ኢትዮጵያ ደስ ብሏታል
ፈርኦኖቹ ለኢትዮጵያ እጅ ሰጡ
– ዋልያዎቹ የጀግና ማህፀን ትሩፋቶች
በአለምሰገድ ሰይፉ
የዚች ሀገር ጠላቶች አንገት ይድፉ፣ ኢትዮጵያ አሸናፊ ሀገር ናት፡፡ በተፅዕኖም ስር ማሸነፍ የምትችል ታሪካዊ ሀገር፤ በእግር ኳሱም መድረክ ይህ እውነታ መንፀባረቅ ችሏል፡፡ ዘንድሮ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ኢትዮጵያ በሁለንተናዊ መልኩ ታግዳለች፡፡ የተሰናዳው ስታዲየም ኢንተርናሽናል ውድድር የማስተናገድ አቅም የለውምና ታላቁን የኮትዲቭዋር የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ በባዕድ ሜዳ ታካሂድ ዘንድ የተፈረደባት ሀገር ሆናለች፡፡
ሟርት
ይህ ዜና እንደተሰማ ብዙሀኖች ለኢትዮጵያዊነት የተቆረቆሩ እንዳሉ ሁሉ ሁሌም ፅልምተኛነት የሚጠናወታቸው ወገኖች በራሳቸው ሀገር ላይ ተሳለቁ፡፡ በሜዳዋና በደጋፊዋ ፊት ምንም ማምጣት የማትችል ሀገር ሁሉንም ማጣሪያ ከሜዳዋ ውጪ ተጫውታ ምን ልታመጣ ነው? በማለት ተዘባበቱ፡፡ አፍ ማሟሻ የሆነው ፌዴሬሽንም እንዳሻው ተብጠለጠለ፡፡ ኢትዮጵያም በማላዊ 2ለ1 ስትሸነፍ ደግሞ “ሳይጀመር የተጠናቀቀው የአፍሪካ ዋንጫ የማጣሪያ ጉዞ” ተብሎ በእኛው ኢትዮጵያዊያውያን ጋዜጠኞች ዘንድ ተዘገበ፡፡ ግላዊ ስሜት ከኢትዮጵያዊ ማንነት ጋር ያልተለየበት የተደባለቀ ፍላጎት፤ ብዙሃኖች በኢትዮጵያ ማሸነፍ መፈንጠዝን ቢሹም ሁሌም ሀገርን በማኮሰስ ለሚደሰቱት ወገኖች ግን ሟርት ነበር፡፡ እኛ በጊዜ፣ ከአፍሪካ ዋንጫ ተሸንፈን መሸኘትን ማየት፤
ኢትዮጵያና ግለኛ ጥቅም የተምታታባቸው
ቂመኞች የኢትዮጵያ ስፖርት የእውነት ጠላቶች ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ ስታሸንፍ ከመቶ ሚሊዮን በላይ ሕዝብ መፈንጠዙ ከማስደሰቱ በላይ ጥቂቶች በስፖርቱ ላይ ለመንገስና እኔ ብቻ ልታይ ከሚል ጠባብ ስሜት አንፃር የእናት ሀገር ኢትዮጵያ ማሸነፍ ከልብ አያስፈነጥዛቸውም፡፡ ለይምሰል ግን ሰው እንዳይታዘባቸው አብረው ከፊል ደስታን ይጋራሉ፡፡ እነዚህ የስፖርት ጠላቶች የሚጠፉበት ቀን ይናፍቀኛል፡፡
ፈርኦኖቹ ለኢትዮጵያ እጅ ሰጡ በግድቡም ይቀጥላል
ግብፅ ኃያሏ የአፍሪካ የኳስ ንጉስ፤ በተለይ ደግሞ ለዘመናት ኢትዮጵያን የጎል ጎተራ በማድረግ የምትታወቀው ሀገር ሁሌም ስታሸማቅቀን ኖራለች፡፡ የትውልድ ቅብብሎሽ የሚያስተምረን ሀቅ ሁሌም ፈሪነታችንን ነው፡፡ እነርሱ ኃያል፣ እኛ ደግሞ የበታች፤ እውነታውም እንደዛ ነበር፡፡ እኛና ግብፅ ስንገናኝ ፀሎቱ ማሸነፍ ሳይሆን የሽንፈቱ የግብ መጠን እንዲቀንስ መፀለይ ነበር፡፡
ዛሬ ይህ ዘመን እንደፈጣሪ ፈቃድ እየተሻረ ነው፡፡ ሜዳችሁ ለአፍሪካ እግር ኳስ ውድድር አይመጥንምና ሁሉንም ጨዋታ በስደት ሜዳ ታደርጉ ዘንድ ተፈረዶባችኋል የተባለችው ሀገር ከሜዳዋና ከደጋፊዋ ውጪ በባዕድ ሀገር የፈርኦኖቹን ሐውልት ከስር መሠረቱ ነቅንቀውታል፡፡ በሚጣፋጥ ውብ ጨዋታና የ2ለ0 ጎል አይነኬ የሚመስለው የፈርኦኑ መልዕክተኛ በባዕድ ሀገር ሽንፈትን ተጎንጭተዋል፤ ይህ የዘመን ቅብብሎሽ በአላማ ፅናት በማይደራደረው ኢትዮጵያዊ ትውልድ እውን ሆኗል፡፡ ለዚህ ስኬት ላበቃችሁንና ድርብ አላማ አንግባችሁ ወደፍልሚያው ለገባችሁት ተጫዋቾችና በአሰልጣኝ ውበቱ አባተ ለተመራው የአሰልጣኞች ቡድን ላቅ ያለ ምስጋና ይገባችኋል፡፡
እናንተ ለአፍሪካ ዋንጫ ባታልፉም የጀግና ማህፀን ትሩፋቶች ናችሁ
እግር ኳስ ውስጥ ፖለቲካ አለ፡፡ ይህ እውነት ነው፡፡ እናንተ ደግሞ በዚህ ቀውጢ ጊዜ ለኢትዮጵያ የማይተካ ውለታ ፈፅማችኋል፡፡ ቢቻል ለኮትዲቭዋሩ የአፍሪካ ዋንጫ ብታልፉ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ልባዊ ምኞት ነው፡፡ ነገር ግን ይህ ሳይሳካ ቢቀር እንኳን የታሪካዊቷን ኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ተቀናቃኝ ግብፅን ለዛውም በሜዳችሁ የሚገባችሁን አድቫንቴጅ ተነጥቃችሁም በባዕድ ሀገር ታሪካዊቷን ተቀናቃኝ ሀገር ድል በመንሳታችሁ መላው ኢትዮጵያዊ በእናንተ ኮርቷል፡፡ ልባም የኢትዮጵያ አንባሳደሮች ናችሁ፡፡ ይህ ገድል በግድቡም ይቀጥላል፡፡
ኢትዮጵያ ደስ ብሏታል ፈርኦኖቹ ለኢትዮጵያ እጅ ሰጡ – ዋልያዎቹ የጀግና ማህፀን ትሩፋቶች በአለምሰገድ ሰይፉ
ተመሳሳይ ጽሁፎች