Google search engine

“ለዋንጫው ለመፎካከር የሚያግደን ነገር የለም” “የትኩረት ማጣት ችግራችንና ቸልተኛ መሆናችን ወደ ቀጣዩ ዙር እንዳናልፍ አድርጎናል” አስቻለው ታመነ (ፋሲል ከነማ)    

 

ፋሲል ከነማ ከአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ካፕ የውድድር ተሳትፎው በሁለተኛው ዙር ላይ ተሰናብቶ ከወጣ በኋላ ወደ ሀገር ውስጥ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታው ሊመለስ ችሏል።

የፋሲል ከነማው የአማካይ ስፍራ ተጨዋች አስቻለው ታመነም ቡድናቸው በቱኒዚያው ክለብ ሴፋክሲያን በአጠቃላይ ውጤት 1-0 ተሸንፎ ከውድድሩ ከወጣ በኋላ ስለነበራቸው ተሳትፎ፣  ከቡድናቸው ጋር በተያያዘ እና ሌሎችንም ጥያቄዎች በማከል ከጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ /G.BOYS/ ለቀረቡለት ጥያቄዎች ምላሹን ሊሰጥ ችሏል።

ቃለ-ምልልሱም በሚከተለው መልኩ ቀርቧል።

ሊግ፦ በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ካፕ በቱኒዚያው ክለብ ሴፋክሲያን በጠባብ ውጤት በመሸነፍ የሁለተኛው ዙር ላይ ልትሰናበቱ ችላችኋል፤ ከውድድሩ ለመውጣታችሁ ምክንያቱ ምንድን ነበር?

አስቻለው፦ የብሩንዲውን ክለብ በመጀመሪያው ዙር ላይ ስንፋለም በሜዳችን ላይ ውጤቱን ጨርሰን ስለሄድን ነበር በመልሱ ጨዋታ ብዙም ሳንቸገር ወደ ቀጣዩ ዙር ያለፍነው። በሁለተኛው ዙር ላይ ግን ምንም እንኳን ከትልቅ ቡድን ጋር ብንጫወትም ማለፍ የምንችልባቸው አጋጣሚዎች ሊኖሩን ቢችሉም የሜዳችን ጨዋታ ላይ አሸንፈን ባለመሄዳችን ምክንያት እና የመልሱ ጨዋታ ላይም በተለይም ደግሞ ተጭነናቸው ለመጫወት ብንችልም አቻ ልንወጣም የምንችልበት ዕድል ሊኖረን ቢችልም ከዳኝነት በደሎች ጋር በተያያዘ ብዙ ነገር ተደርጎብን ያን ለመቋቋም የቻልንበት አጋጣሚ ቢኖርም በእግር ኳስ ላይ በሚፈጠር አጋጣሚ በጠባብ ውጤት ተሸንፈን ከውድድሩ ልንሰናበት ችለናል።

ሊግ፦ የኢትዮጵያ ቡድኖችም ሆኑ የብሄራዊ ቡድናችን ቀደም ሲል በነበሩት ዓመታት ላይ አብዛኛውን  ጊዜ ከሰሜን አፍሪካ ክለቦች ጋር ሲጫወቱ በመልሱ ጨዋታ ላይ ብዙ ግብን ያስተናግዱ ነበር፤ እናንተ ግን በጠባብ ውጤት ለመሸነፍ ችላችኋል፤ ይህ ሊሆን የቻለበት ምክንያት አለ?

አስቻለው፦ በእርግጥ ከእዚህ ቀደም ተደርገው በነበሩ አንድ አንድ የመልስ ጨዋታዎች ላይ ጥሩ ውጤትን ያስመዘገቡ እና ወደ ተከታዩ ዙርም ያለፉ አንዳንድ ቡድኖቻችን ቢኖሩም አሁን አሁን ላይ ግን ቡድኖች የኢትዮጵያ ክለቦቹን ሊገጥሙ ሲመጡ እንደ በፊቱ አይነት እቅድ የላቸውም፤ በብሄራዊ ቡድን ደረጃም ሆነ በክለብ ደረጃ እየተለወጥን ስለመጣንና በተለይም ደግሞ በብሄራዊ ቡድን ደረጃ ስኬታማ በመሆን ላይ ስላለን የሚሰጠን ግምት ጥሩ ስለሆነ እንደከዚህ ቀደሙም ስንት እናግባባቸው የሚለው ነገር አሁን ላይ ስለቀረና በሜዳቸው ላይም ቻሌንጅ ስላደረግናቸው ነው በጠባብ ውጤት የተሸነፍነው። በመልሱ ጨዋታ ወደ ቀጣዩ ዙር ሊያሳልፈን የሚችል ዕድልም ሊገጥመን ከጫፍ ደርሶ ነበር። ይህ ሁሉ ሊሆን የቻለውም በብሄራዊ ቡድናችን ስኬታማ መሆን መቻልና ኳሳችን ደግሞ በዲ ኤስ ቲቪ እየታየ ስለሆነና ለውጥንም እያሳየ ስለሆነ የእነዚህ ድምር ውጤትም ነው በጠባብ ውጤት ለመሸነፍ ምክንያት የሆነን።

ሊግ፦ ከኢንተርናሽናል ውድድር መልስ ወደ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ተሳትፎ ተመልሳችኋል፤ ከፋሲል ከነማ ምን ውጤት ይጠበቅ?

አስቻለው፦ ፋሲል ከነማ ሀገሪቷ ውስጥ ካሉት ክለቦች ትልቁ እና ጠንካራ የሆነም ነው፤ ሁሌ የሚጫወተው ሻምፒዮና ለመሆንም ነው። አሁን ላይ በእዚህ ሰዓት ከኢንተርናሽናል የውድድር ተሳትፎ ውጪ በመሆናችን ሀሳባችን ሳይበታተን የኳሱን ትኩረት ወደ ሀገር ውስጥ የሊግ ውድድር አድርገናል። ከአመራሮቻችን ከሚሰጡን መመሪያዎች በመነሳትም ሆነ የራሳችን እቅድም ጭምር ስለሆነ ሊጉን ከዜሮ በመጀመርና በነጥብ ከሚበልጡን ቡድኖች ጋርም ያለንን የነጥብ ልዩነት አጥብበን ለሻምፒዮናነትም ነው የምንጫወተው።

ሊግ፦ በቤትኪኔጉ የአምስተኛው ሳምንት ጨዋታ የቀድሞ ቡድንህን የምትፋለምበት አጋጣሚ ይኖርሃል፤ በእዚህ ጨዋታ ዙሪያ የምትለው ነገር ካለ ?

አስቻለው፦ ቅ/ጊዮርጊስ የሀገሪቷ ትልቁ እና  የቀድሞ ክለቤ ቢሆንም ግጥሚያውን በተለየ መልኩ የምጠብቅበት ሁኔታ አይኖርም። ለሁሉም  ቡድኖች እንደምዘጋጀው ግጥሚያም ነው ለውድድሩ በጥሩ ስነ-ልቦና ላይ ሆኜ የምዘጋጀው። አሁን ትንሽ ትልቅ የምትለው ቡድን የለም። ሁሉም ፈታኝም ናቸው። ቻሌንጅ ተደራርገህም ነው የምትሸናነፈው።

ሊግ፦ ባለፈው ዓመት የሊጉን ዋንጫ አጥታችኋል፤ ዘንድሮስ?

አስቻለው፦ የእኛ ዓላማ እና እቅድ ከስራ አመራሮቹም ሆነ ቦርዱ ለእኛም ሆነ ለአሰልጣኞቹ እንደተነገረን  ሻምፒዮና መሆን ነው። ከእዛም በተጨማሪ በኢንተርናሽናል የውድድር መድረክ ላይ ከእዚህ ቀደም በነበረን ያለፉት ተከታታይ ዓመታቶች ላይ የመጀመሪያ ዙር ላይ ነበር የምንወድቀው። ዘንድሮ ያ ሪከርድ ተሻሽሏል። በቀጣይ ጊዜ ላይ ደግሞ የክለቡን አንድ ደረጃ ከፍ አድርጎ ማሳየት ከእኛ የሚጠበቅ ነው።

ሊግ፦ በክረምቱ የተጨዋቾች ዝውውር መስኮት ክለባችሁ እንደ እነ ያሬድ ባየህን፣ ሙጂብ ቃሲምን፣ በረከት ደስታን የመሳሰሉ ወሳኝ ተጨዋቾችን ሊያጣ መቻሉ አይጎዳውም? ስለ አዲሱ ስብስባችሁስ ምን ነገርን ትላለህ?

አስቻለው፦  አንድ ቡድን የሚመሰረተው ረጅም ጊዜ አብሮ በመቆየት ነው። አብሮ ሲቆይም ቡድኑ ውስጥ የሚያመጣው ጥሩነት አለ። በደንብም ትላመዳለህ። ክለባችንን የለቀቁት ልጆች ለፋሲል ከነማ ትልቅ ነገርን የሰሩ ናቸው። ለወደፊቱም ብዙ ነገርን ለሚጫወቱባቸው ክለቦች መስራት ይችላሉና እነሱ የመረጡትን አድርገዋል። የሄዱት ተጨዋቾች እንደሚጎዱን ግልፅም ነው። ወደ እኛ ቡድን ስለተቀላቀሉት አዳዲስ ተጨዋቾች ደግሞ ማለት የምፈልገው ቡድኑን እየተላመዱትና እየተዋሀዱት ሲመጡ  ጥሩ ነገሮችን ይሰራሉ ብዬም ነው የማስበው።  ከእኛ ጋር በመሆንም ጥሩ ውጤትን እንድናመጣም ይረዱናል ብዬም አስባለው።

ሊግ፦ በቤትኪንጉ የእዚህ ዓመት የውድድር ፉክክር ምን መልክ ይኖረዋል ብለህ ታስባለህ?

አስቻለው፦ ውድድሩ ምንም የሚገመት ነገር አይኖረውም። እንደከዚህ በፊቱ የሊጉን ዋንጫ የእከሌ ቡድን ይበለዋልም አትልም። ሜዳ ላይ እንደምናየው ተመጣጣኝ የሆነ ነገርን እየተመለከትንም ነው። ትልቅ ቡድን የምትለው ትንሹን ሲያሸንፍ ተፎካክሮት ነው። ተፈትኖም ነው የሚያሸንፈውና ከወዲሁ እከሌ ሻምፒዮና ይሆናል፤ እከሌ ይወርዳል የምትልበት ጊዜ አይደለም፤ ሊጉ ገፋ ሲል ስለ ሁሉም ነገር ብንናገርም ነው የሚሻለው።

ሊግ፦ በውድድር ዘመኑ አንተንስ በምን መልኩ እንጠብቅህ፤ በቅ/ጊዮርጊስ የነበረህን የቀድሞ ብቃትህን ዳግም ታሳያለህ?

አስቻለው፦ አዎ፤ የመጀመሪያ እቅዴ ከቡድኔ ጋር ሻምፒዮና መሆን መቻል ነው። አስታክኬ ደግሞ ዓምና ወደ ፋሲል ከነማ ቡድን መጥቼ በጉዳትና በሌሎች ምክንያቶች የሚጠበቅብኝን አቋሜን አላሳየሁም፤ ጥሩ ጊዜንም አላሳለፍኩም ነበር። ከእዛ በመነሳት ዘንድሮ በመልካም ጤንነት ላይ ስለሆንኩና ፈጣሪም ጤናውን በእዚህ መልኩ አስቀጥሎልኝ ልጓዝ እንጂ የሚያውቀኝ ህዝብ በሚጠብቀኝ መልኩ ነው መጓዝን የምፈልገው።

ይቀጥላል

ሊግ፦ እንደ እናንተ ሁሉ በኢንተርናሽናል ውድድር ላይ ዘንድሮ የተሳተፈው የቀድሞ ቡድንህ በመጀመሪያው ዙር ላይ ከውድድሩ ወጥቷል፤ የሜዳ ላይ የመጀመሪያ ጨዋታን አለመጠቀም መቻል ክለቦቻችንን እየጎዳ ነው ማለት ይቻላል?

አስቻለው፦ አዎን ከላይም ገልጬዋለሁ። ቅ/ጊዮርጊስ በሜዳው አሸንፏል። ግን ግብ ማስተናገዱ ሊጎዳው ችሏል። በሜዳችን ላይ ስንጫወት ያሉት መዘናጋቶች የትኩረት ማጣት እና ቸልተኛነታችን ነው እየጎዱን ያሉት። እነዛ ምክንያቶች ዋጋ እያስከፈሉንም ነው። ቅ/ጊዮርጊስ የወደቀውም በእዚሁ ችግር ነው።

ሊግ፦  ወደ ብሄራዊ ቡድን እናምራ በአልጄሪያ የምናደርገው የቻን ተሳትፎ አለ፤ ከእዛ ውጪም የአፍሪካ የማጣሪያ ጨዋታዎች አሉብን፤ በእነዚህ ዙሪያዎች ላይ ምን አልክ?

አስቻለው፦ አሁን ላይ በጥሩ መስመር ላይ የሚገኝ ቡድን ነው ያለን። በሚገባም የተገነባ ቡድን አለን።  እግር ኳስ በተጨዋቾች ዘንድ አብሮ መቆየት ውጤትን ያስገኝልሃል። ይሄን አሁን ያለው አሰልጣኝም በሚገባ ያምንበታል። ቡድኑን ስለሚያውቀው የእሱ መቆየትም ጥሩ ነው። በእሱ ፍልስፍናና ሀሳብ ውስጥም እየሄደ ያለ ነው። ሪትም ውስጥ የገባ ቡድን ስላለንና ጠንካራም ስለሆንን ጥሩ ውጤትን እናመጣለን። እንደ ግል ደግሞ አንድ ነገር ማለት የምፈልገው ከእዚ በፊት በውድድሮቹ ላይ ውጤት ባይቀናንም ተሳትፎ ያደረግኩበት ጊዜ ነበር፤ አሁን ላይ ግን በጥሩ ሁኔታ የሚገኝ ቡድን ስላለን ታሪክ ለመስራት ዝግጁ ነኝ።

ሊግ፦ አንድ ነገር በማለት ወደ ማጠቃለሉ እናምራ?

አስቻለው፦ ስለ ክለቤ ፋሲል ከነማ ሳወጋ ባለፉት አራት እና አምስት አመታቶች ላይ ትልቅነቱን ያስመሰከረ ቡድን ነው። ሁሌም ለሻምፒዮናነት ነው የሚጫወተው። ለእዚህ ክለብ የቡድኑም ካፒቴን ነኝና በእኔ የአመራር ዘመን እንደ ግል የሚጠበቅብኝን ነገር በማድረግ ክለቡ ዋንጫ እንዲያነሳ ምኞቴ ነው። በግሌም እንደ ቡድንም የዘንድሮ ሻምፒዮና ለመሆንም ነው የተዘጋጀነው።

spot_img
ተመሳሳይ ጽሁፎች

አስተያይት ያስፍሩ

እባክዎን አስተያይትዎን ያስፍሩ
እባክዎን ስምዎን እዚህ ያስገቡ

ትኩስ ዜናዎች

%d bloggers like this:
P