Google search engine

“ኢትዮጵያ ቡናን የመጫወቻ ቦታ አሳጥተን አሸንፈናቸዋል”
ኤፍሬም ዘካሪያስ /ሐዋሳ ከተማ/

#በመሸሻ_ወልዴ

የኢትዮጵያ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ሻምፒዮና ዘንድሮ በተመረጡ የተለያዩ የክልል ከተማ ስታዲየሞች ላይ ሲካሄድ የቀየ ሲሆን ይኸው ግጥሚያም በብሔራዊ ቡድናችን ጨዋታ ምክንያት ከተቋረጠ በኋላም በድጋሚ ከረቡዕ ዕለት አንስቶ ቀጣይ ተረኛ በሆነችው የድሬዳዋ ከተማ ላይ ጨዋታዎቹ ተከናውነው ቅዱስ ጊዮርጊስ ከሰበታ ከተማ ጋር አቻ ሲለያይ ሐዋሳ ከተማ ደግሞ በምኞት ደበበ ብቸኛ ግብ ኢትዮጵያ ቡናን 1-0 አሸንፏል፤ ድሬደዋ ከተማም በዳንኤል ሀይሉ ብቸኛ የፍፁም ቅጣት ምት ግብ ጅማ አባጅፋርን በተመሳሳይ 1-0 ውጤት ጨዋታውን በድል ሲወጣ ሌላ በተደረገው ጨዋታም የሊጉ መሪ ፋሲል ከነማ በሙጂብ ቃሲም ሁለት ግቦች 7 የሚደርሱ ቋሚና ተጠባባቂ ተጨዋቾችን በኮቪድ በመያዛቸው ምክንያት በግጥሚያው ሊያገኛቸው ያልቻለውን ወላይታ ዲቻን 2-0 ሊያሸንፍ ችሏል፡፡
የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ የእዚህ ሳምንት ጨዋታን አስመልክቶም ድል ከቀናቸው ቡድኖች መካከል ሐዋሳ ከተማ ኢትዮጵያ ቡናን በረታበት ጨዋታ ላይ ጥሩ እንቅስቃሴን ያደረገውንና ለቡድኑም ግብ ማስቆጠር ኳስን አመቻችቶ በማቀበል ምክንያት የሆነውን ኤፍሬም ዘካሪያስን የሊግ ስፖርት ጋዜጠኛው መሸሻ ወልዴ በተለያዩ ጥያቄዎች ዙሪያ አናግሮት ተጨዋቹ ምላሽን በሚከተለው መልኩ ሰጥቷል፤ ተከታተሉት፡፡  

በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ስላደረጉት ጨዋታ

“በመጀመሪያው አጋማሽ እነሱ ኳሱን ተቆጣጥረው ለመጫወት ሲሞክሩ እኛ ደግሞ በመሀል ሜዳው ላይ ያሉትን የእነሱን ተጨዋቾች ከተከላካይ ክፍላቸውም ጋር ሆነ ከአጥቂው ክፍላቸው ጋር ኳስን ምቾት ባለው መልኩ እንዳይጫወቱና ለአጥቂው ክፍላቸውም የተመቻቹ ኳሶችን እንዳያደርሱ የመጫወቻ ቦታውን /ስፔሱን/ ስለዘጋንባቸው እንደዚሁም በመረጡት አጨዋወት ውስጥም ምንም አይነት ቀዳዳን እንዳያገኙ ስላደረግናቸውም ቡናዎች በሚፈልጉት መልኩ እንዳይጫወቱ አድርገናቸዋል፤ በዚሁ የጨዋታ ክፍለ ጊዜም የእኛ ቡድን የግብ ሙከራዎችን በማድረግም ጥሩ ነበር፤ እኔም ያደረግኩት የግብ ሙከራም ነበር”፡፡ የሁለተኛው አጋማሽ ሲጀመር ደግሞ በእዛው እንቅስቃሴ ውስጥ ሆነን ግጥሚያችንን ብንጀምርም ከመጀመሪያው አጨዋወታችን ግን ትንሽ በመውጣታችን እነሱ ኳሱን በመቆጣጠርና ወደ እኛ የግብ ክልልም በመምጣት ጥሩ ሊጫወቱ ችለዋል፤ ወዲያው ግን መልሰን ወደነበርንበት እንቅስቃሴ ውስጥ በመግባታችንና ጥሩም ለመጫወት በመሞከራችን በአጠቃላይ በመረጥነው አጨዋወት ውስጥ እነሱን የመጫወቻ ቦታ ስላሳጣናቸው ልናሸንፋቸው ችለናል”፡፡

ስለነበራቸው ጠንካራ እና ደካማ ጎን

“የኢትዮጵያ ቡናን በተፋለምንበት ጨዋታ የእኛ ጠንካራ ጎን የነበረው ካለንበት ደረጃ አንፃር የግድ 3 ነጥብ ያስፈልገን ስለነበር ግጥሚያውን ለማሸነፍ የነበረን ቁርጠኝነት፣ እንደዚሁም ደግሞ ተጋጣሚያችን ጠንካራና ጥሩ ቡድን ከመሆኑ አንፃር ብዙ ድካምንና ሩጫን በጠየቀው ጨዋታ እስከ መጨረሻው ሰዓት ድረስ ኳሱን ሳንሰለች መጫወታችን ለፈለግነው ውጤት ጭምር ሊያበቃን ችሏል፤ ወደ ክፍተት ጎን ሳመራ ደግሞ እኔ ብዙም አልታየኝም፤ ቡድናችን ከሌላው ጊዜ አኳያ ኳስን ሲያገኝ በመጫወትና ወደፊት በመሄድም  የተሻለ ሆኖ የቀረበበት ጨዋታም ነበርና ይሄን ነው ለማስቀጠል የምንፈልገው”፡፡

ኢትዮጵያ ቡናን ማሸነፋቸው ይገባቸው እንደሆነ

“አዎን፤ የድል ውጤቱ ለእኛ ይገባናል፤ ምክንያቱም ካስቆጠርነው ግብ ውጪ ተደጋጋሚ የግብ እድሎችን የፈጠርነው እኛ ነንና!”

ያገኙት የድል ውጤት ስለሚፈጥርላቸው ነገር

“በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ዘንድሮ ማሸነፍ እየተገባን ያጣናቸው ብዙ ውጤቶች አሉ፤ በነበረብን የትኩረት ማነስ ችግርም እነዛን ውጤቶች ማጣታችን እድለኞች አላደረገንም፤ ከኢትዮጵያ ቡና ባደረግነው ጨዋታ ግን እነሱ ቀላል የሚባሉ ቡድን ስላልነበሩ ከ7 ጨዋታ በኋላ ያገኘነው ድል እኛን በጣሙን ሊያነሳሳን የሚችል ነው፤ ቡናን ማሸነፋችን ለጨዋታው ምን ያህል ከፍተኛ ትኩረት እንደሰጠነው ያሳየን ግጥሚያ ነው፤ በጨዋታው ከዚህ ቀደም ተጫውተው የማያውቁ ወጣት ተጨዋቾችንም ልንጠቀምባቸው ችለናል፤ ይሄ የድል ውጤት እነሱን በጣም የሚያነሳሳቸው እና እኛን ሲኒየሮችንም ይበልጥ እንድንጠናከር የሚያደርገንም ስለሆነ የውጤቱ መገኘት ለቀጣዮቹ የቡድናችን ጨዋታዎች ከፍተኛ ግብአትንም ነው ሊፈጥርለት የሚችለው”፡፡

ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉን በምን ደረጃ ላይ ሆነው ያጠናቅቁ እንደሆነ

“በቅድሚያ በዚሁ የአሸናፊነት መንፈስ በመቀጠል በደረጃው ሰንጠረዥ ወደፊት መጠጋትን ነው የምንፈልገው፤ የውድድር ዘመኑ ሲጠናቀቅ ደግሞ አሁን ባላን ወቅታዊ አቋም ለእያንዳንዱ ጨዋታዎቻችን ከፍተኛ ትኩረት ሰጥተን ሊጉን ከ1ኛ እስከ አራተኛ አለያም ደግሞ እስከ አምስተኛ ባለው ደረጃ ላይ ሆነን ማጠናቀቅ ነው የምንፈልገው”፡፡

በሐዋሳ ከነማ ክለብ ውስጥ ስላለው ወቅታዊ አቋም እና ከኢትዮጵያ ቡና ጋር በነበረው ጨዋታ ጥሩ ስለመንቀሳቀሱ

“በዚህ ቡድን ቆይታዬ እስካሁን ክለቡን ከመጥቀም አንፃር በራሴ የምችለውን ነገር ሁሉ እያደረግኩኝና ጥሩም እየተጫወትኩኝ ነው፤ እግር ኳስን ጥሩ ለመጫወት ደግሞ መሯሯጥ እና መልፋትም አለብህና ያንን እኔ በሜዳ ላይ እያሳየሁኝ ነው፤ ቡናን በገጠምንበት ጨዋታ ጥሩ ልንቀሳቀስ የቻልኩት ተሯሩጬ ስለተጫወትኩኝና የሜዳውም ሰፊ አለመሆን ለእንቅስቃሴዬ ምቹ ስለሆነልኝም ነው፤ የቡና አጨዋወት በሰፊ ሜዳ ላይ ሲሆን የእነሱን የመጫወቻ ስፍራ ለመዝጋት በጣም ስለሚከብድና ኳስንም ብዙ ፖሰስ ስለሚያደርጉ ለተጋጣሚ ቡድኖች በጣም ያስቸግራል፤ የሜዳው ሰፊ አለመሆን የእኛን ቡድንና እኔንም በጣም ጠቅሞኛል፤ ከዛ ውጪም ከስር አድገው የመጡት ልጆችም አንድአንዶቹ የመጀመሪያ ጨዋታቸውንም ነው ያደረጉት እኔን በማገዙም በኩል አስተዋፅኦዋቸው የጎላም ነበርና ለዛም ነው ጥሩ ልንቀሳቀስና ቡድናችን በምኞት ደበበ አማካኝነት ላስቆጠረው የድል ግብም ኳሱን በማቀበል እኔ ምክንያት ልሆንም የቻልኩት”፡፡

በተቃራኒነት የቀድሞ ቡድኑን ስለመፋለሙ

“ኢትዮጵያ ቡና ብዙ ነገርን የተማርኩበት እና እግር ኳስንም በምን መልኩ መጫወት እንዳለብኝ ጠንቅቄ ያወቅኩበት ቡድን ነው፤ ክለቡ ለአራት ተከታታይ ዓመታት የቆየሁበት ስለሆነም የኳስ እድገቴ በአብዛኛው እዛ ቡድን ውስጥም ነበርና እነሱን በተቃራኒነት ሆነህ ስትገጥም የምታደርገው ፍልሚያ ጫና ቢኖረውም የሚሰማህ የደስታ ስሜት ግን በጣም ከፍ ያለ ነው፤ ይሄን በተደጋጋሚ ጊዜ ከእነሱ ጋር ስጫወት አይቼዋለው፤ በአሁኑ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ላይም ከእነሱ ጋር በነበረን ጨዋታ ላይ ተቃራኒ ሆኜ ስጫወት ጫናው እንዳለ ቢሆንም ይሄ ግን እግር ኳስ ስለሆነና ለለበስከው ማሊያም ጥሩ ግልጋሎትን መስጠት ስላለብህ ለእኔ ጨዋታው ጥሩ ስሜትን ነው የፈጠረልኝ፤ የቀድሞ ቡድንህን በምትፋለምበት በእንደዚህ ያሉ ጨዋታዎች ላይ ደግሞ ጥሩ መንቀሳቀስ ከሁሉም በላይ መልካሙ ነገር ነው፤ ምክንያቱም የአንተ ጥሩ መጫወትህንና በእንቅስቃሴም ጥሩ ሆነህ መታየትህን የሚፈልጉና ደስ የሚላቸውም የቀድሞ ደጋፊዎችም አሉና በግጥሚያው ጥሩ ተጫውቼ መውጣቴ በጣም ደስ ብሎኛል”፡፡

ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ በዲ.ኤስ.ቲቪ ስለመተላለፉና የእናንተና የቡና ጨዋታ ይሄን ሽፋን ስላለማግኘቱ

“ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ያደረግነው ጨዋታ ረቡዕ ዕለት ብዙ ሙከራዎች ተደርገው ጨዋታው በዲ.ኤስ. ቲቪ ሊተላለፍ አለመቻሉ ሁለታችንንም እድለኛ አላደረገንም፤ ያለፈው አልፏልም ነው የምለው፤ እስከአሁን ግን ይሄ የሊግ ጨዋታ የቀጥታ ስርጭትን አግኝቶ በዲ.ኤስ.ቲቪ እየተላለፈ መሆኑ ለሁላችንም የሀገራችን ተጨዋቾች ትልቅ ጥቅምን ነው እየፈጠረልን የሚገኘው፤ ጨዋታዎቹ ሲታዩ ያለህን ችሎታና አቅም በሚገባ ታውቅበታለ፤ ከዛ ውጪም ሰዎች ምን አይነት ችሎታ እንዳለህም ይረዱልሃል፤ ሌላው ስታድየም የማይገቡ ሰዎች በቤታቸው እና በየመዝናኛ ቦታ ላይ ሆነውም ስለ እኛ ሀገር ተጨዋቾች በቂ ግንዛቤ እንዲኖራቸው እና ከዚህ ቀደም የነበራቸውን አመለካከትም እንዲቀይሩ የሚያደርግም ሁኔታዎች እየተፈጠሩም ስለሆነ ይሄ በጥሩነቱ ሊጠቀስ የሚገባው ነው፤ የኢትዮጵያን ኳስ ከዚህ ቀደም ሳይመለከቱ አይረባም ይሉ የነበሩ ብዙ ነበሩ፤ አሁን ግን ጨዋታው ሲተላለፍ ኳሱ ያምራሉ የሚሉና ተጨዋቾችንም ባገኙት አጋጣሚም የሚያበረታቱም በርካቶች ናቸውና የሰዉ አመለካከት በመቀየሩ በጣሙን ነው ደስ ያለኝ”፡፡

የዋልያዎቹ ለአፍሪካ ዋንጫ ማለፍ ስለፈጠረበት ስሜት

“ያን ዕለት ሆቴል ውስጥ ሆነን ኳሱን እየተከታተልን ነበርን፤ በመጨረሻም የአጠቃላይ የጨዋታ ውጤቶቹን ካወቅን በኋላ የዋልያዎቹን ለአፍሪካ ዋንጫ የማለፋቸውን ብስራት ስናደምጥ ሁላችንም በጣም ደስ ብሎን ጮህን፤ ደስታችንን እየገለፅን በነበርንበት ሰዓት ላይም እኛ ካለንበት ሆቴል ጀርባ ያሉ ሰዎች ምን ነገር እንደተፈጠረ አላወቁም ነበር፤ እኛ ስንጮህ አደጋ ነገር የተፈጠረ ነበር የመሰላቸው፤ ያላወቁትን ነገር ስንነግራቸው እና ኢትዮጵያም ለአፍሪካ ዋንጫ ማለፏን ስናበስራቸው እነሱም ደስ አላቸውና የደስታችን ተካፋይ ሆኑ፤ ዋልያዎቹ ለእዚህ ክብር በመብቃታቸው ልክ ከ31 ዓመት በፊት ለአፍሪካ ዋንጫው እንዳለፍነው አይነት አሁንም በድጋሚ ሁሉም ተጨዋች ላይ በድጋሚ ከፍተኛ መነሳሳትን ፈጥራል፤ ይሄ በመሆኑም ቡድናችን ላገኘው ውጤት ከመጀመሪያው ቡድን አንስቶ እስከ አሁኑ ቡድን ድረስ ያሉት ሁሉም ተጨዋቾችና ኮቺንግ ስታፉ ሊመሰገኑ ይገባል፤ ትልቅ ክብርም ይገባቸዋልና እኔም በዚሁ አጋጣሚ ሀገራችንን ለዚህ ታላቅ ስኬት ላበቁት የቡድኑ አባላቶች እንኳን ደስ አላችሁ እያልኩ፤ ከፍተኛ ምስጋናዬንም እገልፅላቸዋለው”፡፡

ለአፍሪካ ዋንጫ ያለፉትን የዋልያዎቹን ስብስብ ስለመቀላቀል

“ይሄማ ዋንኛው ፍላጎቴ ነው፤ አሁን እንኳን ለአፍሪካ ዋንጫ ማለፋችንን ሳውቅ ራሱ ምናለ የእዚህ ቡድን አባል ሆኜ ባለታሪክ ብሆን ብዬ ራሱ ተመኝቼያለው፤ ስለዚህም ቀጣይ በሚኖሩት የብሔራዊ ቡድን ምርጫ ላይ ራሴን በሚገባ በማዘጋጀት የእዚሁ ቡድን አንዱ አካል ለመሆንና ወደ ካሜሮኑ የአፍሪካ ዋንጫ ከሚጓዘው ቡድን ውስጥም አንዱ ተጨዋች ለመሆን በርትቼ በመስራት ከፍተኛ ጥረትን አደርጋለው”፡፡

በመጨረሻ

“ሐዋሳ ከተማ በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ተሳትፎው ግጥሚያዎቹን እያደረገ የሚገኘው የቡድኑ ተጨዋቾች የተለያዩ ጥቅማጥቅሞችን ካለማግኘት ጋር በተያያዘ በብዙ ችግሮች ተከበን ነው፤ ቡድናችን ይህን ክፍያ ነገ ከነገ ወዲያ ይፈፅምልናል ብለንም ነው ታግለንና ለፍተንም እየተጫወትን የምንገኘው፤ ስለዚህም ይሄ ቡድን ጥሩና የተሻለ ውጤትንም ለማስመዝገብ አቅሙ ያለው በመሆኑም የክለቡ ሀላፊዎች በዚህ ዙሪያ ቢያስቡበት መልካም ነው የሚሆነው”፡፡

https://t.me/Leaguesport

spot_img
ተመሳሳይ ጽሁፎች

አስተያይት ያስፍሩ

እባክዎን አስተያይትዎን ያስፍሩ
እባክዎን ስምዎን እዚህ ያስገቡ

ትኩስ ዜናዎች

%d bloggers like this:
P