በመሸሻ ወልዴ
የኢትዮጵያ ቡና እግር ኳስ ክለብን በካፒቴንነት በመምራት እና የመሃል ሜዳውም ላይ በመጫወት ቡድኑን በጥሩ
ሁኔታ እያገለገለ ይገኛል፤ ይሄ ተጨዋች አማኑኤል ዩሃንስ ሲሆን ተጨዋቹን ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ የኢትየጵያ ቡና ክለብ
በአዲሱ የቡድኑ አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ እየተከተለ ስላለው የጨዋታ ታክቲክ፣ ዘንድሮ ቡና ስለሚኖረው አቋም፣ ስለ
እራሱና ስለ ኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ጥያቄዎችን አንስተንለት ምላሹን በሚከተለው መልኩ ሰጥቶናል፤ ተከታተሉት፡፡
የኢትዮጵያ ቡና ክለብ ውስጥ ስላለው የእስካሁን የተጨዋችነት ቆይታው
“በኢትዮጵያ ቡና ከተስፋ ቡድኑ አንስቶ እስካሁን የነበረኝ የተጨዋችነት ቆይታዬ ለእኔ መልካም የሚባሉ ጊዜያቶችን
ያሳለፍኩበት ሲሆን በእዚህ ጊዜ ውስጥም እኔ በክለቡ ክለቡም በእኔ ደስተኛ የሆንበትን ወቅት ለመመልከት
ችያለውና ያ መሆን መቻሉ ሁሌም ነው የሚያስደስተኝ፤ እንደዚያም ሆኖ ግን ለእኔ ትንሽ ነገሮችንከባድ ያደረገብኝን
ሁኔታ አላጋጠመኝም ብዬም ለመዋሸት አልፈልግም፤ ይህም ምንድን ነው ከተስፋ ቡድኑ ባደግኩበት ሰሞን አካባቢ ገና
ወጣት ተጨዋች ከመሆኔ አኳያ እና በቂም የጨዋታ ልምዱ ያልነበረኝ ተጨዋች ስለሆንኩም በበርካታ የክለቡ
ደጋፊዎች ፊት ታጅቦ መጫወቱ በተወሰነ መልኩ ቸግሮኝ ነበርና ያንን ፈፅሞ አልረሳውም፤ በኋላ ላይ ግን የሲኒየር
ተጨዋቾቻችን ከአጠገቤ መኖራቸው ነገሮችን እያቀለሉኝ መጡና በፍጥነት ለቡድኑ በጥሩ መልኩ ለመጫወት ቻልኩ”፡፡
ኢትዮጵያ ቡና ውስጥ ባለህ ቆይታ ከደጋፊዎች ጋር ባለመግባባት ደረጃ ልዩነቶችን የፈጠርክባቸው አጋጣሚዎች አሉ?
“በፍፁም! እንዲህ ያሉ ነገሮች እስካሁን እኔን አጋጠመውኝ አያውቁም፤ ከዛ ይልቅ ከእነሱ ጋር በሜዳ ላይም ሆነ
ከሜዳ ውጪ በምንገናኝባቸው አንድአንድ አጋጣሚዎች መልካም የሆኑ ግንኙነቶችም ነው ያለኝ፤ የቡና ደጋፊዎች ዛሬ
ለደረስኩበት ደረጃ ትልቁን አስተዋፅኦ አድርገውልኛል፤ የእነሱ ድጋፍና ማበረታታትም ነው ለእዚሁ ያበቃኝና በእዚሁ
አጋጣሚ በጣሙን ላመሰግናቸው ነው የምፈልገው”፡፡
በኢትዮጵያ ቡና በቆየህባቸው ጊዜያቶች በጣሙን ስለሚቆጭህ ነገር
“በኢትዮጵያ ቡና ውስጥ በነበረኝ ያለፉት አራት ዓመታት የተጨዋችነት ቆይታዬ ለእኔ በጣም የሚቆጨኝ ነገር ቢኖር
በእዚህ ትልቅ እና ዝነኛ ክለብ ውስጥ እየተጫወትኩ ለአንድም ጊዜ የፕሪምየር ሊጉንም ሆነ የጥሎ ማለፉን ዋንጫ
እስካሁን ድረስ ለማንሳት እና ድሉንም ለማሳካት አለመቻሌ ነው፤ ከሁሉ በላይ ደግሞ በእዚህ የሊግ ውድድር ውስጥ
በተለይ ምርጦቹ የቡና ደጋፊዎች ከሚሰጡን ከፍተኛ እና የአማረ ድጋፍ አንፃር እነሱን በውጤት አስደስተን
ልናስጨፍራቸው አለመቻላችን በዋናነት ይቆጨኛል”፡፡
የኢትዮጵያ ቡና ክለብ ውስጥ ውልን ከማራዘም እና ካለማራዘም ጋር በአንተ ዙሪያ ብዙ ነገሮች ሲባሉ ከርመዋል….
ሁኔታውን ከአንተ አንደበት ብንሰማው?
“የኢትዮጵያ ቡና ክለብ ውስጥ ባለኝ የተጨዋችነት ቆይታ እስከ ሰኔ 30 ቀን ድረስ ቀሪ የአንድ ዓመት ውል ቢኖርብኝም
በክረምቱ ወራት ላይ ተጨማሪ ውል ከማራዘም ጋር በተያያዘ እኔና ቡድናችን በሚገባ ተነጋግረናል፤ በመጀመሪያው
ንግግራችንም ያለመስማማት ሁኔታዎች ነበሩ፤ በኋላ ላይ ግን ከቡድኑ ባሻገር ከኮቺንግ ስታፉ እንደዚሁም ደግሞ
ከቡድኑ አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ ጋር እስከቅርብ ጊዜያቶች ድረስ በብዙ ጉዳቶች ላይ ተነጋግረንና ተግባብተን ለቡድኑ
ለተጨማሪ ዓመታት ልጫወት በምችልበት ሁኔታ ላይ ለመስማማት ከመጨረሻው ጫፍ ላይ የደረስንበት አጋጣሚዎች
ተፈጥረው የነበረ ቢሆንም ፊርማዬን እንዳላኖር የዝውውር መስኮቱ መዘጋት መቻሉ ላለማራዘሜ ምክንያት ሆኗልና
የአንደኛው ዙር ውድድር ሲጠናቀቅና የዝውውር መስኮቱ በድጋሚ ሲከፈት የውል ዘመኔን የማራዝምበትና ለቡድኑም
በቀጣዮቹ ዓመታት ልጫወትበት የምችልበት እድሉ እንደሚኖረኝ ተስፋን አደርጋለሁ”፡፡
በኢትዮጵያ ቡና የተጨዋችነት ቆይታው በውጪ ሀገር እና በሀገር ውስጥ አሰልጣኞች ሰልጥኖ እንደማለፉ ያለውን
ልዩነት በምን መልኩ እንደሚመለከተው
“የእግር ኳስን በውጪ ሃገር እና በሃገር ውስጥ አሰልጣኞች ስትሰለጥን በጣም ልዩነት አለው፤ያም ሆኖ ግን እኔ
ከገዛኸኝ ውጪ በሌሎች የሃገር ውስጥ አሰልጣኞች ያልሰለጠንኩ በመሆኑ በዚህ ላይ ብዙ ነገሮችን ባልል በጣም ነው
የምመርጠው፤ ሆኖም ግን ካየሁት ነገር በመነሳት ለማለት የምፈልገው ገዛኸኝ በነበረበት ሰአት እሱ ጥሩ እና
ስማርትም የሆነ አሰልጣኝ ነው፤ ጥሩ ጥሩ ልምምዶችንም ያሰራን ነበር፤ በፖፓዲች እና በጎሜዝ በምንሰለጥንበት
ሰሞን ደግሞየእነሱ ልምምዳቸው ሁሉ በጣም ጠንካራዎች ነበሩና በሁሉም የአሰልጣኞች ዘመን ጊዜ ግን እኔ
የሚጠበቅብኝን ልምምዶች በብቃት ሰርቼ አሳልፌያለሁና ያ ሁሌም የሚያስደስተኝ ነው”፡፡
ኢትዮጵያ ቡና በአሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ አማካኝነት እየሰለጠነ ይገኛል፤ አሰልጣኙን ከጅማሬው ከሚከተለው አዲስ
የጨዋታ ታክቲክ አኳያ ልምምዶቹን በምን መልኩ ተመለከትካቸው? ለአንተስ የጨዋታው ታክቲክ ተመችቶሃል?
“አዎን፤ በጣም ተመችቶኛል፡፡ ያንን ስልህ ነገሮችን ያለምክንያት አይደለምየምነግርህ፤ የኢትዮጵያ ቡና ክለብ ጋር
ለተጨማሪ ዓመታት በውል ማራዘሚያ ዙሪያ በተነጋገርንበት ሰአት በደመወዝ ዙሪያ አውርተን ነበር፤ አሰልጣኙ እኔን
በጣም እንደሚፈልገኝ እና በእኔም ደስተኛ መሆኑን በነገረኝ ሰአትና ክለቡም ለቀጣዩ ጊዜያቶች ከቡድኑ ጋር
እንድቀጥል ስለሚፈልግ በዋናነት የተነሳው ጉዳይ ቢኖር በአጨዋወቴ ዙሪያ ነበር፤ ከአሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ ጋር በእዚህ
ጉዳይ እሱ የሙያው ባለቤት በመሆኑ በብዙ ነገር አውርተን ተግባብተናል፤ እንደውም አንድ ለማለት የምፈልገው ነገር
ቢኖር መሼ የእውነት ነው የምልህ እኔ ብቻ ሳልሆን የቡና 29ኙም ተጨዋቾች በአሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ ላይ ካዩት
ስልጠናና ልምምድ በመነሳት ሁላችንም የእዚህ ቡድን ተጨዋቾች በእሱ የተጨዋቾች ስብስብ ውስጥ ለመሆንና
ለመሰልጠንም መቻላችን በጣም እድለኞች እንደሆንም ነው ያደረገን”፡፡
ኢትዮጵያ ቡና በአዲስ አበባ ሲቲ ካፕ ኤሌክትሪክን ሲፋለም አሰልጣኙ አንተን ከምትታወቅበት የመሃል ተጨዋችነት
ይልቅ የመስመር ተጨዋች አድርጎ ስላጫወተህ ደስተኛ አልነበርክም ስለመባሉ
“ኢትዮጵያ ቡና በሲቲ ካፑ ጨዋታአሌክትሪክንሲፋለም እኔ ለቡድኑ የተሰለፍኩትበቀጥታ ከብሄራዊ ቡድን
መልስበመምጣት ነበር፤ ከክለቤ ጋርም የመለማመጃ በቂ ጊዜንም አላገኘውም ነበር፤ ያም ሆኖ ግን አሰልጣኙ እኔን
ያየበት መንገድ ነበርና ከምታወቅበት የአማካይ ስፍራ ተጨዋችነት ውጪ ወደ መስመር አውጥቶ አጫውቶኛል፤ እንደ
ሙያና ፕሮፌሽን ሁላችንም የየድርሻችንን ልናውቅ ይገባል፤ እኔ ተጨዋች እስከሆንኩ ድረስ አሰልጣኜ በሚያዘኝና
ተጫወትም በሚለኝ ስፍራ ልጫወት ራሴን በሚገባ አዘጋጃለው፤ በእዚያን ዕለት ጨዋታም ያን ትህዛዝ አክብሬም ነው
ስጫወት የነበረው፤ ይሄ እንዳለና ሁሉንም እያወቅኩት ግን አማኑኤል በዛ ስፍራ ላይ መጫወቱ አስኮርፎታል ብሎም
ደግሞ ደስተኛም አላደረገውም የሚሉት አካላቶች ከየት አምጥተው ወሬውን እንደሚነዙት አላውቅም፤ እንደ ቡና
ተጨዋችነቴ እኔ በእዚህ ስፍራ ላይ ነው መጫወት የምፈልገው ማለት አልችልም፤ ሁሉም ውሳኔዎች የአሰልጣኙ
ናቸው፤ አሰልጣኙ ተጫወት በሚለኝ ስፍራ ሁሉ መጫወትም ግዴታዬ ነው፡፡ በኤሌክትሪኩ ጨዋታ እኔ በተሰለፍኩበት
የመስመር ስፍራ ደስተኛ እንዳልሆንኩ ብዙ ነገር ሊባል ይችላል፤ እኔ ግን ደስተኛ አይደለውም የሚል ነገርን በአንደበቴ
አላልኩም፤በኤሌክትሪኩ ጨዋታ በአሠልጣኙ ስር የመስመርም የመሀልም ተጨዋች ሆኜ ለክለቡ ልጫወት
ችያለው፤ ከእዚያን ጊዜ አንስቶም በቡድኑ ውስጥ ደስተኛ ሆኜም ነው ስራዬን እየሰራሁ የምገኘው”፡፡
ኢትዮጵያ ቡና በሲቲ ካፑ ተሳትፎው ስኬታማ ለመሆን አልቻለም፤ የፕሪምየር ሊጉንም ጅማሬ በሽንፈት ጀምሯል፤
በእዚህ ዙሪያ ቡድናችሁን አስመልክተህ የምትለን ነገር ካለ….?
“ኢትዮጵያ ቡናን አስመልክቶ በሲቲ ካፑና በፕሪምየር ሊጉም የመጀመሪያ ጨዋታችን ጅማሬ ላይ ከወዲሁ
ከምንከተለው አጨዋወት በመነሳት አሁን ላይ እያስመዘገብን ስላለው የውጤት ማጣት እንደ ቡድኑ ተጨዋችነቴ
ብዙ የሚያሳስበን ነገር አይኖርም፤ ቡና አሁን በያዘው አጨዋወት ስህተቶቹን እየቀነሰ እና እያረመም የሚጓዝ ቡድን
ስለሆነ ክለባችን በያዘው አጨዋወት እና አካሄድ እምነቱ አለኝ፤ አሰልጣኙም አዲሱን የጨዋታ ታክቲክ በቡድኑ ውስጥ
እንዲተገበር ለማድረግም ጥሩ ስራን እያሰራን ስለሆነም ከወዲሁ ውጤት ማምጣቱም ላይ ያለንበት ደረጃ የአሁን ሰአት
ላይ ገናም ነው፤ ስለሆነም እኛ ተጨዋቾች ለእሱ የጨዋታ ታክቲክ ትግበራ ሙሉ ለሙሉ ለመግባት በእያንዳንዱ
ልምምድ ላይ በጣም ትኩረት አድርገን መስራት ይኖርብናልናበጨዋታ ላይም ሆነ በልምምድ ሜዳ ላይ እሱን ልናግዘው
ይገባል፤ ለሚከተለው የጨዋታ ታክቲክም ወደ እሱ ሃሳብ ሙሉ ለሙሉ ስንመጣም በእርግጠኝነት የሆነ ነገርን
መፍጠር የምንችልበት ነገር አለን፤ ይሄ ደግሞ ለኢትዮጵያ ቡና ብቻ ሳይሆን ሃገርን ለሚጠቅም እንደዚሁም ደግሞ
ለሌሎችም ማሳየት የምንችልበት ነገር አለናይህን ለመተግበር እኛ ተጨዋቾች በጣም መስራት ነው ያለብን፤እሱ
ለሚለው ሀሳብም አሰልጣኙን ማገዝ አለብን፤ በሜዳ ላይ በሚያሰራን እና በሚያሳየን ነገርም መጓዝ አለብን፤
ደጋፊውም ቢሆን እንደደጋፊነቱ ማድረግ ያለበትን ነገር ያድርግ፤ የቡናን ደጋፊ እኔ አድርግ ማለት አልችልም፤
ምክንያቱም ከዚህ በፊት የነበረውን ሁሉንም ነገር ያውቀዋልና አሰልጣኙን በጣም ቀርቦት ከእሱ ጎንም ከቡድኑ
ጎንም ሊሆን ይገባዋል፤ ሁላችንም ተባብረን እሱን ካገዝነው ቡና ጥሩ ቡድንም ጥሩ ውጤትም ይኖረዋል”፡፡
የኢትዮጵያ ቡናን የተጨዋቾች ስብስብ በምን መልኩ እንደሚገልፀው
“ኢትዮጵያ ቡና የያዘው የተጨዋቾች ስብስብ በወጣት ተጨዋቾች ላይ የተዋቀረ ቢሆንም ለጥሩነት ምንም አይነት
ጥርጥር የለኝም፤ ተጨዋቾቹ ወደ እኛ ሲመጡ ለአሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ አጨዋወት ይመጥናሉ፤ ቡድኑንም ይጠቅማሉ
ተብለው ነውና ይህን ልንቀበል ይገባናል፤ ከእዛ ባሻገር ደግሞ የመጡትን ብዙዎቹን ተጨዋቾችም የምናውቃቸው
ናቸው፤ ወጣቶችና በጣም አቅምም ያላቸው ናቸው፤ ለሊጉ አዲስ የሆኑም ተጨዋቾች አሉ፡፡ ይሄ ስብስብና
የተጨዋቾች አቅምም ወደ ስራ ሲገባና ስንጣመር ሁላችንም ደግሞ አቅማችንን አሁን ካለንበት ሁኔታም በበለጠ
በሜዳ ላይ መጠቀም ከቻልን ጠንካራውን እና ምርጡን ቡናን የምናገኝበት ጊዜም ሩቅ አይደለምና በያዝነው
የተጨዋቾች ስብስብ በክለቤ ሙሉ እምነት ነው ያለኝ”፡፡
በቅዱስ ጊዮርጊስ የተሸነፋችሁበት የሲቲ ካፑ የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታ የኢትዮጵያ ቡናን ደጋፊ አስኮርፏል፤ ስለጨዋታው
የምትለን የተወሰነ ነገር ካለ…?
“ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር በነበረን የሲቲ ካፑ የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታ ቡድናችን ምንም እንኳን ሽንፈትን በእነሱ አስተናግዶ
በውጤት ደረጃ ደጋፊዎቻችንን ያስኮርፍ እንጂ ወደ ዋንጫ ሳናልፍ የቀረነው በጨዋታ ተበልጠን አይደለም፤ ለእዛም
እንደይበልጥ ማረጋገጫ የሁለታችንንም ጨዋታ በቪዲዮ መመልከታችን ለቀጣይ ጊዜ በርካታ ፍልሚያዎቻችን
ክፍተቶቻችንን እንድናይበት እና በተግባር ደረጃም ወደውጤታማነት በምን መልኩ እንደምንመጣ፤ የቡናን የጨዋታ
ታክቲክም አሁን ላይ ያለው እንዳለ ሆኖ ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ ለማድረግም በምን መልኩ መስራት እንዳለብንም
የተረዳንበት ሁኔታ አለና ያ ጨዋታ ለእኛ የማይረሳ ነው፤ የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ቡድናችንን ሲያሸንፍ የእኛ ተጨዋቾች
በራሳችን የግብ ክልል ላይ በፈጠሩት ጥቃቅን ስህተት ነው፤ እንደዚህ አይነት ስህተቶች ደግሞ በእግር ኳሱ ላይ
ያጋጥማሉ፤ ከዚህ ጨዋታ መማር አለብን፤ይሄ ጨዋታ ለቀጣዮቹ ጨዋታዎቻችን ስህተቶችን በምን መልኩ መቀነስ
እንዳለብህ እና ስህተትንም ከቀነስን ደግሞ ተጋጣሚህ ምንም አይነት የጨዋታ እድል እንዳይኖረው ስለምታደርገው ይሄን
በመረዳት ወደተሻለ ውጤታማነትና ምርጥ ቡድንነት መምጣት መቻላችን የማይቀር ጉዳይም ነው፡፡ በእግር ኳስ ላይ
ደግሞ የሚሰራ ሰው ይሳሳታል፤ የእኛ ቡድን ደግሞ ስህተቱን እያወቀ ይገኛልና ስህተቶቻችንን እየቀነስን ስንሄድ
ቡድናችን ከሁሉም የተሻለ ቡድን ይሆናል ብዬም ተስፋ አደርጋለሁ”፡፡
በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በሚኖራችሁ የውድድር ቆይታ በእዚህ አመት ከእናንተ ምን ውጤት ይጠበቅ?
“ኢትዮጵያ ቡና በእዚህ ዓመት ላይ ያቀደው ዋንኛ ዓላማው የአንድ ቡድን ምን አይነት ቅርፅ ኖሮትና የራሱም የሆነ ጥሩ
ቡድንን ሰርቶ በማሳየት በሜዳ ላይ በውጤት ደረጃ ጠንካራ ተፎካካሪ ለመሆን መቻል ነው፤ ይሄን የመጀመሪያ እና
የኢትዮጵያ ቡናን መለያ የሆነን ጨዋታም በተግባር ለማሳየትም ጠንክረን እየሰራን ነው ይሄን ስል ደግሞ በሚገኙት
አጋጣሚዎች ለዋንጫው ፉክክር አንጫወትም ማለቴ እንዳልሆነ ግን ሊታወቅልኝም ይገባል”፡፡
የኢትዮጵያ ቡና እና የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ተጨዋች እንደመሆንህ አሁን ላይ ካለህ ወቅታዊ አቋምህና ብቃትህ
በመነሳት ስለቀጣይ ጊዜ የኳስ ህይወትህ ምን የምትለው ነገር አለ?
“በኢትዮጵያ ቡና ክለብም ሆነ በብሄራዊ ቡድን ውስጥ ባለኝ የተጨዋችነት ቆይታዬ ሁሌም ራሴን ጥሩ ተጨዋች እና
ተፎካካሪ አድርጌ ለመቅረብ ጠንክሬ ነው ልምምዴን የምሰራው፡፡ የብሄራዊ ቡድን ላይ ተመርጦ ለመጫወት በክለብህ
ቆይታ ጥሩና የተሻለ ተጨዋች መሆን ይጠበቅብሃል፤ ከዛ በመነሳት ስለ ቀጣይ ጊዜው የኳስ ህይወቴ አሁን ላይ
የማስበው እግዚአብሄር በሁሉም ነገር ይረዳኝ እንጂ በእዚሁ ደረጃ በመዘጋጀት ነው የሃገሪቱ ጥሩና የተሻለ ተጨዋች
ለመሆንን እያለምኩኝ የምገኘው”፡፡
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ኮትዲቩዋርን በማጣሪያው ጨዋታ ስላሸነፈበት ውጤትና ለካሜሩን የአፍሪካ ዋንጫ
ስለማለፍ እድላቸው
“የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የኮትዲቩዋር አቻውን ሲያሸንፍ እኛ ጋር የሆነ አቅም አለ ማለት ነው፤ ከጨዋታው በፊት
ማንም ይሄንን ውጤት አልጠበቀም ነበር፤ በማሸነፋችን በጣም ተደስተናል፡፡ አሁን ላይ ያለንን ከፍተኛ ተነሳሽነትንም
ልንመለከትበትም ችለናል፡፡ ኮትዲቩዋር በእግር ኳሱ ትልቋ ሃገር በመሆኗና የምድቡም ጠንካራዋ ቡድን ስለሆነች እሷን
ማሸነፋችን ወደ አፍሪካው ዋንጫ ለማለፍ የሚኖረንን እድል ይበልጥ የሚያሰልፍን ይሆናልና በእዚህ ቡድን ስብስብ
ውስጥ እኔም በመኖሬ ራሴን እንደእድለኛ ጭምር ነው የምቆጥረው፡፡
የአፍሪካ ዋንጫው ላይ ስለማለፍ እድላችን ከቀጣይ 8 ወራቶች በኋላ በምናደርጋቸው ጨዋታዎች የእኛን ሁኔታዎች
የሚወስኑ ቢሆንም ጠንክረን ሰርተን በመምጣት እና ቀሪዎቹንም ጨዋታዎች በማሸነፍ ወደ አፍሪካ ዋንጫው ከሰባት
ዓመታት በኋላ ዳግም የምንመለስበት ሁኔታ እንደሚኖረን ተስፋን አደርጋለሁ”፡፡
በመጨረሻ
“የኢትዮጵያ ቡና ክለብ ውስጥ ባለኝ የተጨዋችነት ቆይታዬ ደጋፊዎቻችን ምን ያህል ለእኔ ጥሩ ፍቅርና ክብር እንዳላቸው
በሚገባ አውቃለሁ፤ ይህንንም በተደጋጋሚ ጊዜም አይቻለሁ፤ ይሄ የሆነው ደግሞገና በወጣትነት እድሜዬ ላይ
በምገኝበት ሰአት መሆኑ ብዙ ነገሮችን ለክለቡ እንድሰራ የሚያነቃቃኝ እና የሚያበረታታኝም ስለሆነ እነሱን ሁሌም
እንደምወዳቸው እና እንደማመሰግናቸው በእዚሁ አጋጣሚ ለመናገር እፈልጋለው”፡፡