Google search engine

“አዳነ እያነቃቃን ነው፤ የእሱ  መምጣት ለአሸናፊነት ስነ-ልቦና ይጠቅመናል” ሄኖክ አዱኛ /ቅዱስ ጊዮርጊስ/

 

ሄኖክ አዱኛ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዋንጫን ከቀድሞ ክለቡ ጅማ አባጅፋር ጋር ለማንሳት ችሏል፤ ወደ ቅ/ጊዮርጊስ ካመራ በኋላ ደግሞ ይህን ዋንጫ ለማንሳት ሳይችል ቀርቷል፤ ለቅ/ጊዮርጊስ በኮሪደር ስፍራ ላይ እየተጫወተ የሚገኘው ይኸው ተጨዋች ከዚሁ ክለቡ ጋር ዋንጫ አለማንሳቱን ተንተርሶ በጣም እንደሚቆጭና የእሱም ስኬት በአንድ የፕሪምየር ሊግ ድል ብቻ ፈፅሞ እንዲቆም እንደማይፈልግ ለዝግጅት ክፍላችን አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡ ሄኖክ በእዚህ ዙሪያም ሲናገር “የሊጉን ዋንጫ ከዚህ በፊት ከቀድሞ ክለቤ ጅማ አባጅፋር ጋር ለማንሳት ችያለው፤ ያኔም በመጣው ውጤት ተደስቻለው፤ የእኔ ስኬት በዚህ ድል ብቻ እንዲቆም አልፈልግም፤ ወደ ቅ/ጊዮርጊስ ሳመራ ይህን ድል ጠብቄ ነበር፤ እስካሁን አላሳካሁትም፤ ከእዚህ ትልቅ ቡድን ጋር ሌላ ተጨማሪ ዋንጫን ማግኘት እፈልጋለው፤ ለዛም ነው ይህን እልሜን ለማሳካትም ጥረት በማድረግ ላይ የምገኘው” በማለት ሄኖክ አዱኛ አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡

የቅ/ጊዮርጊሱ ሄኖክ አዱኛን በተለያዩ ጥያቄዎች ዙሪያ ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ ያናገረው ሲሆን ከእነዛም መካከል ስለ ቡድኑ የቀድሞ ተጨዋችና አሁን በቡድን መሪነት ወደ ክለቡ ስለመጣው አዳነ ግርማም አንስተንለት የሚለው ይኖረናል፤ የመጀመሪያው ጥያቄያችን ስለ ፕሪ-ሲዝን ዝግጅታቸው ነው፤ ሊግና ሄኖክ የሚከተለውን ቃለ-ምልልስ አድርገዋል፡፡

ሊግ፡- የቅ/ጊዮርጊስ የፕሪ-ሲዝን ዝግጅት ምን ይመስላል?

ሄኖክ፡- እስካሁን አሪፍ የሆነ ልምምድን እየሰራን ነው፤ በአብዛኛውም የቅንጅት /ኮርድኔሽን/ ስራ ላይ ነው በማተኮር እየተለማመድን የሚገኘው፤ ሌላው ኢንዱራንስ ላይም በማተኮርም ጠንካራ ስራን ሰርተናል፤ አሁን ላይ የብሔራዊ ቡድን ተጨዋቾችም ተቀላቅለውን እየተለማመዱም ይገኛልና ከእነሱ ጋርና ወደ ቡድናችን ከመጡት አዳዲስ ተጨዋቾችም ጋር በደንብ ስንዋሃድ ክለባችን የበለጠ ምርጥ ይሆናል፤ በአሁን ሰዓት እየሰራን ባለው ስራም ደስተኛ ሆነናል፡፡

ሊግ፡- ወደ ቅ/ጊዮርጊስ አዳዲስ ተጨዋቾች መጥተዋል፤ ስለ እነሱ ምን ማለት ይቻላል?

ሄኖክ፡- የመጡት ልጆች ወጣቶችና ቡድናችንንም በደንብ መጥቀም የሚችሉ ናቸው፤ በአንዴም ነው የተግባባናቸው፤ የእነሱን ጥሩነትም ውድድሩ ሲጀመር የምናየው ነው የሚሆነው፡፡

ሊግ፡- ቅ/ጊዮርጊስ አዲሱን አሰልጣኝ በማስመጣት ነው የፕሪ-ሲዝን ልምምዱን የጀመረው፤ እስካሁን ከሚያሰራችሁ ልምምድ በመነሳት ስለ እሱ ምን የምትለው ነገር አለ? ከአንደበቱ ከወጡ ቃላቶችስ ውስጥ ምን የነገራችሁ ነገር አለ?

ሄኖክ፡- የቡድናችንን አዲስ አሰልጣኝ በልምምድ ወቅት እንደተመለከትኩት ጠንክሮ የሚሰራ ሰውን ይፈልጋል፤ ከዛም በተጨማሪ ሁሉንም ተጨዋች አንዱን ከአንዱ ሳያበላልጥም ነው የሚያየው፤ ሌላው ከአንደበቱ ሲወጣ ያስተዋልኩት ሜዳ ላይ ልምምዱን በደንብ አድርጎ የሰራ ተጨዋች ለቡድኑ በቋሚነት ይጫወታልም ብሏልና አሁን ላይ ሁሉም ተጨዋች ልምምዱን ተግቶና ጠንክሮ እየሰራ ይገኛል፡፡

ሊግ፡- ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ሊጀመር እየተቃረበ ነው፤ በ2014 ቅ/ጊዮርጊስ ምን ነገርን አቅዷል?

ሄኖክ፡- ቅ/ጊዮርጊስ ሁሌም ቢሆን አንድና አንድ እቅዱ የሊጉን ዋንጫ በየዓመቱ ማንሳትና በአፍሪካ ክለቦች ደረጃም ውድድር ውስጥ ገብቶ የምድብ ድልድል ውስጥ መግባትን ነው፤ ከእነዚህ ነገሮች ውጪ አቅዶም አያውቅም፤ ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ ጊዜ የሊጉን ዋንጫ ያነሳ ነበር፤ አሁን ግን ካለፉት አራት ዓመታቶች አንስቶ ይህን የድል ክብሩ እያጣው ይገኛል፤ ከእዛም መነሻነት አሁን ላይ በቡድኑ ውጤት ማጣት ዙሪያ የተከፉትን ምርጦቹን ደጋፊዎች እንደዚሁም ደግሞ ለቡድኑም ብዙ ነገሮችን እያደረጉ የሚገኙትን አመራሮቹን ለማስደሰትና በውጤትም መካስን ስለፈለግን የእዛ የእኛ እቅድ አካል የሆነውን ልምምዳችንን ጠንክረን እየሰራን ነው የምንገኘው፡፡

ሊግ፡- የቅ/ጊዮርጊስ የቦርድ አመራር ወደ ልምምድ ሜዳ በመምጣት እንደሚጎበኛችሁ ሰማን፤ ወደ እናንተ ሲመጡ ምን ይሏችኋል?

ሄኖክ፡- እነዚህ አመራሮች ለክለቡ ካላቸው ጥልቅ ፍቅር የተነሳ ሜዳን ከማመቻቸት አንስቶ እየመጡ እያበረታቱን ነው፤ አይዟችሁ፤ ከጎናችሁም ነን እያሉ ጠንክረን እንድንሰራና የራቀንንም ውጤት ወደ ቤቱ እንድንመልሰውም እየነገሩን ነው፤ ከዛ ውጪም በካምፓችን ያለው የቡድን መንፈስም አሪፍ እንዲሆንም እያደረጉ ይገኛልና በዚህ ሊመሰገኑ ይገባል፡፡

ሊግ፡- ቅ/ጊዮርጊስ የቀድሞ የክለቡን ዝነኛ ተጨዋች አዳነ ግርማን ወደ ክለቡ በቡድን መሪነት አስመጥቷል፤ ይሄን እንዴት ተመለከታችሁት?

ሄኖክ፡- አዳነ ግርማ የቅ/ጊዮርጊስን ባህልና አጠቃላይ በክለቡ ውስጥ ያለውን ሁኔታም ከእኛ በተሻለ መልኩ የሚያውቅ ስለሆነ የእሱ በቡድን መሪነት ወደ እኛ መምጣት በጣም ይጠቅመናል፤ አዳነ ለቅ/ጊዮርጊስ ብቻ አይደለም ለሀገርም ትልቅ ስራን የሰራ ተጨዋች ነው፤ አሁን ለክለቡ በቡድን መሪነት ከመጣ በኋላም ለእኛ ስለ ክለቡ በደንብ እየነገረንም ይገኛል፤ ከማማከር ውጪ እያነቃቃንም ነው፤ የእሱ ማነቃቃትም ለአሸናፊነት ስነ-ልቦናችንም የሚጠቅመን ነገር ስላለ መምጣቱን ወደነዋል፡፡

ሊግ፡- ከጅማ አባጅፋር ጋር እንጂ ከቅ/ጊዮርጊስ ጋር የሊግ ዋንጫን አላነሳህም፤ በዚህ ዙሪያ ምን አልክ…..?

ሄኖክ፡- ይሄን ድል ባለማሳካቴ በጣም ተቆጭቼያለው፤ ምክንያቱም ወደዚህ ቡድን ስመጣ ይህን እልም ሰንቄ ነበር፤ ወደ ቅ/ጊዮርጊስ ስትመጣ የቱም ተጨዋች አንድና አንድ አልሞ የሚመጣው ከክለቡ ትልቅነት አንፃር ዋንጫን ማግኘት ይፈልጋል፤ እኔ ግን ከጅማ አባጅፋር ጋር እንጂ ከቅ/ጊዮርጊስ ጋር ይህን ድል ላሳካው አልቻልኩም፤ ስለዚህም የሊጉ ዋንጫ ክብሬ በአንድ ብቻ ተወስኖ እንዲቀር ስለማልፈልግ የዘንድሮም ዋና እልሜ ይህን ዋንጫ ከቅ/ጊዮርጊስ ጋር ማግኘት ነው፡፡

ሊግ፡- በ15ኛው የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ክለባችሁ ቅ/ጊዮርጊስ ይካፈላል፤ በውድድሩ ዙሪያ ምን ትላለህ? ምን ውጤትስ ለማምጣት ተዘጋጅታችኋል?

ሄኖክ፡- የሲቲ ካፑ ውድድር ለእኛ ብቻ ሳይሆን ለሁሉም ክለቦች አቋማቸውን የሚፈትሹበት ውድድር ነው፤ በዝግጅት ጊዜ ከሰራነው ልምምድ በመነሳትም በቤትኪንጉ ላይ በተቀናጀ መልኩ ይዘን ለምንቀርበው ቡድን የሚረዳንና የሚጠቅመንም ነው፤ በዚህ የውድድር ተሳትፎአችን ላይ ክለባችን እንደ ፕሪምየር ሊግ ተሳትፎው ሁሉ ተደጋጋሚ ዋንጫዎችን ማንሳት ችሏል፤ ዘንድሮም በኳስ ላይ የሚፈጠረውን ነገር ቀድሞ ማወቅ ባይቻልም የእዚህ ውድድር አሸናፊነቱ ለቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ውድድር ተሳትፎ ስነ-ልቦና ስለሚጠቅመን ዋንጫውን ለማንሳት ነው የምንጫወተው፡፡

ሊግ፡- ከእግር ኳስ ህይወትህ ጀርባ ባለቤትህ አለች፤ እሷ እንዴት ትገለፅ?

ሄኖክ፡- ባለቤቴ ፅዮን ቴዎድሮስ ትባላለች፤ ለአራት ዓመታት በጓደኝነትና ለአንድ ዓመት ደግሞ በትዳር ህይወት ውስጥ አብረን እየኖርን ነው፤ ኳስ ጨዋታን በመከታተልም ከእኔ ጎን ሆና ብዙ ነገሮችን የምታደርግልኝም ነችና በጣም ላመሰግናት እፈልጋለው፡፡

ሊግ፡- በመጨረሻ….?

ሄኖክ፡- የቅ/ጊዮርጊስ ደጋፊዎች ለእኛ የሚሰጡን ድጋፍ ሁሌም ከልባችን አይጠፋም፤ ድንቅ ደጋፊዎች አሉን፤ ዘንድሮ እነሱን በውጤት ለመካስ የምንችለውን ሁሉ እናደርጋለን፤ ከዛ ውጪም እኔም በዘንድሮ ተሳትፎዬ ለቡድኔ የሚቻለኝን ሁሉ ጥረት አድርጌ ክለቤን ለመጥቀምና  ለብሔራዊ ቡድንም ዳግም ለመመረጥ ጠንክሬም እሰራለው፤ ይህን ካልኩ 2014 ፈጣሪ ሀገራችንን ሰላም እንዲያደርግልን በመመኘት ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች መልካም የመስቀል በዓል እንዲሆንላችሁም ምኞቴ ነው፡፡

spot_img
ተመሳሳይ ጽሁፎች

አስተያይት ያስፍሩ

እባክዎን አስተያይትዎን ያስፍሩ
እባክዎን ስምዎን እዚህ ያስገቡ

ትኩስ ዜናዎች

%d bloggers like this: