በአሁን ሰዓት በፕሪምየር ሊጉ ባህርዳር ከተማን በማሰልጠን ላይ ይገኛል፤ ከእዛ በፊት በነበረው የሙያው ቆይታው ደግሞ ከፕሮጀክት ቡድን አንስቶ ወልቂጤ ከተማን ጨምሮ የተለያዩ ክለቦችን ማለትም ባህርዳር ከተማን በረዳትነትና እንደዚሁም ደግሞ ደብረማርቆስ ዩንቨርስቲን ሌላው ከከፍተኛው ሊግ ወደ ሱፐር ሊግ ሊያስገባው የቻለውን አውስኮድን ኢትዮጵያ ውሃ ስራዎችን ኢኮስኮንና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ለማሰልጠንም ችሏል።
ይህ አሰልጣኝ የባህርዳር ከተማ ያፈራው ደግአረገ ይግዛው ሲሆን በሙያ ቆይታው በፊዚካል ኢዱኬሽን ኤንድ ስፖርት ዲፕሎማና በስፖርት ሳይንስ ደግሞ የመጀመሪያውን ድግሪውን ለመያዝ የቻለ ነው። በአሰልጣኝነቱም እስከ ካፍ ኤ ላይሰንስ ድረስም ሊጓዝ ችሏል። ከእዚህ አሰልጣኝ ጋር የሊግ ስፖርት ጋዜጠኛው ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ /G.BOYS/ ከቡድናቸው ጋር በተያያዘና ሌሎችንም ጥያቄዎች አንስቶለት ተከታዩን ምላሽ ሊሰጥ ችሏል፤ ተከታተሉት።
ሊግ፦ በቅድሚያ ለቃለ- ምልልሱ ፈቃደኛ ስለሆንክ ከልብ እናመሰግናለን?
ደግአረገ፦ እኔም በጣም አመሰግናለሁ።
ሊግ፦ በባህርዳር ከተማ የአምስት ሳምንታት ቆይታ ነበራችሁ፤ ያ ጊዜ በእናንተ በኩል እንዴትና በምን መልኩ አለፈ?
ደግአረገ፦ ያው ውድድሩን እንደተመለከትከው የፕሪምየር ሊጉ ፉክክር ትንሽ ጠንከራ ነው፤ ይሄን ክለብ ስረከብና ቡድኑንም ስቀላቀል ስራዎቹ ፈታኞችም ናቸው ሀላፊነቱም ቀላል እንዳልነበሩም የተረዳዋቸው ነገሮች ነበሩ፤ ያም ሆኖ ግን ስራዎችን ስትሰራና አንድ ነገርን አሳካለው ብለህ ስታስብ አልጋ በአልጋ የሆነ ነገር እንደማይጠብቅህም የተረዳዋቸው ነገሮች ነበሩና ይሄን ከባድ ሀላፊነትን ስረከብ ለውጥ አመጣለሁ የሚል ስሜቱም አብሮኝ ስለነበር እያንዳንዱ ጨዋታና ቀን ለእኔ ፈታኝ ነበር። ከእዛ ውጪም ተጨዋቾቼ ለስራ ያላቸው ተነሳሽነትም ከፍተኛ በመሆኑና የኮቺንግ ስታፉም በቀናነት በጥሩ መልኩ በስራ እያገዙኝም በመሆኑ ስራዬን አቅልሎኝ ቆይቷል። በእዚህ የውድድር ቆይታዬም ከምንም ነገር በላይ ደግሞ የቀድሞ የቡድኑ አሰልጣኝ ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱም በዝግጅት ወቅት የተሰሩ ስራዎች ምን ይመስሉ እንደነበሩና የተጨዋቾቻችን ስብስብና የመጡበትን መንገድ በተመከተም ምን ይመስላል በሚልም ክሊር በሆነ ሁኔታ ከክለቡ የቴክኒክ ስታፍ ጋር በመሆንም ገለፃ የተደረገልኝ ነገር ስላለና ከገለፃው ውጪም ይህ ትልቅ እገዛም ነው በአርድ ኮፒ የነበሩ ስራዎችን በተመለከተም ሊሰጠኝ በመቻሉና እንዳገኝም በመደረጉ በእዚሁ አጋጣሚ ኢንስትራክተሩ የሰሩትን ስራ ሳላደንቅም አላልፍም። የእሳቸው ስራ ለአገራችንም ትልቅ ተሞክሮ ነውም ብዬ አስባለሁ። በሙያው እንዲህ ያሉ ሽግግሮች በሌሎች ክለቦች ቢኖርም ለስፖርታችን እድገት ጥሩ ነው ብዬም አስባለሁና ለስራዬ መቃናት ተጨዋቾቹ ባሉበት ክለቡ ምን መልክ እንዳለሁ ያወቅኩበት ሁኔታም አለና ይሄ ስራዬን ሊያቀልልኝ ችሏል። ስለ አምስት ሳምንቱ ውድድር በተመለከተ ጨዋታዎቹ ከተማችን ላይ እንደመካሄዱ ትልቅ ድባብና ድምቀት ነበረው። ተጨዋቾቻችንም በእያንዳንዱ ጨዋታ ላይ መሻሻሎችንም ያሳዩበት ነው። ከጨዋታ ወደ ጨዋታ በቡድናችን ላይም እድገቶችንም ተመልክተንበታል። የሚቀሩን ነገሮች እንዳሉ አመላካች ሁኔታዎችንም አይተንበታል። ከእዚህ መነሻነትም በቀሪዎቹ ጨዋታዎቻችን ላይ ክፍተቶቻችንን በመመልከት የተሻለ ቡድን ለመገንባት ጥረትን እናደርጋለን። በእስከአሁኑ ጉዞአችን የውጤት መመዘኛው ብዙ ስለሆነ የተመዘገበው ስኬት ለእኛ ጥሩ የሚባል ውጤት ነው። ሆኖም ግን እንደ ቡድን ለመቃኘት የምፈልገው ከጨዋታ ወደ ጨዋታ ለውጥ ያሳየንበትና በራስ የመተማመን ብቃታቸውም ከፍ እያለ የሄደበት ሁኔታም ነበርና የባህርዳር ከተማ ቆይታችን መልካም የሚባል ነው።
ሊግ፦ ወደ ድሬዳዋ በማምራትም ቀጣይ ግጥሚያዎችን ማድረግ ጀምራችኋል፤ የውድድር ዘመኑ ሲጠናቀቅ እናንተ ምን ውጤትን ማምጣት አልማችኋል?
ደግአረገ፦ በድሬዳዋ ከተማ ያደረግነው የመጀመሪያው ጨዋታችን ጠንካራውን መድን ተፋልመን ነው 3-2 የረታንበት ሁኔታ የነበረው። ይህ ውጤት ከመመራት ተነስተንም ያሸነፍንበት በመሆኑ ለእኛ መልካም የሚባል ውጤትም ነው። በእዛ ጨዋታ ተደጋጋሚ የጎል እድሎችን ለመፍጠር በመቻላችንና በስነ-ልቦናው በኩልም ልጆቻችን ጥሩ ሆነው ስለተገኙም ጨዋታውን ለማሸነፍ ችለናል። ይሄ የአሸናፊነት ጉዞም እንዲቀጥልም እንፈልጋለን። ከእዛም ውጪም በዕለቱ ፍልሚያ በራሳችን ጥንቃቄ ጉድለትም ጎሎችን ልናስተናግድ የቻልንበት አጋጣሚም ነበርና ይሄን ለቀጣዩ ጊዜ ልናርመው ይገባል። የውድድር ዘመኑ ሲጠናቀቅ ከወዲሁ እኛ ልናሳካው ያሰብነው ግብ በሁለት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ደጋፊዎቻችን የሚደሰቱበትና ለሀገር ኩራት ሊሆን የሚችለውንም ጠንካራውን ባህርዳር ከተማ ክለብን ለመገንባት እና ከእዛ ውጪም አስተማማኝ በሆነ ውጤትም የውድድር ዘመኑን የሚጨርስ ቡድን እንዲኖረንም ነው እየሰራን የምንገኘው።
ሊግ፦ የእዚህ ቡድን ጠንካራና ክፍተት ጎኑ ምንድን ነው?
ደግአረገ፦ በእስካሁኑ የውድድር ጉዞአችን በተለያዩ መንገዶች ቡድናችንን እንደተመለከትኩት ብዙ ስራዎችን የሚጠይቁና በግልፅም የሚታዩ ነገሮች አሉ። ጠንካራው ጎናችን እንደ ቡድን ለመጫወት መሞከራችንና ልጆቻችን ለስራቸው ያላቸው ተነሳሽነት ጥሩ መሆኑ ነው። ክለቡ የአንድ ሰው ጥገኛ እንዲሆን አለመፈለጋችንም ጥሩ ጎን ነው። የመድኑን ጨዋታ እንደተመለከትከው በሶስቱም የጨዋታ ዲፓርትመንት ላይ የሚገኙ ተጨዋቾች ናቸው ማለትም የተከላካይ ክፍሉ ተጨዋች ተስፋዬ፣ የአማካይ ክፍሉ ተጨዋች ፉዐድና የአጥቂው ክፍሉ ተጨዋች በሀብታሙ አማካኝነት ጎሎችን ለማስቆጠር የቻልነውና ቡድናችን በእዚህ መልኩ እንዲገነባም ነው የምንፈልገው። ጎል ከየትኛውም ተጨዋች እንዲገኝም እንፈልጋለን። እንደ ክፍተት የማየው ነገር ደግሞ አንድ ነገርን ብቻ ነቅሰን የምናወጣው አይደለም። በሂደት ልንጠግናቸው እና ልናሻሽላቸው የሚገቡ ነገሮች አሉ። በየቦታው የቡድኑን ባለንስ ማስተካከል ይጠበቅብናል። ከእዛ ውጪም ወደ ሶስተኛው የግብ ክልል ብንደርስም የጎል እድሎችን ብንፈጥርም አጨራረሱ ላይ ያሉብን ክፍተቶች ስላሉ እነዛ የሚታረሙ ይሆናል።
ሊግ፦ የሊጉ ቡድኖች በተቀራረበ ነጥብ ላይ ይገኛሉ፤ በውድድር ዘመኑ እናንተን የትኛው ቡድን ያሰጋችኋል? የእዚህ ዓመት ውድድርንስ ማን በበላይነት ያጠናቅቃል?
ደግአረገ፦ አሁን ባለው ሁኔታ አሸናፊውን ክለብ ቀድሞ ማወቅና መለየት አይቻልም። ከወዲሁ ድምዳሜ መስጠትም ይከብዳል። እንደ እኔ እይታ የዘንድሮ እያንዳንዱን ጨዋታ ሳየው ግጥሚያው ክፍት ነው፤ ማንም ሻምፒዮና መሆን ይችላል። ማንም ደግሞ ከስጋት ነፃ ሊሆንም አይችልም። እኛም በእንደዚህ አይነት እቅፍ ውስጥ ጭምርም ነው የምንገኘው። አሁን ላይ ከመሪዎቹ ተርታ አካባቢ ብንገኝም በተቻለን አቅምና መጠን የነቃ ተሳትፎን በማድረግ የአመቱ መጨረሻ ላይ የምናመጣውን ውጤት አብረን የምናየው ነው የሚሆነው። ለእኛ ስጋት ሊሆንብን የሚችለውን ቡድን በተመለከተ እኛ ለሁሉም ክለቦች እኩል ክብር ነው ያለን ተወዳዳሪዎቹ ጠንካራ ስለሆኑም ስጋቶች የሚሆኑብን ሁሉም ናቸው። አሸናፊውን ቡድን በተመለከተ ከላይ እንደገለፅኩትም ቡድኖች በወጥ አቋም ላይ የማይገኙበት ሁኔታ ስላለ አሁን ላይ ባለድሉን ቡድን ማወቅ አይቻልም።
ሊግ፦ በአማራ ደርቢ ጨዋታ ከፋሲል ከነማ ጋር አቻ ለመለያየት ችላችሁ ነበር፤ ያን ግጥሚያ በምን መልኩ ገልፀህ ታልፈዋለህ?
ደግአረገ፦ የደርቢው ጨዋታ ልዩ ድባብ የታየበት ነበር፤ በተለይም ከተመልካች ጋር ተያይዞ ከሶስት ቀናቶች በፊት ጀምሮ ጥሩ ድባብ እንዲኖረው የተደረገበትና ለከተማውም ስፖርት መነቃቃትን የፈጠረ ነው ብዬም አስባለሁ። ይህ የደርቢ ጨዋታ አንተም ከእዚህ በፊት እንደምታውቀው የቅ/ጊዮርጊስና የኢትዮጵያ ቡና ደርቢ ጨዋታ ነበር የሚታወቀው፤ አሁን ግን ያን የሚወዳደር ምንአልባትም ደግሞ ወደፊት ትልቅ ትኩረትን የሚስብ የደርቢ ጨዋታ ይሆናል ብዬ አስባለውና ይሄ ጨዋታ ፍፁም ስፖርታዊ ጨዋነት በተሞላበት ሁኔታ በመጠናቀቁ በጣም ደስ ብሎኛል። ሌሎች ውድድሮችም በእዚህ መልኩ ቢጠናቀቁ ጥሩም ነው እላለሁ። በሜዳ ላይ ስለነበረው እንቅስቃሴ ጨዋታው ለተመልካች አዝናኝ ነበር። ብዙ የግብ ዕድሎች የተፈጠሩበት ሁኔታም ስለነበር ሰዉ ተደስቶ የወጣበት ግጥሚያም ነበር። ይህ ግጥሚያ በአቻ ውጤት ቢጠናቀቅም ከጨዋታውም ሶስት ነጥብ ይዘን መውጣት የነበረብን ግን እኛ ነበርን።
ሊግ፦ የፍፁም ቅጣት ምቱ ሲሰጥባችሁ በውስጥህ ምን አይነት ስሜት አደረብህ?
ደግአረገ፦ በጨዋታው ጥሩ እንቅስቃሴ እያደረግን ስለነበርና የግብ ዕድሎችንም እየፈጠርን ስለነበርን ከእዛ ውጪም በየትኛውም ሰዓት ላይ ጎል እንደምናስቆጥርም እምነቱ ስለነበረኝ ያን ያህል የተፈጠረብኝ መጥፎ ስሜት አልነበረም። እኔ እንደውም የፍፁም ቅጣት ምቱ ሲሰጥ ልጆቹን እንዲረጋጉም ነው ሳደርግ የነበረው ምክንያቱም ፋሲሎች ያን የፍፁም ቅጣት ምት ያገኙት እኛ ጥሩ በሆንበት ሰዓት ነው። ግጥሚያውን ማሸነፍ የምንችልበት ሁኔታ ሊኖር እንደሚችልም ስነግራቸውም ነበርና ያን ሁኔታን ጭምርም ነው ስመለከት የነበረው።
ሊግ፦ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ታሪክ ውስጥ ብዙ ስራ ሰርተው ያለፉ ፈጣሪ ነፍሳቸውን ይማረውና ኢንስትራክተር መንግስቱ ወርቁ፣ ማስተር ቴክኒሺያን ሀጎስ ደስታ፣ አሰልጣኝ ስዩም አባተ እንደዚሁም ደግሞ አሁን ያሉት ኢንስትራክተር ካሳሁን ተካ፣ አሰልጣኝ አስራት ሀይሌ፣ ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ፣ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ የመሳሰሉት ባለሙያተኞች ተብሎ በእናንተ ደረጃ ላይ ተደርሷል፤ እነሱን በእዚሁ መልኩ ካነሳን አንተ በምን መልኩ የምትገለፅ አሰልጣኝ ነህ?
ደግአረገ፦ የጠራካቸው አሰልጣኞች በሙሉ ለሀገራቸው እግር ኳስ ትልቅ ድርሻቸውን ያበረከቱና ብዙም የደከሙ ናቸው። እንደ አጋጣሚ ሆኖ ደግሞ ከጠራካቸው አሰልጣኞች ውስጥ በኢንስትራክተር መንግስቱ ወርቁ፣ በኢንስትራክተር ካሳሁን ተካና በአሰልጣኝ አስራት ሀይሌ እንደየቅደም ተከተላቸው ተጨዋች ሆኜ በቅ/ጊዮርጊስ፣ በባህር ሀይልና በጉምሩክ ቡድኖች ውስጥ ሰልጥኜም አሳልፌያለውና ያ እኔን እድለኛ ያደርገኛል። እንደ ሙያው ቆይታዬ እነሱን ስመለከት ለእግር ኳሱ የየራሳቸውን አስተዋፅኦ ለእግር ኳሱ አበርክተዋል። ከእዛ መነሻነት ራሴን አሁን ላይ ስመለከት በእነሱ ደረጃ ላይ መቀመጥ ይኖርብኛል ብዬ አላስብም። እኔ ከፊቴ ብዙ ስራ የሚጠብቀኝ አሰልጣኝ ነኝ። በጀማሪ ደረጃ የምገኝም ነኝ። ያም ሆኖ ግን እልሜ ሩቅ ነው። በስፖርቱ መድረስ የሚገባኝ ጥግ ቦታ ድረስ መድረስ እፈልጋለሁ። ስራዬን በቁርጠኝነት እየሰራውም ነው የምገኘው። ያን እልሜንም እንደማሳካው እርግጠኛ ነኝ።
ሊግ፦ ከአንተ የፕሮጀክት ቡድን የወጡና ጥሩም ደረጃ ላይ የደረሱ ተጨዋቾች እንዳሉ አውቃለሁ፤ ስለ እነሱ ምን ማለት ይቻላል? በተለይ አሁን ላይ ለክለብህ እየተጫወተ ስለሚገኘው በረከት ምን ትላለህ?
ደግአረገ፦ አዎን፤ ለእዛ ደረጃ የደረሱ ብዙ ተጨዋቾችን መጥቀስ ይቻላል። ከእነዛም መካከል ያሬድ ባየህ እስከ ብሄራዊ ቡድን ደረጃ ላይ ሊደርስ ችሏል። ከእኔ ጋር አሁን በድጋሚ ስራም ላይ ተገናኜተናል። አሁን ላይ ደግሞ ሌላኛውን ተጨዋች በረከትንም መጥቀስ ይቻላል። ይህን ተጨዋች በተመለከተ መናገር የምፈልገው እሱ ጠንካራ የሆነ ልጅ ነው። ከልጅነቱ ጀምሮ የራሱን ጥረት ስላደረገም ነው ለእዚህ ደረጃ የበቃው፤ የሰውነት ብቃቱን ስትመለከት በብዙ ሰዎች እይታ ውስጥ የሚገባ ተጨዋች አይደለም። የበረከት የአህምሮ ጥንካሬውም በጣም ይገርመኛል። ታክቲክን የመረዳት አቅሙም ከፍ ያለ ነው። በአስተማማኝ ሁኔታም ለክለባችን እየተጫወተም ነውና ወደፊት ትልቅ ደረጃ ላይም ይደርሳል።
ሊግ፦ የእግር ኳስ ተጨዋች ነበርክ፤ ወደፊት አሰልጣኝ እሆናለው ብለህ ሩቅ አልመህ ነበር?
ደግአረገ፦ የተጨዋችነት ዘመን ላይ ሆነህ ይህን ነገር አታስበውም። በጣም የሚገርም አጋጣሚ ግን ያኔ በዝግጅት ወቅት ላይ የምንሰራቸውን ስራዎች የመፃፍ እና በአህምሮዬ የማስቀመጥ ተሰጥኦ ነበረኝ። ከረጅም አመታት በፊትም ኢንስትራክተር መንግስቱ ወርቁ አሁን ላይ ነፍሱን ፈጣሪ ይማረውና በገነት ሆቴል ውስጥ በቲዎሪ ደረጃ የክላስ ትምህርት ሲሰጠን በማስታወሻዬ እይዝ ስለነበርና በባህርዳር ውስጥም ላሰለጠኑኝ አሰልጣኞች ለምሳሌ አሁን ላይ የበረኛ አሰልጣኝ ሆኖ እያገለገለ ለሚገኘው የቀድሞው የቡድኑ አሰልጣኝ አሻግሬና ጋሽ ግርማን ለመሳሰሉ ባለሙያተኞች እሰጣቸውም ነበርና ያኔ አሰልጣኝ ስለመሆን ጭራሽ አላሰብኩም ነበር። በኋላ ላይ ግን ወደ ስልጠናው ውስጥ ገብቶ ስለመስራቱ ተነሳሽነቱ ስላደረብኝ ተጨዋች ሆኜ ነው ኢንስትራክተር ካሳሁን ተካ የሰጡትን የአንደኛ ደረጃ ኮርስ ከወሰድኩ በኋላ አሁን ላይ እስከ ካፍ ኤ ላይሰንስ በመድረስ ሙያው ላይ ዘልቄ ገብቼበት እየሰራው ነው የምገኘው።
ሊግ፦ በፕሪምየር ሊግ ደረጃ ስታሰለጥን ወልቂጤ ከተማ ለአንተ የመጀመሪያ የሊጉ ክለብህ ነው?
ደግአረገ፦ አዎን። ይሄ ቡድን ለእኔ ብዙ ትምህርትን ያስገኘልኝ ክለብ ነው። ከህዝብ ጋር ያስተዋወቀኝም ነው። በሁለት ዓመት የክለቡ ቆይታዬም ከእዚህ ቡድን ጋር በተያያዘ ህዝቡ ኳስን በጣም እንደሚወድ ተመልክቻለሁ። ጠንካራ ቡድንንም ለመስራት ችለናል። ያን ቆይታዬን መቼም ቢሆን የማልረሳውና የተደሰትኩበትም ነው። በተለይም የክለቡ ፕሬዘዝዳንት አቶ አበባው ሰለሞን ከክለቡም ሆነ ከእኔ ጎን ሆኖ ብዙ ስራን የሰራ በመሆኑ እሱንና የቦርዱን አመራሮች እንደዚሁም ደጋፊዎቹን ለማመስገን እፈልጋለው። ለእነሱ ያለኝ አክብሮትም ከፍ ያለ ነው።
ሊግ፦ ስለ ቤተሰብህ አንድ ነገር በለን?
ደግአረገ፦ ባለትዳርና የሶስት ልጆች አባት ነኝ፤ ለእነሱ ትልቅ አክብሮትም አለኝ። በተለይም ደግሞ ባለቤቴ ውጤት በመጣም ሆነ ባጣን ሰዓት ነገሮችን ቀለል በማድረግ ለስራዬ መቃናት ብዙ ነገሮችን እያገዘችኝ ነውና እሷ እንድትመሰገንልኝ እፈልጋለሁ።
ሊግ፦ በመጨረሻ?
ደግአረገ፦ በእስከዛሬ የሙያ ቆይታዬ ከጎኔ ሆነው ብዙ የረዱኝ አካላቶች አሉ። ከእነዛ መካከልም በጣም ላመሰግናቸው ከምፈልጋቸው ሰዎች መካከል የቅርብ ጎደኞቼ የሆኑት ትንሳሄ ካሳን /ቡቹ/ እና አሁን ላይ የኢትዮጵያ ቡና የቡድን መሪ የሆነውን ሙልጌታ አስፋውን ነው። ከእነሱ ሌላም ወላጅ እናቴም የጋዜጠኞች ትንተና ሁሉ አይቀራትም ብዙ ነገሮችን ለእኔ ትነግረኛለችምና እሷም ትመስገንልኝ። በመጨረሻም የባህርዳር ከተማ የቦርድ አመራሮችና ደጋፊዎችም በእኔ ላይ እምነትን ጥለው ስራዬን እንድሰራ እያደረጉኝ ስለሆኑም እነሱም ይመስገኑ።