ለኢትዮጵያ ቡናና ለቡድኑ ደጋፊዎች “ትንሹ ልዑል” አቡበከር ናስር ቡድኑን ከተቀላቀለበት ጊዜ አንስቶ በሜዳ ላይ ለሰጣቸው ግልጋሎት የእንቁ ያህል ነው የሚመለከቱት፣ ይህ ድንቁ የአጥቂ ስፍራ ተጨዋች በኳስ ጨዋታ ዘመኑ ለቡና ሲጫወት 6 ዓመታት ቆይታ ያደረገ ሲሆን የተሳካ ጊዜንም አሳልፏል። ባሳለፍነው ዓመትም 29 ግቦችን አስቆጥሮ የጌታነህ ከበደን ሪከርድ በመስበር የምንጊዜውም የሊጉ ኮከብ ግብ አግቢ ተጨዋችነትን ክብርም ይዟል። አቡበከር በኳስ ተጨዋችነት ቆይታው ለቡናና ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድንም ሜዳ ሲገባ የሚያሳያቸው ልዩ የኳስ ጥበቡ እና ጎል አስቆጣሪነቱም የደቡብ አፍሪካውን ቡድን መመሎዲ ሰንዳዌንስን አማሎት ከእጁ እንዲያስገባው አድርጎት በመጪው ሳምንት መጀመሪያ ወደ አዲሱ ቡድኑ ለመቀላቀል ወደ ደቡብ አፍሪካ ያመራል።
የኢትዮጵያ ቡናው አቡበከርን ከክለቡ ጋር መለያየትን አስመልክቶም ተጨዋቹ የመጨረሻ ጨዋታውን ከአርባምንጭ ከተማ ጋር ትናንት ያደረገ ሲሆን የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎችም በባህርዳር ስታድየም ሽኝትን አድርገውለታል። ደጋፊዎቹና ክለቡም በደቡብ አፍሪካ የተሳካና መልካም ጊዜ እንዲገጥመውም ተመኝተውለታል። እሱም ለተደረገለት ሽኝት አመሰግናለው የሚል ቲሸርት አሰርቶ አፀፋዊ ምላሽን ለቡድኑ ደጋፊዎች፣ ለስፖርት ቤተሰቡ፣ ለሚዲያ እና ከእሱ ጎን ለሆኑት ሁሉ ሊሰጥም ችሏል። በዕለቱ ከአርባምንጭ ጋር በነበራቸው ጨዋታ ምንም እንኳን ሽንፈትን ቢያስተናግዱም ጨዋታውን ለመሩት አልቢትሮችም ምስጋናውን ገልጿል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የኢትዮጵያ ቡናው አቡበከር ናስር የመጨረሻ የክብር የሽኝት ፕሮግራም በነገው ዕለት የክለቡ ካምፕ በሚገኝበት ለቡ አካባቢ የሚደረግ ሲሆን በርካታ ደጋፊዎች እና የተጨዋቹ አድናቂዎች ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።