Google search engine

አቤል ከበደ ስለሚያደንቃቸው ተጨዋቾች ስለ ኮሮና ቫይረስ እና በተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ይናገራል

በመሸሻ ወልዴ /G.BOYS/

የኢትዮጵያ ቡና እግር ኳስ ክለብን በዘንድሮው የውድድር ዘመን በመቀላቀል ጥሩ እንቅስቃሴን እያሳየ የሚገኘው እና በብዙዎች ዘንድም አድናቆትን እያተረፈ ያለው አቤል ከበደ ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተገናኘ ጉዳይና ሌሎች ጥያቄዎችን የሊግ ስፖርት ጋዜጣ ድረ ገፅ ጠይቆት ምላሹን በሚከተለው መልኩ ሰጥቶናል፡፡
ስለ ኮሮና ቫይረስ
“ቫይረሱ ወደ እኛ ሀገር ከመግባቱ በፊት ይሄ ወረርሽኝ በትልልቆቹ የአውሮፓ ሀገራት ተስፋፍቶ ነበርና በጣም ከባድ መሆኑን በሚገባ ለማወቅ ችያለው፤ በሽታውም ውድድሮችን እስከማቋረጥም ደርሷል፤ እኛ ሀገር ሲገባ ደግሞ እነሱ ይህን ቫይረስ መቆጣጠር ካቃታቸው እኛስ ምን እንሆናለን ጉዳቱም የከፋ ይሆናል የሚለው ነገር በአህምሮዬ ቢመጣም መጀመሪያ አካባቢ ላይ በፈጣሪም እርዳታ ጥሩ አስተሳሰብ ኖሮን ልንቆጣጠረው ብንችልም ይሄ ህመም አሁን ደግሞ ተለዋዋጭነቱን እያሳየ በመሆኑ አሁንም ሳንዘናጋ በቂ የሆነውን ጥንቃቄ እስከመጨረሻው ሰዓት ድረስ ልናደርግ ይገባናል”፡፡
ኮሮና ቫይረስ ከገባ በኋላ ቤት ውስጥ ነው የምትውለውና በጣም የናፈቀህ
“ከእግር ኳስ ተለይቶ መኖርና ለእንደዚህ ያህል ቀናትም መቆየት በጣም ከባድ ስለሆነ እኔን በዋናነት የናፈቀኝ ነገር ቢኖር እግር ኳስን መጫወትና መጫወት ብቻ ነው፤ ከዛ ደግሞ የቡድኔ ጓደኞች፤ በተለይ ደግሞ ለቡና እንደመጫወቴ ከጓደኞቼ ጋር ልምምድ መስራት እና ወደ ጨዋታ መመለስ እንደዚሁም ደግሞ በቡና ደጋፊዎች ፊትም ስታድየም ላይ መጫወትና ያለኝንም አቅም ለቡድናችን ደጋፊዎችና ስፖርት አፍቃሪው ማሳየት በጣም ናፍቆኛል”፡፡
ከኮሮና ቫይረስ መግባት በኋላ ጊዜያቶችን በምን መልኩ እንደሚያሳልፍ
“በቤትም ሆነ በሰፈር ደረጃ ብዙም ሰው በማይበዛበት ጊዜያት ለራሴ ሊጠቅሙኝ የሚችሉ ስፖርቶችን ነው የምሰራው፤ ከእነዛም መካከል ከኳስ ጋር የተያያዘ ለምሳሌ ማንጠባጠብ፣ ለእኔም እውቀት ሊሰጡኝ የሚችሉ የልምምድ ስራዎችንና የሰውነቴም ኪሎ እንዳይጨምር የሚያስችሉ ስራዎችን እሰራለው”፡፡
በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ጥሬ ስጋ አትብሉ ተብሎ የሚበሉ አሉ፤ ምን ትላለህ? አሁን ላይ አንተስ
እንደ ስፖርተኝነትህ ምን እየተመገብክ ነው?
“ከኮሮና ቫይረስ መግባት በኋላ በአሁን ሰዓት በተደጋጋሚ ጊዜ በመመገብ ላይ ያለሁት አትክልቶችንና ፓስታን ነው፤ እነሱን በፊትም ቢሆን እመገባቸዋለውኝ፤ ጥሬ ስጋን አትብሉ የሚል መመሪያም በመተላለፉ እኔ በበዓል ጊዜ ራሱ አልበላውምና መመሪያውን ማክበር ለራስ ነውና በዚህ በኩል እየተጠነቀቅኩኝ ነው ያለሁት፤ ጥሬ ስጋን ስለሚበሉ ሰዎች ደግሞ ማለት የምፈልገው ጥሬ ስጋውን እኮ እስከ መጨረሻው ድረስ አትብሉ አልተባሉም ይሄ ጊዜ እስኪያልፍም ነው አትብሉ የተባሉትና እያማራቸውም ቢሆን ቁርጡን ከሚበሉ ቁርጥ አድርገው ቢተውት ጥሩ ነው”፡፡


በእግር ኳስ ተጨዋችነት ዘመንህ በየቦታው የአንተ ምርጦች
“ከግብ ጠባቂ ይድነቃቸው ኪዳኔ ነው፤ እሱ ጥሩ ችሎታ ያለው ብልጥና ልምድ ያለው ተጨዋች ነው፣ እንደዚሁም ደግሞ በብስለቱም ብዙ የሚጠቅምክና በልምምድ ላይም በጣም የሚለፋ ተጨዋች ስለሆነ ቀዳሚው ምርጫዬ ነው፤ ከተከላካይ ደግሞ አሁን ለአዳማ ከተማ የሚጫወተው ቴዎድሮስ በቀለ ይመቸኛል፤ በመከላከያ ክለብ እንደ ይድነቃቸው ሁሉ አብረን ተጫውተናል፤ ቴዲ ፊዚካሉ ከእኛ ሀገር ተጨዋቾችም ለየት የሚልና በምታሳልፈው የትኛውም የመከላከል ክፍል ላይ በብቃቱና በትንፋሹም ጥሩም ስለሆነ ከዛ ውጪም እንደ አሰልጣኝም የሚመክርህ አይነት ተጨዋችም ስለሆነ እሱን መርጬዋለው፤ ወደ መሀል ተጨዋች ሳመራ ደግሞ የእኛው አማኑኤል ዩሃንስ ምርጫዬ ነው፤ እሱ አስተውሎ ነው የሚጫወተው፤ በዛ ላይ ኳስ ይነጥቅልሃል፣ ያደራጅልሃል፤ ሜዳውንም አካሎ ይጫወታልና ልዩ ተጨዋች ነው፤ ወደ አጥቂዎች ስሄድ ደግሞ አቡበከር ናስር ቀዳሚ ምርጫዬ ነው፤ አቡኪን እንደምታየው ገና ወጣት ተጨዋች ነው፤ ምርጥ ብቃት ድፍረት እና ፍጥነትም አለው በተለይ ደግሞ ጎል ላይ ፊትለፊት ከተቃራኒ ቡድን ተጨዋቾች ጋር ሲገናኝ እነሱን አልፎ ግብ የሚያስቆጥርበት መንገድ ለየት ያደርገዋል”፡፡
በእግር ኳስ ጨዋታ ዘመንህ የአንተ ምርጡ ጨዋታ
“ለኢትዮጵያ ቡና በቋሚ ተሰላፊነት የተጫወትኩበትን ከሐዋሳ ከተማ ጋር ያደረግነውን ነው በዋናነት የምጠቅሰው፤ ያ ግጥሚያ ጥሩ እንቅስቃሴ ያደረግኩበት ከመሆኑ ባሻገር ማራኪ ግብም ያስቆጠርኩበት ነው”፡፡
በኮሮና ቫይረስ ከቤተሰቦችህ ጋር ብዙ እንደማሳለፍህ ምን የተለየ ነገር አጋጥሞአል
“የእውነት ነው፤ በወረርሽኙ ምክንያት በዚህ ደረጃ ከቤተሰቦቼ ጋር ውዬ አላውቅምና ከቤት ስለማልወጣ ቤተሰቦቼን አሁን ላይ በተደጋጋሚ ጊዜ አብሬያቸው ስውል ያስተዋልኩት ነገር ከማውቃቸው በላይ እንዳውቃቸው አድርጎኛል፤ ከዛ በተጨማሪ ስለ ብርታታቸውና ክፍተታቸውም ብዙ የተረዳሁበት ነገርም ስላለ እነሱን በምን መልኩ ነው መደገፍ የሚገባኝ እንዴትስ ነው የምረዳው የሚለውንና ስለስብህናቸውና ስለማንነታቸውም ስላወቅኩኝ በጣም ደስ ብሎኛል”፡፡
የኢትዮጵያ ፕሮፌሽናል እግር ኳስ ተጨዋቾች ማህበር ተቋቁሟል፤ ምን ትላለህ?
“ይሄ ማህበር መቋቋሙ ጥሩ ነው፤ ምክንያቱም ከዚህ ቀደም ለተጨዋቾች የቆመ እና የሚከራከር አካልን ሰምተን አናውቅምና፤ ለምሳሌ የተጨዋቾች ደመወዝ 50 ሺ ብር ተብሎ ሲወሰን ማንም ምንም አላለም ነበር፤ አሁን ግን ይሄ ማህበር በብዙ ጉዳዮች ላይ ለእኛ ለመቆም ስለመጣ ከዚህ የሚያስከፋ ነገርም ሊያጋጥም ስለሚችልም አጠቃላይ የሀገሪቱ ተጨዋቾች ከጎኑ ሆነን አባል በመሆን መተዳደሪያ ደንቡን በማወቅ ልናግዘው ይገባል”፡፡
በኮሮናው ቫይረስ የአንተስ የበጎ አድራጎት ተግባር
“ለኮሮና ቫይረስ መከላከያ እንዲሆን ተብሎ በቅድሚያ በእዚህ የበጎ አድራጎት ስራ ላይ እንድሰማራ ያደረጉኝ እኔ ያሰብኩት ሳይሆን በሰፈሬ አዲስ ሰፈር የሚገኙ የቡና ደጋፊዎች ናቸው ጉዳዩን በማንሳትና በማስተባበርም አንድአንድ ነገሮችን እንዳደርግ ያናገሩኝ፤ ወዲያውም ነው እኔንም በማሳተፍ አዲስ ሰፈር አደይ አበባ ጋር ነው የቡና ዓርማ ያለበት ሮቶ ነበርና እዛ አካባቢ በመገኘት በሚቻለን አቅም እኔና ሌላው የቡድናችን ተጨዋች የሆነው ሀይሌ ሆነን ከሌላው ህብረተሰብ ጋር በመሆን ድጋፍን ያደረግነውና በዚህ አጋጣሚ ደጋፊዎቹ አሁን ከሰሩት በጎ ስራ በተጨማሪ ሌላም ሊሰሩት ያሰቡት ነገር አለና በዚህ አጋጣሚ በጣም ላደንቃቸው እና ላመሰግናቸውም እፈልጋለው”፡፡
በመጨረሻ….
“ኮሮና ቫይረስን አስመልክቶ እስካሁን ድረስ በሚዲያ ደረጃ ከዚህ ወረርሽኝ ራሳችንን እንዴት መከላከል እንዳለብን ትምህርት እየተሰጠን ይገኛልና ይሄን ተግባራዊ በማድረግ እስከ መጨረሻው ሰዓት ድረስ ልንጓዝ ይገባል፤ ስፖርተኞችን በተመለከተ ደግሞ ይሄ ቫይረስ እንደሌላው ማህበረሰብ ሁሉ እኛንም የጎዳንና ከምንወደው ሙያም ያራቀን በመሆኑ የባሳ እንዳንጎዳ በዚህ የእረፍት ጊዜ ሰውነታችን ሊጨምር ስለሚችል ምንም ነገር ሳያታልለን ሰውነታችንን በስፖርት ጠብቀን በስነ-ልቦናም ራሳችንን አዘጋጅተን ጥሩ ጊዜ ስለሚመጣ የበለጠ ጠንካራ መሆን አለብን እላለው”፡፡

spot_img
ተመሳሳይ ጽሁፎች

አስተያይት ያስፍሩ

እባክዎን አስተያይትዎን ያስፍሩ
እባክዎን ስምዎን እዚህ ያስገቡ

ትኩስ ዜናዎች

%d bloggers like this:
P