በመሸሻ ወልዴ
“ባህር ዳር ዘንድሮ ጥሩ ውጤት እንዲያመጣ ቡድኑ ውስጥ ያለው ችግር ሊፈታ ይገባል”
ባህር ዳር ከተማ በሳምንቱ አጋማሽ ኢትዮጵያ ቡናን 3ለ2 አሸንፏል፤ ቡድኑ ይህን ጨዋታ በድል ከተወጣ በኋላም የደረጃ ለውጥን ሊያስመዘግበ ችሏል፤ ሁለቱ ክለቦች ባደረጉት በእዚህ ጨዋታ በሜዳ ላይ ስለነበረው እንቅስቃሴና በማሸነፋቸው ዙሪያ እንደዚሁም ደግሞ ስለ እነሱና ስለተጋጣሚያቸው እንቅስቃሴ የቡድኑ ውጤታማው ተጨዋች ወሰኑ ዓሊ ከጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ ጋር ቆይታን አድርጎ በእዚህ መልኩ ምላሹን ሰጥቷል፡፡
ሊግ፡- የባህር ዳር ከተማ ቆይታህ የተመቸህ ይመስላል፤ እርግጥ ነው?
ወሰኑ፡- አዎን፤ ቆይታዬ በጣም አሪፍ ነው፤ ዘንድሮም አራተኛ ዓመቴን ይዣለው፤ በተለይ ደግሞ ቡድናችንን በአሰልጣኝነት ለመምራት የተቀላቀለን አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ የቡድኑ ተጨዋቾች ላይ የፈጠረው ነገር ትልቅ እና ጥሩ ነገር ስለሆነም በእዚህ ዓመት ለሻምፒዮናነት ነው የምንጫወተው፡፡
ሊግ፡- አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ ወደ ቡድናችሁ ከመጣ በኋላ ምንድን ነው የፈጠረው ነገር?
ወሰኑ፡- በዋናነት በአሰለጣጠን ዘይቤው ነው፤ ቡድኑ ጥሩ ኳስን እንዲጫወት ይፈልጋል፤ ከእዚያ ባሻገር ደግሞ ራሱም ወጣት ስለሆነም ከእኛ ጋር እንደጓደኛም ሆኖ በመቅረብም ነው ልምምድ እያሰራን ያለውና ደስ የሚል ነገርን እያሳለፍን ይገኛል፡፡
ሊግ፡- በእግር ኳስ ተጨዋችነት ዘመናችሁ አንተም አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝም ለኢትጵያ መድን ተጫውታችኋል፤ ይሄ ሁኔታ ያመሳስላችኋል፤ መጫወቱን ታውቃለህ?
ወሰኑ፡- በሚገባ ነዋ! ያኔ በጣም የሚገርምህ ልጅ ሆኜ ነው ፋሲል ተካልኝን ለመድን ሲጫወት አየው የነበረው፤ በወቅቱም በባህሪው የሚያስገርም እና ጥሩ ተጨዋችም ነበር፤ በኋላ ላይ ደግሞ እኔ አድጌ ወደ መድን ክለብ ለመጫወት ስገባ አሰልጣኛችን የነበረው አስራት ኃይሌ ስለእሱ ብዙ ነገሮችን ይነግረን ነበር፤ ከእነዛ ውስጥም በተለይ ስለፋሲል በጣም አስተዋይነት ደጋግሞ ይነግረን ነበርና ስለ እሱ ብዙ ነገሮችን እኔ ሳላውቀው በደንብ ያወቅኩት በአሰልጣኝ አስራት ኃይሌ አማካኝነት ነው፡፡
ሊግ፡- በኢትዮጵያ መድን በነበረህ ቆይታ አንተን ያሰለጠነህ አሰልጣኝ አስራት ኃይሌ የአሁኑን አሰልጣኝህንም ፋሲል ተካልኝን ሊያሰለጥነው ችሏል፤ በእዚህ ዙሪያ የምትለው ነገር ካለ? ስለ አስራት ከዚህ በፊት ብዙ ነገር ብለሃልና አስራት ለአንተ ምን ማለት ነው?
ወሰኑ፡- በኢትዮጵያ መድን እኔን በቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ውስጥ ደግሞ ፋሲል ተካልኝን አሰልጥኖን ያሳለፈው አሰልጣኝ አስራት ኃይሌ የእውነቴን ነው የምነግርህ በጣም ትልቅ እና ለሙያውም ሟች የሆነ ሰው ነው፤ ቀጥተኛ እና እውነተኛም አሰልጣኝ ነው፡፡ አስራት ማለት ለእኔ አባቴም ጭምር ነው፤ በጣምም ነው የምወደው፤ መካሪዬ ጭምር ነው፤ ስለ እሱ ምን ብዬ እንደምገልፅም አላውቅም፤ ለእኔ ህይወት እዚህ ደረጃ ላይ መድረስም ትልቅ ነገርን አድርጎልኛልና ባገኘሁት አጋጣሚ ሁሉ ሳላመሰግነው አላልፍም፡፡
ሊግ፡- ለባህር ዳር ከተማ እየተጫወትክ ከመሆኑ አንፃር የሊጉን ጅማሬያችሁን እንዴት ትገልፀዋለህ? ስለጠንካራ እና ደካማ ጎናችሁስ ምን ትላለህ?
ወሰኑ፡- በፕሪምየር ሊጉ የአሁን ተሳትፎአችን በአብዛኛው ጥሩና ጠንካራ ጎን ቢኖረንም ክፍተቶችም አለብን፤ ከክፍተቶቻን ውስጥም በተለይ ጎል ካገባን በኋላ የምንዘናጋው ነገር አለ፤ ከዛ ውጪም መከላከሉም ላይ ድክመት አለብን፤ ሌለው ደግሞ ከክለባችን ጋር በተያያዘም ከመብት ጥያቄ ጋር በተያያዘ እኛ ተጨዋቾች ባልተከፈለን ደመወዝ ላይ ከክለቡ ጋር ልዩነትን የፈጠርንበትም አጋጣሚ ስላለ እና ሁላችንም ደስተኛ ስላልሆንም ይሄን ለቡድናችን የቀጣዮቹ ጊዜ ውጤታማነት ስንል እኛ የሜዳ ላይ ችግሩን ክለቡ ደግሞ ከወርኋዊ ክፍያ እና ጥቅማቅም ጋር ባለው ነገር ያለውን ችግር በፍጥነት ሊያስተካክለው ነው የሚገባው፡፡ ያን ክለቡ ካስተካከለም ካለው ጥንካሬ አንፃር ቡድናችን አሁን ካስመዘገበው ውጤት የተሻለ ውጤትም ያመጣል፡፡
ሊግ፡- የባህር ዳር ከተማ ደጋፊዎች በአንተ አንደበት እንዴት ነው?
ወሰኑ፡- የባህር ዳር ደጋፊዎች በአደጋገፍ ስልታቸው እና በአይበገሬነታቸው ከብዙዎቹ ይለያሉ፤ በተለይ በዛ ሞቃታማ እና ከባድ ፀሐይ ላይ ሆነው ስናሸንፍም ሆነ ስንሸነፍ 90 ደቂቃ ሙሉ እየጨፈሩና ከጎናችንም ሆነው ሲደግፉን ልዩ ስሜት ይሰጣሉና በእዚህ አጋጣሚ እነሱ የጀርባ አጥንታችን መሆናቸውንም መናገር እፈልጋለው፤ በጣምም አመሰግናቸዋለው፡፡
ሊግ፡- የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የዘንድሮ ጨዋታችሁ ላይ የቆጨህ ግጥሚያ አለ?
ወሰኑ፡- አዎን፤ በጣም የቆጩኝ ጨዋታዎች ሶስት ናቸው፤ እነሱም ጅማ አባጅፋርን በ5 እና 6 ግብ ልዩነት ማሸነፍ እየቻልን አቻ የወጣንበት ሀድያን ማሸነፍ እየቻልን አቻ የወጣንበት እና ፈፅሞ ደግሞ ጨዋታውን በማይገልፀው መልኩ በፋሲል ከነማ የተሸነፍንበት ጨዋታ የሚያስቆጩ ናቸውና በሁለተኛው ዙር እነሱን ስናገኝ የምንበቀላቸውም ነው የሚሆነው፡፡
ሊግ፡- በፋሲል ከነማ ስለተሸነፋችሁበት ጨዋታ ብዙ ነገር ሲባል ሰምተናል፤ ባህርዳር ከተማ መሸነፍ የለበትም በሚል ግን እኮ 3 ግቦች ነው የተቆጠረባችሁ?
ወሰኑ፡- ፋሲልን ስንፋለም የእውነት ነው እንዳገኘነው የግብ እድልና ጨዋታችን መሸነፍ አልነበረብንም፤ እኛም ነበርን ካገኘናቸው ሰባት የግብ እድሎች ውስጥ አራቱን ጎሎች አስቆጥረን ልናሸንፍ የነበረውና ያገኘናቸውን የግብ እድሎች በአግባቡ አለመጠቀማችን በጨዋታው ትልቅ ዋጋን ከፍለን እንድንወጣ አድርጎናል፡፡
ከፋሲሎች ጋር በነበረን ጨዋታ እነሱ እኛ ላይ ጎሎች ማስቆጠራቸው በኳስ የሚያጋጥም ነው፤ የእኛ ጥሩነት የነበረው ደግሞ በጨዋታ ላይ ብቻ ነው፤ ጥሩ መሆን ጎል ካላስቆጠርክ ብዙም ትርጉም የለውም፤ እነሱ ያገኙትን አጋጣሚ በመጠቀም ጎል በማግባት ከእኛ የተሻሉ ሆነው ጨዋታውን አሸንፈዋልና፤ እኛን ስላላሸነፍን ጥሩ አያስብለንም፤ ከተሸነፍክ ሁሌም ተሸነፍክ ማለትም ነው፡፡
ሊግ፡- ኢትዮጵያ ቡናን ያሸነፋችሁበት ጨዋታ ምን መልክ ነበረው? ተጋጣሚያችሁ ይዞት የመጣውንስ እንቅስቃሴ እንዴት ትገልፀዋለህ?
ወሰኑ፡- ኢትዮጵያ ቡና ይዞት የመጣው አዲሱ አጨዋወት ደስ ይላል፤ አዲሱ አሰልጣኝም ጥሩ ነገርን በሜዳ ላይ ለማሳየት ችሏል፤ ያም ሆኖ ግን የእኛ ቡድን እነሱ እንደዚህ እንደሚጫወቱ መቶ ፐርሰንት ተዘጋጅቶበት ነበር የመጣው እና እነሱ በሚሳሰቱበት ቀዳዳ እየሄድን ነበር ቶሎ ጎሎች ለማስቆጠር የጣርነውና በእዛም ማሸነፉ ተሳክቶልናል፤ በእዚሁ ጨዋታ እኛ ቡናን እናሸንፍ እንጂ መጨረሻ ላይ የያዝነውን ውጤት ለማስጠበቅ ወደ ኋላ ሸሽተን ስንጫወት አንድ አንድ ነገሮች ተፈጠሩ እንጂ ቡና በጣም ደስ የሚል አጨዋወትን ነው ይዞ የመጣው፤ ይሄ አጨዋወቱ ግን እንደ ባህር ዳር አይነት እንደዚሁም ደግሞ እንደ አዲስ አበባ ስታድየም የመሳሰሉት ላይ እንጂ ሌላ ክልል ላይ ወጥተህ እንደዚህ አይነት አጨዋወት እጫወታለው ቢል ትንሽ ሊከብደው ይችላል ከሜዳው አንፃር እንጂ የቡና የአጨዋወት ዘይቤው በጣም ደስ ይላል፤ እኔም የወደደኩት ነው፤ አሰልጣኙም ጥሩ ቡድንን ነው የሰራው፡፡
ሊግ፡- ኢትዮጵያ ቡናን ለማሸነፍ የረዳችሁ ሌላስ ተጨማሪ ነገር ነበር፤ በእንቅስቃሴስ ማን የተሻለ ነበር?
ወሰኑ፡- ከኢትዮጵያ ቡና ጋር በነበረን ጨዋታ ሁለታችንም ጥሩ ፉክክር ብናደርግም በአጨዋወት ዘይቤ እነሱ የተሻሉ ነበሩ፤ ያም ሆኖ ግን እኛ ወደሜዳ የገባንበት ዋናው ዓላማ ጨዋታውን ለማሸነፍ ብቻ ነበርና ያ ሊሳካልን ችሏል፡፡
ሊግ፡- ባህር ዳር ከተማን በቀጣዮቹ ፍልሚያዎች እንዴት እንጠብቀው? ምን ውጤትስ ዘንድሮ ታስመዘግባላችሁ? ቡድናችሁ ውስጥስ ችግር አለ?
ወሰኑ፡- አዎ፤ ችግርማ አለ፤ ያንን ተቋቁመንም ነው እየተጫወትን የምንገኘው፤ የደመወዝ ጉዳይ ቡድናችን ውስጥ አሳሳቢ ነገር ሆኗል፤ ባለፈው የጎንደር ጨዋታም ላይ ሶስቱ ዜጋ ተጨዋቾች ያልተጫወቱትም ከዚሁ ጋር በተያያዘ ጉዳይም ነበር፡፡ የባህር ዳር ከተማ ክለብ ዘንድሮ ስለሚያመጠው ውጤት ማለት የምፈልገው ነገር ቢኖር የአሁን ሰዓት ላይ ባለው ጥሩ ቡድን በክለቡ እና በተጨዋቾቹ መካከል ከደመወዝ ክፍያ ጋር በተያያዘ ያለው ችግር ከተፈታ የተሻለ ውጤት ዘንድሮ ይኖረዋል፤ ያለዚያ ግን ከቡድኑ ጋር አሁን ላይ ባለው ሁኔታ መቀጠል በጣም ከባድ ነገር ነው፤ ክለቡ ደመወዛችንን እንዲሰጠን በተደጋጋሚ ጊዜ ነግረናቸዋል፤ ያም ሆኖ ግን ምላሽ የሚሰጠን ሰው የለም፤ አሁን በክለቡ ይሄ ነው ብለህ የምትጠይቀው አካልም የለም፤ በእዚህ ሁኔታም የመጀመሪያው ቅሬታ አሰሚም እኔ ነኝ፤ በእዚሁ ሁኔታ አልቀጠልም፤ ምንአልባትም ሁኔታው በእዚህ ከቀጠለ ግማሽ ዓመት ላይም ከቡድኑ ጋር ልለያይ እችላለው፡፡
ሊግ፡- በእግር ኳሱ ቀጣይ የጨዋታ ጊዜያቶችህ አንተን እንዴት እንጠብቅህ?
ወሰኑ፡- የእግር ኳስን ሁሌም ስጫወት ለክለቤ ጥሩ ውጤት ከማስመዝገብ ባሻገር ለብሔራዊ ቡድንም ተመርጬም መጫወትን ነው የምፈልገው፤ አሁን ፋሲል ተካልኝ ይዞት የመጣው አጨዋወትም ለእዛ ደረጃ የሚያደርሰኝና የተመቸኝም ስለሆነ ከአምና ብቃቴ ዘንድሮ በተሻለ መልኩ እንደምቀርብ እና የምመኘውን ነገር ሁሉ እንደማገኝ ተስፋ አለኝ፡፡
ሊግ፡- በተለያየ ስም ትጠራለህና የአንተ ስም ወሰን ነው ወይንስ ወሰኑ?
ወሰኑ፡- ትክክለኛው የመታወቂያ ስሜ ወሰኑ ዓሊ ነው፤ ብዙዎቹ ግን ወሰን ብለው ነው የሚጠሩኝና እኔም በእዚህ ስም ስጠራ ነው በጣም ደስ የሚለኝ፡፡
ሊግ፡- በመጨረሻ…?
ወሰኑ፡- የባህር ዳር ደጋፊና ህዝብ ለእኛ ብዙ ነገርን አድርጎልናል፤ በተለይ ደግሞ ለእኔ ትልቅ ነገር አለው፤ እነሱን ሁሌም ነው ከጀርባዬም ስላሉ ላመሰግናቸው የምፈልገው፡፡