Google search engine

“ኢትዮጵያ ቡናን የሚፈትነው ማንም የለም፤ ለሻምፒዮናነትም ነው የምንጫወተው”
ሀይሌ ገ/ትንሳኤ /ኢትዮጵያ ቡና/

#በመሸሻ_ወልዴ

በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሻምፒዮና ኢትዮጵያ ቡና ድሬዳዋ ከተማን 3-2 በሆነ ውጤት በማሸነፍ በሊጉ የመሪነት ስፍራ ላይ ሊቀመጥ ችሏል፤ የዳኝነት ችግሮች በተስተዋለበት፣ ሁለቱ የድሬዳዋ ከተማ ተጨዋቾች በረከት እና ዳንኤል በቀይ ካርድ ከሜዳ በተወገዱበት የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ቡና ባለ ድል ሲሆን ግቦቹን የቡድኑ ካፒቴን አማኑኤል ዩሃንስ በፍፁም ቅጣት ምት ሁለቱን ደግሞ ሀብታሙ ታደሰ በጨዋታ ባስቆጠሯቸው ግቦች አሸናፊ ሲሆን ለድሬዳዋ ከተማ ደግሞ አንዱን ኢታሙና ሌላኛዋን ደግሞ ዘነበ ከበደ /አዩካ/ በፍፁም ቅጣት ምት በማስቆጠር ቡድኑ በባዶ ከመሸነፍ የዳነበትን ግብ ሊያስቆጥሩ ችለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ቡና በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ሻምፒዮና እስካሁን ባደረጋቸው ሶስት ጨዋታዎች ከወልቂጤ ከተማ ጋር አቻ በመለያየት እንደዚሁም ደግሞ ፋሲል ከነማንና ድሬዳዋ ከተማን በማሸነፍ በ7 ነጥብ ሊጉን ከወዲሁ ሲመራ ክለቡ የአሁን ሰዓት ላይ እየተጓዘበት ስላለው መንገድ ድሬዳዋ ከተማን ስላሸነፈበት ጨዋታ ስለ ዘንድሮ የውድድር ዘመን ተሳትፎአቸው እና ቡድናቸው ስለሚከተለው የጨዋታ እንቅስቃሴ እና ከራሱ ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ዙሪያ ለክለቡ ባለፉት ሁለት ተከታታይ ግጥሚያዎች ጥሩ እንቅስቃሴ እያሳየ ያለውን የቀኝ መስመሩን የተከላካይ ስፍራ ተጨዋች ሀይሌ ገ/ትንሳኤን የሊግ ስፖርት ጋዜጣ አዘጋጁ መሸሻ ወልዴ አናግሮት ምላሹን ሰጥቶታል ተከታተሉት፤ መልካም ንባብ፡፡  

ሊግ፡- ኢትዮጵያ ቡና ድሬዳዋ ከተማን አሸንፎ የቤትኪንጉ መሪነት ላይ ተቀምጧል፤ ቡድናችሁ ስላገኘው ድልና ስለ ሊጉ አጀማመራችሁ ምን ትላለህ?

ሀይሌ፡- ኢትዮጵያ ቡና በድሬዳዋ ከተማ ላይ የተቀዳጀው ድል እንደ ቡድን ሊንቀሳቀስ በመቻሉና በማጥቃት ላይም ያተኮረን እንቅስቃሴን ልንከተል ስለቻልን ነው፤ ቡድናችን በተጋጣሚው ላይ ያገኘው ድል በጣም ጥሩ እና እኛን በመሪነት ረድፉ ላይ እንድንቀመጥ ያደረግን ስለሆነም በጣም ያስደሰተን ነው፤ ከዛ ውጪም የሊጉ አጀማመራችንን ከጨዋታ ወደ ጨዋታ እያሻሻልንና ጥሩም ነገርን እያሳየንም እንድንጓዝ እያስቻለን ነውና ይሄ ጉዞአችን ሊቀጥል ነው የሚገባው፡፡

ሊግ፡- ኢትዮጵያ ቡና በሊጉ ጅማሬ ላይ ምን አይነት ጥንካሬንና ክፍተትን እያሳየን ይገኛል?

ሀይሌ፡- እስካሁን ባደረግናቸው ጨዋታዎች በጠንካራነት ሊጠቀስ የሚችለው ነገር ቢኖር የአሰልጣኛችንን ታክቲክ ተግባራዊ ለማድረግ የምንሞክርበት መንገድ እና በየጨዋታው እንቅስቃሴ ላይ ግጥሚያዎችን ለማሸነፍ ቁርጠኛ ሆነን የምንጫወትበት መንገድ ነው፤ ለዛም እንዲረዳን የልምምድ ሜዳው ላይ የሚሰጠንን ታክቲክ በአግባቡ ስለምንሰራ ያንን ያህል እየተቸገርንም አይደለም፤ ሌላው በክፍተትነት ሊነሳ የሚችለው ከጨዋታ ጨዋታ ይሄ ችግር ይኖራል፤ ያ አለ ብለን ስለምናስብም የሚጎድለንን ነገር እያስተካከልን ወደ ሜዳ እንገባለን፤ መጨረሻ ላይም ምርጡንና የተሻለ የሚባለውን ኢትዮጵያ ቡናን እንገነባለን፡፡

ሊግ፡- ለአትዮጵያ ቡና ጥሩ እንቅስቃሴን ማድረግ ጀምረሃል፤ ራስህን ከዓምናው አንፃር ስትመዝነው?

ሀይሌ፡- በጣም ለውጥ አለኝ፤ ከጅማሬው ክለቤን በጥሩ ሁኔታ እያገለገልኩትም ነው፤ ከአምናው የሚሻለውን ሀይሌም በራሴ ላይ ልመለከት ችያለሁ እና በቀጣይ ጊዜው የቡድኔ ጨዋታ ላይ ደግሞ ምርጥ የሚባል ብቃቴን ለማሳየት እዘጋጃለው፡፡

ሊግ፡- የኢትዮጵያ ቡና አጨዋወት ተመችቶሃል?

ሀይሌ፡- በጣም፤ እንቅስቃሴው የሚታይ እና ጥሩም ነገርን የምትመለከትበት ስለሆነ ይመቻል፤ ይሄ አጨዋወት በተለይ ደግሞ ከውጪ ሀገር ብሔራዊ ቡድኖች ጋር ስንጫወት እነሱን ከጉልበት ይልቅ ኳስን መሰረት ባደረገ መልኩ በምን መልኩ በመጫወትበልጠናቸው ማሸነፍ እንድምንችልም ምልክትን የሚያሳይ ስለሆነም ያ ተመችቶኛል፡፡

ሊግ፡- ለኢትዮጵያ ቡና ስትጫወት ከእዚህ በፊት አንድአንዴ ኳስ ሲበላሽብህ ከደጋፊ ተቃውሞ ሲቀርብብህ የተመለከትንበት አጋጣሚ ነበር፤ አሁን ደግሞ ደጋፊው አንተን ማሞገስ እና ማድነቅ ጀምሯል፤ ይሄ የሆነው ምንአልባት በፊት በደጋፊ ፊት ስትጫወት ከጫና አንፃር እንቅስቃሴ ሊበላሽብህ ስለቻለና አሁን ደግሞ ያለ ደጋፊ በመጫወትህ ይሆን?

ሀይሌ፡- እንደዛ እንኳን አይደለም፤ ጫናን ፈርቼም አላውቅም፤ ኳስን በተመለከተ ሜዳ ላይ አንድአንዴ ጥሩ ላትሆን ትችላለህ ይሄ ደግሞ አይደለም በእኛ ሀገር ታላላቅ በሚባሉት የውጪ ሀገር ተጨዋቾችም ላይ የሚያጋጥም ነው፤ ከዛ ውጪ ደግሞ ቡናን በምፈልገው መልኩ በጣም እንዳልጠቅም ያደረገኝ ነገር ቢኖር ደግሞ ረዘም ላለ ጊዜ ጉዳት አጋጥሞኝ ብዙ ጨዋታዎች አልፎኝ ነበር፤ ይሄ በችሎታዬ ላይ ተፅህኖ አድርጎብኛል፤ አሁን ግን አሰልጣኜ ካሳዬ አራጌ የሚሰጠኝን የጨዋታ ታክቲክ በአግባቡ ስለምሰራ እና በእኛ ውስጥም ያለው የቡድን መንፈስ ጥሩ ስለሆነ የእዚህ ዓመት የሊግ ጅማሬዬን በጥሩ መልኩ እያስኬድኩት ነው፤ ለዛም ነው ደጋፊዎቻችንም ከወዲሁ እያበረታቱኝ ያሉት፡፡

ሊግ፡- ለኢትዮጵያ ቡና በምትጫወትበት የጨዋታ ስፍራ መከላከሉ ላይ ያተኩራል፤ ወደፊት ብዙ አያጠቃም የሚሉ አሉ፤ ይሄ ከራስህ ችግር ወይንስ ከአሰልጣኝህ ውሳኔ?
ሀይሌ፡- የጨዋታ እንቅስቃሴዬን በሚመለከት ስለ እኔ ብዙ የሚባል ነገር አለ፤ በተለይ ደግሞ ለምን ወደፊት ሄዶ አያጠቃም የሚለው ነገርንም ስሰማ ነበር፤ በዛ ደረጃ የሚመክሩኝም አሉ፤ በፊት ስጫወት አጠቃ ነበር፤ አሁን ግን አሰልጣኜ እየነገረኝ ያለው የአንተ የመጀመሪያ ስራ መከላከል ነው፤ ያን በአግባቡ ከተወጣህም በኋላ የቡድኑን ሚዛን እየጠበቅክ ወደፊት እያጠቃ ትጫወታለህ ስላለኝ በእሱ ውሳኔ ነው በመጫወት ላይ የምገኘው፡፡

ሊግ፡- ኢትዮጵያ ቡና የያዘው የተጨዋቾች ስብስብ ምርጥ የሚባል ነው?
ሀይሌ፡- አዎ፤ ያም ሆኖ ግን እኛ የምናምነው በያዝነው የተጨዋቾች ስብስቡ ሳይሆን በቡድን ስራው ነው፤ አንዱ አንዱን ተክቶ መጫወት የሚችሉ ተጨዋቾች አሉን፡፡

ሊግ፡- እግር ኳሳችን በዲ.ኤስ.ቲቪ መተላለፍ ጀምሯል፤ ምን አልክ?
ሀይሌ፡- ይሄ መጀመሩ በጣም ጥሩ ነው፤ ለብዙ ተጨዋቾቻችንም በሜዳ ላይ በሚያሳዩት ብቃት ወደ ባህር ማዶ ሄደው ለመጫወትም ያስችላችኋል፤ ምክንያቱም ከእዚህ በፊት ስለ እኛ ሀገር ተጨዋቾች የሚወራው እና የሚነገረው በሬዲዬ፣ በጋዜጣ እና በኢንተርኔት /ድረ-ገፅ/ ላይ ነበር፤ አሁን ግን ዲ.ኤስ. ቲቪ ሁሉን ነገር ቁልጭ አድርጎ ያሳያል እና በዛ ልንጠቀምበት ይገባል፤ ሌላው ሊጋችን በዲ.ኤስ. ቲቪ መተላለፉ ማን ጥሩ ነው? የትኛውስ መጥፎ ነው የሚለውን ስለሚያስመለክተንም የኢትዮጵያን እግር ኳስ ከሀሜት የነፃ እንዲሆንም ያደርገዋል፡፡

ሊግ፡- ኢትዮጵያ ቡናን ሊጉ ሲጠናቀቅ የት ደረጃ ላይ እንጠብቀው? በውድድር ዓመቱስ የቱ ቡድን ነው ፈታኝ የሚሆንበት?
ሀይሌ፡- በቤትኪንግ ሊጉ አሁን ላይ የያዝነው አጀማመር በጣም ጥሩ ነው፤ ሻምፒዮና ለመሆንም ነው የምንጫወተው፡፡ ኢትዮጵያ ቡናን የሚፈትነው ክለብም  ማንም የለም፡፡

ሊግ፡- በመጨረሻ….?
ሀይሌ፡- ወደ ኢትዮጵያ ቡና ከመጣሁበት ጊዜ አንስቶ በቡድኑ ውስጥ ባለኝ የተጨዋችነት ቆይታ በጣም ደስተኛ ነኝ፤ ከእዚህ ቡድን ጋርም የተለያዩ ድሎችን መቀዳጀትም እፈልጋለው፤ ይህን ካልኩ ሌላ ለማለት የምፈልገው ነገር ቢኖር ካለኝ ጥሩ ችሎታ አንፃር ወደ ቡድኑ ገብቼ እንድጫወት መስመሩን የዘረጋልኝን ፈጣሪ ነፍሱን ይማረውና አሰልጣኝ ስዩም አባተን እንደዚሁም ደግሞ ቤተሰቦቼን ከዛ ውጪም በቡና ተስፋ ቡድን ውስጥ ገብቼ እንድጫወት እድሉን የፈጠረልኝን አሰልጣኝ ዮሴፍ ተስፋዬን ላመሰግናቸው እፈልጋለሁ፡፡

https://t.me/Leaguesport

spot_img
ተመሳሳይ ጽሁፎች

አስተያይት ያስፍሩ

እባክዎን አስተያይትዎን ያስፍሩ
እባክዎን ስምዎን እዚህ ያስገቡ

ትኩስ ዜናዎች

%d bloggers like this:
P