፈታኝ ሊግ መጥተን ነው የፕሪምየር ሊጉን የተቀላቀልነውና ለእዚህ ላበቃን አምላክ ምስጋና ይድረሰው”፡፡

ሊግ፡- በከፍተኛ ሊግ ተሳትፎአችሁ ዘንድሮ ፕሪምየር ሊጉን መቀላቀል ዋንኛ እቅዳችሁ ነበር?

አሰልጣኝ እስማሄል፡- በፍፁም፤ በዛ ደረጃ አስበን አልነበረም ወደ ውድድሩ የገባነው፤ እኛ ጠንካራ የሊጉ ተፎካካሪ ለመሆን ነበር ስንጫወት የነበርነው፤ ምክንያቱም ቡድናችን ባለፉት ዓመታት ላለመውረድ ሲጫወት ነበርና፡፡

ሊግ፡- ወደ ፕሪምየር ሊግ ማለፉን ግን አሳካችሁት?

አሰልጣኝ እስማሄል፡- ማንም በዚ ደረጃ እኛን ያሰበን አልነበረም፤ እንደሁም የትም አትደርሱም ተብለንም ነበር፤ በኋላ ላይ ግን ከጨዋታ ወደ ጨዋታ በምንጓዝበት ሰዓት ጠንካራ ተፎካካሪ ሆነንና እናሸንፋለንም ብለን ገብተን ስለምንጫወት ወደ ፕሪምየር ሊጉ የሚያሳልፈንን ውጤት ልናመጣ ቻልን፡፡

ሊግ፡- በውድድር ዘመን ጉዞአችሁ በተለየ መልኩ ያየከው ነገር ምንድን ነው?

አሰልጣኝ እስማሄል፡- ከሁሉ በላይ ቅድሚያ የምሰጠው የአሸናፊነት መንፈሳችንን ነው፣ ሌላው ጎሎችን የምናገባና ብዙ ጎል የማይቆጠርብንም መሆኑ ነው፤ በዘንድሮ ተሳትፎአችን ባደረግናቸው 22 ጨዋታዎች 2.5 ፐርሰንት ጎልን ስናስቆጥር 0.5 ፐርሰንት ደግሞ ጎሎች ያልተቆጠሩብን መሆኑን ስታይ ይህ ጥንካሬያችንን የሚያሳይም ነው፡፡

ሊግ፡- የአዲስ አበባ ከተማ እግር ኳስ ክለብን በወጣት ተጨዋቾች መገንባት መቻላችን ወደ ፕሪምየር ሊግ እንድናልፍ ካደረጉን ምክንያቶች ውስጥ አንዱ ነው ብለሃል፤ ተጨዋቾቹን በምን መስፈርት ልታመጧቸው ቻላችሁ?

አሰልጣኝ እስማሄል፡- ለአንድ እና ለሁለት ዓመታት ያህል እነዚህን ተጨዋቾች ከእኛ ተቃራኒ ሆነው ሲጫወቱ ስንመለከታቸው ነበር፤ ያኔም ስማቸውን ከየሚጫወቱበት ቦታም ጋር በመመዝገብ ስይዝም ነበር፤ ለአንድአንዶቹ ድጋፍ የምናደርግላቸውም ነበሩ፤ በተለይ ፍፁም ጥላሁንን በቡና የተተኪው ቡድን ውስጥ ከነበረበት ጊዜ ጀምሮ ወደ ክለቡ ለማምጣት ፍላጎት ቢኖረንም በአሰልጣኙ ፈቃደኛ አለመሆን አጥተነው ነው በድጋሚ ከከፋ በማስመጣት የቡድናችን ተጨዋች ልናደርገው የቻልነውና የምልመላችን መልካም መሆንም ነው ለስኬቱ እንድንበቃ ያደረገን፡፡

ሊግ፡- በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ምን አይነት ቡድንን ይዛችሁ ነው የምትቀርቡት?

አሰልጣኝ እስማሄል፡- በኳስ ዓለም ውስጥ ፍፁም ባትሆንም፤ ውለታ ባይኖርም የተወሰኑ ክፍተት ቦታዎች አሉብንና እነዛን እንሸፋፍናቸዋለን፤ የተሰራን ቡድን ማፍረስ ከባድም ነውና አብዛኛዎቹን ተጨዋቾች በማስቀረት ነው ጥሩ እግር ኳስን የሚጫወት ቡድንን ይዘን በመጪው ዓመት ላይ የምንቀርበው፡፡

ሊግ፡- ከኢትዮጵያ ቡናውና ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ስኬታማው ተጨዋች አቡበከር ናስር አንደበት የአንተ ስም በተደጋጋሚ ሲጠራና እስማሄል ይመስገንልኝ ሲልም ይሰማል፤ በእዚህ ዙሪያ እና ስለ ችሎታው የምትለው ነገር ካለ?

አሰልጣኝ እስማሄል፡- አቡበከር ናስርን እናቱ ወልደዋለች፤ ለእሱ እዚህ ደረጃ ላይ መድረስም ብዙዎች አስተዋፅኦም አላቸው፤ ከእነዛ መካከልም እሱ እኔን በተደጋጋሚ ያመስግነኝ እንጂ ከእኛ በላይ መመስገን ያለበት የሐረር ሲቲ ክለብ ባለቤት የነበረው ነዲን አህመድ ነው፤ እሱ በግል ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ በማውጣት ያቋቋመው ቡድን ውስጥ በመጫወቱ ነው ለእዚህ ደረጃ ሊበቃም የቻለው፤  እኛም ልጅ ሆነን ስላገኘነው እና መልምለንም ስላሰለጠንነው ነው እድለኛ የሆንነው፤ እሱን በተመለከተ መጀመሪያ ላይ በሰፈሩ ጉቶ ሜዳ ነው የእኛ የሐረር ሲቲ የታዳጊ ቡድን በመጣበት ወቅት የሰፈሩ ልጆች ካላስሞከራችሁት ሜዳ አንለቅም ሲሉን ተውነው፤ ያኔ እኔ ራሴን አሞኝ ስለነበር አልመጣሁም ነበር፤ ከቀናት በኋላ በነበረው ልምምድ ግን ያ ቀጭን የነበረው ልጅ 22 መገናኛ አካባቢ በሚገኘው ሜዳ ላይ ለምርጫ በመጣበት ወቅት ነው ልመርጠው የቻልኩት፤ ይህን ተጨዋች በአንድ የወዳጅነት ግጥሚያም ላይ 4 ደቂቃ ሲቀር ቀይሬ አስገብቼውም ሁለት ለጎል የሚሆን ኳስ በማቀበልም ልዩ ችሎታ እንዳለውም አሳይቷል፤ ከዛ ውጪ ለኢትዮጵያ ታዳጊ ብሔራዊ ቡድን የእኛ ሁለቱ ሚኪያሶች በተመረጡበት ወቅትም በጊዜው የቡድኑ አሰልጣኝ ለነበረው አጥናፉ ዓለሙ የአቡበከርን ችሎታ ስለማውቅ አንድ ያልታየ ልጅ አለ ብዬ ስነግረውና ፈቃደኛ ሆኖም ሊመለከተው ስለቻለም ጭምር ነው የእኔን ስም በመጥራት ስላሰለጠንኩትም ሊጠራኝ የቻለው፤ የአቡበከርን ችሎታ በተመለከተ ለእኔ አሁንም ገና ነው፤ ችሎታውን  ከዚህ በላይ ማሳደግ አለበት፤ ያኔም ለታላቅ ደረጃ የመብቃት እምቅ አቅምም አለው፡፡

ሊግ፡- በመጨረሻ?

አሰልጣኝ እስማሄል፡- ለመላው የእስልምና እምነት ተከታዮች በሙሉ እንኳን ለኢድ አልፈጥር በዓል አደረሳችሁ እላለው፤ ከዛ በመቀጠል ደግሞ ወደ አሰልጣኝነቱ ሙያ ከገባሁበት ጊዜ ጀምሮ ከእኔ ጎን በመሆን ጥሩ እገዛን ያደረጉልኝ አካላቶች አሉ፤ እነሱም ባለቤቴ ዚያዳ ሻሚል፣ የቀድሞ እግር ኳስ ተጨዋች ያሬድ የማነ፣ ገዛኸኝ መንግስቴና ሀብታሙ ደነቀ በስራዬ ላይ ጥሩ ክትትልና ድጋፍን ሲያደርጉልኝ ነበርና ለእነሱ ምስጋናዬን አቀርባለው፤ ሌላው ላመሰግናቸው የምፈልገው በስልጠናው ዓለም ላይ ኮርሶችን ከመስጠት ጀምሮ በሙያዬ በጥሩ መልኩ እንድጓዝ እያደረጉኝ ያሉት ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱና ኢንስትራክተር ዳንኤል ገብረ ማሪያምም አሉና እነሱና አጠቃላይ የአዲስ አበባ ከተማ እግር ኳስ ክለብ አባላቶችና አመራሮችም ይመስገኑልኝ፡፡

ይህን ካልኩ አንድ ልጨምር የምፈልገው ነገር መንግስት የሐረር ሲቲን ቡድን በአንድ ወቅት ብዙ ገንዘባቸውን በማውጣት ላቋቋሙት እንደ አቶ ነዲን አህመድ ያሉ ባለሀብቶችን በማበረታታት እና በመደገፍ ወደ ስፖርቱ የሚመጡበትን መንገድ ቢፈልግ ሀገር በእግር ኳሱ እንደምታድግ ነው፡፡

spot_img
ተመሳሳይ ጽሁፎች

አስተያይት ያስፍሩ

እባክዎን አስተያይትዎን ያስፍሩ
እባክዎን ስምዎን እዚህ ያስገቡ

ትኩስ ዜናዎች

%d bloggers like this:
P