በመሸሻ ወልዴ /G.BOYS/
ኢትዮጵያ ቡናዎች በክረምቱ የተጨዋቾች ዝውውር መስኮት ነዋሪነቱን በአሜሪካ ሀገር አድርጎ ለነበረው የቀድሞ አሰልጣኛቸው ካሳዬ አራጌ የጨዋታ ፍልስፍና ይሆናሉ በሚል በአሁን ሰዓት የተለያዩ ተጨዋቾችን እያስፈረሙ ሲገኝ ከእነዚህ ተጨዋቾች መካከልም በክለብ ደረጃ ለኒያላ፣ ለኤሌክትሪክ፣ ለሐዋሳ ከተማ እና በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ደረጃም በመመረጥ ለመጫወት የቻለው ታፈሰ ሰለሞንም ይገኝበታል፡፡
አትዮጵያ ቡና ታፈሰ ሰለሞንን ወደ ቡድኑ በማምጣቱና የግል ንብረቱም ሊያደርገው በመቻሉ የተጨዋቾች አመላመሉ በደጋፊዎቹ ዘንድም እየተወደደለት ይገኛል፡፡ ኢትዮጵያ ቡናን በመሀል ሜዳው ስፍራ ለማገልገል ዘንድሮ ቡድኑን የተቀላቀለው ታፈሰ ሰለሞን በፕሪምየር ሊጉ የእስከዛሬው የተጨዋችነት ቆይታው በብዙዎች የእግር ኳስ አፍቃሪዎችም ሆነ በየክለቡ ደጋፊዎች ባለው ችሎታው የሚወደድና የሚደነቅ ተጨዋች ሲሆን በተለይ ደግሞ ለአጥቂዎች በሚያቀብላቸው ጣጣቸውን የጨረሱ ኳሶችና በእንቅስቃሴም የተቃራኒ ቡድን ተጨዋቾችን በመቀነስ እና ራሱም ወደ ግብ ቀጥተኛ ኳሶችን በመምታት በሚያደርግው የግብ ሙከራና በሚያስቆጥራቸው ግቦችም ተለይቶ ይታወቃል፡፡
የኢትዮጵያ ቡናን ፊርማ በቅርቡ ያኖረው ታፈሰ ሰለሞን በዝውውሩ መስኮት በቅ/ጊዮርጊስ፣ በፋሲል ከነማ እና በሰበታ ከተማ ቡድኖች በጣሙን ተፈልጎ የነበረ ሲሆን ይሄ ተጨዋች ማረፊያው ኢትዮጵያ ቡና ከመሆኑም በፊት በቅርቡ ባደርግንለት ቃለ-ምልልስ ወደ ቅ/ጊዮርጊስ የማመራ ይመስለኛል ብሎን እንደነበር ይታወሳል፤ ታፈሰን በእዚህ እና በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ላይ አዲሱን ክለቡን ኢትዮጵያ ቡናን ከተቀላቀለ በኋላ ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ አናግሮት ምላሹን እንደሚከተለው ሰጥቷል፡፡
ሊግ፡- በቅርቡ ከአንተ ጋር ባደረግነው ቃለ-ምልልስ ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ የማመራ ይመስለኛል ብለህ ነበር፤ አሁን ላይ ግን መገኛህ እና አዲሱ ቡድንህ ኢትዮጵያ ቡና ሆኗል፤ እንዴት የሀሳብ ለውጥን አደረግክ?
ታፈሰ፡- እውነት ነው፤ ቅዱስ ጊዮርጊሶች ከዛሬ ሁለት ዓመት ጀምሮና በእዚህም የክረምቱ ወራት እኔን የመውሰድ ከፍተኛው ፍላጎት ስለነበራቸው ወደ እነሱ የማመራ ይመስለኛል ብዬ ተናግሬ ነበር፤ በኋላ ላይ ግን በአንድ አንድ ጉዳዮች ላይ በተለይ ደግሞ ከአጨዋወት ጋር በተያያዘ ከራሴ ጋር በመነጋገርና መለስ ብዬም በማሰብ ወደ እነሱ ሳላመራ ቀርቻለው፤ በዝውውሩ መስኮት ከቅ/ጊዮርጊስ ውጪ የእኔ ሌሎቹ አማራጮቼ የነበሩት ኢትዮጵያ ቡና፣ ፋሲል ከነማና ሰበታ ከተማ ሲሆኑ በኋላ ላይ የእኔ የሜዳ ላይ አጨዋወት ኢትዮጵያ ቡና ከሚከተለው የጨዋታ ፍልስፍና ጋር አብሮ የሚሄድ ስለሆነ እንደዚሁም ደግሞ ለአዲስ አበባ ክለብም መጫወትን ስለፈለግኩ ቡናን ምርጫዬ አድርጌ ልፈርም ችያለሁ፡፡
ሊግ፡- ኢትዮጵያ ቡና በመጪው የውድድር ዘመን በአዲስ አሰልጣኝና በአዲስ አጨዋወት ሜዳ ላይ ይቀርባል፤ ስለአሰልጣኙና ስለአጨዋወቱ ምን የምታውቀው ነገር አለ?
ታፈሰ፡- የኢትዮጵያ ቡና እግር ኳስ ክለብ በአዲስ መልክ ከአሜሪካን ሀገር ያስመጣው የቀድሞ ተጨዋቹንና አሰልጣኙን ካሳዬ አራጌ ከእዚህ ቀደም በነበረው የቡድኑ ረዘም ያለ ቆይታው ሲጫወትም ሆነ ሲያሰለጥን ብዙ ባልደርስበትም እንደዚሁም ደግሞ ብዙ ባላውቀውም ስለ እሱ ከሰዎች እንደሰማሁት ከሆነ ግን ሲጫወት ጎበዝ እንደነበርና ኳስንም ከእሱ ላይ መንጠቅ በጣም አስቸጋሪ እንደሆነ በአሰልጣኝነቱም ጊዜ ይከተለው በነበረው የአጨዋወት ፍልስፍና ኳስ ላይ መሰረት ያደረገን እንቅስቃሴ የሚከተል ቡድንን የሰራ መሆኑና በተለይ ደግሞ በእሱ አጨዋወት ውስጥ ሁሉም ተጨዋች አጥቂ መሆኑና ብቸኛ አጥቂ የሚባል ነገር እንደሌለው ነው የሰማሁትና በእዚሁ አጨዋወት ውስጥ ሆኜ ነው ራሴን ብቁ ተጨዋች አድርጌ በማቅረብ ለቡና ከእኔ የሚፈልገውን ጥቅምና ውጤታማ ግልጋሎትን ልሰጥ የተዘጋጀሁት፡፡
ሊግ፡- ለኢትዮጵያ ቡና ፊርማህን ካኖርክ በኋላ በውስጥህ ምን አይነት ስሜት ነው የተፈጠረብህ?
ታፈሰ፡- ለአዲሱ የውድድር ዘመን ወደ ቡና በመምጣቴ በጣም ደስ ብሎኛል፤ ምክንያቱም ኢትዮጵያ ቡና ትልቅ ቡድንና በብዙዎችም ዘንድ የማወደድ ክለብ በመሆኑ ነው፤ ከእዛ ውጪም ደጋፊዎቹ የእኔን ወደ ክለቡ መምጣት በጣም ይጓጉና ይፈልጉ ስለነበር እንደዚሁም ደግሞ ያልጠበቁትም ነበርና በኋላ ላይ ሁሉም ነገር እውነት መሆኑን ሲያውቁ እንኳን ደስ አለ፤ እንኳንም ወደ ኢትዮጵያ ቡና ክለብ በሰላም መጣህም ሲሉኝ ነው የበለጠም የተደሰትኩት፡፡
ሊግ፡- ኢትዮጵያ ቡናን መቀላቀልህና ፊርማህንም ማኖርህ ሙሉ ለሙሉ ተረጋግጧል፤ በክለቡ ቆይታህ ምን አይነት ጊዜን የምታሳልፍ ይመስልሃል?
ታፈሰ፡- በኢትዮጵያ ቡና የተጨዋችነት ቆይታዬ ጥሩ ጊዜን እንደማሳልፍ ከወዲሁ የእርግጠኝነት ስሜት ይሰማኛል፤ ይሄን የምልህ ደግሞ ያለምክንያት አይደለም፤ ኢትዮጵያ ቡና ኳስን ተቆጣጥሮ ለመጫወት የሚሞክር ቡድን ነው፤ በእንደዚህ አይነት አጨዋወት ውስጥ ደግም እኔ ከምፈልገው አይነት እንቅስቃሴ ጋር ቡድኑ አብሮ የሚሄድ ስለሆነ በክለቡ ጥሩ ጊዜ ይኖረኛል ብዬ አስባለው፡፡
ሊግ፡- ኢትዮጵያ ቡናን በሜዳ ላይ እንቅስቃሴም ሆነ በውጤት ደረጃ በምን መልኩ እንጠብቀው?
ታፈሰ፡- ኢትዮጵያ ቡና ያለፉትን ሁለትና ሶስት አመታቶች በውጤትም ሆነ በሜዳ ላይ እንቅስቃሴው በምን መልኩ እንዳሳለፈ አውቃለው፤ ቡና በእነዛ ጊዜዎቹ ደከም ብሎም ቀርቦ ነበር፤ አሁን ላይ ግን ስለ መጪው ቡድናችን ከወዲሁ እያሰብን የምንገኘው በመጀመሪያ የድሮውን ኢትዮጵያ ቡና የጨዋታ እንቅስቃሴ መመለስ ነው፤ ከዛ ደግሞ ቡድኑ በሂደት ውጤታማ የሚሆንበትን ነገር በአዲሱ አሰልጣኛችን የአጨዋወት ፍልስፍና ለማምጣት ጥረትን እናደርጋለን፤ በእግር ኳስ ጨዋታ ሁሌም ጥሩ እንቅስቃሴ ሲኖርህ ውጤት ይኖርሃል፤ ቡድናችን አሁን ላይ እንደ እነ አማኑሄልን እንደዚሁም ደግሞ ሌሎችም ጥሩ ብቃት ያላቸውን ተጨዋቾች ይዟል፤ ከመጪው ጊዜ ጀምሮ ደግሞ በአጨዋወት ደጋፊው ብቻ ሳይሆን ህዝቡም የሚወደውን ቡናን ከውጤታማነት ጋር የምንመልሰው ይመስለኛልና ለእዛ ሁሉም በትህግስት ይጠብቀን ነው የምለው፡፡
ሊግ፡- በመጨረሻ…..?
ታፈሰ፡- ኢትዮጵያ ቡና በሀገሪቱ የስፖርት ታሪክ ውስጥ በብዙዎች ዘንድ ከመወደዱ አንፃር ለእዚህ ቡድን ለመጫወት መምጣቴ በጣም ነው ያስደሰተኝ፤ ለእዚህ ቡድንም ከመጣሁ በኋላ ከእኔ የሚጠበቀውን ነገር ሁሉ ለማበርከት ዝግጁም ነኝ፤ ይህን ካልኩ በኋላ በክረምቱ የተጨዋቾች ዝውውር መስኮት ወደተለያዩ ክለቦች ለማምራት ጥያቄዎች ቀርበውልኝ እና ለአንዳንዶቹም ደግሞ እፈርማለሁም ብዬ ወደ እነሱ ሳልመጣ በመቅረቴ ያስከፋኋቸው ካሉ በእዚህ አጋጣሚ ይቅርታ መጠየቅን ነው የምፈልገው፡፡