Google search engine

“ኢትዮጵያ ቡና የያዘው አጨዋወት የሚያድግ እና በቀጣይነትም ውጤታማ የሚያደርገው ነው” ወንድሜነህ ደረጄ /ኢትዮጵያ ቡና/


በመሸሻ ወልዴ /GBOYS/

ኢትዮጵያ ቡናና ሲዳማ ቡና የአዲስ አበባ ስታድየም ላይ ዛሬ ከ9 ሰዓት ጀምሮ ተጠባቂውን የሊጉን ጨዋታ ያደርጋሉ፤ ይህን ጨዋታ በተመለከተ እና ስለ ኢትዮጵያ ቡና የሊጉ ተሳትፎ የቡድኑ ጠንካራ የተከላካይ ስፍራ ተጨዋች ወንድሜነህ ደረጀ ከሊግ ስፖርት ጋዜጣ ጋር ቆይታን ያደረገ ሲሆን፤ የተጨዋቹ ቃለ-ምልልስም በሚከተለው መልኩ ቀርቧል፡፡
ሊግ፡- በመጀመሪያ እንኳን ለጥምቀት በዓል በሰላም አደረሰህ?
ወንድሜነህ፡- እናንተንም እንኳን አደረሳችሁ፤ አመሰግናለሁ፡፡
ሊግ፡- የጥምቀት በዓልን የት እና እንዴት ነው የምታከብረው?
ወንድሜነህ፡- በዓሉን በሰፈሬ በተለምዶ አጠራር አህያ በር አካባቢ እና በአማኑኤል ቤተክርስትያን ነው የማሳልፈው፤ በዓሉን የማከብርበትም ሁኔታ ታቦቱ በእኛ ሰፈር በኩል ስለሚያልፍ የአማኑኤልን ታቦት በማስወጣትና በማስገባትም ነው፡፡
ሊግ፡- የጥምቀት በዓልን አስመልክቶ ማስተላለፍ የምትፈልገው መልዕክት አለህ?
ወንድሜነህ፡- አዎን፤ በመጀመሪያ ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች በመቀጠል ደግሞ ለኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች እና ለቤተሰቦቼ እንዲሁም ለእናንተ መልካም በዓል እንዲሆንላችሁ እመኛለው፡፡
ሊግ፡- ኢትዮጵያ ቡናን ተቀላቅለህ እየተጫወትክ ይገኛል፤ ቡድኑ ተመችቶሃል?
ወንድሜነህ፡- አዎን፤ በጣም ነው የተመቸኝ፤ ምክንያቱም ክለቡ በጣም ጥሩ እና ለእኔም አጨዋወት ስለተስማማኝ ነው፤ ከዛም ውጪ በተሰለፍኩባቸው ጨዋታዎች ሁሉ አበረታች እና ለወደፊቱም የኳስ ህይወቴ ማማር መልካም ነገሮችንም የተመለከትኩባቸው ነውና በክለቡ ከምነግርህ በላይ በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡
ሊግ፡- ኢትዮጵያ ቡና አሁን የያዘው አጨዋወት የሚጠቅመውና የሚያዋጣው ነው ወይንስ በተቃራኒው?
ወንድሜነህ፡- በጣም ነው እንጂ የሚያዋጣው፤ አጨዋወቱ ለቡና ብቻ ሳይሆን ለሀገር ጭምርም ነው የሚጠቅመው፤ አሁን ላይ እኛ የያዝነውን አይነት እንቅስቃሴም ብዙዎቹ አይጠቀሙበትም እንጂ የሀገራችን አብዛኛው ተጨዋቾችም የሚችሉት ነው፤ ከዛ ውጪም እኛን ኢትዮጵያኖች ከሌሎቹ አፍሪካ ሀገራት የሚለየን ኳስ ይዘን መጫወታችንም ነውና ይሄንንም ነው ልናስቀጥል የሚገባን፤ ቡና ግን ይህን እየተጠቀመበት ስለሆነ ለወደፊቱ ክለቡን በጣም ነው ውጤታማ የሚያደርገው፤ ይሄ ግን በአንዴ በችኮላ አይሆንም፡፡
ሊግ፡- የኢትዮጵያ ቡና አጨዋወት ከሌሎች ክለቦች ይለያል?
ወንድሜነህ፡- በጣም፤ የኢትዮጵያ ቡናን አጨዋወት የሚለየው በቡድኑ ውስጥ ከዚህ በፊት የተለመደ አይነት ኳስን መስርቶ የመጫወት ነገር ነበር፤ አሁን ግን ተሻሽሎ የቀረበ ነገር አለ፤ ይኸውም አሁን እኛ የምንጫወተው በረኛን ጭምር ተጨዋች አድርገን ነው፤ በረኛን እንደ ተጨዋች ነው የምንጠቀምበት፡፡
ሊግ፡- ኢትዮጵያ ቡና በያዘው አጨዋወት በመልካምነቱ ወይንም ደግሞ በጥሩነቱ የምትጠቅሰውና ሊያስተካክል ይገባዋል የምትለው ነገር?
ወንድሜነህ፡- ኢትዮጵያ ቡና ውስጥ በጥሩነቱ ደረጃ ሊጠቀስ የሚችለው ነገር ኳስን ይዘንና ተቆጣጥረን መጫወት መቻላችን ነው፤ የምንሰራቸውን ስህተቶች ደግሞ ክፍተቶቻችን ስለሆኑ እነዛን መቀነስ ከቻልን በጣም ጥሩ የሆነ ቡድንን መስራት እንችላለን፡፡ አሁንም አሪፍ ቡድን ነው ያለን፡፡ አንዳንዴ የምንሰራቸው ስህተቶችም የያዝነው የአጨዋወት ሲስተም የፈጠረው ነውና እሱን እየተላመድን ስንሄድና ማስተካከል ስንችል ጥሩ ቡድንን እናያለን ብዬ አስባለሁ፡፡
ሊግ፡- ኢትዮጵያ ቡና በፕሪምየር ሊጉ የስምንት ሳምንታት ጨዋታዎች በሚጠበቀው መልኩ ብዙም ውጤታማ መሆን አልቻለም፤ ከእዚያ አኳያ ክለባችሁን እንዴት ነው የምትመዝኑት?
ወንድሜነህ፡- አሁን ላይ ያለን ውጤት እኛን፣ ኢትዮጵያ ቡናን፣ እንደዚሁም ደግሞ ደጋፊዎቻችችን ይመጥናል ብለን አናስብም፤ ግን ኢትዮጵያ ቡና በአሁን ሰዓት ለውጥ ላይ ነው የሚገኘው፤ ከአሰልጣኝ ጀምሮ፣ ከቡድን አወቃቀር ጀምሮ ለውጥ ላይ ስለሆነ ቶሎ ውጤት ማግኘት በአንዴ አይሆንም፤ አዲስ አጨዋወት ስለያዝን ውጤት ማምጣቱ ላይ ጊዜ የሚጠይቅ ነው፡፡ ስለዚህ ይሄን ልንጠብቅ ይገባል፤ ያኔ ቡናን በጨዋታ ብቻ ሳይሆን በውጤትም ጭምር የሚመጥን ቡድን በሜዳ ላይ ይዘን እንቀርባለን፡፡
ሊግ፡- ለኢትዮጵያ ቡና ውጤት ይዞ ከመውጣት አንፃር ሳይሳካለት ቀርቶ የሚቆጭህ ጨዋታዎች አሉ?
ወንድሜነህ፡- አዎን፤ መጀመሪያ ማሸነፍ እየተገባን ያላሸነፍነው የጅማ አባጅፋር ጋር ያደረግነው ጨዋታ ነው፡፡ በዛ ፍልሚያ ሶስት ነጥብ ይዘን መውጣት እየተገባን ሳናሸንፍ ቀርተናል፡፡ ሌላው ከባህር ዳር ከተማ ጋር የነበረን ጨዋታ ነው፤ ክለባችን በጣም ጥሩ የነበረ እና ተጋጣሚውንም በልጦ የተጫወተ ቢሆንም ተደጋጋሚ ጎል ባለማስቆጠሩ ነጥብ ይዞ ሳይወጣ ቀርቷል፤ ሶስተኛው ግጥሚያ ደግሞ ከፋሲል ከነማ ጋር የነበረን ጨዋታ ነው፤ በዚህ ግጥሚያ ቢያንስ ነጥብ ተጋርተን መውጣት ይጠበቅብን ነበር፡፡
ሊግ፡- በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የእስካሁኑ ጨዋታችሁ በእንቅስቃሴ ደረጃ ተበልጠናል ብለህ የምትጠቅሰው ግጥሚያ አለ?
ወንድሜነህ፡- በፍፁም የለም፤ እኛ እስካሁን ባደረግናቸው ጨዋታዎች ሁሉ በእንቅስቃሴ በኩል በልጠን እንጂ ተበልጠን ከሜዳ አልወጣንም፤ የምንበልጣቸውም ኳስን በደንብ አድርገን ተቆጣጥረን ስለምንጫወትም ነው፡፡
ሊግ፡- ኢትዮጵያ ቡናና ሲዳማ ቡና ዛሬ ተጠባቂውን የሊጉን ጨዋታ ያከናውናሉ፤ በሁለቱ ቡድኖች ፍልሚያ ማን ባለድል ይሆናል?
ወንድሜነህ፡- የኢትዮጵያ ቡናና የሲዳማ ቡና የዛሬው ጨዋታ በሁለታችንም ክለቦች መካከል ጥሩ ፉክክር የሚደርግበት ቢሆንም እነሱ ያለፈውን ጨዋታ አሸንፈው እኛ ደግሞ ሁለት ተከታታይ ጨዋታዎችን ተሸንፈን ከመምጣታችን አኳያ ለእኛ በስነ-ልቦናው በኩል ከበድ የሚልብን ይመስለኛል፡፡ ያም ሆኖ ግን በእዚህ ሰሞን ላይ የሰራነው ልምምድ ይሄን ጨዋታ በብቃት ለመወጣት እንድንችል ተደርጎ በመሆኑ ከግጥሚያው ጥሩ ውጤት ይኖረናል፡፡
ሊግ፡- የኢትዮጵያ ቡናን የተጨዋቾች ስብስብ እንደራስህ እይታ በምን መልኩ ትገልፀዋለህ?
ወንድሜነህ፡- ኢትዮጵያ ቡና በስኳዱ የያዛቸው የተጨዋቾች ስብስብን በተመለከተ በአብዛኛው ወጣቶችን ያማከለ ነው፤ ሲኒየር የሚባሉትም ገና ወጣት ተጨዋቾች ናቸው፡፡ በወጣት የተሰራ ቡድንም ስለሆነ ከዚህ ትኩስ ኃይል በቀጣይነት ጥሩ ነገርን ማየት ይቻላል፡፡
ሊግ፡- አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌን ከወዲሁ ምን አይነት አሰልጣኝ አድርጋችሁ ሳላችሁት?
ወንድሜነህ፡- የኢትዮጵያ ቡናው አሰልጣኝ በስልጠና ብቃቱም ሆነ በስብህናው በጣም ይለያል፤ እሱ ሁሌም ጥሩ እግር ኳስን ተጫውተህ እንድታሸንፍለት እና ካልሆነ ደግሞ ባታሸንፍ እንኳን ጥሩ ጨዋታን እንድታሳየው ይፈልጋል፤ እግር ኳስ ማለት እንግዲህ እንዲህ ነው፤ ተመልካቹ በኳስ እንዲዝናና የሚፈልግ አሰልጣኝም ነው፤ ስራን ሲያሰራን እንደ ትህዛዝ ብቻ ሳይሆን እንደውንድም እና ጓደኛም ጭምር ሆኖ ስለሆነ የሚቀርበን በእሱ በጣም ደስተኛ ሆነን ኢትዮጵያ ቡና ውስጥ እንገኛለን፡፡
ሊግ፡- ለኢትዮጵያ ቡና መጫወት ምን ስሜት ይሰጣል?
ወንድሜነህ፡- አዎን፤ ስሜቱ በጣም ለየት ይላል፤ በተለይ ደግሞ የአዲስ አበባ ልጅ ከሆንክ በሁለት መንገድ ነው ሁኔታውን የምትመለከተው፤ ይኸውም ለኢትዮጵያ ቡና መጫወት ሁሌም ትፈልጋለህ በተለይ ደግሞ ከልጅነት አንስቶ ለመጫወት የተመኘክ ከሆነ እና ያ ከተሳካልህ ለየት ይላል፡፡
ሊግ፡- በኢትዮጵያ ቡና ውስጥ የያዝከውን የመከላከል አጨዋወት በተለይ ደግሞ ብዙ ነገሮችህን ከቀድሞው ምርጥ የሀገ

ራችን እግር ኳስ ተጨዋቾቻችን ጋር የሚነነፃፅሩህ አሉ?
ወንድሜነህ፡- የኢትዮጵያ ቡና ውስጥ በአሁን ሰአት በሜዳ ላይ የምጠቀምባቸውን የጨዋታ እንቅስቃሴዎች ይዤ በመምጣት እዚህ ደረጃ ላይ ያደረስኳቸው ገና በሰፈር ደረጃ በፕሮጀክት ላይ ስጫወት ጀምሮ ነው፤ ያኔ በአሰልጣኞች የሚነገርህ ነገር አለ፤ እዛ ላይ ሰርቼ በመምጣቴ ነው አሁን ላይ በጥሩ መልኩ ልጫወት የቻልኩት፡፡
ሊግ፡- በሜዳ ላይ ያለህ የራስ መተማመን ብቃትህም ከፍተኛ ነው ይሄስ ከምን መጣ?
ወንድሜነህ፡- የመጀመሪያው ነገር የእራሴን ኳሊቲ ማወቅ መቻሌ ነው፤ እኔ ምን ነገር አለኝ ብዬም እዘጋጃለሁ፡፡ ያኔ ራስህን ስታውቀው እና ምን ማድረግ እንዳለብህም ስትረዳ በሜዳ ላይ የምታውቀውን ነገር ነው የምታደርገው፤ ከዛ የበለጠ ነገርን አታደርግም፤ እኔ ብዙ ጊዜ ኳስ ስጫወት ምንም ነገርን አልፈራም፤ ደፋር ነኝ፤ ለዛም ነው ኮንፊደንስ ያለኝ ተጨዋች የሆንኩትና እነዚህ ነገሮች ተደማምረው ነው ጥሩ ተጨዋችነቴን ላመጣውም የቻልኩት፡፡
ሊግ፡- በእግር ኳስ ህይወት ደስተኛ ነህ?
ወንድሜነህ፡- በጣም እንጂ፤ ተከፍቼም አላውቅም፡፡ ኳስን መጀመሪያ የተጫወትኩት ለአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ነው፤ ለልደታ ክፍለ ከተማም ለሱሉልታ ከተማም በኋላ ላይም ለባህር ዳር ከተማም ተጫውቻለሁ፡፡ በእነዚህ ቡድኖች ውስጥ ሁሉ ጥሩ ጊዜን ነው ያሳለፍኩት በተለይ ደግሞ አብሬያቸው የተጫወትኳቸው ተጨዋቾችና ያሰለጠኑኝ አሰልጣኞችም ለእኔ ጥሩ መሆን ብዙ ነገርን አድርገውልኛልና ይሄን ፈፅሞም አልረሳውም፡፡
ሊግ፡- በእግር ኳስ ተጨዋችነትህ ከፍተኛ ደርጃ ላይ ደርሰሃል?
ወንድሜነህ፡- በእዛ ደረጃ ላይ እገኛለሁ ብዬ አላስብም፡፡ ያም ሆኖ ግን ማሳካት ያሉብኝን ነገሮች ከወዲሁ እያሳካዋቸው ናቸው፤ እነዚህም ልጅ ሆኜ በፕሮጀክት ደረጃ ኳስን ስጫወት የፕሪምየር ሊጉ ላይ ገብቼ እጫወታለሁ፤ ለኢትዮጵያ ቡናም እጫወታለሁ፤ ለብሄራዊ ቡድንም ተመርጭ እጫወታለሁ የሚል ህልምና እቅዶች ነበሩኝ እነዚህንም ባቀድኳቸው መልኩና ከተናገርኩት አንፃር እያስኬድኳቸው ናቸው የምገኘውና ትንቢቶቼ እየተሳኩልኝ ነው፤ አሁን የቀረኝ ነገር ቢኖር የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ውስጥ በተደጋጋሚ ጊዜ በመመረጥ ሃገሬን ማገልገሉና በፕሮፌሽናል ደረጃ ኳስን መጫወት መቻል ነው፡፡
የፕሮፌሽናል ተጨዋችነት እድልንም ለማግኘት ጥረትን እያደረግኩ ነው፤ ከኤጀንቴም ጋር በዚህ ጉዳይ ዙሪያ እየተነጋገርኩም ነው፤ ይሄ ሁሉ የሚሆነው ግን የአሁኑን ቡድኔን በሚገባ መጥቀም ከቻልኩ በኋላ ነው፡፡
ሊግ፡- የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች አሁን ላይ ለእናንተ?
ወንድሜነህ፡- የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች በአሁን ሰዓት የሚሰጡን ድጋፍ በጣም ደስ ይላል፤ እነሱ በሜዳ ላይ ከምናሳየው ነገርም በመነሳት ስለእንቅስቃሴያችንም ብዙ ነገርም ገብቷችኋል፤ አቅም እንዳለንም አውቀዋል፤ አቅም ያለው ቡድን ደግሞ ጊዜ ያስፈልገዋል፡፡ ያ ነገር ስለገባቸውም እኛ ሁላችንም የቡድኑ ተጨዋቾችም በደጋፊዎቻችን ደስተኛ እየሆንን ነው፡፡ ለእነሱ ባሳየናቸው ነገር ተሸንፈን እንኳን ጥሩ ነገርን እያሳየን ነውና በሚሰጡን ድጋፍ ደስተኛ ነን፤ በጣምም እናመሰግናቸዋለን፡፡
ሊግ፡- ከኢትዮጵያ ተጨዋቾች የሙሉዓለም ረጋሳ አድናቂ እንደሆንክ ይነገራል፤ ከባህር ማዶ ተጨዋቾችስ ውስጥ የምታደንቀው፤ የማን ክለብስ ደጋፊ ነህ?
ወንድሜነህ፡- ሙሉዓለምን አዎን በጣም ነው የማደንቀው ከባህር ማዶ ተጨዋቾች ግን የመጀመሪያ ደረጃ ሰጥቼው የማደንቀው ሊዮኔል ሜሲን ነው፤ በመቐተል ደግሞ የአርሰናልም ደጋፊ ነኝና ኦዚልን አደንቀዋለው፡፡
ሊግ፡- በመጨረሻ…..?
ወንድሜነህ፡- የጥምቀት በዓል ለሁላችንም የሰላም የፍቅር እንዲሆንልን እመኛለሁ፡፡

spot_img
ተመሳሳይ ጽሁፎች

አስተያይት ያስፍሩ

እባክዎን አስተያይትዎን ያስፍሩ
እባክዎን ስምዎን እዚህ ያስገቡ

ትኩስ ዜናዎች

%d bloggers like this:
P