Google search engine

“እርስ በርስ በመጠላለፍና በመጠራጠር ቡናን ማትረፍ አይቻልም” “መስዑድ የቡና ምልክት በመሆኑ ክለቡ እንዲቆይ እየፈለገ ያሠነበተው አሰልጣኙ ነው” አቶ ክፍሌ አማረ የኢትዮጵያ ቡና የደጋፊዎች ማህበር ፕሬዝዳንት

በተለይ ለሊግ ስፖርት

“እርስ በርስ በመጠላለፍና በመጠራጠር ቡናን ማትረፍ አይቻልም”
“መስዑድ የቡና ምልክት በመሆኑ ክለቡ እንዲቆይ እየፈለገ ያሠነበተው አሰልጣኙ ነው”
አቶ ክፍሌ አማረ የኢትዮጵያ ቡና የደጋፊዎች ማህበር ፕሬዝዳንት

በአለምሰገድ ሰይፉ

በ2003 ዓ/ም የውደድር ዘመን አንድ የሊጉን ዋንጫ ማንሳት የቻለው ኢትዮጵያ ቡና በድጋሚ የዚህ አይነቱን ውጤት ለማሳካት የክለቡ ደጋፊዎች ፍላጎት ቢሆንም ሂደቱ የተገላቢጦሽ ሆኖ ከውጤት ማጣት ባሻገርም የክለቡ ደጋፊዎች ‘‘የእኛ” ነው የሚሉት ምርጥ አጨዋወትም በሂደት እየደበዘዘ መጥቷል፤ ከዚህም ባሻገር በአንድ ጥላ ስር ያሉት የክለቡ ሰዎችም በሃሳብ ልዩነት ውስጥ መሆናቸው ደግሞ ሂደቱን የበለጠ አስፈሪ አድርጎታል፡፡ ባለፈው ጊዜ በሂልተን ሆቴል በተጠራው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይም የኢትዮጵያ ቡና መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ ያሳወቀውም እውነታ ከላይ የተነሳውን ሀሳብ የበለጠ የሚያጠናክር ይመስላል፡፡ በእለቱ የቀረበው አጀንዳም የበለጠ የሚያነጣጥረው በደጋፊ ማህበሩ ላይ በመሆኑ ለዛሬ ከፕሬዝዳንቱ አቶ ክፍሌ አማረ ጋር የሊግ ስፖርት ጋዜጣ ማኔጂንግ ኤዲተር አለምሰገድ ሰይፉ አጭር ቆይታ አለው፤ በነገራችን ላይ ከጋዜጣችን ባሻገር ወቅታዊ መረጃዎችን WWW.LEAGUESPORT.NET ላይ ማግኘት ትችላለችሁ፡፡

ሊግ፡- የክለባችሁን ወቅታዊ ሁኔታ እንዴት ትገልፀዋለህ?
አቶ ክፍሌ፡- የክለባችን ሀኔታ ጥሩ ሊባል የሚችል አይደለም፡፡ በሜዳ ላይ ከሚታየው ውጤት አንፃር አጀማመሩ ጥሩ ቢመስልም በ20 አመት የውድድር ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ አራት ተከታታይ ጨዋታዎችን በመሸነፍ በጣም መጥፎ ሊባል የሚችል ጊዜና የደጋፊውንም አንገት ያስደፋ አጋጣሚ ነው፡፡
በዚህም ምክንያት አሰልጣኙ እንዲሰናበት የተደረገበትና አመራሩም አካባቢ አለመረጋጋት የተፈጠረበት ጊዜ በመሆኑ ለቡና በጣም አስቸጋሪ ሁኔታ ነው ማለት ይቻላል፡፡
ሊግ፡- ባለፈው ጊዜ የደጋፊው ቁጣ በከፍተኛ ደረጃ በመነሳቱ የተወሰኑ የቦርድ አባላት በገዛ ፈቃዳቸው ከሃላፊነታቸው ለቀው ተመልሰው መጥተዋል፡፡ ይሄን እውነታ እንዴት ትገልፀዋለህ?
አቶ ክፍሌ፡- ኢትዮጵያ ቡና አሁን ለደረሰበት ትልቅ ደረጃ ላይ እንዲገኝ የላቀ ሚና የተጫወቱት እነ መቶ አለቃ ፈቃደ ማሞ እና ይስማሸዋ ስዩምን የመሳሰሉ ታላላቅ የክለቡ ምልክት የሆኑ ሰዎች በገዛ ፈቃዳቸው ራሳቸውን ከሃላፊነት ማግለላቸው የሚታወቅ ነው፤ ይህም የሆነበት ምክንያት ቡድኑ በሜዳ ላይ የሚያስመዘግበው ውጤትና እንቅስቃሴ በእጅጉ የወረደ በመሆኑ ደጋፊው በከፍተኛ ደረጃ ቁጣውን በመግለፁ ነው፡፡
እርግጥ ነው ተቃውሞው በጨዋነትና እጅግ በሰለጠነ መንገድ ቢሆን እኛም እንቀበለዋለን፤ ነገር ግን እጅግ ስብዕናን የሚነኩና ህይወታቸውን በሙሉ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ለኢትዮጵያ ቡና ታላቅነት የደከሙ ሰዎችን ስብዕናቸውን በሚነካ ሁኔታ ቤተሰባቸውን ጨምሮ መሳደብና ማዋረድ ተገቢ ነው ብዬ አላስብም፡፡
ሊግ፡- ባለፈው ጊዜ ሂልተን ሆቴል በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የክለቡ መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ ኢትዮጵያ ቡና ጠንካራ የሆነ የደጋፊ ማህበር እንደሌለው ያምናል፤ አንተስ በዚህ ዙሪያ ምን ትላለህ?
አቶ ክፍሌ፡- ይህን ጥያቄ ከመመለሴ በፊት የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴው ሚና ምን ነበር? የሚለውን ጥያቄ ልመልስልህ፡፡ በዚህ ኮሚቴ ውስጥ የተካተቱት ግለሰቦች ለኢትዮጵያ ቡና ያለማቋረጥ ገንዘባቸውን፣ ውድ ጊዜአቸውን እና ሁለንተናቸውን ለክለቡ አሳልፈው የሰጡ ናቸው፤ ይህም ኮሚቴ የተመሰረተው ታህሳስ 24/2010 በመንገድ ትራንስፖርት አዳራሽ በተደረገ ስብሰባ ነበር፡፡
ምክንያቱ ደግሞ ላለፉት 8 አመታት ክለባችን በአጨዋወቱም ሆነ በውጤቱ ውራ እየሆነ በመሄዱ ደጋፊው “ቡናን መልሱልን” የሚል ጥያቄ በማንሳቱ ይሄን ክፍተት ለመድፈንም ታስቦ ነው ይህ ኮሚቴ የተመረጠው፡፡ በመሆኑም ማህበራችን ይሄን ሃላፊነት በመውሰድ ኢትዮጵያ ቡናን ወደላቀና ዘመናዊ አካሄድ ሊያመራ የሚያስችለውን ጥናት እንዲያዘጋጅ ነው አባላትን በመምረጥ ለቦርዱ በማቅረብና እውቅና በመስጠት ወደሃላፊነት እንዲገባ አድርጓል፡፡
ሊግ፡- የተሰጣቸውን ሃላፊነትስ በአግባቡ ተወጥተዋል ብለህ ታምናለህ?
አቶ ክፍሌ፡- ከመነሻው ይህ መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ የተቋቋመው የደጋፊ ማህበሩ ጠንካራ ባለመሆኑ ነው፤ ደጋፊ ማህበሩ በሰው አደረጃጀትም ሆነ በፋይናንስ ረገድ ጠንካራ አቋም የሌለው በመሆኑ በዘመናዊ አደረጃጀት እንዲተካ በመታሰቡ መፍትሄ አፈላላጊ ኮሜቴው ከሚያጠናቸው ጉዳዮች መካከል የሚካተት ነው፡፡ በአሁኑ በሰለጠነው እና በ21ኛው ክፍለ ዘመን ደጋፊዎች የሚያነሱትን ጥያቄ በአግባቡ መመለስ የሚያስችል የማህበር አደረጃጀት እንደሌለን እኔም አምናለሁ፡፡
ሊግ፡- ስለዚህ ደጋፊ ማህበሩ ደካማ ነው በሚለው አቋማቸው ትስማማለህ ማለት ነው?
አቶ ክፍሌ፡- አዎ፤ በሚገባ እስማማለሁ፡፡
ሊግ፡- የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሜቴውን ህጋዊነት የክለቡ ቦርድና የደጋፊ ማህበሩ አመራር አምኖ ይቀበላል?
አቶ ክፍሌ፡- አዎ፤ ታህሳስ 24/2010 በተደረገው አጠቃላይ የማህበሩ ስብሰባ ላይ የኢትዮጵያ ቡና የልብ ደጋፊ የሆኑና ክለባችን አሁን ካለበት አዝጋሚ ጉዞ ተላቆ ወደዘመናዊ አደረጃጀትና በፋይናንሱም ረገድ ፈርጣማ አቅም እንዲኖረው በማሰብ ነው ይህ ኮሚቴ የተቋቋመው፡፡ ክለቡም ይሄን እውነታ በመረዳት በደብዳቤ አረጋግጦ የፃፈው በመሆኑ ህጋዊነቱን አምነን የምንቀበለው ጉዳይ ነው፡፡ ነገር ግን ይህ ህጋዊነት በክለቡና በማህበሩ ስር ነው እንጂ እንደ ቋሚ ኮሚቴነት የሚወሰድ አይደለም፡፡ የክለቡን ሁለንተናዊ ችግሮች ፈትሸው ለክለቡ እንዲያቀርቡና አመራሩም ከዚህ መነሻነት እርምጃዎችን በመውሰድ አሁን ካለበት አዝጋሚ ጉዞ የማላቀቅ አካሄድ ነው፡፡ እኔ በተለይ በግሌ ይህ ጥናት እንዲቀርብና በተግባር ደረጃ ግቡን እንዲመታ ደጋፊውም የአመራርነት ሚናው ከፍ እንዲል የምችለውን ነገር ሁሉ አድርጌያለሁ፤ የኮሚቴውንም እውቅና አምንበታለሁ፡፡
ሊግ፡- እንደዛ ከሆነ እነርሱ ያዘጋጁት ሰነድ ወደተግባር እንዲለወጥ ማህበራችሁ ለምን አልተንቀሳቀሰም?
አቶ ክፍሌ፡- ይሄን አካሄድ በሁለት መልኩ ነው የማየው፤ በአሁኑ ጊዜ ክለቡ ያለበት ችግርና መፍትሄው በሚለው ጥናት ላይ ማህበራችን እስከመጨረሻው ከመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴው ጋር እየሰራ ነበር፡፡ መጀመሪያ ላይ የክለቡና የማህበሩ ጥናት እንዲሰራ ነበር የታሰበው፡፡ ከዚህ አንፃር የማህበሩ መቅደም ሲገባው የክለቡ መዋቅር እንዲቀድም ተደረገ፡፡ ይህም ማለት 40 ፐርሰንት ደጋፊው የአመራርነት ሚና እንዲኖረውና 60 ፐርሰንት ደግሞ በቡናው ዘርፍ ያለው አካል እንዲይዘው የሚል ፕሮፖዛል ሲቀርብ ይህ ጉዳይ በቀጥታ የሚመለከተው የክለቡን ቦርድ ነው፡፡ በመሆኑም ይህ ጥናት ለክለቡ የስራ አመራር ቦርድ ቀርቦለት መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴውም ያዘጋጀውን ሰነድ ኢስት ዌስተርን በሚባል ሆቴል አቀረበ፡፡ የስራ አመራር ቦርዱም ሰነዱን ከተቀበለ በኋላ ያለውን እውነታ አይተን ምላሽ እንስጥ በሚል ለሌላ ጊዜ ቀጠሮ ተያዘ፡፡
ከዚያም ነሐሴ 9/2010 ዓ/ም በኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴል ጥሪ ተደርጎ የክለቡ ቦርድ፣ የማህበሩ አመራሮችና የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሜቴው በተገኙበት በተደረገው ውይይት ቦርዱ አሁን ባለው ሁኔታ ያቀረባችሁትን ሰነድ ሙሉ ለሙሉ ለመቀበል አንችልም፡፡ ነገር ግን በቦርዱ ውስጥ ደጋፊ ማህበሩ የነበረው ሁለት ውክልና ወደ አራት ከፍ እንዲልና በጠቅላላ ጉባኤው የነበረው ሁለት ውክልና ወደሰባት ከፍ እንዲል በማለት በጥቂቱ ሊባል በሚችል ሁኔታ መፍትሄ አፈላላጊ ኮሜቴው ያዘጋጀውን ሰነድ ተቀብሏል፡፡ የተቀበለበት አግባብ ግን በተሸራረፈ ሁኔታና ግልፅ ውይይትና መናበብ በሌለበት መልኩ ነው፡፡ እዚህ ላይ አንድ መታወቅ ያለበት እውነታ የሁሉም ተልዕኮ አንድና አንድ ቡናን ወደላቀ ጉዞ ለማድረስ ቢሆንም እርስ በርስ መጠራጠርና መጠላለፍ በመኖሩ ብቻ የተፈለገው አካሄድ ግቡን መምታት አልቻለም፡፡ እንደማህበራችን እምነትና አቋም መፍትሄ አፈላላጊው ኮሚቴው ያቀረበው ሰነድ እጅግ ዳይናሚክ የሆነና ክለቡን በዘመናዊነት ከትውልድ ወደትውልድ የሚያሻግር ጥናት ነው፡፡
ከዚህ አንፃር ሁላችንም የምንወደው ክለባችን ኢትዮጵያ ቡና ወደላቀ ደረጃ እንዲሸጋገር ከተፈለገ የእኔ የምንለውን ትተን መተኳኮስና መጠላለፍን ወደጎን በመተው በጋራ መስራት አለብን፡፡ በተረፈ ማህበሩ ይህ ሰነድ ወደተግባር እንዲለወጥ አልታገለም ላልከኝ ጥያቄ ጥናቱ ከተጠናቀቀ ገና አጭር ጊዜ በመሆኑ፣ በሃላፊነት ተመርጠን የምናገለግልበት ተርም እየተጠናቀቀ በመሆኑና አሁን ያለው የማህበር አደረጃጀት ይሄን ለማድረግ የተጠናከረ አቋም የሌለን በመሆኑ ይሄን ማድረግ አልቻልንም፡፡ ከዚህ በተረፈ ማህበራችን መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴው ያቀረበውን ሃሳብ መቶ ፐርሰንት ይስማማበታል፡፡
ሊግ፡- በመሃከላችን ምንም ክፍተት የለም እያልክ ነው?
አቶ ክፍሌ፡- እንደዛ ማለቴ አይደለም፤ እርግጥ መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴው ለደጋፊ ማህበሩ የሰጠው ግምት ዝቅተኛ ስለነበር በመሃል ክፍተቶች ነበሩ፡፡ ይሄን እውነታም በተለያየ ጊዜ በግልፅ ነግረናቸዋል፡፡ ማህበሩ የሚሰጣችሁን አስተያየቶች ጥናቱ ውስጥ ክተቱት ብለናቸዋል፡፡ ከዚህ በተረፈ እኔ እንደማህበሩ ፕሬዝዳንትነቴ ለጥናቱ መሳካት እስከመጨረሻው ጊዜ ድረስ አብሬያቸው ነበርኩ፡፡ ከዚህ በተረፈ በደጋፊ ማህበሩ ባሉ ጥቂት ግለሰቦችና በመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ ውስጥ ባሉ ጥቂት ሰዎች መካከል አለመግባባት እና የጥርጣሬ መንፈስ ያለ በመሆኑ በማህበሩና በክለቡ፣ በመፍትሄ አፈላላጊው እና በክለቡ በኩል ጥርጣሬ በመኖራቸው ጤናማ ግንኙነት ነበር ለማለት አልችልም፡፡
ጤናማ ግንኙነት ባለመኖሩ ምክንያት ደግሞ ነገ ኢትዮጵያ ቡናን ትልቅ ደረጃ የሚያደርስ ጥናት ወደተግባር እንዳይለወጥ እንቅፋት ፈጥሮአል ብዬ አስባለሁ፡፡
ሊግ፡- አንተም ቀደም ብለህ እንዳመንከው እስከመጨረሻው ጊዜ ድረስ አብረሃቸው ሰርተህ መፍተሄ አፈላላጊ ኮሚቴው ጋዜጣዊ መግለጫ ለመስጠት 10 ቀን ሲቀረው ከእነሱ የተለየህበት ምክንያት ምንድነው?
አቶ ክፍሌ፡- የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሜቴው አባላትን ከመምረጥ፣ ከማስመረጥ፣ ከማደራጀት፣ ከመሰብሰብና አዳራሽ ከማዘጋጀት አንስቶ አብሬያቸው በመሪነት ሚና የበኩሌን ተወጥቼአለሁ፡፡ በኋላ ላይ ያለውን ሁኔታ በተመለከተ ለጋዜጠኞች ጋዜጣዊ መግለጫ መሰጠት አለበት የሚል ሃሳብ መጣ፡፡ በአጋጣሚ ደግሞ መቶ አለቃ ፈቀደ ማሞና ይስማሸዋ ሪዛይን ያደረጉበት ጊዜ በመሆኑ ክለቡ አለመረጋጋትና ድንጋጤ የተፈጠረበት ጊዜ ነበር፡፡ እናም ይሄን ጊዜ ጠብቆ ጋዜጣዊ መግለጫ መስጠት ተገቢ አይደለም፡፡ ይልቁንስ መጋቢት 16 ማህበሩ ጠቅላላ ጉባኤ የሚጠራ በመሆኑ ያጋጠማችሁን ችግሮችና የሰነዱን ይዘት ለጉባኤው ብታቀርቡ ይሻላል፡፡
በተረፈ በዚህ ጊዜ ጋዜጣዊ መግለጫ በመስጠቱ ጉዳይ ላይ አልስማማም አልኩ እንጂ ባቀረቡት ጥናት ከመላው የኮሚቴ አባላት ጋር አጋርና ቤተሰብ ብቻ ሳልሆን አካሄዳቸውንም እደግፋለሁ፡፡ በመሃል የተፈጠረው ልዩነት ጋዜጣዊ መግለጫ በመስጠቱ ሃሳብ ብቻ ነው፤ ከዛ በተረፈ የተለየ አላማ የለኝም፡፡
ሊግ፡- ከዚህ በኋላ ባለው ሁኔታ መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላቱ ለመስራት ፈቃደኛ አለመሆናቸው ብዙ የተደከመበትን ሰነድ ፍሬ አልባ አያደርገውም?
አቶ ክፍሌ፡- በእኔ በኩል እነርሱ የያዙት አቋም ተገቢነት የለውም ነው የምለው፡፡ የደጋፊ ማህበሩ፣ ቦርዱም ሆነ በመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ ውስጥ ያሉት እጅግ የተከበሩና በተሰማሩበት የስራ መስክ የላቀ ውጤት ያስመዘገቡት ግለሰቦች የሁላችንም ግብ ኢትዮጵያ ቡናን ወደትልቅ ደረጃ ማድረስ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ይሄን ያህል ለፍተውና ደክመው “ነገሩን እዚህ ጋር ትተነዋል” ማለት አይጠበቅባቸውም፡፡ ሁላችንም እያገለገልን ያለነው በበጎ ፈቃደኝነት ነው፡፡ ቡና ከክለብም በላይ እንዲሆን ለማስቻል ሁላችንም የየራሳችን የሆነ አሻራ አለን፡፡ በመሆኑም ቡና በዘመናዊ አደረጃጀት ዘመን ተሻጋሪ ክለብ እንዲሆን ለማስቻል ራሳቸውን ሳያገሉ ሁሌም በአዎንታዊ ጎኑ ከማህበሩና ከደጋፊው ጋር በመተጋገዝ ይህ ብዙ የተለፋበት ጥናት ወደተግባር እንዲለወጥ መስራት አለባቸው እንጂ “በቃን” ማለታቸው ተገቢነት እንደሌለው አምናለሁ፡፡
ሊግ፡- ምን መደረግ አለበት ትላለህ?
አቶ ክፍሌ፡- እንደእኔ እምነት ይህ አለመግባባት ሊመጣ የቻለው በስራ አመራር ቦርዱ፣ በደጋፊ ማህበሩና በኮሚቴው በኩል ቅንነት አለመኖርና እርስ በእርስ ጥርጣሬ በመፈጠሩ ነው፡፡ በነገራችን ላይ ይህ መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ ያዘጋጀው ሰነድ አይደለም አንድ የቡና ክለብን የሃገሪቱን እግር ኳስ አስተሳሰብ ሊለውጥ የሚችል ጥልቅ ጥናት ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ካየነው እረስ በእርስ በመጠላለፍና በመጠራጠር ኢትዮጵያ ቡናና ማትረፍ ስለማይቻል ይህንን ነገር ወደጎን ትተን ቡናን ወደላቀ ምዕራፍ ለማሸጋገር እጅ ለእጅ ተያይዘን ልንሰራ ይገባል፡፡
እንደሚታወቀው ቡና በአሁኑ ጊዜ ከፍተኛ የሆነ የፋይናንስ ችግር አለበት፤ በዚህ ምክንያትም ተፎካካሪ ክለብ መሆን አልቻለም፡፡ ታላላቅ አቅም ያላቸውን ተጨዋቾች ለማስፈረምም ተቸግረናል፡፡ በዚህም ምክንያት ከጊዜ ወደ ጊዜ በአጨዋወትም ሆነ በውጤት ረገድ ወደኋላ እየቀረን ነው፡፡ በዚህ ሳብያም በሃገሪቱ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ደጋፊ በሂደት ሊበተን ይችላል፡፡
ከዚያ ግፋ ሲልም አዲስ አበበ ውስጥ እንዳሉትና በፋይናንስ አዘቅት ውስጥ ገብተው ወደ ኋላ እንደቀሩት እና ሊፈርስ ሁሉ እድል ያለው በመሆኑ እስከአሁን እያንዳንዳችን የከፈልነው መስዋዕትነት ብዙ ሊባል የሚችል ባለመሆኑ አሁን ጠንክረን መስራት ይጠበቅብናል፡፡ ይህም ማለት ክለቡ ህዝባዊነትን መላበስና አስተማማኝ የሆነ የፋይናንስ አቅም ሊፈጥር የግድ ይላል፡፡ ክለቡን ላለፉት 20 እና 30 አመታት እዚህ ደረጃ እንዲደርስ ያደረጉት ግለሰቦች በእድሜና በሌላ ምክንያት ከክለቡ ዞር ቢሉ ለክለቡ አለኝታ ሊሆኑ የሚችሉ ደጋፊዎች ማግኘት አዳጋች ስለሚሆን ክለቡን ፕሮፌሽናሎች ብቻ የሚመሩትና አስተማማኝ የፋይናንስ አቅም ኖሮት በውጤታማነቱ የላቀ ክለብ እንዲኖረን ለማስቻል ተጋግዘን መስራት እንጂ አንዳችን ከሌላችን ጋር በመተኳኮስ ቡናን ለማዳን ስለማንችል አንድ ቦታ ቆም ብለን ልናስብ ይገባል ባይ ነኝ፡፡
ሊግ፡- ስለተጨዋቾች ጥራት ስታነሳ አንድ ነገር ትዝ አለኝ፤ አሰልጣኝ ጎሜዝ አንድ የሚያነሱት ቅሬታ እንዳለ ሰምቼ ነበር፤ “ከእኔ እውቅና ውጪ ወደዘጠኝ የሚደርሱ ተጨዋቾች ደጋፊ ማህበሩ አስፈርሟል” ሲሉ እናንተን ይወቅሳሉ፤ ይህ አባባል ምን ያህል እውነት ነው?
አቶ ክፍሌ፡- ይህ ፈፅሞ ውሸትና ሃሰት ነው፤ ሲጀመር በኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ታሪክ እንደአሁኑ አሰልጣኝ ፍፁም የሆነ ስልጣንና የፈለገውን እንዲያደርግ እድል የተሰጠው ሙያተኛ የለም፡፡ እስከዛሬ ስራ አመራር ቦርዱ በተጨዋቾች ግዥ ላይ ጣልቃ ይገባል ስለሚባል እንደውም ይሄን እውነታ እኔ ራሴ በቅርበት ስለነበርኩ ሁኔታውን ጠንቅቄ አውቃለሁኝ፡፡ ክለቡ መስዑድ መሃመድ የኢትዮጵያ ቡና ልዩ ምልክት ነው፤ ሙሉ ዘጠና ደቂቃ እንኳን ባይጫወት ሰላሳ ደቂቃም ቢሆን ተቀይሮ እየገባ እንዲጫወት ብታቆየው ይሻላል” ሲባል “ፈፅሞ አልቀበልም፤ እኔ ነኝ የምወስነው” በማለት መስዑድን እንዲሰናበት አድርጓል፡፡ ይሄም የሚያሳየው እውነታ ቦርዱ ምን ያህል ለአሰልጣኙ የሰጠው ነፃነት የተለየ እንደነበር የሚያሳይ እውነታ ነው፡፡
ከዚህ በተረፈ አሰልጣኙ ከክለቡ እንዲሰናበቱም በአንፃሩም እንዲመጣለት የጠየቃቸው ተጨዋቾች ነበሩ፡፡ እንደውም እዚህ ላይ የአሰልጣኝ ጎሜዝ ችግር እንዲመጣለት የፈለጋቸው ተጨዋቾች በነበሩበት ክለብ ቀሪ ውል ያላቸው ተጨዋቾች ነበሩ፡፡ ውል ያለው ተጨዋች እንደማይመጣ እየታወቀ መጠየቁ በራሱ ተገቢነት የለውም፡፡
እንደውም ኢትዮጵያ ቡና አድርጎት በማይታወቅ ሁኔታ አሰልጣኙ ስለፈለገውና የእርሱን ጥያቄ ለማሟላት በማሰብ ሲባል ቡቻ ቡና በሌለው ገንዘብ ለካሉሻ እስከ ሁለት መቶ ሀምሳ ሺህ ብር በመክፈል እንዲመጣ ተደርጎለታል፡፡ ከእዚህ በተረፈ ሌሎቹ ተጨዋቾች ለቡና መፈረም ስላልፈለጉና በገንዘብ እጥረት ነው መምጣት ያልቻሉት፡፡
ሲጀመር ዘንድሮ ወደ ክለባችን ዘጠኝ ተጨዋቾች አልመጡም፤ ወደ ክለባችን የመጡትም ተጨዋቾች ካሉሻ አልሀሰን ፣ አህመድ ረሺድ /ሽሪላ/፣ ተመስገን ካስትሮና ተካልኝ ደጀኔ ናቸው፡፡ ከዚህ በተረፈ ዘጠኝ ተጨዋቾችም አልመጡም፤ እሱ ራሱ በተለያዩ ሚዲያዎች እንደገለፀው ተጨዋቾቹ የመጡት በራሱ ፍላጎትና ምርጫ ብቻ ነው፡፡ ምናልባት ከወልድያ የመጣው ዳንኤል ደምሴ ካልሆነ በቀር ሁሉም ተጨዋቾች ወደኢትዮጵያ ቡና የመጡት በአሰልጣኝ ጎሜዝ ፍላጎት እና ጥያቄ ከመሆኑ አንፃር በዚህ ረገድ አሰልጣኙ ያቀረበው ቅሬታ ሃሰት መሆኑን ላረጋግጥልህ እወዳለሁ፡፡
ሊግ፡- አመሰግናለሁ?
አቶ ክፍሌ፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡

spot_img
ተመሳሳይ ጽሁፎች

አስተያይት ያስፍሩ

እባክዎን አስተያይትዎን ያስፍሩ
እባክዎን ስምዎን እዚህ ያስገቡ

ትኩስ ዜናዎች

%d bloggers like this:
P