Google search engine

“አባቴን በቅርብ ለማስታመም ስልና በገ/መድህን ለመሰልጠን ሲዳማ ቡና ፈርሜያለሁ”ቴዎድሮስ ታፈሰ (ሲዳማ ቡና)

 

በመከላከያ ክለብ የተጨዋችነት ቆይታው ተስፋ ቡድኑን ጨምሮ ላለፉት ስምንት ዓመታት እግር ኳስን በጥሩ ብቃቱ ተጫውቶ አሳልፏል፤ በዚህ ቡድን ቆይታውም በቡድኑ የአማካይ ስፍራ ተጨዋችነቱ የሚያሳየው ምርጥ የጨዋታ እንቅስቃሴዎቹ በብዙዎቹ የእግር ኳስ ስፖርት አፍቃሪዎች ዘንድ እንዲያስደንቀው ቢያደርገውም የሊጉን ዋንጫ ለማንሳት ካልቻሉት ጥሩ ተጨዋቾች ውስጥ አንዱ መሆኑ ደግሞ እድለኛ እንዳይሆን አድርጎታል፡፡

የመከላከያ ክለብ ሲነሳ በመሀል ሜዳው ላይ 15 ቁጥርን አጥልቆ ስለሚጫወተው ቴዎድሮስ ታፈሰ የስፖርት ቤተሰቡና የእግር ኳሱ ባለሙያዎች በአድናቆት ብዙ ያሉ ሲሆን ይህ ተጨዋች በተለይ ለአጥቂ ክፍል የቡድን አጋሮቹ በሚያቀብላቸው ጣጣቸውን የጨረሱ ኳሶችና በቅጣት ምት አመታቱ እንደዚሁም ደግሞ በታታሪ ተጨዋችነቱና በአልሸነፍ ባይነቱም ተለይቶ የሚታወቅ ሲሆን በዘንድሮ የከፍተኛ ሊግ የውድድር ዘመን ወደ ታችኛው ሊግ ወርዶ የነበረውን ክለባቸውን ከሁለት ዓመት ቆይታ በኋላ ወደነበረበት ፕሪምየር ሊግ እንዲያልፍ በማስቻል ስላደረጉት ጥረት፣ እንደዚሁም በመከላከያ ክለብ ውስጥ ስለነበረው የእስካሁን ቆይታና በክረምቱ የተጨዋቾች ዝውውር መስኮት አሳዳጊ ክለቡን በመልቀቅ ወደ አዲሱ ክለቡ ሲዳማ ቡና ስላደረገው ዝውውር የሊግ ስፖርት ጋዜጣ አዘጋጅ ከሆነው ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ /G.BOYS/ ጋር ቆይታን አድርጎ ምላሽን ሰጥቶታል፤ ቃለ-ምልልሱም በሚከተለው መልኩ ቀርቧል፡፡

ሊግ፡- መከላከያ ከወረደበት ከፍተኛው ሊግ ወደሚያውቀው ፕሪምየር ሊግ ዳግም ተመልሷል፤ ለእዚህ ውጤት እንዴት ሊበቃ ቻለ?

ቴዎድሮስ፡- መከላከያ መጀመሪያ ወደታችኛው ሊግ ሲወርድ የወረደበት መንገድ በራሱም በውጪም ችግር የተነሳ አወራረዱ ጥሩ አልነበረምና ያ በሁሉም የቡድኑ ተጨዋቾችና አመራሮች ዘንድ ከፍተኛ የቁጭት ስሜትን ፈጥሮብን ስለነበር ይህን ቡድን ዳግም ወደነበረበት ሊግ መመለስ አለብን በሚል ከፍተኛ ስሜት ተነሳስተን በአሰልጣኛችን ጥሩ የአሰለጣጠን ብቃት በእኛ ተጨዋቾች ጥሩነት፣ በክለባችን አመራሮች ያላሰለሰ ድጋፍና በደጋፊዎቻችንም ከቡድኑ ጎን ቆመው በሚሰጡን ብርታት ይህን ታሪካዊ ክለብ የምድቡ አሸናፊ እንዲሆን በማድረግ ወደ ትልቅ ክለብነቱና ወደ ፕሪምየር ሊጉም እንዲቀላቀል አድርገነዋልና ይሄ ለመሆን በመቻሉ በጣም አስደስቶኛል፡፡

ሊግ፡- ወደ ፕሪምየር ሊጉ ያለፋችሁበት መንገድ ይገባችዋል?

ቴዎድሮስ፡-አዎን፤ ዓመቱን ሙሉ ማለት ይቻላል ጠንካራና ጥሩ ቡድን ነበረን፤ በስብስባችንም ምርጥ ተጨዋቾችን ይዘን ነው የተጓዝነው፤ ከዛ ውጪም ወደ ዝግጅት ጊዜው የገባነው በጊዜ ስለሆነም በአሰልጣኛችን ዩሃንስ ሳህሌ የተሰጠንን ታክቲክ በእልህና ቡድናችንም ወርዶ ስለነበርም በቁጭት ስሜት ላይ ሆነን ስራችንን በአግባቡ ስለሰራን ወደ ፕሪምየር ሊጉ ማለፋችን ሲያንሰን እንጂ የሚበዛብን አይደለም፡፡

ሊግ፡- በመከላከያ ውስጥ በነበረህ የተጨዋችነት ቆይታ ብዙ ሰዎች ችሎታህን አድንቀው አልፈዋል፤ በቡድኑ ስላሳለፍከው ጊዜ ምን ትላለህ? በአዲሱ ቡድን ቆይታህስ በመጪው ዓመት ላይ ምን ነገርን ታሳየናለህ?

ቴዎድሮስ፡- በቡድኑ ቆይታዬ በጣም ጥሩ ጊዜን ነበር ያሳለፍኩት፤ መከላከያ ደግሞ እኔን ከስር ጀምሮ ኮትኩቶ ያሳደገኝና ለከፍተኛ እውቅናም ያበቃኝ ቡድን ነውና ደስ በሚል መልኩ ነው ክለቡ ውስጥ ያሳለፍኩት፤ ባለፉት ስምንት ዓመታት ውስጥም ለቡድኑ ስጫወት ከተስፋ ቡድኑ ጋር አንድ ዋንጫን እንደዚሁም ደግሞ ወደ ዋናው ቡድን ካደግኩኝ በኋላም የጥሎ ማለፍን ዋንጫን ጨምሮ አሁን ላይ ከወረድንበት የከፍተኛው ሊግ ወደ ፕሪምየር ሊጉ በሻምፒዮናነት ምድባችንን በማጠናቀቅ ተጨማሪ ዋንጫንም በቆይታዬ ያገኘሁበት ጊዜም ስለነበር ለቡድኑ የነበረኝ ፍቅር ጥልቅ ነበር፤ ለዚህ ቡድን ስጫወትም በሜዳ ላይ በማሳየው የኳስ ብቃት በብዙዎች የስፖርቱ አፍቃሪዎች እይታ ውስጥ በመግባት አድናቆትን ያገኘሁበት አጋጣሚ ስለነበርና በዛ ውስጥ በማለፌም በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡ ይሄ የኳስ ብቃቴ በአዲሱ ቡድኔ ሲዳማ ቡና ውስጥም ዋናው ነገር ቀድሞ ያውቀኝና ያሰለጥነኝ የነበረውን የአሰልጣኜን ምክር መስማት መቻልም ነውና በጥሩ ችሎታዬ ዳግም እንደምቀጥልም እርግጠኛ ነኝ፡፡

ሊግ፡- ያሳደገክን ከዚህ በፊት ደግሞ አልለየውም ያልከውን ክለብ ግን ከስምንት ዓመታት በኋላ ዘንድሮ ለቀክህ፤ ምነው?

ቴዎድሮስ፡- የእውነት ነው፤ መከላከያ ለእኔ ካደረገልኝ ጥሩ ነገሮች አኳያ ይህን አሳዳጊዬን ቡድን ባለቀው እና ባልለየው ኖሮ እመርጥ ነበር፤ ቡድኑን አሁን ላይ እንድለቅ ያደረገኝ ግን ምክንያት ኖሮኝ ነው፡፡

ሊግ፡- ያን ምክንያት ግልፅ ብታደርግልን?

ቴዎድሮስ፡- ወላጅ አባቴ በተደጋጋሚ ጊዜ ህምምን የሚያስተናግድ ስለሆነ እኔ ከእሱ ርቄ ነበር ኳሱን እየተጫወትኩ የነበርኩት፤ አባቴን እየተመላለስኩም ለማሳከም ሞክሬያለው፤ አሁን በክረምቱ ወራት ራሱ እንኳን እሱን ታምሞ እያሳካምኩት ነው ያለሁት፤ ስለዚህም በዚህ ሁኔታ አባቴን በቅርብ ርቀት ላይ ሆኜ ለማስታመም ስልና ሌላው ደግሞ በመከላከያ ክለብ ውስጥ በነበርኩበት ሰዓት እኔን ከተስፋው ቡድን ወደ ዋናው ቡድን አሳድጎ እንድጫወት ባደረገኝ በአሰልጣኝ ገብረመድህን ሀይሌ ስርም መሰልጠኑን ስለፈለግኩኝ ሲዳማ ቡናን የቅድሚያ ምርጫዬ አድርጌ ለክለቡ ፊርማዬን ለማኖር ችያለው፡፡

ሊግ፡- ሲዳማ ቡናን በዝውውር መስኮቱ ከመቀላቀልህ አኳያ በመጪው ዓመት ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ተሳትፎ የተሳካ ጊዜያትን ታሳልፋለህ?

ቴዎድሮስ፡- ወደ ሲዳማ ቡና ያመራሁት ፈልጌና ወድጄ ነው፤ ከላይ በገለፅኳቸው ምክንያቶችም የቡድኑ ተጨዋች ሆኛለው፤ ይሄ ቡድን የሚሰለጥነው በውጤታማው አሰልጣኝ ገብረመድህን ሀይሌ በመሆኑ ወደ እሱ ጋር ሳመራ የምፈልገው ነገር አለ፤ ከዚህ በፊት በሌላ ክለብ ያላገኘሁትን የሊግ ዋንጫ በዚህ ቡድን ቆይታዬ ማግኘትን እፈልጋለው፤ በአሰልጣኙ ስር ሰልጥኜም በአቋሜ ላይ ከፍተኛ ለውጥን ማምጣት እፈልጋለውና የሲዳማ ቡና ቆይታዬ ቡድኑ እያስፈረማቸው ካሉት ጥሩ ጥሩ ተጨዋቾች አኳያም እየተጠናከረ ስለሆነ እንደ ግልም እንደ ቡድንም ፈጣሪ በፈቀደው መልኩ የተሳካ የውድድር ዘመን እንደሚሆንልኝ ከወዲሁ አስባለው፡፡

ሊግ፡- በመከላከያ ውስጥ በነበረህ ቆይታህ ለአንተ አሳዛኙ ጊዜ የቱ ነበር?

ቴዎድሮስ፡- በ2011 ዓ/ም በነበረን የፕሪምየር ሊጉ ተሳትፎ ቡድናችን የወረደበትን ጊዜ ነው የምጠቅሰው፤ ውሃ እያሳሳቀ ይወስዳል እንደሚለው ተረት አይነትም ጭምር ነበር ከሊጉ የወረድነው፤ ያ ጊዜ ለእኛ ከባድም ነበር፤ ያም ሆኖ ግን ይህን ቡድን ብዙ ለፍተን ዘንድሮ እንዲመለስ አድርገነዋልና ያ የቁጭት ስሜት አሁን ከውስጤ ሊጠፋ ችሏል፡፡

ሊግ፡- መከላከያ ወርዶ አንተ ቡድኑን አለቀቅክም ነበር፤ ለዛ ምክንያት አለህ?

ቴዎድሮስ፡- አዎን፤ ይሄ ቡድን ለእኔ ብዙ ነገሮችን አድርጎልኛል፤ ከፍተኛ ባለውለተኛዬም ነው፤ ስለዚህም በችግሩ ጊዜም ከጎኑ መሆን አለብኝ፤ ይህ ቡድን ወርዶ የታሪክ ተወቃሽ መሆን የለብኝም፤ የድርሻዬንም ልወጣ ከሚል ስሜት ጭምርም ነው ከአሰልጣኛችን ዩሃንስ ሳህሌ ጋር በመነጋገር የጨረስኩትን ውል አራዝሜ ለቡድኑ በመጫወት ከጓደኞቼና ከአሰልጣኞቻችን ጋር በመተባበር ክለቡን ዳግም ወደ ፕሪምየር ሊጉ እንዲያልፍ ያስቻልነው፡፡

ሊግ፡- በመከላከያ ቡድን ቆይታህ ከጥሩ ተጨዋችነት ባሻገር በቅጣት ምት አጠቃቀምህም ተለይተህ ትታወቅ ነበር፤ ይሄ ልምድ ከየት መጣ?

ቴዎድሮስ፡-በሐዋሳ በነበርኩበት ሰዓት ልጅ ሆኜ የቅጣት ምትን በሰፈር ውስጥ እለማመድ ነበር፤ ያን አዳብሬ በመምጣት ነው አሁን ላይ ጥሩ ቅጣት ምት መቺ ለመሆን የቻልኩት፡፡

ሊግ፡- በመከላከያ 15 ቁጥር መለያ በአንተ ይለበሳል፤ ከቁጥሩ ጋር የተያያዘ  ትርጉም አለው?

ቴዎድሮስ፡- ይሄን መለያ እለብስ የነበርኩት ዝም ብዬ ነበር፤ በኋላ ላይ ግን በጣም የማደንቀው ሴስክ ፋብሪጋዝ ይህን ቁጥር ያደርግም ነበርና በዛ ደስ ብሎኝ ይሄን ቁጥር ወደድኩት፡፡

ሊግ፡- “አቱሼ” እያሉ ሲጠሩ ሰማን፤ የቅፅል ስም መጠሪያህ ነው? ምን ማለትስ ነው?

ቴዎድሮስ፡- ስያሜው ምን ማለት እንደሆነ አላውቅም እንጂ በተደጋጋሚ ጊዜ በዚህ ስም ነው ጓደኞቼ የሚጠሩኝ፤ አሁን እንደ ቅፅል ስሜ ያህልም ሆኗል፤ እናቴም ደግሞ አቡሽ እያለች ትጠራኛለችና መጠሪያ ስሜ ከወዲሁ እየጨመረ ሊመጣ ነው መሰለኝ፡፡

ሊግ፡- የዘንድሮ እረፍት ጊዜህን በምን መልኩ እያሳለፍክ ነው?

ቴዎድሮስ፡- ልክ ውድድራችንን እንዳጠናቀቅን በፊትም ከሰፈርና ከቤት ብዙ አልወጣም ነበርና የዘንድሮውንም ደግሞ በህመም ላይ የሚገኘውን አባቴን በማስታመም ነው ጊዜውን እያሳለፍኩ ያለሁት፤ አሁን ላይ በአባቴ ጤንነት ላይም ጥሩ ነገርን እየተመለከትኩም ነው የምገኘው፡፡

ሊግ፡- ስለ ውሃ አጣጪህ የምትለን ነገር ካለ?

ቴዎድሮስ፡- እሷ ወደ መከላከያ ተስፋ ቡድን ሳልመጣ ጀምሮ አብረን ስለተማርን ጥሩና ምርጧ  ጓደኛዬ ናት፤ አሁን ላይ አብረንም ነው ያለነው፤ ሀና ኤልያስ ትባላለች፤ በጣም ጥሩ ሰው ናት፤ ከፈጣሪ የተሰጠችኝ የትዳር አጋሬም ናትና ከኳሱ ህይወቴ ጀርባ ለእኔ ለምታደርገው ነገር በሙሉ በጣም ላመሰግናት እፈልጋለው፡፡

ሊግ፡- ጣሊያን ሻምፒዮና የሆነችበትን የዘንድሮውን የአውሮፓ ዋንጫ የመከታተል እድል አግኝተሃል?

ቴዎድሮስ፡- አዎን፤ ጨዋታዎቹን ተመልክቼያለው፤ ጣሊያን በዚህ ውድድር ከሌሎቹ ሀገራት በተለየ መልኩ የተሻሉ ነገሮችን ስትሰራ ነበርና ያሳካችው ድል የሚገባት ነው፡፡

ሊግ፡- በመጨረሻ….?

ቴዎድሮስ፡- በእግር ኳስ ጨዋታ ዘመን ቆይታዬ ከክለብ ተጨዋችነት ጀምሮ እስከ ኢትዮጵያ ብሔራዊ የተተኪው ተስፋ ቡድን ድረስ ኳስን ልጫወት ችያለው፤ በኳስ ህይወቴም የሀገርን መለያ ጭምር አጥልቄ ስለተጫወትኩ በጣም ደስተኛ ነኝ፤ ከዚህ በኋላ በሚኖረኝ ቆይታ ደግሞ ባለኝ ብቃት ላይ የእግር ኳስ ባለሙያዎችና እኔን የሚያደንቁኝ ሰዎች ከሚነግሩኝ ነገሮች በመነሳት የሚጎሉኝ ነገሮች ላይ ሰርቼ ምርጥና ለሀገር ዋናው ብሔራዊ ቡድን የምጠቅም ተጨዋች መሆንን ስለምፈልግ ለዛ እየተዘጋጀው፤ ሌላ ማለት የምፈልገውም ዲ.ኤስ.ቲቪ የሀገራችንን እግር ኳስ እያስተላለፈ ያለበት መንገድ ለኳሳችን እድገትና ለውጥ አንዱ ራስን ማሳያ ነውና በዛ በጣም ደስ ሊለኝ ችሏል፡፡

spot_img
ተመሳሳይ ጽሁፎች

አስተያይት ያስፍሩ

እባክዎን አስተያይትዎን ያስፍሩ
እባክዎን ስምዎን እዚህ ያስገቡ

ትኩስ ዜናዎች

%d bloggers like this: