በመሸሻ ወልዴ /G.BOYS/
የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግን ዘንድሮ ለተቀላቀለው የሀድያ ሆሳህና እግር ኳስ ክለብ ለመጫወት ፊርማውን ያኖረው አፈወርቅ ኃይሉ የእዚህ ዓመት የሊጉ ተሳትፎአቸው በውድድሩ ላይ መቆየት መቻል መሆኑን በመጥቀስ ሻምፒዮና ለመሆን የሚችሉበት ዕድሉም ካለ ያን እንደማይጠሉም ለሊግ ስፖርት ጋዜጣ አስተያየቱን ሰጥቷል፤ ከወልዋሎ አዲግራት ዩንቨርስቲ ክለብ ወደ ሀዲያ ሆሳህና ያመራውን ይኸው ተጨዋች አጠር ያሉ ጥያቄዎችን አቅርበንለት ምላሹን በሚከተለው መልኩ ሰጥቶናል፡፡
ሊግ፡- ወልዋሎ አዲግራትን በመልቀቅ ወደ ሀድያ ሆሳዕና አምርተሃል፤ አዲሱ ክለብህ እንዴት የቅድሚያ ምርጫህ ሆነ?
አፈወርቅ፡- የወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርስቲ ክለብ የውል ጊዜዬ እንደተጠናቀቀ መጀመሪያ ላመራ የነበርኩበት ቡድን የባህር ዳር ከተማ ክለብ ነበር፤ ያም ሆኖ ግን በአማራና በትግራይ ክልል አካባቢዎች ባለው ያልተረጋጋ የፖለቲካ ሽኩቻና የሰላም መደፍረስ አንፃር ወደ እዛ ሄጄ መጫወቱ በቤተሰቦቼም ሆነ በእኔ ዘንድ ስላልተፈለገ የሀድያ ሆሳዕናን ክለብ የመጀመሪያ ምርጫዬ አድርጌ ለቡድኑ ለመጫወት ፊርማዬን አኑሬያለሁ፡፡
ሊግ፡- የሀዲያ ሆሳህና የፕሪ- ሲዝን ዝግጅት ምን ይመስላል?
አፈወርቅ፡- ለኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የዘንድሮ የውድድር ዘመን ተሳትፎአችን በአሁን ሰዓት ክለባችን እያደረገ ያለው የፕሪ ሲዝን ዝግጅት በጣም ጥሩ ነው፤ ሁላችንም ተጨዋቾች በወጣትነት ዕድሜ ላይ የምንገኝ ከመሆናችን አንፃርም ራሳችንን ለመለወጥ ጠንክረን እየሰራንም ስለሆነ የእዚህ ዓመት ላይ ጥሩ ቡድንን የምናሳይም ነው የሚመስለኝ፡፡
ሊግ፡- ሀድያ ሆሳህናን በእዚህ ዓመት ከመቀላቀልህ አኳያ የተሳካ ጊዜያትን ታሳልፋለህ? ቡድናችሁስ ምን ውጤትን ያመጣል?
አፈወርቅ፡- በሀድያ ሆሳህና በሚኖረኝ የዘንድሮ የውድድር ዘመን የተጨዋችነት ቆይታ ጥሩ ጊዜን ከፈጣሪ እርዳታ ጋር እንደማሳልፍ አስባለሁ፤ በተለይ ደግሞ አሁን ላይ በእግር ኳሱ የላቀ ደረጃ ላይ መድረስንም ስለምፈልግ እልሜ ሁሉ ይሳካልኛል ብዬም እያሰብኩ ነው፤ በእዚህ ዓመት የምናስመዘግበውን ውጤት በተመለከተም ሀድያ ሆሳዕና ከታች የመጣ ቡድን ቢሆንም የመጀመሪያው ዋና አላማችን ሊጉ ላይ መቆየት መቻል ነው፤ ሻምፒዮና ለመሆን የምንችልበት እድሉም ካለን ያን የምንጠላው አይደለም፡፡
ሊግ፡- በኢትዮጵያ እግር ኳስ ያሳለፍካቸው ጊዜያቶች የተሳኩ ነበሩ?
አፈወርቅ፡- አዎን፤ የእግር ኳስን ከባንክ ተተኪ ቡድን አንስቶ በዋናው ቡድን ደረጃ ለየካ ክፍለ ከተማ፣ ለድሬዳዋ ከተማ እና ለወልዋሎ አዲግራት ዩንቨርስቲ ቡድኖች በጥሩ መልኩ ተጫውቼ አሳልፌያለሁ፤ በእነዚህ ቡድኖች ቆይታዬም የካ ክፍለ ከተማን ወደ ብሄራዊ ሊግ ድሬዳዋ ከተማንና ወልዋሎ አዲግራት ዩንቨርስቲን ደግሞ በጋራ ከጓደኞቼ ጋር በመሆን ወደ ፕሪምየር ሊግ እንዲገባ ያስቻልኩባቸው አጋጣሚዎች አሉና እነዛ የማይረሱ ስኬቶቼ ሆነው አልፈዋል፤ ከእዛ ውጪ ደግሞ ወልዋሎ አዲግራት ዩንቨርስቲ ቡድን ውስጥ ሆኜም ለብሄራዊ ቡድን የመመረጥ እድሉን ያገኘሁባቸው አጋጣሚዎች ተፈጥረውልኝም ነበርና ይሄን ማሳካት መቻሌ የተጨዋችነት ጊዜዬን በጥሩነቱ እንድገልፀው አድርጎኛል፡፡
ሊግ፡- በመጨረሻ…..?
አፈወርቅ፡- በእግር ኳስ ተጨዋችነት ዘመኔ አሁን ላይ ለደረስኩበት ደረጃ ብዙ ነገሮችን ያደረገልኝን ፈጣሪዬን በቅድሚያ ማመስገን እፈልጋለው፤ ከዛ በመቀጠል ደግሞ ኳሱን ስጫወት ከጎኔ በመሆን ላበረታቱኝ ቤተሰቦቼ ብሎም ደግሞ ለመከሩኝና ላሰለጠኑኝ አሰልጣኞቼና ጓደኞቼ እንደዚሁም የሰፈሬ ልጆች ምስጋናዬን ማቅረብ እፈልጋለው፡፡
አፈወርቅ ኃይሉ /ሀድያ ሆሳዕና/ “ዋናው አላማችን በሊጉ መቆየት መቻል ነው”
ተመሳሳይ ጽሁፎች