Google search engine

“በፕሪምየር ሊጉ ላይ ስጋት ይሆንብናል ብዬ የማስበው ክለብ ማንም የለም” አብዱልከሪም መሐመድ /ኢትዮጵያ መድን/

 

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ  የውድድር  ደረጃ እግር ኳስን ለሲዳማ ቡና፣ ለሐዋሳ ከተማ፣ ለኢትዮጵያ ቡና፣ ለቅ/ጊዮርጊስ እና ለፋሲል ከነማ ክለቦች ተጫውቶ አሳልፏል። በአንድ ወቅትም ቅ/ጊዮርጊስ በነበረበት ሰዓት ላይ  ምንም እንኳን የሊጉን ዋንጫ ከፍ አድርጎ ለማንሳት ባይታደልም የኮከብ ተጨዋችነት ክብርን ግን አንድ ጊዜ  ሊያገኝ ችሏል። ይህ  ተጨዋች  የኮሪደር  ስፍራው ተጨዋች አብዱልከሪም መሐመድ  /ተርምኔተር/ ሲሆን  በአሁን  ሰዓት ላይ   ለአዲሱ ክለቡ ለኢትዮጵያ መድን በመጫወት ላይ ይገኛል። ከእዛም ውጪ  የክለቡ ካፒቴን ሆኖ  በመመረጥም ቡድኑን  እያገለገለ ይገኛል።  ከእዚህ  ተጨዋች ጋር  የሊግ ስፖርቱ ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ /G.BOYS/ ቡድናቸው የሊጉን ውድድር  እየመራ ስለመሆኑ፣ ስለ ራሱና ሌሎችን ጥያቄዎች አክለን ይዘንለት ቀርበን ምላሾቹን በሚከተለው መልኩ ሰጥቷል። ተከታተሉት። መልካም ንባብ።

በፕሪምየር ሊጉ ያለፉት ጨዋታዎች ተከታታይ ድል ስለማስመዝገባቸው ሚስጥር

“ላገኘናቸው ተከታታይ ስኬቶች የመጀመሪያውና ዋናው  ምክንያት ውድድሩ ሲጀመር ከደረሰብን ሽንፈትና ደካማ ጎናችን የልምምድ ሜዳው  ላይ ብዙ ነገሮችን ለመስራትና ለመማር በመቻላችን ነው፤ ከእዛ ሲቀጥል ደግሞ ቡድኑ ውስጥ ያለው   አንድነትና ህብረቱ  ጥሩ መሆኑና የቡድን መንፈሱ  ልዩ  መሆኑም  ነው፤ እነዚህ ሁኔታዎችም ናቸው እኛን የጠቀሙን”።

ሲዳማ ቡናን በሰፊ ግብ ስለረቱበት የረቡዕ ዕለት ጨዋታና ስለተጋጣሚያቸው አቋም

“ወደ ጨዋታው ሳመራ ምንም አይነት ጥያቄ የለውም ግ ግጥሚያው ከባድ ነበር። እስካሁን ከገጠምናቸው ጠንካራ ክለቦች መካከልም ሲዳማ ቡና የሚጠቀስ ነው። ያም ሆኖ ግን የእኛ የቅዴሚያ እሳቤ ጨዋታውን የመጀመሪያው አጋማሽ ላይ ጨርሰን መውጣት አለብን ብለን በማሰባችን ጨዋታውን በድል ተወጥተናል። ይሄን ጨዋታ ለማሸነፍ የቻልንበት አንዱ ምክንያትም  ለእያንዳንዱ ግጥሚያ እኩል እና ተመሳሳይ ትኩረትን ሰጥተን ወደ ሜዳ ስለምንገባና ሶስት ነጥብንም ይዘን መውጣት አለብን ብለን ስለምናስብም  በቀጣዩም ጨዋታ ሶስት ነጥብ ከሜዳ ይዘን ለመውጣት ዝግጁ ሆነናል።  የተጋጣሚያችንን ሲዳማ ቡናን የዕለቱ አቋምን በተመለከተ እንደ ሌላው ጊዜ ባይሆኑም ጥሩ ቡድን ነው ያላቸው፤ ከእኛ ጋር ከመጫወታቸው በፊትም  በሐዋሳ ከተማ ተረተውም ነበርና   ሽንፈቱ ሊደራረብባቸው ችሏል”።

የዘንድሮ የሊጉ ውድድር  ሲጀመር ስለነበረው ኢትዮጵያ መድንና አሁን ላይ ስላለው  መድን ምን አልክ?

“የሊጉ ጅማሬ ላይ የነበረው መድን በቅ/ጊዮርጊስ ሰባት ግቦች ተቆጥሮበት የተሸነፈ ስለነበር ጥሩው ነገር ለማሳየት አልቻለም፤ ያኔ ለመሸነፋችን ምክንያት የነበረውም ብዙ ልጆቻችን በጉዳት ላይ ስለነበሩና ባሉት ልጆችም ወደ ሜዳ ለመግባት በመቻላችን ነው። በተለይም ደግሞ የመሀል ተከላካያችን በህመም ያልነበረ መሆኑ በጣም ሊጎዳንም ችሏል።  ከእዛ ውጪ የአቋም መለኪያ ግጥሚያ አለማድረጋችንም ሌላው ጉዳት ነበር። ከእዛ ጨዋታ በኋላ ግን ከሽንፈታችን ተምረን ለመምጣት ስለቻልንና ልጆቻችንም ከጉዳታቸው ሊያገግሙ ስለቻሉ እንደዚሁም ከውጪ የመጡት ተጨዋቾቻችንም ፕሮሰሳቸው ሊያልቅላቸው ስለቻለ በቀጣይ ወደ አሸናፊነት መምጣት አለብን ብለን በማሰባችን የአሁኑን ጠንካራ እና ውጤታማ እንደዚሁም የተሻለ የሆነውን መድንን ልናስመለክት ችለናል”።

የባለፉት ሰባት ሳምንታት ጠንካራና ክፍተት ጎኖቻችሁ ምንድን ናቸው?

“በእግር  ኳስ ጨዋታ ግጥሚያን አሸንፈክም ሆነ ተሸንፈህ ድክመቶች ይኖራሉ። እዛ ላይ ክፍተቶችህን እያረምክ በመምጣትና በጠንካራ ጎን ላይ ደግሞ አንዳንድ ነገሮችን እያሻሻልክ ነው መምጣት ያለብህና የእኛ ቡድን ከዕለት ዕለት ነው ብዙ ነገሮችን ሲሰራ የነበረውና ይሄ ነገር እኛን ጠቅሞናል”።

ለኢትዮጵያ መድን  እየተጫወትክ እንደመሆንህ፤ ስለ ቀድሞ የክለቡ ታሪክ የምታውቀው ነገር አለ?

“ኢትዮጵያ መድን ላለፉት ስምንት ዓመታት በከፍተኛው ሊግ ደረጃ ሊቆይ ቢችልም በፕሪምየር ሊጉ ደረጃ በነበረበት ሰዓት ላይ ትልቅ ስምና ዝና እንደነበረው ለማወቅ ችያለሁ። ወደ ታችኛው ሊግ አስቀድሞ ከመውረዱ በፊትም በተቃራኒነት ሆኜም ተጫውቻለሁ። አሪፍ ቡድን ነበረም። ከትላልቅ ቡድኖች ደረጃ የሚመደብም ነበርና አሁን ላይ የክለቡ አመራሮች ለእኛ ከሚያደርጉልን ነገር በመነሳት እያሰብን የምንገኘው  የእዚሁን ቡድን የቀድሞ ስምና ዝናን እንደዚሁም ደግሞ ጠንካራውን መድንን የሚመጥን ቡድንን ዳግም ለመመለስ መቻልም ነውና ያንን ለማሳየት እየጣርን ነው የምንገኘው”።

በፕሪምየር ሊጉ ለእናንተ የቱ ክለብ ፈታኝ ይሆንባችኋል?

“በፕሪምየር  ሊጉ  ላይ ለእያንዳንዱ ጨዋታ  እኩል ትኩረትን ሰጥተን ወደ ሜዳ ስለምንገባ ስጋት ይሆንብናል ብዬ የማስበው ክለብ ማንም የለም፤ ስለ ስጋት ካነሳንም አንድን ቡድን ሜዳ ላይ ካየነው በኋላም ነው ስለ እሱ የምንነጋገረው። አሁን ሲዳማን አሸነፍን ከእዚህ በኋላ ስለቀጣዩ ጨዋታም ነው የምንዘጋጀውና የምናስበው”።

በፕሪምየር ሊጉ ሀድያ ሆሳዕናም ጠንክሮ መጥቷል……

“አዎን፤ የእዚህ ቡድን ጅማሬው የተሻለ ነው፤ ጥሩ እንቅስቃሴንም እያደረጉ ነው። ነጥቦችንም በመሰብሰብ ላይ ናቸው”።

ፕሪምየር ሊጉ በምን አይነት ሁኔታ የሚጠናቀቅ ይመስልሃል? እንደ አምናው  እስከ መጨረሻው ደረጃ አንገት ለአንገት በሆነ መልኩ የሚጓዝ ይግን መስልሃል?

“የውድድሩ ጅማሬና ፉክክሩ  ደስ የሚልና  ጥሩ የሚባል ነው።  ከስርም ከላይም ያሉት ቡድኖች በተመጣጠነ ሁኔታም እየተጫወቱ ነው። ውድድሩ  እንደ አምናውም የተሻለ ፉክክር ተደርጎበት የሚጠናቀቅም ይመስለኛል”።

የውድድር ሜዳዎችን በተመለከተ

“ብዙ ይቀራቸዋል። ለመጥቀስ ያህል ድሬዳዋ ላይ ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ ከዘነበ በኋላ መጫወቻ ስፍራው አሪፍ አይደለም። አንድ ጨዋታን እንደውም በጭቃ ላይ ተጫውተናል። ከእዛ በኋላ በተወሰነ መልኩ ለመስተካካል ቢሞከርም የሚጎለው ነገር አለ”።

ኢትዮጵያ መድንን በካፒቴንነት እየመራ ስለመሆኑ

“ሀላፊነቱን የሰጠኝ አሰልጣኝ ገብረመድህን ሀይሌ ነው። ይህን ሀላፊነት ስረከብም ከባድ እንደሆነም አውቄ ነው። ምክንያቱም ይህን ክለብ በካፒቴንነት  መምራት መታደል ጭምርም  ነውና ደስተኛም ሆኜም  ነው ልቀበል የቻልኩት”።

ኢትዮጵያ መድን የራሱ የሆነ ሜዳና ካምፕ ያለው ክለብ ስለመሆኑ

“እንዳልኩህ መድን  አዲስ አበባ  ውስጥ የራሱ የሆነና የተሻለ ሜዳ ያለው ክለብ ነው፤ ልምምድንም እዛው ሜዳ ላይ ሰርተን አልፈንበታል። በራስ ሜዳ ላይ ስትሰራም ተጠቃሚ የምትሆንበት ነገር አለ፤ ክለቡ የራሱ የሆነ ካምፕም  አለው። ሊበረታታ የሚገባው ክለብ ነው። ሌሎቹ ቡድኖችም እንደ እሱ የራሳቸው የሆነ ነገርም  ሊኖራቸው ይገባል”።

የሊጉ ውድድር ወደ አዲስ አበባ መጥቶ ሊጠናቀቅ ይችላል ስለመባሉ

“አዲስ አበባ ላይ ጨዋታው መደረጉ በጣም ደስ ይላል። የሚኖረው ድባብም ከክልሎች  የበለጠም ያምራል። ምክንያቱም ወደ ክልል ስታመራ ደጋፊ ያላቸው ቡድኖች ሲጫወቱ ብቻ ነው ሰው ወደ ሜዳ የሚገባው። ስለዚህም አዲስ አበባ ላይ ደጋፊዎች ቡድናቸው ጨዋታ ኖረው አልኖረውም ሁሌ ወደ ሜዳ በመግባት ተጨዋቾችን ያበረታታሉና ይሄን አውቃለሁ”።

በእግር ኳስ ህይወትህ ጥሩ ጊዜን ያላሳለፍከው በፋሲል ከነማ ቆይታህ ነው?

“አዎን፤ እውነትም ነው። እንደሚታወቀው በተለያዩ ክለቦች ውስጥ እግር ኳስን ተጫውቼ አሳልፌያለው። ጥሩ ጊዜን

 

ያላሳለፍኩት ደግሞ በፋሲል ከነማ ነው። ለእዛም ነው ከክለቡ  የኮቺንግ ስታፎች ጋር ባለመስማማቴና በሰጡኝ ምላሽም ለመግባባት ባለመቻል  የልቀቁኝ ደብዳቤ አስገብቼ ከቡድኑ ጋር ለመለያየት የቻልኩትና ከእዛም በኋላ ነው ራሴን ማሳየት አለብኝ በሚል ወደ አዲሱ ቡድኔ ኢትዮጵያ መድን ከወራቶች ቆይታ በኋላ ለማምራት የቻልኩት”።

በተደጋጋሚ እንደ በፊቱ ስምህ በጉልህ አለመጠራቱና የቀድሞ ስምና ዝናን ዳግም  ለመመለስ ስለመዘጋጀትህ

“ከቅርብ ጊዜያቶች ወዲህ የስሜ እንደ በፊቱ በተደጋጋሚ አለመጠራቱ የሚፈጥርብኝ የራሱ የሆነ ተፅህኖ ቢኖረውሞ  በእግር ኳስ አንዳንዴ ሊያጋጥም እንደሚችል ማሰብ አለብህ። ያም ሆኖ ግን ሁሌም ጠንክረህ መስራት ከቻልክና ራስህን ብቁ አድርገህ የምታቀርብ ከሆነ ወደነበርክበት አቋም የማትመለስበት ምንም አይነት ምክንያት የለም”።

ኢትዮጵያ መድንን ስለተቀላቀለበት ሁኔታ

“ወደ ክለቡ ያመራሁት ፋሲል ከነማ እያለሁኝ ከአሰልጣኝ ገብረ መድህን ሀይሌ ጋር  ሲዳማ ቡና በነበረበት ወቅት ግማሽ ዓመት ላይ ከእሱ ጋር ለመስራት ተነጋግረን የነበረ ቢሆንም ከክለቡ አመራሮች ጋር ባለመስማት ነው  ወደ ቡድኑ ሳልገባ የቀረሁት።  ያ ዝውውር ሳይሳካ ቢቀርም ከሌሎች ቡድኖች ጥያቄዎች ቢቀርብልኝም ራሴን ለአዲሱ ዓመት ብቁ አድርጌ በመምጣት ነው የአሰልጣኝ ገብረመድህን ሀይሌውን መድን ልጫወትለት ፈቃደኛ በመሆኔና ከእዚህ በፊትም ይፈልገኝ ስለነበር ዘንድሮ ልቀላቀል የቻልኩት”።

ስለ አሰልጣኝ ገብረመድህን ሀይሌ

“በብዙ አሰልጣኞች ለመሰልጠን ብችልም እሱ ጋር ስሰራ የተመለከትኩት ነገር ቢኖር  አንተ ላይ ስራን የሚሰራው ባፈካለህ ነገር ተነስቶ ነው። ምን አይነት ኳሊቲ እንዳለህ እና ምን ባደርግ ይጠቅመኛል ብሎም ነው ወደ ሜዳ የሚያስገባህ። ከእዛ ውጪም እንደ ቡድን ምን አይነት ቡድንም ነው ብሎ በማሰብም ስራን ይሰራልና ከእዛ አንግል የሚሰጥህ የራስ መተማመን ስሜትም አለና  ለእኔ የተሻለው አሰልጣኝ እሱ ነው”።.

ስለ አስደሳችና የቁጭት ጊዜው

“በጣም የምቆጨው የሊጉን ዋንጫ አለማንሳቴ ነው። በተለይም ደግሞ ደጋግሞ ዋንጫ ከሚያገኘው ክለብ ጋር ይህን እልም አለማሳካቴ ይቆጨኛል። የተደሰትኩበት ጊዜ ደግሞ ቅ/ጊዮርጊስ በነበርኩበት ሰዓት ላይ የሀገሪቱ ኮከብ ተጨዋች ተብዬ ተሸልሜያለውና ያ የማይረሳኝ ነው”።

ስለ ቀጣይ እልሙ

 

“የሊጉን ዋንጫ ማግኘት እፈልጋለሁ። ከእዛ ውጪም ምርጫው የአሰልጣኞች ቢሆንም የተሻለ ስራን ሰርቼ ወደ ብሄራዊ ቡድን ዳግም መመረጥና መጫወት እፈልጋለሁ”።

የኢትዮጵያ መድን የእዚህ ዓመት እቅዱ

“ክለቡ ዘንድሮ ሊጉን የተቀላቀለ ቢሆንም የእኛ ዋናው እሳቤ በእያንዳንዱ ጨዋታ ላይ ጥሩ ውጤትን ይዘን በመውጣት ክለቡን የሚመጥን ውጤት እናስመዘግባለን”።

በመጨረሻ

“እስካሁን ጥሩ ውጤትን እያስመዘገብን ነው። ከዓላ እርዳታ ጋር ይሄ ጉዞአችንን አስቀጥለን ለመጓዝ ጠንክረን እንሰራለን”።

spot_img
ተመሳሳይ ጽሁፎች

አስተያይት ያስፍሩ

እባክዎን አስተያይትዎን ያስፍሩ
እባክዎን ስምዎን እዚህ ያስገቡ

ትኩስ ዜናዎች

%d bloggers like this:
P