አቡበከር ኑሪ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ላይ ኢትዮጵያ መድንን በግብ ጠባቂነት በማገልገል ከጓደኞቹ ጋር በመሆን ቡድኑን በጥሩ ጎዳና ላይ እንዲጓዝ እያደረገው ይገኛል። ወጣቱ ግብ ጠባቂ ይህ አዲሱ ክለቡ እስካሁን ከተጫወተባቸው ክለቦችም ለእሱ በስኬት እየተጓዘበት ያለ ከመሆኑ ባሻገርም የመሰለፍ ዕድሉንም በተደጋጋሚ ጊዜ እያገኘበት በመሆኑም ጥሩ የእግር ኳስ ህይወትን በማሳለፍ ላይ እንደሚገኝበትም ለሊግ ስፖርት ጋዜጣ ከጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ /G.BOYS/ ጋር በነበረው ቆይታ ሊገልፅ ችሏል።
ሊግ ስፖርት ጋዜጣና የኢትዮጵያ መድኑ ግብ ጠባቂ አቡበከር ኑሪ በክለባቸው የሊጉ ተሳትፎ ዙሪያና ሌሎችን ተያያዥ የሆኑ ጉዳዮችን እንደዚሁም ደግሞ ስለ ራሱም የተለያዩ ጥያቄዎችን አቅርበንለት ምላሹን በሚከተለው መልኩ ሰጥቷል፤ ተከታተሉት።
የእረፍት ወቅት ላይ ስለነበራችሁ ቆይታ እና አሁን ላይ ወደ ሊጉ ውድድር ለመመለስ እያደረጋችሁት ባለው ዝግጅት ላይ ስላለው ልዩነት
“የእረፍት ወቅት ላይ ስትሆን እንደ ውድድር ጊዜ አይደለም ራስህን የምታገኘው፤ ምክንያቱም በእዛን ወቅት ላይ ታርፋለህ። ይሄ እረፍት ደግሞ ለአንድ አንድ ቡድኖች ጥቅሞች እንዳሉት ሁሉ ጉዳቶችም አሉት። ይኸውም ጥሩ ውጤት ለሌላቸው ቡድኖች ይሄ እረፍት ራሳቸውን የሚመለከቱበትን ሁኔታ ስለሚፈጥርላቸው ይጠቅማቸዋል ብዬ አስባለሁ። ጥሩ መንገድ ላይ ላሉ ቡድኖች ደግሞ ከጨዋታ ሪትም እንዲወጡ ያደርጋቸዋል ብዬም ነው የማስበው። የእኛን ቡድን በተመለከተ ግን ከእረፍቱ መልስ ወደ ልምምድ የገባነው በጊዜ ነው”።
የሊጉ ውድድር የተቋረጠው እናንተ እየመራችሁ ነበር፤ ከእረፍት መልስ ልምምድን በጊዜ መጀመራችሁ አይጎዳችሁም ማለት ነው?
“እኛን የሚጎዳን ነገር አለ ብዬ አላስብም። ምክንያቱም ከላይ እንደገለፅኩት ቶሎ ወደ ልምምድ ገብተን ከዛሬ ለነገ የተሻለ ነገርን ለማድረግ ስለምንፈልግ ስራችንን በተጠናከረ መልኩ እየሰራን ስለሆነ ነው። በእዛ ላይ ደግሞ የሊጉ መሪ ስለሆንም ሁሉም ቡድን ከእዚህ በኋላና በተለይም ደግሞ የሁለተኛው ዙር በቅርቡ ሲጀመር ለእኛ ጠንክሮና የተለየ ትኩረትም ሰጥቶ ነው የሚመጣብንና ጨዋታዎቹ ሁሉ ከባዶች ናቸው። ያም ሆኖ ግን እኛም ለሚመጡብን ነገሮች ሁሉ ምላሾቹን ለመስጠት ተዘጋጅተናል”።
ኢትዮጵያ መድንን ብዙዎቹ ሰርፕራይዝ ቡድን ነው ስለማለታቸው
“እንደዛ ማለታቸው ትክክል ናቸው። ምክንያቱም ይሄ ቡድን ከታች የመጣና ሊጉን ሲጀምር ደግሞ በአስከፊ ሽንፈት ወደ ጨዋታው የገባ ስለነበርና ከእዛም ሽንፈት ብዙ ነገሮችን በመማር የሊጉ አናት ላይ ሊቀመጥ ስለቻለም ነው”።
ለኢትዮጵያ መድን ሰርፕራይዝ ቡድን ብቻ መባል በቂ ነው ትላለህ?
“አልልም፤ እኛ ከትናንት ዛሬ የተሻለ ነገርን ለመስራት የምንፈልግና ጥረታችንን ሁሉ አጠናክረን በማስጓዝ በሊጉ የተሻለ የሚባል ውጤትን ማስመዝገብ የምንፈልግ ነን”።
የአንደኛው ዙር ቀሪ ሁለት ጨዋታዎች እና የሁለተኛው ዙር ግጥሚያዎችም በቅርቡ የሚከናወኑ ይሆናል፤ የዓመቱ ውድድር ሲጠናቀቅ የት ስፍራ ላይ የምናገኛችሁ ይሆናል?
“የሊጉ ውድድር ሲጀመር ማንኛውም ቡድን ከስር ዲቪዥን ሲመጣ ብዙ ጊዜ ሊጉ ላይ ስለመቆየትን ነው የሚያስበው፤ እኛም ያሰብነው ያንኑ ነው። አሁንም ሊጉ ገና ነው። ብዙ ጨዋታዎች ይቀሩታል። ከእዚህ በመነሳት ሊጉን በእዚህ ደረጃ ላይ ሆነን እናጠናቅቃለን ለማለት ጊዜው አይደለም። ሆኖም ግን እንደ ቡድናችን ሁሉም ተጨዋቾች እሳቤና እምነት ለክለቡ የሚመጥን የተሻለ የሚባል ውጤትን ይዘን ውድድራችንን እናጠናቅቃለን”።
ስለ ሊጉ አጠቃላይ ፉክክር
“ዲ. ኤስ. ቲቪ ከመጣ በኋላ በየጨዋታዎቹ ደስ የሚሉ ነገሮች አሉ። ግጥሚያዎቹ በአንድ በተወሰኑ ቦታዎች ላይ መካሄዳቸው ደግሞ ደጋፊ ላለውም ለሌለውም ቡድን አድቫንቴጁ አንድ ነው ብዬም አስባለሁ። ስለ አጠቃላይ ፉክክሩ ካነሳው ደግሞ የዘንድሮው ውድድር እንደ አምናው ይሆናል ብዬ አስባለሁ። በተለይም ደግሞ ሁለተኛው ዙር ላይ ሁሉም ቡድን ተጠናክሮም ስለሚመጣ ተመልካቹም ጥሩ ነገርን የሚመለከት ይመስለኛል”።
በእኛ ሀገር የሊግ ውድድር ከመላቀቅ ጋር በተያያዘ ብዙ ነገር ተብሎ አልፏል። በእዚህ ዙሪያ ማለት የምትፈልገው ነገር ካለ
“እንዲህ ያሉ ሁኔታዎች እግር ኳስን ወደ ኋላ የሚያስቀሩ ነገሮች ናቸው፤ ያለ ላብህ የምታገኘውም ውጤት ስለሆነም ብዙ ሊሰማህም ይገባል። ኳስ ተጨዋች ስትሆን እንዲህ ያሉ ነገሮች ይገባሃል። የእኛን ኳስን ወደ ኋላ ያስቀረው አንዱ ሁኔታም ይሄ ነውና ድርጊቱ ሊወገዝ ይገባል። ከእዚህ በኋላም ይከሰታል ብዬ አላስብም”።
በመላቀቅ ዙሪያ ዳግም እንዳይኖር ልታስተላልፍ የምትፈልገው ገንቢ መልዕክት
“እግር ኳስ በእኛ ሀገር ገና ነው፤ ብዙ ነገሮችም ይቀረናል፤ አንድ ቡድን በአቅሙና በአቅሙ ብቻ ተጫውቶ ከሜዳ መውጣት እንዳለበትና የላቡን ውጤት ብቻም ማግኘትን እንዳለበት ልናሳውቀው ይገባል። እንዲህ ያሉ ሁኔታዎች ደግሞ በቀጣይነት ወደ ስፖርቱ የሚመጡት ተተኪ ተጨዋቾች ስለሆኑ ለእነዚህ ለታዳጊ ወጣቶችም ጥሩ ነገሮችን ነው አስመልክተን ማለፍ ያለብን ነገ ለሚሰራው ወጣትም ይህ ነገርን ስታሳውቀው እሱም ለሌሎች በመንገር ኳሳችንን በጥሩ ጉዞ ማስኬድ ይቻላል”።
ለኢትዮጵያ መድን በቀጣይነት ሊበረቱበት እና አስቸጋሪ ሊሆኑበት ስለሚችሉት ጨዋታዎች
“ሁሉም ጨዋታዎች ለእኛ ፈታኞች ናቸው፤ ለብቻ ነጥለህ የምትመለከታቸው ግጥሚያዎች የሉም። ምክንያቱም ቡድናችን መሪ ነው። ከመሪ ጋር ስትጫወት ደግሞ ከታች ያለው በጣም ጠንክሮ መጥቶ ይፈትንሃል። ከአጠገብህ ያለውም የአንተን ደረጃ መንጠቅ ስለሚፈልግ ሁሉም ግጥሚያዎቻችን ሁሉ ለእኛ ፈታኞች ናቸው”።
በጣም ጠንካራ እና ካልሆኑ ቡድኖች ጋር ልትጫወቱ ወደ ሜዳ ስትገቡ አሰልጣኛችሁ ስለሚላችሁ ነገር
“ከእዚህ በፊት ለአንድና ለሁለት ክለቦች ሊጉ ላይ ተጫውቼ አሳልፌያለሁ። ወደ ኢትዮጵያ መድን ሳመራ ግን አንድ የተመለከትኩትና የተለየም ነገር ብዬ ያሰብኩት የእያንዳንዱ ቡድን የጨዋታ ኳሊቲ የሚለያይ ቢሆንም ለሁሉም ጨዋታ እኩል ትኩረትን ሰጥተን እንድንገባና ምን ላይ ነው ሰርተን የምንገባውም በሚል አሰልጣኛችን የሚነግረን”።
በኢትዮጵያ መድን ውስጥ በተለየ ሁኔታ የተመለከትከው ነገር
“ከቀድሞ ተጫውቼ ካሳለፍኩባቸው ክለቦች አንፃር በመድን ውስጥ ለእኔ የተለየና በአዲስ መልክ የተመለከትኩት ነገር በእዚህ ቡድን ውስጥ ሆኜ ጥሩ ውጤትን እያስመዘገብን መሆናችንና እኔም ጥሩ የውድድር ሲዝንን እያሳለፍኩኝ ያለሁበት ወቅት መሆኑ ነው። ከእዛ ውጪም ይሄን ክለብ ለየት የሚያደርገው በፋይናንሺያልና በደመወዝ የሚታማም ክለብ ያለመሆኑ ነው፤ ሌላው ደግሞ ህብረታችን ከሁሉም ነገር በላይ ደስ ይላል”።
ለኢትዮጵያ መድን በቋሚ ተሰላፊነት እየተጫወተ ስለመሆኑ
“ይሄን የመጫወት ዕድል ማግኘት ትልቅ ነገር ነው፤ ምክንያቱም ማንኛውም ግብ ጠባቂ ቋሚ ተሰላፊ ሆኖ መጫወትን ይፈልጋል። እኛ ሀገር ደግሞ ብዙዎቹ ክለቦች የውጪ ሀገር ግብ ጠባቂዎችን ነው የሚጠቀሙት ወደ እኛ ጋር ስትመጣ ግን ክለባችን ለሀገር በማሰቡና የሀገር ውስጥ በረኞችንም መጠቀም በመፈለጉ ሶስታችንንም ወጣት በረኞች ከሀገር ውስጥ በመምረጥ እየተጠቀመብን ነው የሚገኘው ወጣቶችና ። ይሄ ለሀገሪቷ ታስቦ የተሰራ ስራ ይመስለኛል። እንደ ክለባችን ሁሉ አሰልጣኛችንም ገብረመድህን ሀይሌ ለሀገር በማሰብ እሱም እየተጠቀመብን ይገኛልና ይሄ ሁኔታ ለሌሎቹ ትምህርት ሰጪም ነው፤ ምክንያቱም እኛ ሀገር ላይ ጥሩ ጥሩ በረኞች አሉ ያጡት የመጫወት ዕድል ነው፤ ወደፊት እምነቱ ከተጣለባቸው ብዙ በረኞች መውጣታቸው የማይቀር ነው”።
ስለ ቀጣይ ጊዜ የኳስ ህይወትና እልሙ
“ብዙ ጊዜ ሰው ስለወደፊቱ ይጨነቃል፤ ያስባል። እኔ ደግሞ ከእዛ ውስጥ የለሁበትም። ምክንያቱም ሁሌም የማስበው ዛሬን ነው። ዛሬን ጠንክረህ ስትሰራም ነው ነገ ለትልቅ ደረጃ የምትበቃው። እኔ ሁሌም የማስበው ዛሬ ያለሁበትን ክለብ በተቻለኝ መጠን ጥሩ ደረጃ ላይ ማድረስና የራሴንም ብቃት ካለፈው ጨዋታ አሻሽዬ በማቅረብ የተሻለ ቦታ ላይ ስለማድረስ ነው”።
ተስፈኛ የሆንክ ግብ ጠባቂ ነህ፤ ወደፊት ለሚመጡ ግብ ጠባቂዎች ማስተላለፍ የምትፈልገው ነገር ካለ
“የምመክራቸው ኳስ የአህምሮ ጨዋታ እንደሆነና ሙያውንም ወደውትም እንዲሰሩት ነው፤ ከእዛ ውጪ ለትልቅ ደረጃ ላይ ለመብቃት የማይቻል ነገር የለም ብዬ ስለማስብም ብዙም መጨነቅ እንደሌለባቸውና ጠንክረው ስራቸውን እንዲሰሩም ነው የምመክራቸው”።
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በቻን የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ስለነበረው ተሳትፎ
“እግር ኳስ ሂደት /ፕሮሰስ/ ነው። ብሄራዊ ቡድናችን በአልጄሪያ ላይ በነበረው ተሳትፎው ተጨዋቾቻችን ጥሩ ልምድን አግኝተውበታል ብዬ አስባለሁ። ሀገርን ወክሎ መጫወት ከባድ ነገር ነው። ስለዚህም ከአሁን በኋላ ይበልጥ ጠንክረን ሰርተን በመምጣት ከሁለት እስከ ስምንት ለሚደርሱ ዓመታት የተሻለ የሚባል ቡድንን ይዘን ልንመጣ ይገባናል”።
ብዙ ጊዜ ቡድኖችም ሆኑ ብሄራዊ ቡድኖች ሽንፈት ሲገጥማቸው ለውጤቱ መታጣት የቅድሚያ ተጠያቂዎች ሲሆኑ የሚታዩት በረኞች ስለመሆናቸው
“የባህርማዶዎቹን ጨምሮ ብዙ ቪዲዮችን እከታተላለሁ። ያን ሳይ የእኛ ፖዚሽን የተለየ የሆነበት ምክንያትም ከላይ ባነሳከው ሀሳብ ይመስለኛልና ለእዛም ነው ነገሮች እኛ ላይ የሚያነጣጥሩት። ምክንያቱም ግብ ጠባቂ ማለት በእግር ኳስ የክለቡን 50 ፐርሰንት ይሸፍናል ነው የሚባለው። በጨዋታ ወቅት አጥቂ ቢሳሳት አማካዩ ይሸፍንለታል። አማካዩ ቢሳሳት ደግሞ ተከላካዩ ይሸፍንለታል። በረኛ ቢሳሳት ግን ኳሷ በቀጥታ ከመረብ ጋር ነው የምትገናኘውና ለእዛ ይመስለኛል እኛ ላይ ትኩረት የሚደረገው። በተለይም ደግሞ በኢትዮጵያ ኳስ ላይ የማይወጣ ኳስ ሲገባ ለሰበቡ በረኛ ይባላል። ስለዚህም ለሁሉም ነገር አስፈላጊው ለበረኞች ትዕግስት መስጠትም ነው። አሰልጣኞችም ጥሩ ጥሩ በረኞችን ካመጡም ድንቅ ድንቅ በረኞችን ሀገራችን እንደሚኖሯትም እምነቴ ነው”።
ከባህርማዶ ስለሚደግፈው ክለብ
“የማንቸስተር ዩናይትድ ደጋፊ ነኝ”።
እሁድ ዕለት አርሰናል 3-2 ማንቸስተር ዩናይትድ የሚል ውጤት ተመዘገበ፤ ስሜትህ በጣም ተጎዳህ?
“የአርሰናል ደጋፊዎች እየጮሁብኝና እያበሸቁኝ ስለነበር ስሜቴ ያን ያህል ባይጎዳም በዕለቱ ግን ትንሽ ደብሮኛል። ያም ሆኖ ግን ማንቼ በጥሩ ሂደት ላይ ያለና ለወደፊቱም ተስፋ ያለው ቡድን ቢሆንም እኛን ያሸነፈው አርሰናል ግን ማሸነፍ የሚገባው ቡድን ነው”።
የእንግሊዝን ፕሪምየር ሊግ ዋንጫ ማን ያነሳል?
“ማንቸስተር ሲቲ”።
ሊጉን እየመራ ያለው ግን አርሰናል ነው፤ ማን. ሲቲ ዋንጫ ያነሳል ያልከው አንተ የማንቸስተር ዩናይትድ ስለሆንክ ነው ወይንስ…?
“ማን ሲቲ ዋንጫ ያነሳል ያልኩት የማን. ዩናይትድ ደጋፊ ስለሆንኩ አይደለም። አርሰናል አሁን ላይ ሊጉን መምራቱ ይገባዋል። ውድድሩ ግን ገና ነው። ማን. ሲቲ ልምድ ያለዎ ቡድን ነው። ከእዛም ባሻገር ስኳዱም በጣም ሰፊ ነው። በተቃራኒው አርሰናል ደግሞ ስኳዱ ሰፊ አይደለም አንድ ተጨዋች ከተጎዳበት ቡድኑ ስለሚሳሳ ጭምርም ነው ሲቲን ዋንጫ ያነሳል ያልኩት”።
ማን.ዩናይትድ የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫን ካነሳ በርካታ ዓመታትን እያስቆጠረ ስለመምጣቱና እንደ ደጋፊነትህ አንተ ጋር ስላለው ስሜት
“ማንቸስተር ዩናይትድን የደገፍኩት ከልጅነቴ ዕድሜ አንስቶ ነው፤ ለመደገፌም ምክንያት የሆነኝ የቀድሞው ግብ ጠባቂ ቫንደርሳርም ነው። እሱን ተመልክቼም ነው በክለቡ ደጋፊነት የተለከፍኩት። እንደውም የእኔ መጠሪያ ስሜ ቫንደርሳርም ነው። ክለብን ስደግፍ ዋንጫ ደስታን ሊሰጥህ ቢችልም ወሳኝ ነው ብዬ ግን እኔ አላስብም። ማንቸስተርን እኔ ስደግፍ ዋንጫን ያውቅ የነበረ ነው። ለመደገፌ ግን ምክንያቱ ዋንጫው ሳይሆን ቫንደርሰርን ስለምወደው ነበርና ከእዛን ጊዜ ጀምሮ ደጋፊ ሆኛለሁ”።
ከእግር ኳሱ ውጪ የተለየ ሆቢህ ምንድን ነው?
“ዋና ደስ ይለኛል፤ ከእዛ ውጪ ደግሞ የፕሌይ ስቴሽን ጌሞችን እጫወታለሁ። በእዛም ጊዜዬን አሳልፋለሁ”።
ከሰዎች ባህሪያት የሚያስደስትህ እና የማያስደስትህ
“ትክክለኛ እና ፊት ለፊት የሚናገር እኔም እንደዛ ስለሆንኩኝ እንዲህ ያሉ ሰዎች በጣም ያስደስቱኛል። ከእዚህ በተቃራኒህ የሆኑ ሰዎች ደግሞ ፈፅሞ አይመቹኝም”።
በበጎ አድራጎት ስራዎች ላይ ተሰማርቶ ያውቅ እንደሆነ
“በእኛ እምነት እንዲህ ያሉ ነገሮች ሲደረጉና በስራው ላይ ስትሰማራህ ሰዎች እንደ እይታህ እንዲመለከትብህ ስለማትፈልግና እንዲህ ነው ብሎ መናገርንም ስለማትፈልግ መረዳዳቱና መተጋገዙ ኖሮ ከብዙ ነገሮች ግን ትርቃለህ። ለወደፊቱ ግን በተለይም በክረምቱ ወራት ላይ በተወለድኩበት አካባቢ በበጎ አድራጎት ዙሪያ ያሰብኳቸው ነገሮች አሉና የእዛ ሰው ይበለን”።
አንድ የመጨረሻ ነገርን ተንፍስና ቆይታችንን እናጠቃል
“ኢትዮጵያ መድን በእዚህ የውድድር ዘመን ጥሩ ነገር እንዲገጥመው እኛ ጠንክረን እየሰራን ነው፤ ሊጉን ከፈጣሪ እርዳታ ጋር በጥሩ ውጤት እንደምናጠናቅቅም ተስፋ አደርጋለሁ። ሊጉን በጥሩ ሁኔታ እንድናጠናቅቅም ብዙዎቹ ምኞታቸውን እየገለፁልንም ነው የሚገኘው። ይሄን ካልኩ ወደ ምስጋና ላምራ ፈጣሪያችንን ዓላ አላምዱሊላህ ማለት እፈልጋለሁ። ቤተሰቦቼንና የኢትዮጵያ መድን አመራሮችንና የኮቺንግ ስታፉን አባላቶች ከእነሱ ውጪም የቡድን አጋር ጓደኞቼንም ለማመስገን እፈልጋለሁ”።